News Feature

ወደ አሜሪካን ግቢ መግባት እየተከለከለ ነው | ፉሪ አካባቢ ፍተሻ ይስተዋላል | የአትክልትና ፍራፍሬ ቸርቻሪዎች በፖሊስ ተዘረፉ

(ቢቢኤን ዜና) በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ መግባትና መዉጣት እየተከለከለ መሆኑ ታወቀ። በልማት ስም ነዋሪዎች ተፈናቅለው በርካታ ቤቶች የፈረሱበት አሜሪካን ግቢ የብዙ ደሃ ነዋሪዎች ህይወት የተመሰቃቀለበት እንደሆነ ይታወቃል።ተለዋጭ ቤት ያላገኙ ተፈናቃይ የአሜሪካን ግቢ ነዋሪዎች ላስቲክና ሸራ ዘርግተው በዳስ ዉስጥ የሚኖሩ መኖራቸው ቢታወቅም ወደ ዉስጥ እንዳይገቡ ፖሊስ እየከለከላቸዉ መሆኑን ለቢቢኤን ገልጸዋል።

መርካቶ አሜሪካን ጊቢ የሚገኘው ታላቁ አንዋር መስጊድ

ቤታቸው የፈረሰባቸው የአሜሪካን ግቢ የቀድሞ ነዋሪዎች መካከል ተለዋጭ ቦታን ያገኙ መኖራቸው ይታወቃል።ባንጻሩ ተለዋጭ ቦታን ያላገኙ ወይም ተለዋጩ ቦታው አይመጥነንም ያሉ ቤተሰቦች መድረሻና ማረፊያ የሌላቸው በመሆኑ ቦታዉ ላይ ዳስ ሰርተው እንደሚኖሩ ይገልጻሉ። እነዚሁ ነዋሪዎች «እቃችንን ከሰራነው ዳስ ገብተን እንዳናወጣ መንግስት መግቢያና መዉጫዉን በፖሊስ አጥሮ እያሰቃየን በመሆኑ እሮሮአችንን ህዝብ ይስማልን» ሲሉ ይጣራሉ።

አሜሪካን ግቢ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰፈሩበት ቦታ ሲሆን ጠንከር ያለ የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይበት ቦታ እንደነበር ይታወቃል። በህወሃት የሚመራዉ መንግስት ቦታዉን በልማት ስም ካፈራረሰዉ በሗላ በስፋራው ለአያሌ አመታት ሰፍረው የነበሩ ነዋሪዎች ህይወት መናጋቱ ቢታወቅም የሚመለከተው አካል አመርቂ መፍትሄን ማምጣት ባለመቻሉ ዜጎች አደጋ ላይ መዉደቃቸው አነጋጋሪ እየሆነ ነው።

ሰዎች የተፈናቀሉበት ልማትና እድገት በተቀላጠፈ መልኩ ባልተከናወነበት መልኩ የብርድ፣የዝናብና የበሽታ ሰለባ በመሆን ዳስ በመስራት በጊዜያዊ መጠለያ ዉስጥ የሰፈሩ ሰዎች ያስቀመጧቸዉን እቃዎች እንዳያነሱ ወይም በእቃዎቹ እንዳይገለገሉ በመደረጋቸው በጣሙን ይማረራሉ «አገር አልባ የሆንን መስሎን እንድንሸማቀቅ ሆነንናል! » ሲሉም ይገልጻሉ።

ማደሪያ ቦታ ተከራይተን ለመኖር አቅም የለንም።ቤት ለመከራየት በቂ ገንዘብ የለንም። ወደ ዳሳችን እንዳንገባ መደረጋችን ደግሞ ድርብ ጭቆና ነዉ የሚሉት ነዋሪዎች ለቢቢኤን በላኩት በድምጽና በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ ክልከላዉን የሚያስፈጽሙት የፖሊስ አካላት ወደ አሚኤሪካን ግቢ ማስገባትና ማስወጣቱ ላይ ምንም አቅም እንደሌላቸዉና ከበላይ አድርጉ የተባሉትን የሚያስፈጽሙ መሆናቸዉን በአዘኔታ ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ቢቢኤን ሁናቴዉን ለማጣራት ወኪሉን ወደ ቦታዉ ልኳል። ፖሊሶቹ መታወቂያን በማየት የተወሰኑ ሰዎችን ፈትሸው የሚያስገቡ ሲሆን ክልከላዉን ግን በተግባር ሲያስፈጽሙ የሚያመላክት የድምጽ መረጃን ለመያዝ ችሏል።

ፉሪ አካባቢ ፍተሻ ይስተዋላል

በልማት፣በመገድ ስራና በኤሌክትሪክ አቅርቦት መንግስት ችላ ያላት ፉሪ ፍተሻ እንደሚከናወንባት ያካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢኤን ገለጹ። ፍተሻዉ በነዋሪዎች ላይ ጫና ለማሳደርና ለማሸማቀቅ የታቀደ መሆኑን ነዋሪዎቹ እያስረዱ፤ ፉሪ አዲስ አበባ ጫፍ ላይ የምትገኝ በመሆኗ የኦሮምያዉ የቄሮ (የወጣቶች) እንቅስቃሴ ወደ አዲስ አበባ ይገባል የሚል እምነት እያየለ በመምጣቱ ሳቢያ «ህወሃት መራሹ መንግስት ፍርሃቱን የሚገልጽበት ድንገተኛ ትርኢት» ሲሉ ነዋሪዎች ሒደቱን ይገልጻሉ ።

በህወሃት የሚመራዉ መንግስት የሸዋ ኦሮሞዎችና ጉራጌዎች ይኖርባታል ብሎ በአይነ-ቁራኛ የሚጠብቃት ፉሪ ቀደም ሲል ጽኑ የቄሮ እንቅስቃሴ የታየባት ቦታ መሆኗንም ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ። ከኦሮምያ የሚነሳዉን ተቃዉሞን ተቀብላ ወደ አዲስ አበባ ታሻግራች ተብላ በህወሃት መራሹ መንግስት ዘንድ በስጋት የምትታየዋ ፉሪ በተደጋጋሚ መንግስትን በመቃወም ህዝባዊ ድምጽ የሚሰማባት በመሆኑ ፍተሻዉ የመንግስትን ስጋት አመላካች መሆኑን ነዋሪዎቹ ዳግም ያስረዳሉ።

በፍሪ አካባቢ በርካታ የጉራጌ ሰፋሪዎች ያሉ በመሆናቸውና ጉራጌዎች መንግስትን ይቃወማሉ የሚል እምነት በመግስት በኩል ያለ በመሆኑ፤ ሊፈጠር የሚችለዉን ህዝባዊ ቁርኝት በመፍራት መንግስት በተደጋጋሚ ጫና እንደሚያሳደር የፉሪ ነዋሪዎች ያስረዳሉ። ሌላዉ ቀርቶ በተለምዶ የምንይዛቸዉን ከዘራዎች ሳይቀር ፖሊሶች ይነጥቁናል የሚሉት የፉሪ ነዋሪዎች፤ እኛን ለማሸማቀቅ መሞከሩ የቅዋሜ ስሜታችንን የሚያጠናክር ቢሆን እንጂ አያለዝበውም ሲሉ ያስረዳሉ።

ፉሪ በተደጋጋሚ በጎርፍ አደጋ እንደምትጠቃ፣ በቂ የመብራት አግልግሎት የማታገኝ፣ በዉስጧ ያሉ ጉራጌ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉና እንዲወጡ በህወሃት በሚመራዉ መንግስት ጫና የሚደረግባቸው መሆኑን ቢቢኤን መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ስራዉን በተገቢው መልኩ አያከናዉንም ተባለ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች የከተማዉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት የቢዝነስ ቢሮዎች ስራቸዉን በተገቢው መልኩ የማያከናዉኑ በመሆናቸው ጉዳይ የማስፈጽም ችግር እንደገጠማቸው አሳወቁ። ደንበኞቹ ለሚገጥማቸው ያልተስተካከለ የዋጋ ጭማሪ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥና ሌሎችንም ችግሮች በተገቢዉ መልኩ ጉዳያቸዉን የሚፈጽምላቸው አካል ማጣታቸዉ እንዳሳዘናቸው ለቢቢኤን ገልጸዋል።

በድርጅቱ ዉስጥ ያሉት ሰራተኖች «ታመናል፣የሻይ ሰዓት ላይ ነን፣የመስክ ስራ አለብን» በሚል ምክያት በስራ ገበታ ላይ እንደማይገኙ ጉዳይ ለማስፈጸም በየቀኑ የሚመላለሱ ደንበኞች አሳዉቀዋል። በጥበቃ ተግባር ላይ የተሰማሩ የድርጅቱ ሰራተኞችን ቢቢኤን ጠይቆ ለመረዳት እንደቻለው ከስራ ገበታ የመሰወሩ ጉዳይ ከላይ ካሉት ሐላፊዎች ጀምሮ እስከታች ባሉ ሰራተኞች የሚፈጸም በመሆኑ ጉዳዩ ለነርሱም ግራ እንዳጋባቸዉ ገልጸዋል።

ለገጠማቸው የኤሌክትሪክ ችግር መፍትሔን ለመሻት ወደ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ቢዝነስ ቢሮ ያቀኑት ደንበኞች ድርጅቱ እራሱ በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያጣበት አጋጣሚ በመኖሩ «ሲስተም በመዘጋቱ መፍትሄ የለንም» የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ።

በተለይ አይር ጤና የሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍ ቢሮ ምንም አይነት ግልጋሎት መስጠት አቁሟል እስኪባል ድረስ ደንበኞች የሚጉላሉበትና የሚቸገሩበት ቦታ መሆኑን ቢቢኤን ከደረሰው የድምጽና የፎቶ ማስረጃ ለማወቅ ችሏል።

ኢትዮጵያ ለኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክን ሀይል በሽያጭ ትልካለች በማለት የህወሃት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ቢገልጹም፤ አገሪቷ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ እጥረት ሳቢያ ችግር ላይ መሆኗ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይዘገባል።ከኤሌክትሪክ ሽያጭ የሚገኘዉ ገቢ በጅ አዙር ወደ ቱባ የህወሃት ባለስልጣናት ኪስ ይገባል የሚል ክስ በተደጋጋሚ ቢዘገብም በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት የሰጠዉ አስተያየት ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም።

በመላ አገሪቱ ያለዉ የኤሌክትሪክ ችግር ሳይቀረፍ ለጎረቤት አገራት በሽያጭ ይቀርባል የሚባለው የኤሌክትሪክ ሐይል የጎረቤት አገራትን ለማላዘብና አገር ዉስጥ ያለዉን ህዝባዊ ተቃዉሞን ለማፈን የሚደረግ የሙስና ተግባር ነዉ የሚል ክስ በተደጋጋሚ እንደሚቀርብ ይታወቃል። የአባይ ግድብ ተገድቦ ሲያልቅ ኢትዮጵያ ሰሜን አፍሪካን የሚያካልል የኤሌክትሪክ ሽያጭ ታከናውናለች በማለት ባለስልጣናቱ በተደጋጋሚ ቢደሰኩሩም፤ የግድቡ ግንባታ ወደ መቋረጥ እየተቃረበና ሰራተኞች ስራቸዉን አቋርጠው ወደ ቀዬአቸዉ እየሄዱ መሆናቸዉን ወይም ወደ ጎረቤት አገር መሰድድ መጀመራቸዉን ምንጮችች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ለደንበኞቹ ግልጋሎት መስጠት ተስኖት ሲንገዳገድ መስተዋሉና እራሱ ድርጅቱ የኤሌክትሪክ እጦት ተጠቂ መሆኑ፤ አገሪቷን መራለሁ የሚለዉ ማእከላዊ መንግስት ነገሮች ከቁጥጥር ዉጪ እንደሆኑበት አመላካች ነዉ የሚል አስተያየት እየተሰጠበት ነው።

የግድቦች ግልጋሎት ተዛንፎ፣ህዳሴ ተብሎ በቦንድ ስም ገንዘብ የተዘረፈበት የአባይ ግድብ ግንባታ ተስተጓጉሎ፣ዜጎች በመብራት እጦት የፈረቃ ግልጋሎት ሲያገኙ፣ በህወሃት የሚመራዉ መንግስት የኤሌክትሪክ ሐይልን ለጎረቤት አገር መስጠት መቀጠሉ መንግስቱ ለአገሩ ህዝብ የሚያስብ አለምሆኑን አመላካች ነዉ በማለት መንግስትን የሚቀናቀኑ አካላት ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባ ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ደንበኞች ተገቢዉን ግልጋሎት የሚሰጣቸው አካል አጥተው መንገላታታቸው ቀጥሏል።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት የአሰራር መዛነፍ የዉስጥ አሰራር ችግር ነዉን? ወይስ በድርጅቱ ዉስጥ የሰረጸ ጥልቅ የስነ-ምግባር ብልሹነት? ብዙዎች የማእከላዊ መንግስቱ ክሽፈት ነዉ በማለት ይመልሳሉ። መሰል የአሰራር ችግሮች በደርግ የዉድቀት መባቻ ክፍለ-ግዜ ተስተዉሏልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ችግር የአይቀሬዉ ለዉጥ አካል ነው የሚል አንደምታ አለ።

ከአፍሪካ መዲናነት ወደ ምሬት መናኸሪያነት 

አዲስ አበባ ዉስጥ ምሬት ሁሉም ቦታ ይሰማል። ሰዉ በመብራት እጦት፣በትራስፖርት ችግር፣በኑሮ ዉድነት ይማረራል። ህዝቡ ህወሃት በሚያደርስብኝ ጭቆና ተንገፈገኩ ቢልም ምሬቱን ወደ ተግባራዊ ለዉጥ አሻግሮ እንዳይነሳ ጫናዉ መቀጠሉ ይስተዋላል። የፖሊስ ስምሪት ጨምሯል፣የመከለከያ ሰራዊት በመዲናይቱ ገብቶ የፍርሃት ጥላን ለማጥለል ይሻል፣ ደንብ አስከባሪዎች የፖሊስን ተግባር የሚጋሩ ይመስላል፣ድህንነቱ በየጎዳናዉ ይርመሰመሳል ይላሉ ነዋሪዎች።

ቢቢኤን ያነጋገራቸዉ ባለሱቆች እንደገለጹት ስኳር ከሚገባዉ በላይ ተወዷል ። የስኳር ዋጋ እስከ ሐምሳ ብር በኪሎ ገብቷል የሚሉት እነዚህ ነጋዴዎች፤ የስኳሩን ያህል ነዳጅ አልተወደደም በማለት ያነጻጽራሉ። ባለሱቆቹ ስኳርን ከአከፋፋዮች ገዝቶ ለተጠቃሚ ለማቅረብ መኮሮኒ፣ፓስታና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን እንድንገዛ እንገደዳለን ይህ ደግሞ አቅማችንን ያቃዉሳል ሲሉ ያማርራሉ። በመንደር ዉስጥ ያሉ ትናንሽ ሱቆች እንደ አቅማችን ስኳር ገዝተን ለደንበኞች ለማቅረብ ብንሞክርም፣ ስኳርን ለማግኘት እንድንገዛ ከምንገድባቸዉ ሸቀጦች በተጨማሪ አቅማችን ከሚችለዉ በላይ አስር ኪሎ ስኳር መግዛት እለብን ሲሉ እየገጠማቸው ያለዉን ችግር ለቢኤን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በማራቆት በህወሃቱ በአባይ ጸሐዬ የሚመራዉ የሙስና ግብረሐይል ብዙ ወንጀሎችን መፈጸሙን ቢቢኤን በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል። በህወሃት የሚመራዉ የኢትዮጵያ መንግስት ስኳርን ወደ ዉጪ በመላክ (ኤክስፖርት በማድረግ) ዳጎስ ያለ የዉጭ ምንዛሪ ወደ ኪሱ ያስገባል የሚል ክስ ይቀርብበታል። ወደ ዉጪ ተላከ የሚባለው ስኳር የዉጭ ምንዛሪ አስገኝቶ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ለዉጥ ሊያመጣ ቀርቶ ለስኳር ፋብሪካዎች ጥገና ሊተርፍ አልቻለም የሚሉ ተንታኞች ከስኳሩ በስተጀርባ ከፍተኛ የህወሃት ዝርፊያ ሊኖር እንደሚችል ፍንትዉ አርገው ያሳያሉ።

በኑሮ ምስቅልቅልታ የሚንገላቱት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በስርዓቱ ከመገፍገፋቸዉ የተነሳ «ወይ ህወሃቶች ይጨርሱን ወይ እኛ እንጨርሳቸዉ! » ወደሚል ተስፋ የመቁረጥ ደረጃ ላይ መድረሳቸዉን ይናገራሉ።  እንደ አንዳንድ አዲስ አበባ ነዋሪዎች አገላልጽ ይህ ህዝባዊ ቁጭት ወደ ተግባራዊ እንቢተኝነት ተቀይሮ ስርዓቱ የሚገፋበት ቀን እሩቅ አለምሆኑን ቢገልጹም ህወሃት መራሹ መንግስት ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎችን ትግራይ ዉስጥ አስገብቶ ማከማቸቱን ያወሳሉ። አዲስ አበባ ዉስጥ የህወሃት አምባገናዊ ጉዝጓዝ እንዳይነሳ የፖሊስ፣የደህንነትና የጦር ሐይሉ ስምሪት የላቀ ቢሆንም ይህ ሐይል ህዝቡን የሚቀላቀልበት ቀን ሩቅ አለመሆኑን የሚተነብዩ ብዙ ናቸዉ።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን የፕሮፓጋንዳ ግዝፈት የታጠረው ማእከላዊ መንግስት ያለ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ኦናዉን ቀርቶ ህዝብን ማወኩ ይነገራል። አዲስ አበባ ፈጣን የባቡር መስመር ስለተዘረጋላት የትራንስፖርት ችግር ይቀረፋል የባቡር መስመሩም ለ አፍሪካ አርአያ ነው ተብሎ ተደሰኮረና የፕሮፓጋንዳ ቀዉጢ ከትላልቅ ባልስልጣናት እስከ ትንሽዬ ካድረዎች ሳይቀር ተነዛ።መንገድ ተቆፈረ፣ትቦ ተሰረሰረ፣ህይወት ታወከ ባቡሩ ለወጥ ሳያመጣና በኤሌክትሪክ ችግር ሲንገዳገድና ሲንተፋተፍ ከተማይቱ ዉስጥ የነገሰዉ የትራንስፖርቴሽን እጦት በዚች አገር ባልተፈጠርኩ ያሰኛል-ይላሉ ዜጎች። «ታክሲ አጣሁ፣ በጨላማ ረጅሙን መንገድ ልወዝወዘው በግሬ ብዬ ወደ ቤቴ ነካሁት፣ ይህ ደግሞ ያንገፈግፋል» ይላሉ የመረራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ።

የኑሮ ዉድነቱ ቢከፋም፤ አዲስ አበባ በጧት ጸሃይ፣ በምሽት ጨረቃዎች መካከል የግዜ ስሌትን ትቆጥራለች። አራት ኪሎ አካባቢ የሚፈነጠቅ የለዉጥ ወጋገንን ዜጎች ይጠብቃሉ። ከሚያንገበግባቸዉ ራብ በላይ፣ በነጻነት ጥማት የሚቃጠሉ በዝተዋል። ህወሃትን ህዝቡ ጠልቶታል። ጥላቻዉን ለመግለጽ አያቅማምም።ዝም ብዬ አልፈነዳም ብሎ ይናገራል።ምሬቱ ታክሲ ዉስጥ፣አዉቶብስ ዉስጥ፣ በየሰልፉ፣በየ ጉሊቱ፣በየንግድ ድርጅቱ፣የመንግስት መስሪያ ቤት ዉስጥ፣ትምርት ቤት ዉስጥና ሁሉም ቦታ ካልደፈረሰ አይጠራም ባዩ በዝቷል።እዚያም እዚም ህወሃት የሚባል መንግስት መረረን በቃን የሚል ድምጽ በመነጫነጭና በሹክሹክታ ይሰማል። ከዚህ «የራሱ ጉዳይ! » ከሚለዉ መሪር ቁጣ ባሻገር፤ በመዲናይቱ ዉስጥ እንደ ራስዳሽን ተራራ የገዘፈ የተዉሞ ዝምታ አይሏል።

ለምግብ ፍጆታ የሚያስፈልጉ ሸቀጣ ሸቀቶች እየጠፉ ነዉ። «ስኳር የስኳር በሽታ ሆኖ በሰው ደም ዉስጥ ግብቶ መሰወሩን አብዝቷል»ተብሎ እስኪቀለድ ድረስ ስኳር ተሸሽጓል። 44ሺ ኩንታልን ስኳርን የጫኑ የጭነት መኪናዎች ወደ ኬንያ ሊያዘልቁት የነበረው ጭነት ሞያሌ ከተማ ዉስጥ መታገቱ ተዘግቧል። የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ሁለት ወር በሙሉ ስኳሩን እንደጫንን ታግተናል፣ ስኳሩ እየተበላሸ ነዉ ብለዉ እሮሮ አስምተዋል። የክልል የግምሩክ ባለስልጣን በኦሮምኛ በሰጠው ቃለ ምልልስ «ስኳሩ ደረጃዉን ያልጠበቀና ተገቢው ሰነዶች ያልቀረቡቡት ነው!! ድንበርን አልፎ ወደ ኬንያ አይዘልቅም» ሲል ዉርድ ከራሴ ብሏል። ከስኳር ጋር የተወዳጁት የህወሃቱ የሙስና ቁንጮ አባይ ጸሃዬና ሌሎችም ቱባ የጦር አበጋዞች በሙስና የተጨማለቀ እጃቸዉ የተልፈሰፈሰ ይመስላል።

ያች የአፍሪካ መዲና የተባለችዉ አዲስ አበባ ከህወሃት የምጸት የከፍታ ዘመን ሰማይ በታች ከፍቷታል። አዲስ እበባ ቂም ይዛለች።እንደ መብረቅ ብልጭ ይላል የሚባለዉ አምባገነናዊያንን የሚያኮማትረው ህዝባዊ ሐይል እስኪፈነጠቅ ድረስ በአዲአ አበባ ዙሪያ ባሉ አጎራባች መንደሮች የጎላ ድምጽን ያሰማሉ «ዳዉን ዳዉን ወያኔ! ቻዉ ቻዉ ወያኔ! ወያኔ ኑገዬ» ይላሉ።ይህ የድምጽ ማእበል በፊንፊኔ (አዲስ አበባ) ሰማይ ላይ ደመና ሆኗል። ይህ ዝናብ ዘንቦ የአዲስ አበባን ምሬት በነጻነት ዶፍ ያጥበው ይሁን? በሒደት የሚታይ ይሆናልና ልብ ያለዉ ልብ ይበል።

የአትክልትና ፍራፍሬ ቸርቻሪዎች በፖሊስ ተዘረፉ

ኑሮን ለማሸነፍ አትክልትና ፍራፍሬ የሚቸረችሩ ለፍቶ አዳሪዎች በፖሊስ መዘረፋቸው ታወቀ።በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ከሶማሌ ተራ እስከ ኸሊፋ ህንጻ ባለው መስመር ላይ አታክልትና ፍራፍሬ እየሸጡ የሚተዳደሩት ደሃ ኢትዮጵያዉያን ፖሊስ በድንገት መጥቶ ለምን እቃቸዉን እንደበተነባቸዉና እንደዘረፋቸዉ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

በስፍራዉ የተሰማሩት ፖሊሶች ጾታ እድሜን ሳይለዩ የአታክልትና ፍራፍሬ ቸርቻሪዎችን በመደብደብ እና የጭንነት መኪና በማምጣት የለፍቶ አዳሪዎቹን እቃ መዝረፋቸው ታዉቋል። ነጋዴዎቹ አቅማቸዉ በቻለው መጠን አምራች ዜጋ ለመሆን እየጣሩ መሆናቸውን ለቢቢኤን የገለጹ ሲሆን፣ ለረጅም ግዜ በመንገድ ዳር ሸቀጣችውን በመዘርጋትና በተንቀሳቃሽ ጋሪ በማዘዋወር የሚነግዱ መሆናቸዉን አሳውቀዋል።በዚሁ የመዉረስና የዝርፊያ ተግባር ላይ ከፖሊስ በተጨማሪ ደንብ አስከባሪዎች መሰማራታቸው ቢቢኤን በጁ ከገባዉ የፎቶ ግራፍ ማስረጃ ለማወቅ ችሏል።

በእድሜ ወጣት የሆኑት የአታክልትና የፍራፍሬ ቸርቻሪዎች «ሸቀጣችንን ለዛሬ መልሱልን ሁለተኛ በተመሳሳይ ንግድ ላይ አንሰማራም» በማለት እያለቀሱ ቢማጸኑም፤ፖሊሶቹ ከመደባደብ በስተቀረ ሆዳቸዉ ሲራራ አልተስተዋለም።ወጣቶቹ በተመሳስይ ንግድ ለመሰማራት ፍቃድ እንዳላቸዉ ተጠይቀው ሲመልሱም «በአነስተኛ እና ጥቃቅን ትደራጃላቹ ይሉናል እንጂ ተደራጅተን ለመስራት በምናድረገው ጥረት አመርቂ ዉጤት አልታየም» ሲሉ የገጠማቸዉን አስረድተዋል።አክለውም «እነርሱ የሚፈልጉን ለፖለቲካ ፍጆታቸዉ ነዉ።እኛ ደግሞ ስራ ሰርተን እራስችንን እና ቤተሰባችንን ለመጥቀም ነዉ» በማለት በአነስተኛ እና ጥቃቅን የመደራጀቱን ኪሳራ ያብራራሉ።በመንግስት ስም መለዮ የለበሱ ፖሊሶችና ደንብ አስከባሪዎች ዘርፈዉናል፣ደብድበዉናል፣ አሳደዉናል። የራሳችን የሆነ የላባችንን ዉጤት ሲዘርፉን፣ ሸቀጥን ለመግዛት የተበደርነዉን እንዳንከፍል ሲያደርጉን፣ እንስራ ባልን ባለ እዳ ሲያደርጉን ህግን የማስከበር መለዮ የለበሱት የመንግስት አካላት እኛን በገሃድ እያስተማሩን ያለዉ ተመሳሳይ የዝርፊያ ወይም የሌብነት ስራ እንድንሰራ ነዉ ብለዋል።

ሁናቴውን የተመለከቱ አንዳንድ ታዛቢዎች፣ በህወሃት የሚመራዉ መንግስት ጉራጌ ነጋዴዎችን ከሱቅ፣ከመንገድ ላይ ችርቻሮ፣ከጉሊት ላይ ምክንያት እየፈለገ ማሳደድ ከጀመረ ቆይቷል ይላሉ። አታክልትና ፍራፍሬ የሚሸጡት ለፍቶ አዳሪዎች ከየተኛው ብሔር እንደሆኑ በዉል ተለይቶ ባይታወቁም ይህ ጉራጌዉ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይመስላል ሲሉ ገልጸዋል።

በጎዳና ላይ የሚደረግ ችርቻሮ በአፍሪካ አገራትና በመካከለኛዉ ምስራቅ በስፋት ይከናወናል። ከአዉሮፓ ጎዳኖች እስከ አሜሪካ ትላላቅ ከተሞች ይኸው የጎዳና ላይ ንግድ የሚተገበር ቢሆንም የየአገራቱ መንግስታታ ንግዱን ፈር ለማሲያዝ ነጋ ዴዎችን ያግዛሉ እንጂ ተመሳሳይ ስራን አይሰሩም የሚል አስተያየት አለ።ቸርቻሪዎቹ በጠራራ ጸሃይ ተዘርፈዋል። ለፍቶ ማደረም ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከለከለ ይመስላል።ምን ይሻላል? የሚለዉ የዜጎች ጥያቄ ነው።

የኦሮምኛ ቋንቋ ትምርት ቤቶች ከአንበሳ አዉቶቢስ ጋር የነበራቸዉ ዉል እክል ገጠመው

በአዲ አበባ ከተማ ዉስጥ ለተከፈቱት የኦሮምኛ ቋንቋ ትምርት ቤቶች የትራንስፖርት ግልጋሎትን ለመፈጸም የኦሮምያ ትምርት ቢሮ ከአንበሳ አዉቶብስ ጋር ተስማምቶት የነበረዉ ዉል እክል እንደገጠዉ ታወቀ። የኦሮምያ የትምርት ቢሮ የተፈራረመዉ ዉል ተግባራዊ ሆኖ ግልጋሎት ሊሰጥ ቀናት ሲቀሩት በህወሃት በሚመራዉ መንግስት ዉሉ እንዲሰረዝ ግፊት ማደረጉን ቢቢኤን ለማወቅ ችሏል።

በኦሮሚያ የትምርት ቢሮ ዉስጥ የሚገኙ የቢቢኤን ምንጮች እንዳሳወቁት ዉሉ ያለቀና ለመተግበር ቀናቶች የቀሩት ቢሆንም የህወሃት ሰዎች ግልጋሎቱን በራሳቸዉ የአዉቶብስ ኩባንያዎች ለመስጠት የፈለጉ እስኪያስመስልባቸው ድረስ ጣልቃ በመግባት ዉሉ እንዲስተጓጎል ጫና አድርገዋል ሲሉ የትምርት ቢሮ ምንጮች ለቢቢኤን አሳዉቀዋል።

የህወሃትን ጣልቃ ገብነት ተከትሎ የኦሮሚያ ትምርት ቢሮ ሌላ የአዉቶብስ ግልጋሎትን እየፈለገ መሆኑን የገለጹት የቢቢኤን ምንጮች፤ ህወሃት ጣልቃ የማይገባበትን የተሻለ ግልጋሎት ለተማሪዎቹ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑ ታዉቋል። አስቸኳይ መፍትሄን ለማምጣትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስቀጠል «ኦዳ» የተባለዉን የአዉቶብስ ግልጋሎት ለነዚሁ ኦሮምኛ ቋንቋ ትምርት ቤቶች ለማቀረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸዉን አሳዉቀዋል። እነዚሁ የቢቢኤን ምንጮች እክለው እንዳሳወቁት «ኦዳ» አዉቶብስ ለተማሪዎቹ ግልጋሎት መስጠት ሲጀምር ህወሃት ዳግም ጣልቃ ለመግባት የሚጥር ከሆነ ጸቡ ከትምርት ቢሮው ጋር ሳይሆን ከህዝቡ ጋር ነዉ ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በህወሃት የሚመራዉ መንግስት አገሪቷን የሚበዘብዙ የትግራይ ተወላጆች ብቻ የሚቆጣጠሯቸው ኩባንዎች ያሉት እንዳሉት በተደጋጋሚ ይዘገባል።ህወሃት በኢትዮጵያ ቴሌ-ኮምንኬሽን ከሚፈጸሙ ትላልቅ ኮንትራቶች እስከ ተራ የቤት ግንባታ ድረስ በመግባት መስል ኮንትራቶችን እንደሚያበላሽ ወይም ለራሱ ያደርጋል የሚል የህዝብ ብሶት አለ።

ቢቢኤን በቴሌኮምንኬሽን መስሪያ ቤት ካሉ ምንጮቱ ቀደም ሲል ለመረዳት እንደቻለዉ ቴሌ በጨረታ ያቀረበዉን የኮንትራት ስራ የቻይና ኩባንያ ሲያሸንፍ ህወሃቶች ዉሉን በማበላሸትና ጣልቃ በመግባት ጨረታዉን ተቆጣጥረውት ነበር።ህወሃቶች ኮንትራቱን ወስደው ስራዉን ሳይጀመሩ ህወሃቶች በሳምንታት ዉስጥ ጨረታዉን ላሸነፈው የቻይና ኩባንያ መልሰዉ ኮንትራቱን በመስጠት 20 ሚሊዮን ዶላር እጅ-በጅ ማትረፋቸዉን የቴሌ ምንጮች አሳዉቀዋል።ህወሃቶች በኦሮም ያ የትምርት ቢሮና የ አንበሳ አዉቶቢስ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸው በቢዝነሱ አለም ዉስጥ እየገነቡት የመጣው ከመተን ያለፈ ማን አለብኝነትና እብሪት ዉጤት መሆኑን እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

የኦሮምያ የትምርት ቢሮ ከአንበሳ አዉቶብስ ጋር የተዋዋለው ዉል ህወሃት ጥቅም ቢያገኝበት ኖሮ አይሰረዝም ነበር በማለት የሚገልጹት ምንጮች ምን አልባትም የህወሃት ባልስልጣናት የሙስናና የስርቆት ዉጤት የሆነው «ሰላም» ባስ በኦሮምያ ዉስጥ ሲንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥቃት እደረሰበት በመሆኑና ለኪሳራ በመዳረጉ፤ ቂመኛው ህወሃት ብድር ለመመለስ ፈልጎም ሊሆን ይችላል ሲሉ ተሳልቀዉበታል።የኦሮምያ የትምርት ቢሮ ያለ ህወሃት ፍቃድ «ኦዳ» አዉቶብስን አሰማርቶ እንደምን ስራዉን ማቀላጠፍ ይቻላል? የሚለዉ አነጋጋግሪ ነው። ዉጤቱ ግን በሒደት የሚታይ ይሆናል።

1 Comment

1 Comment

 1. NANA

  October 11, 2017 at 5:34 am

  WHEN I read fake fictitious stories

  IT MAKES ME LOVE TPLF MORE . JOIN THE OMNI POTENT AND OMNI PRESENT TPLF AND FIGHT POVERTY .

  FAKE NEWS MAKES PEOPLE LOVE TPLF MORE .THE OPPOSITE IS HAPPENING TO THESE LIE MACHINE MEDIAS .

  THE MORE THEY LIE , THE MORE PEOPLE LIKE TPLF /EPRDF.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top