ነፃ አስተያየቶች

ህወሃት-ኢህአዴግ የሚመራው የኢኮኖሚ ስርአት የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እያደረገ ነው? የማህበራዊ እሴት ፋይዳዎችን መነሻ ያደረገ ፍተሻ

ክፍል  አንድ

ኤድመን ተስፋዬ

ማህበራዊ እሴት (Social Capital) ክኢኮኖሚ እድገት ጋር በተጋመደ መልኩ ሲታይ ግለሰቦች በቡድን በመሆን በእምነት፣በትብብር ለጋራ አላማ በአንድ የኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የመንቀሳቀስ አቅምአቸውን የሚገልፅ ነው። ማህበራዊ እሴት ለኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ለመሆኑ አመላካቹ ደግሞ ህብረተሰቦች ከልዩነት ይልቅ በአንድ ትስስር ለጋራ ጥቅም በአንድነት በመንቀሳቀስ የሚያመጡት ውጤት የላቀ መሆኑ ነው፡፡ የማህበራዊ እሴትን ጥቅም ከኢኮኖሚ እና ከፓለቲካዊ ጥቅሙ አኳያ ስናየው፣ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ህብረተሰቦች እንዲሁም ከሁለት በላይ የሆኑ የግለሰቦች ስብስብ አንድ በሚያደርጋቸው የጋራ ልማድ፣መተማመን በጋራ በሚያደርጉት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወጪን (EconomicTransaction Cost ) የመቀነሱ እና የማስቀረቱ ሁነት የሚጠቀስ ነው። ከፖለቲካዊ ፋይዳው አኩአያው ስናየው ደሞ ነፃ እና ገለለትኛ የሆኑ ተቋማት እንዲፈጠሩ መንስኤ በመሆን ለዲሞክራሲ መዳበር ያለው ፋይዳ ይጠቀሳል፡፡በሌላ ብኩል ደሞ የማህበራዊ እሴት አንድን የማህበረሰብ ብቻ በላቀ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ስርአት ኧንዲፈጠርም መንስኤ ይሆናል።

ይህም ማለት እንደ እኔ እምነት ማህበራዊ እሴት ብዙሃኑን ህዝብ ተጠቃሚ ለሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ እድገትም ሆነ አንድን የማህበረሰብ ብቻ በላቀ ተጠቃሚ ለሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ስርአት  መንስኤ ስለመሆኑ ለመፈተሽ ለማህበራዊ እሴት መዳበር መንስኤ የሆኑትን ግብአቶች መነሻ በማድረግ እና ከግለሰባዊ ነፃነት እና  ከመንግስታዊ ስርአት ጋር በመግመድ ማየቱን ተገቢ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡

በዚህ ፅሁፍ የኢኮኖሚ ዕድገት  ሲባል  በቁጥር ብቻ የሚገለጠውን እድገት ሳይሆን ከታች የጠቀስኩአቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በሟሟላት የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ እድገት ስለመሆኑ አንባቢ ልብ ሊለው ይገባል፡፡ 1ኛ) ብቃት ያላቸው ተቋማት (ኢንስቲቱሽንስ)፣ 2ኛ) የመሰረተ ልማት ተቋማት (ኢንፍራስትራክቸርስ)፣3ኛ) የማይክሮኢኖሚክ እንቫይሮንሜት፣4ኛ) የህክምና ተቅዋምና የመሰረተ-ትምህርት ጉዳይ፣ 5ኛ) ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒካል ማሰልጠኛ ተቋማት (ኢንስቲቱሽን)፣ 6ኛ) ብቃት ያለው የዕቃዎች መገበያያ ሁኔታ፣ 7ኛ) ብቃት ያለው የሰራተኞች ገበያ፣ በተለይም የሰለጠነ የሰው ኃይል ሁኔታ፣ 8ኛ) የተቀላጠፈ የባንኮችና የፊናንስ ካፒታል ገበያና አሰጣጥ፣ 9ኛ) ብቃት ያለው የቴክኖሎጂ ዝግጅት፣ 10ኛ) የገበያ ስፋት ጉዳይ፣፣ 11ኛ) የንግድ ውስብስብነትና መቀላጠፍ፣ 12ኛ) የፈጠራ ጉዳይ(Innovation) ፡፡

ማህበራዊ እሴት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ቀብድ የሚሆነው በምን መልኩ ነው?  ማህበራዊ እሴት ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ እንዴት ነው ተፅእኖ ሊኖረው የሚችለው ?   በምንስ መልኩ ነው ማወቅ የምንችለው?  የማህበረሰባዊ እሴት መጎልበት እና መድቀቅ በምን መልኩ ነው መንግስታዊ ስርአት ላይ የሚንጠለጠለው? ለማህበረሰባዊ እሴት መጎልበት የግለሰብ ነፃነት ለምንድን ነው አስፈላጊ የሚሆነው? አንድ መንግስታዊ ስርአት የህብረተሰቡን ማህበረሰባዊ እሴት ኧንደመሳሪያ በመጠቀም የተወሰነን የህብረተሰብ ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት ሊፈጥር ይችላል ወይ ? ከፈጠረስ በአንድ ኢኮኖሚ ስርአት ላይ የተወሰነን የህብረተሰብ ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት ለመፈጠሩ ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?የሚሉ ጥያቄዎችን በመዳሰስ እና መነሻ በማድረግ ህወሃት በሚመራው የሃገራችን የኢኮኖሚ ስርአት ተጠቃሚው ብዙሃኑ ህዝብ ነው ወይስ የተወሰነው (የተመረጠው) የሚለውን ለማየት እሞክራለው።

ጠቃሚው ጉዳይ የምታውቀው ምንድን ነው ሳይሆን፣ ማንን ነው የምታውቀው የሚለው ጥቅስ ከማህበረሰባዊ እሴት የሚገኝን ቱርፋት የሚያሳይ ነው፡፡ ማህበረሰባዊ እሴት ቤተሰብ፣ጓደኛሞች እና ማህበራት አደጋን፣ቀውስን፣ድህነትን ለመቅረፍ እና ለማጥፋት በጋራ በሚያደርጉት እንቅስቀሴ እንደግለሰብም ሆነ እንደህብረተሰብ ከሚያገኙት ጥቅም መመሰሉ ማህበረሰባዊ እሴትን ከኢኮኖሚያዊ እድገት አኩአያ ለማየት የሚያስችል መነፅር ይፈጥርልናል፡፡ ማህበረሰባዊ እሴት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ቀብድ ስለመሆኑ እና ከኢኮኖሚው ስርአት ማነው ተጠቃሚው የሚለውን  ለማየት የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳን ከመንደርአዊ፣ ከአውታራዊ(Network)፣ከተቋማዊ እና ከጋራ ተግባር ተኮር እንቅስቃሴያዊ አኩአያ ማየቱ ግዴታ ይመስለኛል፡፡

የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳን  ከመንደርአዊ ፋይዳው አኩአያ የሚያየው አተያይ ማህበረሰባዊ እሴት በአካባባዊ ድርጅት ማለትም በማህበራት፣በክለብአት እና በሲቪክ ቡድናት ውስጥ ያለውን ፋይዳ መነሻ ያደርጋል፡፡ ይህ ከላይ በጠቀስኩአቸው ስብስቦች የሚገለፀው የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳ ስኬቱ የሚለካው የመንደራዊውን ኑሮ እና የኑሮ ደህንነት ከማሻሻሉ አኩአያ ነው፡፡ ይህም ማለት የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳ ስኬቱ የመንደሩን ድህነት እና የጋራ ችግር ለመቅረፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ የተንጠለጠለ ነው እንደማለት ነው፡፡ አለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመላክትቱ በኬንያ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ መንደራዊ ድርጅቶች እንዲሁም በሩዋንዳ ከሶስት ሺህ በላይ የግብርና ማህበራት እና ከሰላሳ ሺህ በላይ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮሩ ኢመደበኛ መንደራዊ ድርጅቶች ቢኖሩም መንደራዊውን ኑሮ እና የኑሮ ደህንነት በማሻሻል ለአሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ሚናቸውን ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያቶች የአቅም ውስንነት እና በነባራዊ ሁኔታ የአካባቢውን ኑሮ እና የኑሮ ደህንነት የሚያሻሽሉበት ስልጣን የሌላቸው አለመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ለስርአቱ ሎሌ ከመሆን ያለፈ ቡድናዊ ስልጣን የሌላቸው በመሆኑ የተነሳ ነው እንደማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል በቬትናም የሚኖሩ ከ አስራ ሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ አካባቢያዊ ድርጅቶች አካባቢያዊ እውቀትን፣መተማማንን ለጋራ ችግራቸው መፍቻ መሳሪያ በማድረግ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ህዝቦችን በ አራት አመት ከድህነት ወለል (በቀን ከ 1.50 ዶላር በሚለው ስሌት) ለማውጣት ችለዋል፡፤ ለዚህ ስኬታቸው ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የማእከላዊ መነረግስቱን ህግ ባከበረ መልኩ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚወስኑበት ስልጣን ያላቸው በመሆኑ የተነሳ ነው፡፡

የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳን  ከአውታራዊ(Network)ፋይዳው አኩአያ የሚያየው አተያይ ማህበረሰባዊ እሴትን ከላይ ወደታች እና ከታች ወደላይ የሚኖርን አውታር መነሻ በማድረግ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖርን የጎንዮሽ እና የቁልቁል አውታራዊ ትስስርን ለእይታው መነሻ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ እይታ መሰረት ማህበረሰባዊ እሴት ቤተሰቦች፣ እና ህብረተሰቦች ለጋራ አላማ በጋራ የሚንቀሳቀሱበት የውስጠ ስብስብን በአንድ በኩል በሌላ መልኩ ብሄርን፣ሀይማኖትን ፆታን መነሻ ባደረገ መልኩ የሚኖር ስብስብን መነሻ በማድረግ የማህበራዊ እሴት ፋይዳን ከአውታራዊ ፋይዳ አኩአያ ይመለከታል።

በህንድ፣ በባንግላዴሽ እና በቦትስዋና የማህበራዊ እሴት ፋይዳን ከአውታራዊ ፋይዳ አኩአያ  የሚፈትሹ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከአንድ ህብረተሰብ መሀል የወጡ ቡድኖች፣ቤተሰቦች እና ክለቦች የጋራ እሴቶቻቸውን፣መተማመናቸውን እና የጋራ አላማቸውንለአውታራቸው መነሻ በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ስብስቦች ብሄርን፣ሀይማኖትን ፆታን ለአውታራቸው መነሻ ካደረጉ ስብስቦች ይልቅ የአካባቢያቸውን ኑሮ እና የኑሮ ደህንነት በማሻሻል ለአሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ችለዋል፡፡

የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳን  ከተቋማዊ ፋይዳው አኩአያ የሚያየው አተያይ ማህበረሰባዊ እሴት ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ለሲቪክ ተቋማት መመስረት ካላቸው ፋይዳ አኩአያ ያያል፡፡ በዚህ አተያይ መሰረት በህብረተሰቦች መሀል ያለን ህብረሰባዊ እውቀት፣ ልማድ፣ መተማመን እና ትብብር  መነሻ ያደረገ ለጋራ አላማ ለሚያስተሳስር ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማት መመስረት እና መኖር ማህበረሰባዊ እሴት ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በመንደር ደረጃ ያለን ከፍ ሲልም በሀገር ደረጃ ያለን ማህበረሰባዊ እሴትን (ብዙውን ጊዜ በሀገር ደረጃ ያለ ማህበረሰባዊ እሴት በሉአላዊነት ይገለፃል) መነሻ አድርጎ  የሚቋቋም ተቋም ህብረተሰቦችንም ሆነ ህዝቦችን ለጋራ አላማ ከማንቀሳቀስ ባለፈ የተገደበ የስልጣን ዘመን እንዲኖር ከፍተኛ ሚና በመጫወት አንባገነናዊ ስርአተ መንግስት እንዳይፈጠር መንስኤ ሲሆን በሌላ መልኩ መንግስት ቅጥ ባጣ በመልኩ በኢኮኖሚያዊ ስርአት ላይ የሚያደርገውን ጣልቃገብነት በመገደብ  በጠንካራ ፖለቲካዊ መሰረት ላይ በተገነባ ኢኮኖሚያዊ ስርአት የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ የሚያሻሽል ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲኖር መንስኤ ስለመሆኑ የጀርመንን እና የጋናን ተሞክሮ በዋቢነት በመጥቀስ የዚህ አተያይ አቀንቃኞች ይገልፃሉ፡፡

የማህበረሰባዊ እሴት ፋይዳን  ከጋራ ተግባር ተኮር እንቅስቃሴያዊ ፋይዳው አኩአያ የሚያየው አተያይ ከላይ የተጠቀሱትን አውታራዊራዊ እና ከተቋማዊ ፋይዳን ወደ ተግባር ለመተግበር ማህበረሰባዊ እሴት ከፍተኛ ሚና እንዳለው የሚገልፅ ነው፡፡ የኢኮኖሚክስ አስተምህሮት በተለይም የተፈጥሮ ሀብት እና የአየር ንብረት ኢኮኖሚክስ አስተምህሮት ህልዮቶች እንደሚተነትኑት የጋራ በሆነ አላማ እና ንብረት ላይ በጋራ ለመንቀሳቀስ እና ለመጠቀም ትብብር ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

የዚህ ትብብር ውጤታማነት ደግሞ የሚንጠለጠለው ህብረተሰቡ ከገነባው አውታር እና ተቋማት ጥንካሬ ነው፡፡ ይህ ህልዮት ከህልዮት ባለፈ እውነታ ስለመሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ፣ ተቋማት፣ድርጅቶች ወዘተ የጋራ ንብረታቸው በሆነው አለማያ ሀይቅን በትብበር (በትብብር መጠቀም ማለት ሀይቁን በጋራ በም,መንከባከብ ማለት ስለመሆኑ አንባቢ ልብ ሊለው ይገባል) ከመጠቀም ይልቅ በፉክክር በመጠቀማቸው እንዲሁም በሚያሳዝን ሁኔታ ከሀይቁ በቅርብ ርቀት የተጎለተው የአለማያ ዩኒቨርስቲ የአካባቢውን ህብረተሰብ ማህበራዊ እሴቶች ህብረተሰቡ ሀይቁን በመተባበር እንዲጠቀም መሳሪያ ባለማድረጉ የተነሳ ሀይቁ የመድረቁ ሀቅ ማሳያ ይመስለኛል፡፡

ከላይ የጠቀስኩአቸው የማህበረሰባዊ እሴቶች ፋይዳ ማህበራዊ እሴት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ቀብድ ስለመሆናቸው በቂ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በሁአላ የሚመጣው ትልቁ ጥያቄ ማህበረሰባዊ እሴትን ለኢኮኖሚያዊ እድገት ግብአት ለማድረግ መሰረታዊው ነገር ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡

እውቁ ኢኮኖሚስት አማርታሲያን ሴን Development as Fredom በሚለው ዘመን ተሸጋሪ መፅሀፉ ኢኮኖሚያዊ መሻሻልን መነሻ ባደረገ መልኩ በአመታዊ አማካይ ሀገራዊ ምርት ማእከልነት ከሚገለፀው ግለሰባዊ ልማት ሰፋ ያለ ስለመሆኑ ያትታል፡፡ እንደ ሴን እምነት በአመታዊ አማካይ ሀገራዊ ምርት ስሌት መነሻነት የሚገለፀው ግለሰባዊ ገቢ የማህበረሰብ አካል የሆነን ግለሰብ ነፃነት ለማስፋት እና ለማሳደግ መንስኤ ቢሆንም ነፃነት በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር  ( የት/ም እና የጤና  አገልግሎቶች ወዘተ)እንዲሁም በፖለቲካ እና በሲቪል መብቶች (የመወያየት እና የደህንነት ነፃነት)  ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡

እንደ እኔ እምነት ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማምጣት አንባገነናዊ ስርአትን፣ድህነትን፣ ኢፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ስርሀትን እና የሀብት ክፍልን፣ ስሌታዊ በሆነ መልኩ አንድን ህብረተሰብ የማደህየትም ሆነ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲስተምን፣ አድሎአዊ እና ቂም የዥ ስርአትን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ነፃነት ለኢኮኖሚ እድገት ሂደት ዋነኛ ማእከል የሚሆነው በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው። እነሱም በሚዛናዊ እና በውጠታማዊ ምክንያቶች የተነሳ ነው፡፡ ይህም ማለት  በኢኮኖሚ እድገት ሂደት ውስጥ የኢኮኖሚያዊ መሻሻል ሊመዘን የሚገባው ህዝቡ ካለው ነፃነት ስፋት አኩአያ ሲሆን። ኢኮኖሚያዊ መሻሻሉ በነባራዊነት የውጤታማነቱ መንስኤ ደግሞ  የነፃ ግለሰቦች እንቅስቃሴ ነው እንደማለት ነው፡፡

ከላይ የጠቀስኩት የእውቁን ኢኮኖሚስት ሴንን ንድፈ ሀሳባዊ ምሳሌ መጥቀሱ እንደ እኔ እምነት ነፃነት ለግለሰብም ሆነ ለግለሰቦች ስብስብ ውጠታማ ነት ለማሳየት ይረዳል፡፡ ሴን Development as Fredom እንደገለፀው ሁለት አርሶ አደሮች እያንዳዳቸው አንድ አንድ ሄክታር መሬት እና ተመሳሳይ የሆነ የግብርና ግብአት ለግብርናቸው እንቅስቃሴ ይጠቀማሉ እንበልና እናስብ ነገር ግን ከእርሻ መሬታቸው እና ከእለት ተእለት ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ኑሮቸው በተገናኘ ያላቸው ነፃነት (ይህ ነጣነታቸው ከመሬት ባለቤትነነት፣ በነፃነት ከመሰባሰብ እና ከመደራጀት፣ ወዘተ ሊገለፅ ይችላል) ግን ልዩነት አለው፡፡ ይህ ልዩነት በግብርና ምርታማነታቸው ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል ? የሴን ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ነባራዊውን ሀቅ የሚያሳየን መፅሀፍ ነባራዊ የሀገራትን ተሞክሮ ከንድፈ ሀሳብ ጋር በማገናኘት ከላይ በጠቀስኩአቸው ግለሰቦች መሀል ያለው የነፃነት ልዩነት ለግብርና ምርታማነት ልዩነት መንስኤ ስለመሆኑ ያሳየናል፡፡ ይህም በእኔ እምነት ማህበረሰባዊ  እሴትን ለኢኮኖሚያዊ ልማት መሳሪያ ለማድረግ ነፃነት ዋነኛው ግብአት ስለመሆኑ ማሳያ ከመሆኑ ባለፈ ያለ ነፃነት ማህበረሰባዊ እሴት የተወሰነ (የተመረጠ) የህብረተሰብ ተጠቃሚ ለሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ልማት እንጂ ብዙሃኑን (አንጻራዊ በሆነ መልኩ) ተጠቃሚ ለሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ልማት ግብአት ሊሆን እንደማይችል ማሳያ ነው፡፡

በክፍል ሁለት ጽሁፌ ህወሃት-ኢህአዴግ የግለሰብ ነፃነትን በማጎልበት  ማህበራዊ እሴቶችን ለኢኮኖሚ እድገት ግብአት ከማድረግ ይልቅ ግለሰባዊ ነፃነትን በማድቀቅ እና ማህበራዊ እሴቶችን በመጠቀም የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ የኢኮኖሚ ስርአት እንደፈጠረ ለማየት እሞክራለው።

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top