News Feature

የዘንድሮ ኢሬቻ  | ከቢሾፍቱ የተጠናቀረ ዘገባ በማህሌት ፋንታሁን*

የኢሬቻ በዓል ከሚከበርበት እለት 3ት ቀናት ቀደም ብለን ነበር ቢሾፍቱ የገባነው።
በዋዜማዎቹ ቀናት
★★★

ማህሌት ፋንታሁን

በከተማዋ በዓሉን የተመለከቱ ባነሮች በሆቴሎች፣ መንገዶች እና አደባባዮች ሲለጠፉ ፤ የባህል ልብሶች፣ ስከርፎች፣ ኮፍያዎች እንዲሁም የተለያዩ ጌጣጌጦች በየመንገዱ እና በየሱቁ ሲሸጡ ፤ ገበያውም ሞቅ ብሎ እስከ በዓሉ እለትም ቆይቷል። ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ የበአሉ ታዳሚዎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል። በዓሉ አንድ ቀን ሲቀረው ፤ የኦሮሞ ባህል ልብስ በለበሱ የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ከተማዋ ደምቃ ነበር፤ አልፎ አልፎም በመንገድ ላይ ጭፈራ ነበረ፤ የበቀለ ገርባ፣ የመረራ ጉዲና፣ የዋቆ ጉቱ እና የሌሎች ኦሮሞ ጀግኖችን ምስል የያዘ የመኪና ላይ ስቲከር መነሃሪያ አካባቢ ሲሸጡ አይተናል፤ የሚሸጡት ልጆችም ጮክ ብለው “የኦሮሞ ጀግኖችን የያዘ ምስል ለመኪና” እያሉ ነበር የሚሸጡት። [እነዚህ ስቲከሮች የበአሉ እለትም በተመሳሳይ መልኩ ሆራ አርሰዲ ድረስ በሚወስዱ መንገዶች ሲሸጡ ነበር] በዓሉ ወደ ሚከበርበት ሆራ አርሰዲ ሃይቅ መግባት አይቻልም። ከተማ ውሰጥም የኦሮሚያ ፖሊሶች በብዛት አልፎ አልፎም የፌደራል ፖሊሶች ይታዩ ነበር። ይህ እና በዓሉ 1 ቀን ሲቀረው ከመንግስት የተሰጠው መግለጫ ህዝቡ እንዲሰጋ እና በበዓሉ ቀንም የሚከሰት መጥፎ ነገር ሊኖር እንደሚችል ፍርሃት ነበር።

 

የበዓሉ እለት
★★★
የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎች ከለሊቱ 10 ሰአት ጀምሮ ነው ወደ ሆራ አርሰዲ እየጨፈሩ ማለፍ የጀመሩት። ኢሬቻ የሚከበርበት ሆራ አርሰዲ ለመሄድ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ከመሆኑ በፊት ደርሰናል። አየሩ ዝናባማ ነበር። ጠዋት ቢሆንም በመንገዳችን በቡድን በቡድን ሆነው እየጨፈሩ ይሄዳሉ። ስንደርስ ወደ ሃይቁ መግቢያ ጋር ያለው የበዓሉ መድረክ ላይ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የተወሰኑት ተቀምጠው የተቀሩት ቆመው ይታያሉ። ሆራ አርሰዲ ደርሰን ስንመለስ ዝናብ ማካፈት ጀመረ። መድረኩ ላይ የጭፈራ ድምፅ ይሰማል። መድረኩን ቄሮዎች ተቆጣጥረውታል። የገዳ ምልክት የሆነው ባለ ጥቁር ቀይ ነጭ ባንዲራን ሰቅለዋል። ጭፈራው የሳባቸው በአካባቢው የሚገኙ የነበሩ ወጣቶችም ወደመድረኩ ተቀላቅለው ለመጨፈር ተመሙ። ዝናቡ እየዘነበ ነው። ካፍታ ቆይታ በኋላ “Down down weyane” የሚል በጋራ የሚሰማ መፈክር ከመድረኩ ይሰማ ጀመር። መድረኩ አካባቢ የነበሩ ወጣቶቹ ወደ መድረኩ መሄዳቸውን ቀጠሉ። “Down down weyane”!!! ይህን መፈክር መድረኩን ከሞሉት ወጣቶች ሙሉ ይሰማ ነበር። የምናየው እና የምንሰማው አስደነቀን። ዝናቡ እየዘነበም ቢሆን በቡድን እየጨፈሩም ሆነ በተናጠል ወደ ሆራ አርሰዲ የሚደረገው ጉዞ አልተቋረጠም።

የኦሮሚያ ፖሊሶች ፍተሻ ቦታ ላይ ከፎሌዎች ጋር ሆነው ከመፈተሻቸው ውጪ በአሉ በሚከበርበት አካባቢ አልነበሩም። ከአምና እና ካቻምናው በጠነከረ መልኩ ወደ ሆራ ከሚሄዱትም ሆነ ከሚመለሱት “ያ ወያኔ!” ፣ “እምቢ! አንገዛም” ፣”በቃን!” የሚሉ መፈክሮች በብዛት ተሰምተዋል። ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ወገኖች በተቀናጀ ሁኔታ እርዳታ ሲሰበሰብ ነበር።

 

እነ በቀለ ገርባ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ጃዋር፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩ እና ሌሎችን በስም እየጠሩ አወድሰዋል። “በቀለ ገርባ እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ያስተዳድሩን” ፣ “መንግስት ራሱ አሸብሮ፤ ንብረታችንን መሬታችንን ሰርቆ እኛን አሸባሪ ይላል” ፣ “ጃዋር የኛ ኦኤም ኤን የኛ”፣ “ቻው ቻው ወያኔ!” ብለዋል— ቄሮዎች። የበቀለ ገርባን ምስል በትልቁ የያዙ ወጣቶች በርከት ብለው፤ በቀለ እንዲፈታ ሲጠይቁ እና መፈክር ሲያሰሙ ነበር። ጠዋት የበዓሉ መድረክ ላይ በመደነቅ የሰማነው “Down down weyane” መፈክር፤ ቀኑን ሙሉ በየመንገዱ እና ሆራ አርሰዲ ሃይቅ ጋር ሲሰማ ነው የዋለው። አምና አንድ ጀግና ወጣት ያስጀመረው “Down down weyane” መፈክር ብዙ ሺህ ወጣቶች ሲሉት ነበር። ባለቤትነቱ የእውቁ ባለሃብት ዲንቁ ደያሳ የሆነው ሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በር ላይም በስፒከር የተለቀቁ የተቃውሞ እና ሌሎች የኦሮምኛ ዘፈኖች ተከፍተው በርካቶች ተሰባስበው ሲዘፍኑ ፣ ሲጨፍሩ ነበር። ከቀኑ ወደ 10 ሰአት አካባቢ ሲሆን የኦሮሚያ ፖሊሶች በጭነት መኪና ሆነው ከተማዋን ሲዞሩ በዙሪያቸው ያሉ ምስጋናቸውን በጭብጨባና በጩኸት ሲገልፁ አይተናል።
ከሞላ ጎደል በጥቂቱ እይታ ይህን ይመስል ነበር የዘንድሮ ኢሬቻ። ድሮም በሰላም ያልቅ የነበረውን በዓል አምና መንግስት ራሱ በሰላም እንዳያልቅ ካደረገ በኋላ “በሰላም ተጠናቀቀ” እያልን እንድንገረም እና እንድንደሰት መሆኑ በጣም ያበሳጫል። አምናም አንድም ሰው መሞት እማይገባ እንደነበር እና የአምናውን ስህተት አጉልቶ ያሳየ ሆኖ ነው ያለፈው የዘንድሮ ኢሬቻ።

ክብር አምና በኢሬቻ በአል ላይ መንግስት በወሰደው እርምጃ ለተሰዉ!

* ማህሌት ፋንታሁን የዞን 9 ጦማሪና በገዢው መንግስት ታስራ የተፈታች እህት ናት::

2 Comments

2 Comments

 1. CHEBUD

  October 3, 2017 at 12:35 am

  የቴዎድሮስ ጭካኔና የፈጸሙአቸውን ግፎች በሚመለከት ኢንጂነር ታደለ ብጡል ‹‹ቴዎድሮስና አለማዮ›› በሚለው መጽሐፋቸው ከጻፉት ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1.የሸፈተባቸውን ቸኮልን ለመውጋት ወደ ደንበጫ ሄደው ሳለ ቸኮል አመለጣቸው። ከአሽከሮቹም ስድሳ ሰዎች ተማርከው ስለነበረ እነሱን በገበያ ላይ ሰቀሉአቸው። አንደኛው ከቴዎድሮስ አሽከር ጠመንጃ ሲቀማ ተይዞ ነበርና ያንን ሰው ከመድፍ አፍ ላይ አስጠግተው አስቁመው የመድፍ ጥይት እንዲተኩስ አዘዙ። ሲተኮስም ሰውየውን ብትንትኑን አውጥቶ ገደለው በማለት አለቃ ዘነበ ጽፈዋል።
  2.ግራዝማች ዓለሜ የሸፈቱ ጊዜ አንዱ አሽከራቸው ተይዞ መጣ። ከንጉሡ ችሎት በቀረበ ጊዜም ቴዎድሮስ የሞት ፍርድ ካስፈረዱበት በኃላ፣ መቅደላ፣ ወራሂመኖ፣ ደላንታ፤ ዋደሌ ጦርህን ከዚህ ሰው ደም ያላስነካህ ጠላቴ ነህ ብለው በመናገራቸው ያ ሁሉ ሕዝብ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሁሉም በጦር ሲወጋው ብትንትኑ ወጥቶ ለምልክት እንኳ የሚታይ ሥጋው ከመሬት ላይ ጠፋ።
  3.ደጃች ተድላ ጓሉን ለመያዝ አጤ ቴዎድሮስ ገስግሰው በድንገት ደርሰው በተዋጉ ጊዜ ስምንት ሺህ ሰዎችን ማረኩ። ይህን ሁሉ ምርኮኛ እንጅባራ ላይ ሰብስበው ራሱን ሲያስቆርጡ ውለው ጊዜው ሲመሽ የተረፈው ሰው ተቆጥሮ አደረ። ሲነጋጋ ንጉሡ ተነስተው ያደሩትን ሰዎች አምጣ ብለው አስቀርበው ሁሉንም እቆርጠው ፈጁት። ያን ሁሉ ክምር ሬሳ እየተዘዋወሩ ሲያዩ ከሬሳው አንዱ አለሞተ ኖሮ ሲንፈራገጥ አዪት። ቴዎድሮስም ተቆጥተው ‹እንዲሁ ሳትገድሉ ነው የጣላችኋቸው› ብለው ያን የሚንፈራገጠውን ራሳቸው ገድለው ሌላ ሁሉ እታየ ያልሞተው እንዲገደል አዘዙ። ሁሉም ካለቁ በኋላ ይህን ሁሉ ጠላቴን በጄ ጥሎ እንዲህ አስተኝቶ ያሳየኝ እግዝአብሔር ይመስገን፣ ብለው መሬት ይህን ጠላቴን በጄ ጥሎ እንድህ እተኝቶ ያሳየኝ እግዝብሔር ይመስገን፣ ብለው መሬት ስመው ከድንኳናቸው ገቡ።
  4.በ1859 ዓ.ም የአማራ ሣይንት ሰዎች ሊክዱ ነው ብለው ስለነገሩዋቸው ቴዎድሮስ ከአማራ ሣይንተ 400 ሰዎች አስይዘው ሁሉንም በጎራዴ አስደብድበው ፈጁዋቸው። አንድ ሰው ከዋድላ ሰዎች ጋር ቢጣላ ከቴዎድሮስ ዘንድ መጥቶ ዋድሎች ሊከዱዎት ነው ብሎ ነገራቸው። ቴዎድሮስም ለዋድላ ሰዎች ገንዘብ እሰጣለውና ሁሉም ተሰብስበው ይምጣ ብለው አዋጅ አስነገሩ። ይህንንም አዋጅ የሰማው ሕዝብ፣ እረኛ እንኳ ሳይቀር በሙሉ ተሰብስቦ መጣ። አፄ ቴዎድሮስም በራስ አድሉ የሚመራውን የየጁን ጦር ዙሪያውን አስከብበው ስድስት መቶ ሰዎችን በጎራዴ ፈጁአቸው። ይህን የግፍ አገዳደል ያዩት ራስ አድሉ ሌሊቱን አምልጠው መሸፈታቸውን አለቃ ተክለ ኢየሱስ ጽፈዋል።
  5.የመጫና የአገው ሰዎች ሊሸፍቱ ነው ብሎ አሳባቂ ነገራቸው። ቴዎድሮስም አራት መቶ የመጫና የአገው መኳንንት ሰብስበው ዙሪያውን በእሾህ አጥር አጥረው ሱሬ ብቻ እያስታጠቁ ራቁታቸውን እንደ ከብት አጎሩዋቸው። እህልና ውኃም እንዳይሰጣቸው አዘዙ። በረሃብና በውኃ ስም የሚሰቃየው ሕዝብም ከአስር ቀን ቦኃላ መሞት ጀመሩ። በ15ኛው ቀን ግን ሁሉም በረሃብና ውኃ ጥም አለቁ።
  6.ቴዎድሮስ ቃሮዳ ከሚባል አገር ሄዱ። ቃሮዳ በአተክልት አብቃይነቱ በተለይ በወይን ሰብል የታወቀ አገር ነበር። አንድ ማድጋ የወይን ጠጅ በጎንደር ባንድ አሞሌ ይሸጥ ነበር። ፈረንጆች የቃሮዳ የወይን ጠጅ ከሀገራችን ወይን ጠጅ የበልጣል ይላሉ።….ያንን ወይን ሀገር በአዋጅ አስነግረው አስነቀሉት። ይህን የሰማ ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ወይኑን ነቀለ። ከዝህ ወዲህ በኢትዮጵያ ወይን ታጣ። ቴዎድሮስ ቃሮዳ እንደደረሱ ሕዝቡን ሰብስቡልኝ ብለው ሕጻናት ሳይቀሩ 1700 ሰዎች ተሰበሰቡ። ይህንን ሁሉ ሰው ቤት እስከቻለ ድረስ በየቤቱ እያስገቡ ሁሉንም በእሳት እያቃጠሉ መጨረሳቸውን አለቃ ወልደማርያም ጽፏል።
  7.አጼ ቴዎድሮስ ወደ ማህደረ ማርያም በወረዱ ጊዜ ካህናቱ ንጉሡን ለመቀበል ከለቻ ከሚባል ሜዳ ላይ ቆመው በጸናጽልና በከበሮ እያመሰገኑ አቀባበል አደረጉላቸው። ይህን ያዩት ቴዎድሮስ በልልኝ ብለው ወታደሩን አዝዘው 450 ካህናት በጎራዴ ተደብድቦ አለቀ። ከዚያም ተመልሰው ደብረታቦር በወጡ ጊዜ ከርብ ጀምሮ እስከ ፍርቃ በር ወታደራቸውን አሰማረተው ሲቆፍርም፣ በመንገድ ሲሄድም የተገኘውን ሁሉ 7700 ሰዎችን አሰባሰቡ።ይህን ሁሉ ሰብስበው በየቤቱ ውስጥ እያጎሩ የታጎሩበትን ቤት በማቃጠል ሲያስፈጁአቸው ዋሉ። ሰው ተቃጥሎ ስያልቅ ጊዜው ስለመሸ ተራፊውን ከሜዳ ላይ እየተጠበቀ ራቁታቸውን እንዲያድሩ አዘዙ። ሌሊቱን ዝናብ ስለዘነበ ሕጻናትና እመጫት ሣይቀሩ በዝናብ ሲደበደቡ አደሩ። በማግስቱ ቴዎድሮስ ያደረውን ሕዝብ ለማቃጠል መጥተው ሰው ከሚቃጠልበት ቤት እየተከፈለ ሲገባ አንድ የአምስት ዓመት ልጅ እናቱን እየጎተተ ‹‹ነይ እንደትናንቱ ዝናብ እንዳይመታን ቶሎ ከቤት እንግባ›› እያለ ሲያለቅስ ፣ እናቱም ስታለቅስ ቴዎድሮስ አይተው ‹‹ለምን ያለቅሳሉ?›› ብለው ጠየቁ። ልጁ የተናገረውን ቢነግሯቸው ‹‹ፈጣሪዬ ምነው እንዲህ ታደረገኛለህ! ወይ እኔን ቶሎ ግደልና ፍጥረት ይረፍ›› ብለው አልቅሰው ሊቃጠሉ የቀረቡትን ሁሉ ማሩት። ይህ ከሆነ ቦኃላ ደግሞ ጣና ሐይቅ ውስጥ ከምትገኘው ምጽርሐ ወደምትባለው ደሴት በደሴቲቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ በቤት ውስጥ እያስገቤ ቤቱን በማቃጠል ጨረሱት።
  8.ዶ/ር ብላንክ ስለ ቴዎድሮስ የጭካኔ ተግባር ከጻፉት ውስጥ አቶ ዳኛቸው የተረጎሙትን ብንመለከት፣ እ.አ.አ ህዳር 21 ቀን 1859 ዓ.ም ከሰዓት በኃላ አጼ ቴዎድሮስ የተመረጡ ጥቂት ፈረሰኛና እግረኛ አስከትለው ከጎንደር ግንብ ውስጥ እየተደበቁ የሚያስቸግራቸውን ሽፍቶች ለማጥፋት መገስገስ ጀምረው አስራ ስድስት ሰዓት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ሰማኒያ ማይልስ ርቀው ያለውን ጎዳና አንድ ጊዜ ስንኳ ሣይቆሙ ሲጓዙ አድረው ወገግ ሲል የጊንደር ከተማ ከሚገኝበት ተራራ ስር ደረሱ። ምንም እንኳን በድንገት ለመድረስ አቅደው የመጡ ቢሆንም፣ የጎንደር ነሪ ሕዝብ ወሬውን ሰምቶ ስለነበር በመጨነቅና በመሸበር ሴቶች ወጥተው በእልልታና በደስታ ሲቀበሉዋቸው በፋሲል ግንብ ተሰግስጎ የነበረውም ሽፍታ ሸሽቶ ከጎንደር ወጣ። ወዲያውም ሽፍቶችን ለማግኘት ሠራዊቱ ቤቱንና ቤተክርስቲያኑንም ሣይቀር መበርበርና መዝረፍ ያዙ። ዳሩ ግን ወዲያውም ሽፍቶችን ለማግኘት ሠራዊቱ ቤቱንና ቤተክርስተያኑንም ሣይቀር ባለማግኘታቸው ከአስር ሺ በላይ የነውን የከተማውን ነዋሪ ሕዝብ እንደ ከብት ሰብስበው ነዱት። ከዝህም በኋላ የጥፋት ሥራቸውን ጀምረው ሕዝቡን፣ ቤቱን፣ ቤተክርስጢያኑንና ቤተመንግስቱንም ጭምር በእሳት አቃጠሉት። ከቀሳውስት መካከል አንዳንዶቹ የደፈሩ አጉረምርመው የንጉሥ ነገሥቱን አፈጻጸም በግልጽ ተቃውመው ስላወገዙ ብዙ መቶ ሽማግሌ ቀሳውስት ወደ እሳተ ተወርውረው ተቃጠሉ። የማቃጠሉ ነገር ከዝህ ላይ ሳይቆም እልል እያሉ የተቀበሉት ሴቶችስ የት አሉ? እነርሱ እልል ባይሉ ኖሮ ሽፍቶች መምጣታችንን የት ያውቁ ነበር? በማለት ሴቶች ሁሉ ተይዘው እንዲመጡ አጼ ቴዎድሮስ በማዘዛቸው ሁሉም ከእነሕይወታቸው ወደተቃጠለው ቤት እየተወረወሩ ነደዱ…ብለዋል።
  9.በሸዋ ተሸመው የነበሩት የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ልጅ አቤቶ ሰይፉ በቴዋድሮስ ላይ ስለሸፈቱ ወደ ሸዋ መጥተው ሙቅምድር በሚባል ቦታ 500 ያህል ሰዎችን ማረኩ። ሁሉነም ቀኝ እጃቸውንና ቀኝ እግራቸውን እየቆረጡ ጣሉአቸው። በዝህም የተነሣ የሚከተለው ተገጠመ

  አጼ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ

  የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሄዱ።

  10 የጋረድ ጦር የዎድሮስ ወዳጅ የነበረውን እንግልዛዊ ፕላዉዲን ሊቀመኳስ ቤል ደግሞ ጋረድን ገደለ፣ የጋረድ ወንድም ቤልን ገደለ። ቴዎድሮስ በበኩሉ በጦርነት ላይ 1500 የጋረድ ሰዎችን ማርኮ ካስገደላቸው በኋላ ጭንቅላታቸውን ተቆርጦ እንደ ካብ እንደተደረገ አለቃ ወ/ማርያምና አለቃ ተክለየሱስ ጽፈዋል።

  ደራሲ ስብሀት ገብረ እግዝአብሔር…ስለካሣ ጭካኔ ሲገልጹ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ ሥጋ ደዌኛን እየሰበሰሁ ያቃጥሉ ነበር። ደብረ ታቦር ጎጆ ሲሰራ ያድራል። ቀን ደዌኛቹ እጎጆው ውስጥ ያታጎሩና እሳት ይለቀቅባቸዋል። ካሣ ከሞከራቸው ብዙ ሥራዎች አንዱ ሥጋ ደዌን በሂህ ዓይነት ከምድረ ኢትዮጵያ ማጥፋት ነበር›› ይላሉ።

  አጼ ቴዎድሮስ የፈጸሙአቸው ግፎች ብዙዎች አልተመዘገቡም። ከሽፍትነታቸው ጀምሮ እስከ እለተ ሞታቸው ሰዓት ድረስ ያለቀው ሕዝብ ብዛት ሥፍር ቁጥረ የለውም። ኋይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ከደጃዝማች ወንድራይድና ሌሎች መሣፍንት ጋር በተደረጉት ጦርነቶች ድል በድል ላይ እየተረማመዱ የመጡት ጊዜ ስለነበረ፣ በጦርነቱ ወክትም ሆነ ከጦርነቱ ቦኋላ በምርከኞች ላይ የተፈጸሙትን ግፎች በሙሉ መዘርዘር ያስቸግራል። ከሰባት ጊዜ በላይ ወደ ወሎ ዚዘምቱ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል፤ የብዙዎቹ ንብረት ወድሞአል፣ አብዛኛው የወሎ ጦር አካለ ጎደሎ ሆኖአል፣ ከአገር ተሰደዋል፣ እንደ እንጨት በእሳት ተማግደዋል። በየሰከንዱ ከሚለዋወጠው ጠባያቸው የተነሳ ሕዝቡን ለምህረት የተባለው ለመዓት፣ ለመዓት የተባለው ደግሞ ለምህረት እተዳረገና ሁሌም መዓትን እየጠበቀ የግፍ ጽዋውን ሲቀበል ኖሮአል።

  በተለይም የራስ አሊ ሁለተኛ ወታደሮች በ1853 ዓ.ም በአይሻል ጦርነት ላይ ካሸነፉ በኋላ ሁሉ ከቴዎድሮስ ጭካኔ አንጻር ተጠንተው ቢጻፉ ኖሮ የሳቸውን ማንነት ይበልጥ ግልጽ ያደርግ ነበር። የሚገርመው ግን ቴዎድሮስ በየትኛውም ዘመን ተደርጎ በማይታወቅ ደረጃ፣ በጥይት እየደበደቡ፣ በጎራዴና በሰይፍ ውስጥ በማጎር እያቃጠሉ፣ ያስጨፈጨፏቸውን ሰዎች ጭንቅላት እያስቆረጡ እንደ ድንጋይ ሲያስክቡ የሚውሉና በመጨረሻም እራሳቸው ‹‹እብድ ነኝ›› ፣ መለታቸውና ቀና ብለው ፈጣሪን እየተማጸኑ፣ ‹‹እባክህን ጌታዬ እኔን ግደልና ፍጥረትህ ይረፍ›› ብለው እስከ መጸለይ የደረሱ ጨፍጫፍ መሆናቸውን ለአስራ አራት ዓመታት አገርቷን የጦር አውድማ በማድረግ በኢኮኖሚ አድቀውና በመጨረሻም በታትነው መሞታቸው እየታወቀ ለማመስገን መጣር አሳፈሪ ከመሆኑም በላይ ያለአግባብ ሕይወታቸውን ባጡት ወገኖች ላይ መቀለድ ይሆናል።›› (ታቦር ዋሚ፣ የውገና ድርሰቶች እና የታሪክ እውነቶች፣ ገጽ. 418-424)

 2. ብርሃኑ

  October 3, 2017 at 9:54 am

  ዋዉ በጣጣጣጣጣም ደስ ደይላል፡፡ ምኑ እንዳትሉኝ!!አዘጋገባቹ እግዜር ያቆያቹ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top