News Feature

ታቦት ለማስገባት የወጡ 3 ወጣቶች በኤሌክትሪክ አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

ከዲ/ን አባይነህ ካሴ

በዛሬዋ ዕለት (ጥር 12 / 2010) 4 ወጣት ሰማዕታት ነፍሳቸውን ለሃይማኖት ሰጡ:: የድል በር መድኃኔዓለም ታቦት ከጥምቀተ ባሕሩ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመለስ በኤሌክትሪክ አደጋ ምክንያት ሠረገላውን ይገፉ ከነበሩት ወጣቶች ሦስቱ ወዲያውኑ ሲያርፉ አንደኛው በሆስፒታል የሕክምና ርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ሶስቱን ሰማዕታት ተቀላቅሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶቻችን ለታቦታቱ ክብር ሲባል በሰው የሚገፋ ሠረገላ እየሠሩ በሚያስደንቅ እና በሚያስመሰግን ላቅ ያለ ደረጃ በዓለ ጥምቀት እንዲከበር የአንበሳውን ድርሻ እየያዙ ነው፡፡ ወጣት ያላት ቤተ ክርስቲያን ሕያዊት ናት፡፡

በጀቱን ከኪሳቸውና ከምእመናንን እየሰበሰቡ እግዚአብሔርን በሚገባ ያከብራሉ፡፡ የሰው ፊት እየገረፋቸውም ቢኾን እነርሱ በዓለ ጥምቀትን በልዩ መልክ ለማክበር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ከተማዎቻችንን በልዩ ልዩ መንገድ ሲያሸበርቋቸው የሚሰስቱት ጉልበትና ጊዜ የላቸውም፡፡ ማድመቅ ብቻ ሳይኾን ሥርዓት በማስከበርም ፖሊስን እያስናቁት መጥተዋል፡፡ ያመነን ሕዝብ መቆጣጠር መድከም ብቻ ነው ትርፉ፡፡

የድል በር መድኃኔዓለም ታቦት በሚያስደንቅ ሕዝብ ታጅቦ በመጓዝ ላይ ነው፡፡ ሠረገላው በጣም ቁመተ ረጅም ነው፡፡ ታቦተ መድኃኔዓለም ወደ መንበረ ክብሩ ሲመለስ በነበረው ደማቅ አሸኛኘት የሠረገላው ግርማ ሞገስ የበለጠ በዓሉን አድምቆታል፡፡ ይህም የኾነው በወጣቶቻችን ብርታት እና ቅንነት ነው፡፡

ከእነዚህ አድማቂዎቻችን መካከል በዘንድሮው በዓለ ጥምቀት አራቱ የክብር አክሊል ተቀዳጅተዋል፡፡ ለታቦታቱ ክብር ሲባል ከብረት የተሠራውን ሠረገላ እያንቀሳቀሱ በውስጥ መንገዶች በኩል እያለፉ ሳለ፤ ድንገት ቁመተ ረጅሙን ሠረገላ ወደ አንድ ቤት ተጠልፎ የሚገባው የኤሌክትሪክ ገመድ ይነካዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ላዩ ብረት፣ መዋቅሩ ብረት፣ ማገሮቹ ብረት፣ መግፊያና መሸከሚያዎቹ ብረት የኾነው ሠረገላ ጨብጠውት የነበሩትን ዐራቱን ወጣቶች እየተቀባበለ ባወረደው የኤሌክትሪክ እሳት ጠበሳቸው፡፡

ሦስቱ ወዲያውኑ በታቦቱ ፊት ወደ ተዘጋጀላቸው መንግሥት በክብር ሔዱ፡፡ አንደኛው ግን በቅርብ ወዳለ ሆስፒታል ደርሶ ርዳታ እየተደረገለት ቢቆይም ቀኑ ናትና ሌሎቹን ሶስት ሰማዕታት ተከትሎ ሄዷል፡፡

ወጣትነት እንደዚህ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ መገኘት ነው!
ደግ እየሠሩ መሞት መታደል ነው፡፡ ክፉ እየሠሩ ሞት የማይነካቸው አሉና፡፡ የእነዚህ ወጣቶች ታሪካቸው የቀድሞው ሳይኾን ይህኛው ነው፡፡ የተገኙት ታቦተ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ ነው፡፡ ከሁሉም ሥራቸው የሚበልጠውን ሲያደርጉ እግዚአብሔር ጠራቸው፡፡ ወጣትነትን ሲያውቁበት እንዲህ ያለ ሽልማት ያስገኛል፡፡

_____

ዐራተኛው ሰማዕት የቀደሙትን ተከትሏቸዋል ቀብራቸውም አሁን ይፈጸማል!

ከጥቂት ሠዓታት በፊት ይህንን ሰማሁ፡፡ ሳያወጋን በመሔዱ በጣም ያሳዝናል፡፡ ምን እንደታየውና ምን እንደተሰማው ለማወቅ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ሳንደርስበት ቀደመን፡፡ ይህ ወንድማችን ስሙ አዳነ ከበደ ይባላል፡፡ የቀደሙት ሦስቱ ደግሞ መኩሪያ ሙሉሰው፣ ሲሳይ ወርቅነህ እና ዳንኤል ገላዬ ይባላሉ፡፡

ጸሎተ ፍትሐታቸው በአሁኑ ሠዓት እየተከናወነ ሲኾን ሥርዓተ ቀብራቸው አሁን ከቀኑ በስድስት ሠዓት ተኩል እንደኾነ ተነግሯል፡፡ ቦታውም እዚያው ድል በር መድኃኔዓለም ነው፡፡ አዎ ይህች ምርጥ ቀን ልታልፋቸው አይገባም፡፡ ታሪክ በሠሩባት ታሪካዊት እና ሰማያዊት ቀን ወደ ተዘጋጀላቸው መንግሥት በይባቤ መላእክት መሔድ ይገባቸዋል፡፡
እንደዚህ ውድ ሕይወታቸውን በመጨከን የሚሰው ወጣቶች ስላሉን ዕድለኞች ነን፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ከፍ ለማድረግ ሲባል ሕይወት ተከፈለ፡፡ በእኛ መዋረድ ቤተ ክርስቲያን ልትከበር ይገባታል፡፡ አይደለም በጉልበታችን፣ በዕውቀታችን እና በገንዘባችን እግዚአብሔርን በነፍሳችን እንዲህ እናከብረዋለን የሚሉ የእሳት ልጅ እሳቶች አሉን፡፡

ወላጆች እና ዘመዶች ልባችሁ በኀዘን ይሰበር ዘንድ አይገባም፡፡ ድንገት በመጠራታቸው መደንገጥ ቢኖርም አንድ ወንድሜ እንዳለው ነፍሳቸውን የገበሩት ከመቅደሱ ሥር ከታቦቱ ሥር ነው፡፡ እነርሱ አለፉ ታቦቱ ግን ተከበረ፡፡ እነርሱ ለታቦቱ ክብር ሲታገሉ እግዚአብሔር ደግሞ በዚያው ወዛቸው ተቀበላቸው፡፡ ስለዚህ ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጥ፡፡ አክብረዋችሁ አስከበሯችሁ እንጅ አላዋረዷችሁም፡፡ በማይመች አካሔድ አላስነወሯችሁም፡፡ እናንተ የሰማዕታት ቤተሰብ ናችሁ፡፡ ትኮራላችሁ እንጅ አታዝኑም፡፡ ነፍሳቸው በእነ ቅዱስ አብርሃም እቅፍ ለመኖሯ አትጠራጠሩ፡፡

የነፍሳቸው ሠርግ ዛሬ ነውና በቃና ዘገሊላው ተከበረላቸው፡፡ የወይን ጠጅ የላቸውም ብላ ድንግል ነግራላቸው ጋኖቻቸው ተሞልተዋል፡፡ ዶኪማስ ጌታውን ለሠርጉ እንደጠራ ሁሉ እነዚህም ሠርጋቸውን መድኃኔዓለምን በመጥራትና ማክበር ፈጸሙት፡፡ የቃናው ሠርግ በጣይ በጉባይ እንደኾነው ሁሉ የእነዚህም ሠርጋቸው በጣይ ባደባባይ ኾነ፡፡ በቃናው ሠርግ እግዚአብሔር ወልድ ነበረ፡፡ በእነርሱም ሠርግ ላይ መድኃኔዓለም ነበረ፡፡ የቃናው ተአምር ለታዳሚዎች ዕጹብ ዕጹብ የሚያሰኝ ነበረ፡፡ የእነዚህም ሞት የሚያስደንቅ ኾኗል፡፡ ያንን ሕዝብ እንዳከበረው የእነዚህንም ሕዝብ ያከብረዋል፡፡ የማይገኝ ሞት ለእነርሱ ኾነ፡፡ ስም አጠራራቸውም አማረ፡፡
በምታልፍ ቀን የማያልፍ ታሪክ ጻፉ፡፡ አጻጻፋቸውም የተለየ ነው፡፡ ታሪክ በብዙ ይጻፋል፡፡ በነፍሳቸው ታሪክ የሚጽፉ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከጥቂቶች መካከል መቆጠር ከመታደል በቀር በሌላ ቃል አይገለጥም፡፡ ወንድሞቻችን በረከታችሁ ይደርብን እያልን እንሰናበታችኋለን፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top