በፈረንሳይ የሚኖሩ የኤርትራ እና አፍጋኒስታን ስደተኞች ደም ተቃቡ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

(BBN) በፈረንሳይ የሚኖሩ የኤርትራ እና አፍጋኒስታን ስደተኞች ደም ተቃቡ፡፡ የፈረንሳይ የወደብ ከተማ በሆነችው ካሌይ የሚኖሩት የሁለቱ ሀገራት ስደተኞች፤ በመካከላቸው በተፈጠረ ግጭት የተነሳ ጥይት መተኮሱም ታውቋል፡፡ ጥይት እስከመታኮስ በደረሰው በዚሁ ግጭት፣ አምስት ኤርትራውያን በጥይት ተመትተው በጽኑ መቁሰላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በጥይት ከተመቱት አምስት ስደተኞች መካከል አራቱ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 18 የሚገመት ኤርትራውያን ይገኙበታል ሲል የጠቆመው ዘገባው፤ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ወደ ሆስፒታል የተወሰደው አምስተኛው ሰው ግን የመትረፍ ዕድሉ አናሳ መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል፡፡ የተጊጂውን ህይወት ለማትረፍ ሆስፒታል መወሰዱንም ዘገባው ያክላል፡፡

በጥይት ተመትተው ከቆሰሉት ስደተኞች በተጨማሪ ደግሞ፤ በዱላ በተፈጸመ ድብደባ አስራ ሶስት ሰዎች የተጎዱ ሲሆን፤ ግጭቱን ተከትሎ ከሰላሳ በላይ አፍጋኒስታውያን እና ከመቶ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል፡፡ በፈረንሳይ ካሌይ ከተማ ደቡባዊ ክፍል በሚኖሩት የኤርትራ እና አፍጋኒስታን ስደተኞች መካከል ግጭት የተፈጠረው፣ ስደተኞቹ ከመንግስት የሚሰፈርላቸውን ቀለብ (ምግብ) ለመቀበል ወረፋ በያዙበት ሰዓት እንደሆነ ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ደግሞ አንድ የአፍጋኒስታን ተወላጅ በእጁ ይዞት የነበረውን የጦር መሳሪያ አውጥቶ ተኩስ በመክፈቱ እንደሆነም ከዘገባዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ዜጎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ አካባቢውን ሄደው የጎበኙት የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራርድ ኮሎምብ፣ የተፈጠረውን ግጭት ‹‹አደገኛ!›› ሲሉ ጠርተውታል፡፡ በዚሁ ስፍራ እንዲህ ዓይነት ግጭት ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የገለጹት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በስደተኞች መካከል የሚፈጸሙ ግጭቶች እየተደጋገሙ መምጣታቸውንም አክለዋል፡፡ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ከከተማዋ ፖሊስ በተጨማሪ የፈረንሳይ የጸጥታ አካላት ወደ ስፍራው እንደተጓዙ ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *