የፌደራል የደህንነት ምክር ቤት በሰሜን ወሎ አፈሳ እየፈጸመ እንደሚገኝ ታወቀ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

የፌደራል ደህንነት ምክር ቤት በሰሜን ወሎ ከተሞች አፈሳ እየፈጸመ እንደሚገኝ ታወቀ፡፡ ይኸው ምክር ቤት፡- በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የህወሓት ጄነራሎች፣ የዘጠኙም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች እና የጸጥታ ኃላፊዎች፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የክልል እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች የተካተቱበት ግብረ-ኃይል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ተከትሎ የተቋቋመ ሲሆን፤ የሚወስዳቸው የኃይል እርምጃዎችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይወሰዱ ከነበሩት እርምጃዎች የተለዩ እንዳልሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በሰሜን ወሎ በሚገኙት ወልድያ፣ ቆቦ እና መርሳ ከተሞች ከቅርብ ቀናት ወዲህ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ተቃውሞውን ተከትሎም በስፍራው የሚገኙ የጸጥታ አካላት ግድያ፣ እስራት፣ እና ድብደባ ሲፈጽሙ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ ይኸው የኃይል እርምጃ በቀጠለበት በዚህ ሰዓት፣ የፌደራል ደህንነት ምክር ቤት የተባለው ግብረ-ኃይል፣ በሰሜን ወሎ አፈሳ መጀመሩ ነው የታወቀው፡፡ በሰሜን ወሎ በተፈጠረው ‹‹ግጭት ተሳትፈዋል›› የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ሲሆን፤ ሰዎችን በማሰር ሂደት ውስጥ በደህንነት ምክር ቤቱ ስር የታቀፉ የጸጥታ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በበኩሉ፤ በሰሜን ወሎ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፣ በወልድያ የተፈጸመውን ግጭት የፌደራል ደህንነት ምክር ቤት እያጣራው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የጽ/ቤቱ ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፡- ‹‹በወልዲያው ግጭት ላይ የፀጥታ ኣካላት ያልተገባ ተግባር ፈፅመዋል መባሉን ተከትሎ ጉዳዩ እየተጣራ ነው፡፡ የፀጥታ አካላቱ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ተጠያቂ የማይደረጉበት ምክንያት የለም፡፡›› ያሉ ሲሆን፤ አክለውም ‹‹ጉዳዩን የፌዴራል የደህንነት ምክር ቤት እያጣራው ነው፡፡ ማጣራቱ ሲጠናቀቅም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል፡፡›› ብለዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ በፌደራል ደረጃ የተዋቀረው የደህንነት ምክር ቤት፣ ግጭት በማጣራት ስም ሰዎችን እያሰረ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡››

በደህንነት ምክር ቤቱ እና በሌሎች የጸጥታ አካላት እስር ቤት የተወረወሩት የሰሜን ወሎ ከተማ ነዋሪዎች፤ በቀጣይ ‹‹ጥፋተኛ›› ተብለው ሊፈረድባቸው እንደሚችል ከወዲሁ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊው ዶ/ር ነገሪ መግለጫ ይህን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ኃላፊው በመግለጫቸው፡- ‹‹በግጭቱ የተሳተፉ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው በህግ ተጠያቂ እየተደረጉ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ ኃላፊው ይህን ማለታቸው፣ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ እና ጥፋተኛ እየተደረጉ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም የአማራ ክልል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር፣ በሰሜን ወሎ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ንብረት ላይ ጉዳት ባደረሱ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ይወሰዳል፡፡›› ብለዋል፡፡ ‹‹ጥፋተኛ›› የተባሉ ሰዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም የክልሉ ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ገልጸዋል፡፡ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ የተሰጡት ሁለቱ መግለጫዎች፣ በሰሜን ወሎ ወልድያ፣ ቆቦ እና መርሳ ከተሞች ሰዎች ‹‹ግጭት ቀስቅሳችኋል›› በሚል ውንጀላ እየታሰሩ እንደሚገኙ ያረጋግጣሉ ተብሏል፡፡

 

BBN News February 2, 2018

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *