ነፃ አስተያየቶች

ቅንጅትና የተማከለ አመራር ያጣው ወቅታዊው የህዝባዊ እምቢተኝነት ወላፈኖች፣ ችግሮቹና የመፍትሔ አቅጣጫዎች (ክፍል 1) – አበባየሁ አሉላ

አበባየሁ አሉላ, ዋሽንግተን ዲሲ

ክፍል አንድ

መግቢያ፦ አንባቢያን ስለድሑፌ ይዘት መጠነኛ ጭብጥ እንዲኖራችው እፈልጋለሁኝ ፣ በዚህም እንደተለመደው ያለፍንባቸውን ለመተንተን ሳይሆን በይዘቱ የምንታገለውን አገዛዝ የኃይል አሰላለፍ በአግባቡ ለመረዳትና በተለይም ዓመታትን ያስቆጠረውና በቅርብ ጊዚያት አድማሱን ያስፋው አስፈሪ የለውጥ ድባብ እየገፋ መምጣቱን ስንመለከት በአገሪቱ የሚታየው የጋመ ሕዝባዊ እምቢተኝነት  ከወትሮውም በላይ አምባገነኑ አገዛዙ የቆመበት መሬት እየከዳው እንደሆነ ምልክቶችን እያየን ነው፤

በአፃሩ በተቃዋሚው ጎራ በተለይም በአገር ቤት እመሬት ላይም ይሁን በውጭ ህዝባዊ ንቅናቄውን አቅጣጫ የማስያዝም ይሁን የመደገፍ መሪነት ማጣትና ፣ ለዚህም በቀጣይ ለዚህ የሚመጥን የተቀናጀ  ኃይል የመፍጠርን አስፈላጊነት ለማሳየትና ፣ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን መጠነ ስፊ በደል፣ ህዝባችን በሥርዓቱ ላይ ያለውን ጥላቻና ጥልቀት ፣ የህዝባዊ ትግሉ ችግሮችና መስናክሎች በማጠቃለያም የምፍትሔ አቅጣጫዎች በማካተቱ ስፋት ያለው መጣጥፍ በመሆኑ ይህንን ክፍል እንድን እንደዚሁም ቀጣዬን ሁለተኛውንም ክፍል ለተቀመጡት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ትርጉም ሰጭዎች መሆናቸውን ከወዲሁ አስገነዝባለሁ፣

አገራችን በማን አለብኝነት  ወደ ከፋ አደጋ እየገፋ የሚገኘው መንግሥታዊ አገዛዝ ፣ በሕወኃት የበላይነት ሥልጣን እርካብ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የስልጣን እድሜውን ጥሩ መሠረት ላይ ያስገኛል የሚላቸውን ዘርፎችን ሁሉ በራሱ ጋሻ ጃግሬነት መዳፍ ሥር ለመምራት ያላሰለሰና የተጠናከረ ተግባር አከናውናል ፣ በዚህም ሁሉንም መንግሥታዊ ፣ ወታደራዊ፣ የስለላ (ደህንነት) ፣ መከላከያ ፣ የፍትህ አካላትና የሚዲያ ተቋማትን ፣ እንደዚሁ ከነዚህ አልፈው ሁለቱንም ዋነኛ  የዕምነ ተቋማትንና በተለጣፊነትና በሽፋንነት የተመሠረተው የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ማለትም በዶ/ር አዲሱ ገ/እግዝሃብሔር የሚመራውና በተመሳሳይ ሁሉም የሙያ ማህበራት ጭምር በዚሁ ስሌትና ቅኝት እንዲዋቀሩ ተደርገዋል፤ በነዚህና መሰል ቁልፍ መስኮች ታማኝ ናቸው የምላቸውን የህወኃት አባላቱንና የዘር ሐረጉን ያለምንም ይሉኝታ ቦታ በማስያዝ ለእድሜው መራዘም ያላሰለሰ ሚና ተጫውታል እየተጫወተም ነው፤

በተመሳሳይም የፓለቲካዊ፣:ወታደራዊና መንግሥታዊ ተቋማትን በተፈለገው መንገድ ለመዘወር ደግሞ የኤኮኖሚውን ዘርፍን መጠቅለል ወሳኝ በመሆኑ በአገሪቱ አሉ የሚባሉ የኤኮኖሚ አውታሮች በፈለፈላቸውና ወሳኝ በሆኑ የህወአት ኩባኒያዎች አሊያም በጥቂት የትግራይ ክልል ግለሰቦች ፣ ለሥርዓቱ ታማኝ በሆኑ ባለሀብቶችና የተጠፈነገ ነው።

በዚህም አንድ የብዕር ሰው  “አገራዊ አጀንዳ” በሚል አጭር ማስታወሻው ሲገልጽ ” በሹመት ስም፣ በሃገር ሰላም ስም፣ በትራንስፎርሜሽን ስም፣ በኢንበስትመንት ማበረታታት ስም፣ ዘራፊዎች በማሳደድ ስም የሚካሄደው ምዝበራ ተጧጥፎ ቀጥሉዋል። የስልጣን ብልግናው በመሬት ዘረፋ ፣በኮንስትራክሽን ግንባታ፣በእንዱስትሪ ሀሳዊ ስብከት፣ በቦርድ አባልነት ተገን በማድረግ፣ በሙልሙል ቢሮክራት መልክም ኢሕአድጋዊ ቅኝት ከጅብ ጅማት እንደተሰራ ክራር ልብላው ልብላው ብቻ ሆነ ” በማለት የህወኃት/ኢሕአድግን ስር የሰደደ አገራዊ  ምዝበራ በአጭር ስንኝ ጥልቀት ባለው መልክ በፁሁፉ አስፍራል ፣

በቅርቡም የአንድ ወዳጄ ወላጅ አባት ልጆቻቸውን ለመጎብኘት አሜሪካ መጥተው ለመጠየቅ ሄጄ ሳለ የአገር ቤቱ ህዝባዊ እምቢተኝነት የተጋጋለበት ሰሞን ስለነበር የሁላችንም ቀዳሚ ጥያቄ የነበረው አገር  ቤት እንዴት ነው ነበርና ይህንን እኔም ለኒህ አባት አንስቼ ሁላችንንም ዞር ዞር በማለት ተመለከቱና መቼም አንድ ለአምስት እዚህ አይደርስም በማለት አገር ቤት ያለውን ስጋት በመፈንጠቅ አሁንስ በሰፈሩበት ቁና እነርሱም መሄጃቸው ደርስዋል በማለት ቀጥለው ደርግኮ የኔ የሚለው ክልልና ዘር የለውም እነዚህኮ ግን ብለው ብዙ አወጉንና ጠባብነታቸው ወሰን እንደሌለው ለማመልከት የሚከተለውን ውስጥ ለውስጥ የሚባለውን አባባል ጠቀሱልኝ ” አይጫንም እንጂ ወንዝ በመኪና መቀሌ ነበሩ አባይና ጣና ” በማለት የነበረውን ቤተሰብ ሁሉ አሳቁን።

በአትዬጵያ ብሔራዊ አንድነት ኩሩ የሆነው ህዝባችን አንድነቱን ጠብቆ በኢትዬጵያዊነት ማዕቀፍ ደምቆ ቢቆይና በተመሳሳይ ልዩ ጌጥዋ የሆኑት የኢትዬጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸው ተጠብቆና ተከብሮ በዕኩልነት ተከባብረው ክልል ሳይለያቸው በአንድነት ቢቆዬ ለአምባገነንና ጠባብ አገዛዝ የማይመቹ መሆናቸውን በመገመት እናት አገራችንን በከፋፍለህ ግዛው መርህ በመሸንሸን ጎሳ ፣ ዘርና ቋንቋን መሠረት በአደረገ ፌድራላዊ መንግሥታዊ ክልሎች በመበለት ሁሉም  በተሰመረለት ክልላዊ ይዞታ ውስጥ እንዲያስብ ሲደረግ ይህንንም አደገኛና ብሔራዊ አመለካከትን ከሥረመሰረቱ ለመሸርሸር  የአዲሱን ትውልድ አመለካከትም በክልል አጥር ውስጥ እንዲያስብ ለማድረግ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት በክልሉ ታሪክና ማንነት ብቻ በይበልጥ እንዲያተኩርና እንዲቀረጽ በማድረግ ብሔረተኝነት እንዲለመልምና እንዲኮተኮት እየተደረገ ነው ።                                                                                                   ከእንግሊዝች ቅኝ አገዛዝ ነፃነቷን በ1960 ዎች ግድም የተቀዳጀችው ጋናን በምሳሌነት ብንመለከት ከእኛ ቀድማ የፍትህና የዲሞክራሲ ቀንዲል በመሆን ለብሔራዊ አንድነታቸው ቀናይ በመሆናቸው በአገራቸው በዘር መደራጀትን ሕገወጥ መሆኑን በሕገመንግሥታቸው ጭምር በመደንገግ ለብሔራዊ አንድነታቸው ቀንአይ ሲሆኑ የእኛ ገዥዎች ገናናይቱንና በነፃነቷ ኮርታ ፣ ታፍራና ተከብራ ለጥቁሩ ህዝቦች ተምሳሌት የሆነችውን እናት አገር  በዘር አጥር በማደራጀት ከልለዋታል።

በዚህም ይዞታ ውስጥ በየክልሉም ይሁን በዋና  ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ የህብረተሰቡ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በእጅግ የሚጣሱ ከመሆናቸውም የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከምን ጊዜውም በላይ የተገደበና የከፋ እንዲሆን ተደርጋል ፤ ይህም አንድ ክልል የሌላውን በደልና ብሶት እንዳይረዳው በአገዛዙና   ጋሻ ጃግሬዎቹ መዳፍ ስር የሚገኘውና  ሁሉም አመራሮችና ጋዜጠኞች ማለት ይቻላል በአንድ አካባቢ ሰዎች የተወረረ የሚድያ ተቋም የቀድሞ የኢትዬጵያ ቴለቢዥን የነበረውና የአሁኑ ( EBC) ማለትም የኢትዬጵያ ብሮድካስትንግ ኮርፓሬሽንም ፣ FBC / ፋና ብሮድካስቲንግ ፣ ዋልታ እንፎርሜሽና ( WEC) ሌሎች ተመሳሳይ ሚድያዎች የሚዲያ ህግን ባልጠበቀ መልኩ ዘዋሪው ድርጅቱ ህወኃት እንደመሆኑ በህወኃት አባላትና በክልሉ ሰዎች የተቀፈደድ በመሆናቸውም ጭምር ከልማትና መንግስታዊ ዜናዎችና  ፕሮፓጋንዳዎች ባሻገር አንድ ክልል ከጎረቤቱ ክልል የተከሰተውን በቀላሉ እንዳያውቅ  ሲገደብ ፤ ማንኛውም የዜና ምንጭ በአገዛዙ ሥር የሚገኙ የሚዲያ ተቃማት ናቸው የሚቆጣጠሩት በዚህም የመረጃ ፍሰቱ ከየትኛውም አቅጣጫ የተገደበ በመሆኑ አገራዊ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ክስተቶች አገዛዙ የሚፈልጋቸውና የሚጠቅሙት ሆነው ካልተገኙ የዜና ሽፋን አያገኙም ከዚህ ፍላጎት ውጭ እመሬት ላይ ያሉ እውነቶች ለመዘገብ ነፃ ጋዜጠኞች የድህረገፅ ጸሃፊያን የሙያ ግዴታዎችን መወጣት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል ፤ በርካታዎች የግል የሚመስሉ ነገርግን ለአገዛዙ ችግር ያልሆኑትም በአዝናኝና ስፓርታዊ ትንተናዎች ሙሉውን ቀን በመጠመድ በአንድ በኩል ከፓለቲካው አስፈሪ ድባብ እራሳቸውን ሲያገሉ በሌላው ዘርፍ ዜጎች በተለይም ታዳጊው ወጣት እይታዎች በአሳሳቢ አገራዊ ጉዳዬች ላይ ትኩረት እንዳይኖረው የበኩላቸውን አዕምሮውን የመስለብና የማደንዘዝ ሚና ይጫወታሉ ።

በተመሳሳይም በተገኘው ጠባብ ቀዳዳ በአገሪቱ መሠረታዊና  ፓለቲካዊ ጉዳዬች ላይ ሰላማዊ ተሳትፎ በማድረጋቸው በርካታ ብርቅዬ እውቅ ጋዜጠኞች፣ የድረገፅ ፅሐፊያን ፣ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎችና አክቲቢስቶች በሽብርተኝነትና ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ስም ክስ እየተመሰረተባቸው በአስከፊ ሁኔታ በየእስር ቤቶች ታጉረው ይገኛሉ ፣ ዘርዝርዝረን ልንጨርስ የማንችላቸው ሰላማዊ  ታጋዬችና በብዙ ሺዎች የሚገመቱ በስም የማናውቃ የኢትዬጵያ ልጆች አምባገነኑን አገዛዝ የተቃወሙና የተቹ የሂሊና እስረኞች ሁሉ የአገዛዙ ሰለባውዎች ሆነዋል ፤ እነዚህ እሥር ቤቶች ሁሉም አዛዥች የህወኃት አባሎች ሲሆኑ ማዕከላዊን ጨምሮ ሁሉም እስር ቤቶች ገራፊዎችና ዘግናኝ ሰቆቃ ፈጻሚዎች እንደዚሁ በአመዛኙ የአንድ ብሔረሰብ አባሎች መሆናቸው ኢትዬጵያ የማን ናት የሚያስብል ነው። በርካታዎችም ታሳሪዎች በሚደርስባቸው ድብደባ ሳቢያ የአካልና የጤና መታወክ ችግር ውስጥ የገቡና ህክምና በመነፈግ የሚሰቃዩ በዚሁ ሳቢያ ለህልፈትም የተዳረጉ እንደነበሩ የዚሁ ሰለባ የነበሩት በመረጃ አስደግፈው እየነገሩን ነው ፤ ይህ የህወኃት/ኢህአድግ አገዛዝ አይኑን በጨው አጥቦ ምንም የፓለቲካም ይሁን የሂሊና እስረኛ ኢትዬጵያ ውስጥ የለም በሚል ዓለማችንን ሲዋሽ ቆይቶ አሁን በህዝባዊ ተቃውሞ በመናጡና በመሰነጉ እስረኞችን እንደሚፈታ በአደባባይ ለመግለፅ ተገዷል ፤ ትልቁ ጉዳይ እስረኞች መፍታት ብቻ ሳይሆን ሂሊናቸውንም መፍታት ካልተቻለ ዛሬ ፈትቶ ነገ ይህንን ተናገርክ ወይም ፃፍክ ብሎ መልሶ ማሰር የሚከለክላቸው ነገር ከቶውንም የለም።

እጅግ የሚያሳዝነው ይህ ሥርዓት በክህደት 27 ዓመት የዘለቀ እንደመሆኑ ብዙ የህዝብ ልጆቹን ያኮላሹበትንና ዘግናኝ ሰቆቃ የፈፀሙበትን ማዕከላዊ እስር ቤት የእነርሱ እጅ እንደሌለበት የደርግ ብቻ አስመስለው  በድፍረት መናገራቸው መላውን የኢትዬጵያን የሕዝብ እጅግ ከማሳዘኑም የሰቆቃው ሰለባ የነበሩት የደረሰባቸውን ሰቆቃ በማሰብ ሲቃ እየተናነቃቸው ድርጊቱን በጀርመን በድምፅና በአሜሪካ ድምፅ በእማኝነትም አጋልጠዋል ።

አንጋፋው  ፓለቲከኛና የፓለቲካ ሳይንስ ምሁር የነበሩት ዶ/ር መራራ ጉዲና አውሮጳ ህብረት ስብሰባ ሲመለሱ በሽብርተኝነት ተፈርጀው ከመኖሪያ ቤታቸው ከቤተሰብ አባሎቻቸው ጭምር  ታፍነው በህወኃት እጅ ለእስር ተዳርገውና ከአራት መቶ ቀናት በላይ ለእስር ተዳርገው ሰሞኑን በህዝብ ግፊት የተለቀቁት ፣ ወደ እስር ሲወሰድ  ያሳተሙት መፅሐፍ የሽያጭ ገቢ ውጭ  ከሚኖሩት ኢትዬጵያዊያን ያገኙት ገንዘብ ጭምር ከቤታቸው በአገዛዙ አሳሪዎች ተወስዶባቸዋል  ዶ/ር መራራ  የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር አባልና በኦሮሞ ወገኖቻችን እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው የፓለቲካ ድርጅት መሪ ናቸው ፤ ከመታሰራቸውም ቀደም ሲል በአንድ ወቅት  ዋሽንግተንና አካባቢው በሚሰራጨው የአዲስ ድምፅ ራዱዬ በነበራቸው ቃለምልልስ በዝዋይ እሥር ቤት ብቻ ከ10,000 በላይ እስረኞች መኖራቸውን  ቃሊቲና መሰል እስር ቤቶች ክልሎችን ሳይጨምር 50 ሺዎች የሚገመቱ የፓለቲካ እስኞች መኖራቸውን ሲገልጽ ይህ አሃዝ  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ በጅምላ የታሰሩትን በአሥር ሺዎች የሚገመቱትን አይጠቀልልም ፤ ይህ የሚያመለክተን ምን ያክል በስፋት ወገኖቻችን እጅ ከወርች በአገዛዙ በአስከፊ ማጎሪያ ቤቶች እንደሚገኙ መገመት ይቻላል ፤ በዚህም የዓለምአቀፉ የሰባዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምኒስቲ እንተርናሽናል ፣ የሰባዊ መብት ረገጣው ከምን ጊዜውም በላይ እየከፋ መሄድንና ኢትዬጵያ ከኤርትሪያ በመለጠቅ በአፍሪካ ሁለተኛዋ አስከፊ አገር መሆኑዋን በየጊዜው በዓመታዊ  ጋዜጣዊ መግለጫው ሲያረጋግጥ በተለይም ጋዜጠኞችን በማሰር ከዓለም እገሮች ኢትዬጵያ ሁለተኝነት ስፍራ እንደያዘች Freedom house ና ሌሎችም በርካታ የሰባዊ መብቶች ተማጋች ድርጅቶች አረጋግጠዋል ።

አገዛዙ ይህንን በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን መጠነ ሠፊ የሰባዊ መብት ጥሰትና አፈና ፣ ዘረኝነትና ሙሰኝነት ሽፋን ለመስጠት ይመቸው ዘንድ የአለምዓቀፉን  ኃያላን መንግሥታትን እራሱን ልማታዊ መንግሥት ነኝ በማለት በሚያገኝው መጠነ ሰፊ ዕርዳታና ይህንንም ሰበብ በማድረግ ከአገሪቱ አቅም  ጋር ሊመጣጠን በማይችል መጠን ከፍተኛ የውጭ ብድር በማግኘት የመሠረተልማት ግንባታ ላይ የሚውል ከፍተኛ  ዕዳ ላይ ኢትዬጵያ መዘፈቃን መረጃዎች ያመለክታሉ  ፣ በዚህም  እንደ Horn of affairs የቅርብ ጊዜ ዘገባ 14 ቢሊዬን የአሜርካን ዶላር ገደማ የውጭ ብድር ዕዳ ያለባት ሲሆን እንደዚሁ መንግሥታዊ አገዛዙ ከአቅም በላይ ለወጠናቸውና ለሚያከናውናቸው መሠረተ ልማቶችና ሌሎች ግንባታዎች፣ በሚል ከፍተኛ የአገር ውስጥ ብድርም ውስጥ መዘፈቁንና በዚህም ከኢትዬጵያ ብሔራዊ ባንክ ብቻ ከ 92.7 ቢሊዬን ብር ብድር በመውሰድ ለረጅም ጊዚያት አለመክፈሉና በተመሳሳይ በዚሁ መልክም ለልማት ባንኮችም ከ 23 ቢሊዬን ብር በላይ ከብሔራዊ ባንክ በተመሳሳይ በብድር መልክ ወጪ መደረጉና ይህም አሁን በአገር ውስጥ ለሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የአደረገ በመሆኑ  ይህንን ችግር ለመቅረፍና የገበያውን ዋጋ ለማረጋጋት ገንዘቡ ለአበዳሪው የብሔራዊ ባንክ መመለስና መክፈል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የአለምአቀፉ ፋይናንስ ቁጥጥር አካል IMF በወቅቱ  ማሳሰቡን መረጃዎች ያመለክታሉ ፣ ከዚህም ወጪ በብዙ ቢሊዬን የሚገመት ገንዘብ የህወኃት ንብረት የሆነው ግዙፍና መላይቱን ሃገር እንደመጅገር ተጣብቶ የሚመጠምጡት ኤፈርት ድርጅትና በርካታ አጋሮች በብድር የተሰጠው የህዝብ ገንዘብ የተበላሸ በሚል እየተሰረዘ እነርሱን ለማፈርጠምና ሌሎችን የማስዋጥ ሚናን ይጫወታሉ ፤ ከዚህም ውጭ በኢትዬጵያ መንግሥታዊ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ  ጉሊት የሚነግድ ድኃ ዜጎችን ጨምሮ ከአገር ውስጥ ገቢዎች ድርጅት በቀጥታ የተናበበ የንግድ ገቢ ግብር የሚያሰላ ማሽን እንዲጠቀሙ ሲገደድ 15% እጅ (consumer tax) የሸማቾች ግብር VAT ( Value added tax)  ከመናጢ ደኃ እስከ ናጠጠ ባለሀብት ጭምር የሚሰበስበው ግብር  ሥራ ላይ ከዋለ በኃላ የግብር  ዕድገቱን በ66.27 እጅ ማሳደጉንና GDP ማለትም የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ዕድገት 21.9 እጅ በአማካይ ከፍ እንዳረገው International knowledge sharing platform በ resurch journal of accounting የኢትዬጵያን መንግሥት መረጃ ዋቢ በማድረግ ዘግባል ፤ ይህ ከቀደምት ሁለት መንግሥታት ሲነፃፀር በዓመት ምን ይክል እጅግ ከፍተኛ ግብር እንደሚሰበሰብና ይህ ገቢ ህወአት /ኢህአድግ በሚመፃደቀው GTP/ Growth & transformation plan  ማለትም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ መገንዘብ አያዳግትም።

 

አገዛዙ ከላይ በተመለከተው ሁኔታ በልመናና በብድር በሚገኝ ገንዘብናን የአገር ውስጡን ገንዘብ ገበያው ከሚፈልገው መጠን በላይ በማተምና ከብሔራዊ ባንክና ከልማት ባንክ በመበደር ግንባታዎችን ሲያከናውን በኤኮኖሚ እድገቱም ከፍተኛ እድገት መመዝገቡን በራሱ አሃዛዊ ምንጭነት የዓለምአቀፉን ትኩረት ለመሳብና ለማዛባት ሲጠቀምበት የተባለውም ዕድገት በብዙ የምጣኔ ሀብት ጠበብቶች ትንተና የተራውን ዜጋ ሕይወት ያለወጠና የመካከለኛ ገቢ የህብረተሰቡን ክፍል  ( Middle class) እንዲፈጠር በቂ አስተዋጽኦ አለማድረጉንና በአገልግሎት ኢኮኖሚ ዘርፍ ትኩረት የተደረገ ሲሆን ዕድገቱ ጥቂት የናጠጡ ከፍተኛ ባለሀብቶች ሲፈጥር በተጉዋዳኝ በብዙ ሚሊዬኖች የሚገመተው ህዝባችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በደህነት አረንቃ ውስጥ መውደቁንና የዕለት ጉርሱን እንኩዋን አማልቶ ሊኖር አለመቻሉን ባለሙያዎች ሲገልጽ ይህንን የከፋ አፈና ፣ የኑሮ እንግልትና ስራ አጥነት አንገሽግሹዋቸው በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ዜጎቻችን በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በአሰቃቁ ሁኔታ የስደት ሰለባ እየሆኑ የበረሃ አሸዋና ባሕር የበላቸው፣ ከዚህ የተረፉትም የጦርነትና የሽብርተኛ ኃይሎች ሰለባ ሲሆኑ ተጠሪ አጥተው በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለአሰቃቂ ሰቆቃ የተዳረጉትም እጅግ ከፍተኛ ናቸው።                                                                                                               ኢትዬጵያ የምትገኝበት መልካምድራዊ  አቀማመጥና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጂኦ ፓለቲካዊ ቀውሶች መሠረት በማድረግ  የኢትዬጵያው  አገዛዝ በሶማሊያ  የውስጥ ጉዳያቸውም ጣልቃ በመግባት በሰላም አስገባሪነት በብዙ ሺዎች የሚገመት ሰራዊት በመላክ  የመጀመሪያዋ አገር ስትሆን በኃላም በ AMISOM ማለትም African Union Mission to Somalia በአውሮጳዊያን አቆጣጠር 2007 ሲመሠረት ቀዳሚውን ሥፍራ በመውሰድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት የአገሪቱ ምክር ቤት ተብዬው ባልወሰነበት ስታዘምት  ፤ በዚህ የሶማሌጉዳይ አሜሪካ ከዚህ በፊት ገብታ የከፋ መስዕዋትነት ከፍላ በሽንፈት የወጣችበት እንደመሆኑ በቀዳሚነት የዓለምአቀፉን ኃያላን መንግሥታት ቀልብ በመሳብና በዚሁም ሰበብ ህዝባችንን ጭምር የሚጨቁንበትን ከፍተኛ ዘመናዊ ወታደራዊ እርዳታዎችን በተለይም ከአሜሪካ በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ኢትዬጵያ ስትሆን ግብፅ በሁለተኝነት ተገኝታለች ፤ በድምሩ በከፍተኛ የጦር ዕርዳታና አገዛዙ እራሱን ለመከላከል በሚያወጣው ከፍተኛ ወጪ እንደ ዓለም አቀፉ ድርጅት ማለትም  The complet global fire powers of the world into full perspective  ( GED) http://www.globalfirepower.com በቅርቡ በአውሮጳዊያን አቆጣጠር 2016 ባወጣው መረጃ የዓለማችንን አገሮች የወታደራዊ ኃይል ደረጃ ማለትም index የሚያወጣው አካል ዘገባ መሠረት ኢትዬጵያ በዓለም 46ኛ በአፍሪካ ከግብጽና አልጄሪያ በመለጠቅ 3 ተኛዋ የታጠቀች ወታደራዊ  ኃያል አገር ሆና ትገኛለች በተጓዳኝ በሶማሊያም ለተከፈለው መስዕዋትነት  በወቅቱ ኢትዬጵያን የጎበኙት የቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ኃያል ሠራዊት መሆኑን አሞግሰው የአሜሪካንን ሰራዊት ከመስዋዕትነት በማዳናቸው ምስጋናቸውን ለኢትዬጵያው አምባገነናዊ የህወአት/ኢህአድግ አገዛዝ ማድረሳቸው የሚታወስ ነው ፤ ነገርግን አንድም በአሜሪካ መሰልጠኑ የሚነገርለት የአጋዚ ኮማንዶ ጦር የህዝባችንን ተቃውሞች በማዳሸቅና በመስበር የፈፅመውን ግፍና በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን በደል በአግባቡ ባለማውገዛቸው  ኢትዬጵያዊያንን በአለም ዙሪያ እጅግ ያሳዘነ ያስቆጣ ክስተት ነበር።

በዓለም የታወቀው የቀይባህርና የአሰብ ወደብ በር ባለቤት የነበረችው ገናናዋ አናት አገራችን ዛሬ ባህር በር የሌላት ጥገኛ አገር ስትሆን የዚህ ዋነኛ መሀንዲስ የነበሩትና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ አሰብ ወደብ የግመል ውኃ መጠጫ ይሆናል ብለው ሲሳለቁ አረቦችና የኢትዬጵያ ጠላቶች ከጥንት ጀምሮ አገራችንን የባሕር በር እንዳይኖራት የነበራቸው ህልም በነዚህ የሕወኃት ቁንጮዎች መሀንድስነት ተሳክቶላቸዋል፣ በዚህም ለእናት አገራችን ህልውናና ድህንነት አደገኛ በሆነ መልኩ የቀድሞ ባህር በራችን በቀን 3.4 ሚልዬን በርሜል የዓለማችን ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ድፍድፍና እንደዚሁ ሸቀጥ በየቀኑ የሚተላለፍበትን ደቡቡን የቀይ ባሕር ወሽመጥ የሚጋራው አሰብ ወደብ በቅርቡ በሳውዲና በተባበሩት አረብ እሜሬት ሙሉ ይዞታነት እጅ ወድቁዋል ፤ ከኤርትራ በረጅም ዓመታት ኮንትራትነት በባለቤትነት ተሰጥቷል በዚህም በተለይ UAE/ United arab emirates  በየትኛውም ባዕድ አገር የሌላትን ቋሚና ብቸኛውን የባህር ኃይል ጦር ሰፈርና ልዩና እጅግ ዘመናዊ የጦር  ወደብም ጭምር በኤርትሪያ አሰብ ዓለም አቀፍ እውሮፕላን አጠገብ በመገንባት ላይ ስትገኝ ይህም  ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የመን ሁቲዎች ላይ የሳውዲ ጥምር ኃይልም የአየር ጥቃትና ሎጅስትክስም ዋናው ስፍራ እዝ ሆኖ አገልግሎት መስጠት መጀመሩና  በተመሳሳይም የጅቡቲ ሪያድ የሚገኙት አምባሳደር በአንድ ወቅት ለሮይተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ጅቡቲም እንደዚሁ በተመሳሳይ ከሳውድ አረቢያ ጋር የጦር ስፈር ሳውዲ እንድትገነባ መስማማታቸውን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን እንደዚሁም Arab Emirates በሶማሌ ነፃይቱ ፑት ላንድ ግዛት ውስጥ የባህር ኃይል እዝ ለመገባት ፣ በሶማሌ በርበራ ዘመናዊ ወደብ በተመሳሳይ ለመገንባት የብዙ ሚሊዬን ዶላር ስምምነት መደረጉን ብሉምበርግ በ November , 2017 በስፋት ሲዘግብ በዋነኝነትም አረብ ኢምሬት የተባበሩት መንግስታትን በኤርትራ ላይ የጣለውን ወታደራዊ ማዕቀብ በመተላለፍ የኤርትሪን ወታደራዊ አቅም በመገንባት 13 ከፍተኛ የአየር ኃይል ካዴቶችን በአገሯ አሰልጥና እንደላከች አትቷል ፤ በጥቅሉ በአሁኑ ወቅት ኢትዬጵያ የራስዋ የሆነ ባህር በር የሌላት /Landlocked የሆነነች አገር እንደመሆንዋ ይህ ደግሞ ከቀደመው ታሪካችን የሚያስገነዝበን አፄ ሚንልክ በውጫሌው ውል ጦርነት ወቅት አሰብም 1880 ግድም በውጭ ኩባንያ ተይዞ ስለነበር ፈረንሳዬች ከጣሊያን እንግሊዝ ጎን በመወገን ኢትዬጵያ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያና ቁሳቁስ በጅቡት ወደብ በኩል እንዳታስገባ ያገድበትን ወቅት ነበር ፤ እንግዲህ ዛሬ ላይ ሆነን  ምንም  የራሳችን የሆነ መግቢያ የሆነ ወደብ በሌለበት ሁኔታና በተለይም ጅቡቲም ብትሆን አንድም የአረብ ሊግ አባል እንደመሆናና ሌሎችም አጎራባች አገሮች ሶማሊያና በተመሳሳይም ሁለቱንም ሱዳኖች ጨምሮ ኃይማኖት ዋነኛው ገፊ ሃይል እስከሆነ ድረስ በእስልምና ስም በእጅ  አዙር አረቦች በአስፈለጋቸው ወሳኝ ወቅት የሚፈልጉትን ተጽዕኖ ለማድረግ የሚከለክላቸው ምንም ነገር አለመኖሩን እንመለከታለን ፣ እነዚህንና የመሳሰሉ ጂኦ ፓለቲካዊ ሁኔታዎች ዛሬም ይሁንለነገውንን ትውልድና እናት አገራችንን በክፉ ጊዜ እንዴት በጠላቶቻችን መዳፍ ስር እንደምትሆን መገመት  ይቻላል፤ በቅርብ ግዝያት ኢትዬጵያ በምትገነባው የህዳሴ ግድብ ሳቢያ ከግብፅ መንግስት ጋር ውጥረቶችን ተከትሎ የግብፅ መንግስት በኤርትራ ውስጥ ጦር ማስፈሯና ይህንንም ተከትሎ የሳውዲና የአረብ ኢምሬትስ በኤርትራ መዲና መታዬት ለቀጠናው ስጋት እንደሆነ ዓለም አቀፍ ሚድያዎች ትንተናዎች መስጠታቸው ተስተውሏል፤

በተመሳሳይ ለሱዳን ይከለላል የተባለውን መሬት አስመልክቶ እንደ ቀድሞው የህወት አመራር አባል አቶ ገብረመድህን አርአያ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ እነ አቶ መለስ ጫካ በነበሩበት ወቅት የሱዳን መንግሥት ለዋለላቸው ውለታ ህወኃት አሁን የተባለውን መሬት በውለታነት ለመስጠት ቃል ተገብቶ እንደነበር በእማኝነት መግለፃቸው የሚታወስ ነው፤ የህወአት ምስረታ 39 ዓመት በዓል መቀሌ በተከበረበት ወቅት የሱዳኑ መሪ አልበሽርና የወቅቱ የሱዳን ስለላው መረብ ተጠሪ የነበሩት በበዓሉ ላይ ተገኝተው ሻቢያንና ወያኔን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ባለድል ለማድረግና እዚህ መድረስ የህወአትን ደፈጣ ጦር በማሰልጠን ፣ በማስታጠቅና በማሰጠለል አጠቃላይ ለህወኃት ድል የተጫወቱትን ሚናና ገድላቸውን ለትግራይ ህዝብ ሲደሶኩሩ የተደረገላቸውን የደመቀ አቀባበል ስንመለከት ሱዳን ኢትዬጵያ እንድትበተንና እንድትበጣጠስ ወደብ አልባና ደካማ አገር እንድትሆን ጥንትም ይሁን በቅርብ የተጫወተችው ሚና ከማናቸውም ሌላ አጎራባች አገር ያልተፈጸመ መሆኑን ኢትዬጵያዊያን ልብ ልንል ይገባል ! ለዚህም ውለታ ነው በአባቶቻችን ደምና አጥንት ተከብሮ የኖረውን መሬት ነው በእጅ መንሻነት ለሱዳን ለመስጠት ነው ህወኃት ጫካ በነበረት ወቅት የገባውን ቃል ለመፈጸም ተነስቶ የነበረው።

ባለ ራዕው መሪ የተባለው መለስ ዜናዊም በብዙ የዓለምን ትኩረት በሚሹ ጉዳዬች አነፍንፎ በመግባት የአየር ብክለትሊቅ ከመሆንም ህዝብን አፍኖ ይዞ በጎረቤት አገራት የሰላም ሸንጋይ በመሆን ራስን የማግዘፍ ስትራቴጂ በመንደፍ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ አፍሪካዊቷ አሜሪካ ለመሆን በቅተው ነበር፤ በዚህም ብዙ ድጋፍ ተችረዋልማለት ይቻላል።

ኃያላን መንግሥታትም ቢሆኑ አይሎ ከተገኘ ወገን ጎን የአገራቸውን Strategic interest /ስልታዊ ጠቄሚታን ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸውንና ምንም እንኳ በአገራቸው የምታየው ፍታዊ ስርዓት ከዋነኛ እሴቶቻቸው አንድ ቢሆንም ለጥቅማቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ ፤  በመላው ዓለምም ይሁን በአገር ውስጥ ሥርዓቱ በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን መጠነሰፊ በደልና የሰባዊ መብት ጥሰት በመቃወም በአለፉት 27  ዓመታት በላይ በዓለም ታላላቅ ከተሞች ኢትዬጵያዊያን  በነቂስ ወጥተው ያልተሰለፉበት፣ ያልተቃወሙበት ወቅትና ጊዜ የለም ፤ በተመሳሳይ የኢትዬጵያ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶችና ምሁራንም ጭምር ምሥክርነት ያልሰጡበትና ያላንካኩት የኃያላን መንግሥታት በር የለም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምናልባትም ከፍልስጤማውያን በበለጠ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ጮኽናል፤ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ጥቁር አሜሪካዊ ባራክ ኦባማ በአለፈው የአፍሪካ መሪዎችን ዋሽንግተን ዲሲ ባነጋገሩበት ወቅት ኢትዬጵያዊያን ከሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች ጭምር መጥተው በነቂስ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን እንቅስቃሴ እስከሚያውክ ሙሉ ቀን ተቃውሞ ሲያደርጉ ፕሬዝዳንቱም ይሁን ሌሎች ባለስልጣናት በሚገባ አስተውለዋል ተመልክተውታልም ፣ እንደዚሁ  የፕሬዝደንቱን የኢትዬጵያ ጉብኝት በወቅቱ በመቃወም ከጉዙዋቸው ቀደም ባሉ ቀናት በአውሮጳውያን አቆጣጠር በ July 3,2015  በነቂስ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ኢትዬጵያዊያን በዋሽንግተን ዲስ ዋይት ሀውስ ፊት ለፊት በመገኘት ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል ፤ ነገር ግን ፕሬዝደንት ኦባማ አዲስ አበባ በሄድበት ወቅት በተቃራኒው ለተቃዋሚ ድርጅቶች ይባሱኑ ማስጥንቀቂያ ነበር የሰጡት እጠቅሳለሁ ” I don’t bite my tongue too much when it comes to those issues.

We are opposed to any group that is promoting the violent overthrow of a government, including the government of Ethiopia, that has been democratically elected ” ብለው ነበር በዚህም ኢትዬጵያዊያን ጥቁር  መሪ የአሜሪካ ፕሬዝደንት እንዲሆን በነቂስ ወጥተው በመምረጥ አሻራቸውን ቢያሳርፉም ኢትዬጵያ ላይ በተከተሉት ፓሊስና በመዲናችን ተገኝተው በአስተላለፉት መልዕክት ለአምባገነኑ አገዛዝ ፓለቲካዊ አቅም በመሰጠቱ ኢትዬጵያዊያን አምርረው አዝነዋል ፣  ነገር ግን ፕሬዝደንት ኦባማ ቀደም ሲል ሌላይቷን አፍሪካዊት ነገርግን ዲሞክራሲያዊት አገር  ጋናን በጎበኙበት ወቅት  የተናገሩትን ጥቅስ ” Africa doesn’t need  Strongmen ,It needs Strong Institutions ” በማለት አፍሪካ ኃይለኛ ወይም አምባገነን መሪ ሳይሆን የምትፈልገው ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት ነው የምትሻው ባለበት አንደበቱ ኢትዬጵያን በጎበኙበት ወቅት በተቃራኒው ያለ ህዝብ ይሁንታ ስልጣን ላይ የቀጠለውን አምባገነና ዘረኛ መንግሥት አሞግሰዋል ፣ ምክንያቱም ጋናዊያን በአፍሪካ ቀዳማይ ዲሞክራሲያዊና ፍታዊ መንግሥት አላቸውና ምንም ቢነገር ጉድለት እስከሌለባቸው የሚከፉበት አይሆንምና  መሪዎችም ከዚህ የጠሩ በመሆናቸው አባባሉን በደማቅ ጭብጨባ ደግፈውታል።

ብዙዎች ኃያላን መንግሥታት መሪዎች አውሮፓ መንግሥታትን ጨምሮ ኢትዬጵያን ከስትራቴጅክ ጥቅማቸው ቀዳሚ መዳረሻ በማድረግ ጎብኝተዋል ድጋፋቸውንም ሰጥተዋል! በዚህም ከፍተኛውን የአሜሪካ ዕርዳታ በማግኘት ከዓለም ቀዳሚዋ ኢትዬጵያ ስትሆን ብርታኒያም በበኩልዋ በቅርብ እርዳታውን መፈተሽ እስከጀመረችበት ጊዜ ድረስ 376 ሚሊዬን የእንግሊዝ ፓውንድ በዓመት በመለገስ ሁለተኛዋ ቀዳማይ አገር ኢትዬጵያ ነች፤ ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ሲከሰት እነዚህ አገሮችና መሪዎች ህዝባችንን የሚሸነግሉት ቢበዛ ” አሳስቦናል ነው” አለዚያም  ጥርስ በሌለው የዓመታዊ ዘገባቸው የአገራት የሰብዓዊ  አያያዝ  ላይ ያላቸውን ጉድለት ሪፓርት በውጭ ጕዳይ ዘርፎቻቸው ያወጣሉ ፣ በአብነትም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ማለትም State department  ኢትዬጵያን  አስመልክቶ የአወጣውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት  ጥሰት  46 ገጽ ሪፓርት ማየት ይቻላል፤ ነገር ግን ለበርካታ አመታት በተከታታይ ዓመታዊ ዘገባዎች ወጥተዋል በዚያው ልክ  ለመልካም አስተዳደር  good governance  መነሻቸው በማድረግ የዕርዳታቸው ቅድመ  መመዘኛ አድርገው የአቀቡበት ወቅት አልነበረም ፤ በአሁኑ ወቅት ህዝባችን የህወአትን አገዛዝ በመቃወም በበርካታ ማዕዘናት ህዝባዊ እምቢተኝነቱን በገለፀበት ወቅት ፣ አረመኔው አገዛዝ በርካታ ዜጎቻችንን በተለይም በኦሮሚያ በጠራራ ፀኃይ በገደለበትና ፣ በብዙ ሺዎች ለጅምላ እሥር በተዳረጉበት ፣ አገሪቱ ወደ አደገኛ ሁኔታዎች እየተገፋች ባለበት ሁኔታና ይህም የአገዛዙ አፈናና ግድያ ሞልቶ ተርፎ ህዝቡንም መሰረት የአደረገ ትግል በሰሜን ጎንደርና ሌሎችም አማራው አካባቢ ህዝቡ እራሱ በምሬት በተለያዩ አግጣጫዎች በድር በገደሉ እጅግ የከፋ የትጥቅ ትግልም ውስጥ መገባቱንና ይህንንም ለመምታት ለማዳሸቅ ዜጎችን በጅምላ በማሰርና በመግደል አሸማቀውታል ፤ ይህንን ውጭ ዜና ምንጮችም በስፋት ሲዘግቡት ነበር ፤ ዜጎቻቸውም ላይ  በነዚህ አካባቢዎች የጉዞ እገዳም በወቅቱ የአደረጉ  አገሮችም በበርካታዎች ነበሩ ፤ ይህ የሰሜኑ ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ብረት ትግል መግባቱ አገዛዙን እጅግ ያሳሰበው ከመሆኑም አልፎ ከህዝቡ ጋር መቃባቱ መሮአቸው ስንብት የሚጠይቁ የሰራዊት አባላት መከሰት ጭምር አገዛዙን ጭንቅ ውስጥ በማስገባቱ ይህንን ከመሳሪያ ጋር የአደገውን ህዝብ ትጥቅ ለማስፈታት ዘመቻ መክፈቱ እልቂቱን የከፋ እያደረገው የቅርብ ጊዜ ክስተትም ነበር።

የአሜርካው ፕሬዝደንት ኦባማ በስምንት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው የኢትዬጵያዋያኑን አቤቱታ ከግምት አስገብተው  ወጣ ብለው ከህዝባችን ጎን አልቆሙም፣ አገዛዙንም አልተጫኑትም፤ ምናልባትም አሁንም ኢትዬጵያ ተሰግቶ ወደነበረው ብሔር ተኮር የመበታተን አደጋ በተጋረጠበት ኢትዬጵያ የሚገኙው ኤምባሲ እልቂቱን በማውገዝ የተለመደ መግለጫ ቢያወጣም አዲስ  የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕም በምርጫ ፉክክራቸው ለማሸነፉ ሲሉ ከአቅም በላይ የገቡዋቸውን ቃሎች በመፈፅምና ባለመፈፀም አኳያ የሚጠብቃቸው የአገር ውስጡ አጣብቂኝ እንደተጠበቀ ሆኖ ፋታ ቢያገኙ እንኳን እንደማናቸውም ቀደምት ፕሬዝደንቶች የአገራቸውን ስልታዊ ጠቀሜታ ቅድሚያ ከመስጠት በስተቀር   በኢትዬጵያ ላይ የሚከተሉት የፓሊሲ ለውጥ ልንጠብቅ ከቶውንም አንችልም ፤ ሌሎችም የአውሮጳ መሪዎችና ካናዳም እንደዚሁ።

ነገር ግን የኢትዬጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች በአማራጭ ኃይልነት አንድነታቸውን አረጋግጠው አንድ የተማከለ ኃይል መሥርተው ቀጣዬን የለውጥ ማዕበል መሸከም የሚችል ድርጅታዊ መዋቅር ገንብተውና ህዝባቸውን ባለቤትና ማዕከል አድርገው ትግሉን የመምራትና የማስተባበር የፈረጠመ ትከሻ እስካልኖረን ድረስ ማናቸውም የኃያላን አገር መሪ የአገሩን ስልታዊ  ጥቅም የሚያስጠብቅ የፈረጠመ መዳፍና አመራር ያላት አገዛዝ ኢትዬጵያ ውስጥ እንዲኖር ይሻሉ  ፣ በአገር ውስጥ ህዝባችንም ይሁን ዓለም አቀፍ ኃያላን መንግሥታት አንድ ትልቁ ሥጋታቸው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በተጨማሪ ፤ ኢትዬጵያ በህዝብ ብዛትም ከአፊሪካ በሁለተኝነት የምትገኝ ትልቅ አገር እንደመሆኑዋ አስተማማኝ ቅድመ ዝግጅት በሌለበት ሁኔታ የሥርዓት ለውጥ ቢከሰት ቀውሱ አሁንም መረጋጋት ባጣውና  ቋፍ ላይ ለአለው የአፊሪካ ቀንድም ጭምር የሚተርፍና ለሶማሊያው አልሸባብ ዓይነት ሽብርተኝነትና እንደዚሁም እንደ አንዳንድ አጎራባች አገሮች እጣ ፋንታ የከፋ ቀውስ፣ ፍልሰትና አንድነትዋን የሚያውክ አደጋ አገሪቱ እንዳያጋጥማት ከፍተኛ ስጋት ይኖራቸዋል ፤ ስለሆነም ምንም ዓይነት መንግስታዊ ለውጥ ሲታሰብ ይህንን ሊተካ የሚችል አማራጭ ኃይል ማየት ይሻሉ!! ስለሆነም የሚመጣውን ለውጥ ሊመራና ህዝቡንም ሊያረጋጋ የሚችል አማራጭ ኃይል ነጥሮ አለመውጣት በተቃዋሚው ጎራ የሚታየው መናቆር የህዝባችንም የዓለም አቀፍ ማህበሩም ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው ፤ አሁን በአገራችን የህዝባችን ጥያቄ ከመብት ጥያቄ አልፎ የህወኃት/ ኢህአደግ አምባገነን አገዛዝ ስልጣን እንዲለቅ በአንድ ድምፅ በመጠየቅ ላይ ነው፤ የህዝቡ ግፊት በየክልሎች ፋታ በመንሳቱ አጣብቅኝ የገቡት ክልል መንግስታትም ከፋዴራሉ ስርዓት ወደ ፍች አይነት ማፈንገጥ መታየቱ  በዚህም ስርዓቱ ወደ እርስ በርስ የክልሎች መገነጣጠል አደጋ ውስጥ አገሪቱን እያስገባ ነው! አሁን በሚታየው ሁኔታ  ግብታዊ ለውጥ ቢከሰት እንኩዋን አገሪቱን ለማረጋጋት ዛሬ ስልጣን ላይ የሚገኘው አገዛዝ መጠናኛ ማሻሻያ በማድረግ በጥገናዊ ለውጥ ማስቀጠል እድል ሊያገኝ ይችላል ፤ ይህም ካልሆነ ከወዲሁ የአንድነት ኃይሉ የተማከለ ኃይል እስካልፈጠረና የስልጣን ክፍተቱን መሙላት የሚችል አስተማማኝ አቅም ከወዲሁ እስካልተገነባ ህዝብን አመፅ ተንተርሶ በግብታዊነት የሚከሰት ለውጥ አሁን ከሚታየው ብሔር ተኮር ግጭት ወደ ሰፊ እልቂት ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

 

መለስ ብለን በአገዛዙ ላይ ብቻ ጣታችንን በመቀሰር በአገራችን ላይ ያጠላውን ቀውስ ማለፍ አንችልም ይልቁንም በጥንቃቄ መገንዘብ ያለብን ዛሬም ቢሆን ለአገራችን ችግር ባለቤቶችም መፍትሄ አምጭዎች እኛና እኛ ነን!

እኛ ደካማና የተከፋፈልን እስከሆንን ማናቸውም አገርና መንግስት የሚቆመው ካየለው ወገን ጎን ነው፤  የኢትዬጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች አንድ ሆነን አንድ ቋንቋ ስንናገር ፣  አብረን በውጭም በውስጥም ጥሩ አማራጭ ኃይል ሆነን ስንገኝ ፣የተማከለ አመራር ለህዝባችን በመስጠት ተጽዕኖ የሚፈጥር አቅም ስንገነባ በርግጠኝነት አሜሪካም ትሁን ሌሎች ኃይላን መንግሥታት የእኛን በር የሚያንኩዋኩበት ወይም ለአምባገነኑ አገዛዝ ማድላት የሚያበቁበት ሁኔታ እንደሚከሰት መገመት አያዳግትም ፤ ፕሮፌሰር በየነ ጰጥሬስ በቅርብ ጊዜ ዋሽንግተን በታደሙበት ስብሰባ በምርጫ 97 የቅንጅት አንድ የተባበረ ኃይልና ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆኑ እርሳቸውንና እንጂነር ኃይሉ ሻወልን የሚመራው አመራር በአሜርካ White House እስከ Oval room ድረስ በመጋበዝ ከአገዛዙ ጋር ለማደራደር የተማፀኑበት ጊዜ ሁሉ እንደደረሱ የአንድነትን ኃይል ለማሳየት ሞክረዋል ይህም የሚያሳየን የሚያሳየን ይህንኑ እውነታ ነው።

በሌላም በኩልም የቅርብ ጊዜ ማሳያ የሚሆነው የጎሬቤት አገር ግብፅ ኃያል መንግሥትና መሪ የነበሩት ሁስኒ ሙባረክ ከእስራኤል በመለጠቅ ከአሜሪካ ብቻ በዓመት 1.3 ቢሊዬን ዶላር እርዳታ ስታገኝ በጥቅሉ በአውሮጳዊያን አቆጣጠር 1948 እስከ 2011 ብቻ 71.6 ቢሊዬን ዶላር የወታደራዊና ኤኮኖሚያዊ እርዳታ ስታገኝ ከፍተኛው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በተመለከተም ለምሳሌ በአንድ ወቅት ብቻ 1200 በላይ የታወቀውን የአሜሪካ M1A1 Abrams battle ታንኮችና ከ 20 በላይ F-16 ዘመናዊ የጦር ተዋጊ አውሮፕላኖች ስትታጠቅና ድጋፍ ስታገኝ በዚሁ ልክ በርካታ ወታደራዊ ስልጠናዎች የምታገኝ አገር ነበረች ፤ በአሜሪካ ፣ በሌሎችም ኃያላን መንግሥታት ፣ በእስራኤልንና በመላው መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ገናናና ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው መሪ የነበሩት ሁስኒ ሙባረክ የግብፅ ህዝብ በአንድ ላይ በመቆሙ ወደ ኃሊት ሳይመለስ እምቢኝ በማለቱ በአንድ ጀምበር ሥልጣንን እንዲለቍ በአሜሪካ መንግሥት መጠየቁና እጣ ፋንታቸውም መወሰኑን ስንመለከት ማንኛውም ኃያል መንግሥት ህዝብ አብሮና ተባብሮ በተቀናጀ መልኩ ከተነሳ የትም እንደማይደርስ በቅርብ ተመልክተናል ።

በግብፅ ለውጥ ውስጥ የጎደለው በለውጥ ኃይሉ የተደራጀ ቅድመ ዝግጅት ባለመኖሩ የሥርዓት ለውጥ ጉልበት ባለውና አይሎ በተገኘው ወታደራዊው አገዛዝ መዳፍ ውስጥ በመውደቁ አገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅና የአካባቢውን ስትራቴጅክ ጥቅም የማስጠበቅ ጉልበት ቢኖረውም፤ የግብፅ ህዝብ የሚመኘውን ፍታዊና ድሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያመጣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባለቤት የአደረገ የሽግግር ሥርዓት ሳይኖረው በመጠለፉ እንደ ኢትዬጵያ በወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ጫንቃው ላይ መሸከም ተገድዋል ፣ ይህ ዓይነት የስልጣን ሽግግር የኢትዬጵያ ህዝብም ባለፉት ሁለት የአገዛዝ ለውጦችም እድሉ አምልጦታል ፣ ያለፈቃድም ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ ከእንደዚህ ዓይነት አምባገነን አገዛዝ ከጫንቃው ላይ ከመሸከም ለመላቀቅ ፈጽሞ አልታደለም ፤ ነገስ ?

በቀደመው ተከታታይ ክፍል ለማሳየት የተሞከረው የአምባገነኑን ሥርዐት የኃይል አስተላለፉን በመጠኑም ቢሆን ለመመልከትና የቆመባቸው ማህበራዊ ኤኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ምሶሶዎችና መሠረቱን ለመዳሰስና በዲፕሎማሲውም ዘርፍ የአገራትን በተለይም የኃያላን መንግሥታትን ኤኮኖሚያዊ ወታደራዊና ፓለቲካዊ ድጋፉን መጠን ለማሳየትና አገዛዙ በወገኖቻችን ላይ በየጊዜው የወሰደውን መጠነ ሰፊ አፈናና  ረገጣ ለመሸፈን በምን ዓይነት ጥበብና የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነት የመንግሥታትን ድጋፍ በሰፊው እንዳገኘ ለማመልከት ሲሆን በዚህ ረገድ የኢትዬጵያ ተቃዋሚ ድሞክራሲያዊ ኃይሎች በተቃራኒው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰቡም ይሁን ለህዝባችን ጥሩ አማራጭ ሆነው ለመውጣት የአለመቻላቸውን መሠናክል በአግባቡ ለመመርመርና ይልቁንም ለአገዛዙ ያነሰና የተዛባ ግምት ባለመስጠት ጥሩ የተባበረና የተማከለ ጠንካራ አቅም በመፍጠር ቢያንስ የተሻለ ቁመናን በመገንባት ትግሉን በአሸናፊነት መውጣት የምንችልበትን መንገድ ለመተለም የባላንጣችንን የኃይል አሰላለፍ ማወቅና በዚሁ ልክ በሁሉም ዘርፍ አቅምን አስተባብሮ መንቀሳቀስ ግድና ወሳኝ  መሆኑን ለማሳየት ነው ።

በተቃራኒው የኢትዬጵያ ፓለቲካ ድርጅቶች በነበሩበት መርገጥ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም የህብረት ትግል ተስኖአቸው  ወደኃሊት ማዝገማቸው ፍንትው ብሎ የታየበት ወቅት ነው ፤ የህዝባችንንም ግፍና መከራ ሞልቶ መሪ ቢያጣም ማናችንም ተቀበልንም አልተቀበልንም ዛሬ እመሬት ላይ የሚታየው የለውጥ ማዕበል ማንም ያልመራው በህዝቡ በራሱ የተመራ ትግል መሆኑን መቀበል ግድ ነው ፤ በቅርብ ጊዚያት ጎረቤት አገር ግብፅም ህዝቡ የሁስኒ ሙባረክን የዘመናት አምባገነናዊ አገዛዝ ከሚሸከመው በላይ ሲሆንበት በማህበራዊ የግንኙነት መረብ መሳሪያነት ታሪቅ አደባባይ በመክተምና አገዛዙን ትንፋሽ በማሳጣት ከጫንቃቸው ማስወገድ ችለዋል ፣ ነገር ግን በተከሰተው  የስልጣን ክፍተት ጎልበት ያለውና በለስ የቀናው ወደ መንበሩ የመውጣት እድል ሲገጥመው የግብፅ ህዝብ የተመኘውን ፍታዊና ድሞክራዊ ስርዓተ ማህበር  ባለቤት መሆን አልቻለም ፤ በአገራችንም የአምባገነኑ አገዛዝ መወገድ አይቀሬ ነው ለዚህም በአንድነቱ ጎራ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት በሌለበት ሁኔታ የሚከሰት ለውጥ መጪውን አሻግሮ ለማየት ከነዚህና መሰል የአካባቢው የህዝብ አመጾች ብዙ መማር እንደሚቻል ለማሳየትም ጭምር ነው።

ኃያላን መንግሥታትም ቢሆኑ በተለይ በኢራቅና ሊቢያ ወዘተ.. አምባገነን አገዛዞችን በማስወገድ ፈሊጥ ብቻ በመመራት የተወሰደው እርምጃ ብዙ የጦር አበጋዞች በመውለድ የርስ በርስ ጦርነቱን መቆጣጠር መሳናቸውና ከዚህም በመማር በሶሪያ የአሳድን መንግስት ያለተተኪ ማስወገድ ይባስኑ ለሽብርተኛ ኃይሎች ክፍተት እንዳይፈጥር ካለፈው በመማር የሩስያን እቅድ በመቀበል ሌላ የተባበረ ኃይል ባለመኖሩ ከአሳድ መንግሥት ጋር ተባብሮ በመጀመሪያ አገሪቱን ወደ ማረጋጋት ፓሊስ መሸጋገራቸውና ምናልባትም ያለፈውን ዓይነት ስህተት እንደማይደግሙም ብዙ የምንማርበትም  ነው።

 

ወቅታዊው ህዝባዊ እምቢተኝነት ትኩሳቶች ችግሮቹና የመፍትሔ  አቅጣጫዎች፤

 

ዛሬ በአገራችን ከምን ግዜውም በላይ እጅግ በከፋና በተባባሰ ሁኔታ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ተባብሶ ቀጥሏል፣

ህዝባችንም በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት ይህ አገዛዝ ስልጣን እንዲለቅ በግልፅ  ጥያቄዎች እያነሳ ይገኛል፤ በርካታ ዜጎችም ይህንን ጨካኝ ፣ ዘረኛና አምባገነን ሥርዓት በመቃወማቸውና አደባባይ በመውጣታቸው ክቡር ህይወታቸውን መስዋትነት እየከፈሉ ይገኛሉ።

 

ከዓመታት በላይ ያስቆጠረው የመላው ኦሮሚያ ወገኖቻችን የመብት ጥያቄ  በአንዲት ግንጪ በምትባል ከተማ የተለኮሰውና ከመሬት ጋር የተያያዘው የመብት ጥያቄ በፍጥነት ተቀጣጥሎና ተዛምቶ ከዚህም ቀደም ሲል ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ በአዲስ አበባ የማስተር ፕላን ማስፋፊያ እቅድ በተነሳው ተቃውሞ ሳቢያ የከፈለውን አስከፊ መስዋትነትና በተለይም የወጣት ልጆቹን በአጋዚ ጥይት መርገፍ የታመቀ ሃዘኑንና በደሉን አንግቦ አምባገነኑ አገዛዝ በተደጋጋሚ ግዝያት ከአደባባይ ሰልፍ እስከ ስራ ማቆም አድማዎች አድርጓል አልፎም በግልፅ ሥርዓቱ ስልጣን እንዲለቅ እየጠየቀ ይገኛል ፤

እነዚህን በአማራው በጎጃምና ጎንደር ህዝብ በነቂስ የህወኃት/ ኢህአደግን አገዛዝ በጎበዝ አለቃ እራስን በማደራጀት በገጠርም ይሁን በከተማ ብረት በማንሳት እስከመፋለም ከመድረሱም በክልሉን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር እራሱንና ልጆቹን በማስራብ ሥራን ከማቆምና የንግድ መደብሮችን በመዝጋት ስራቱን በሁሉም መንገድ ተፋልሟል እየተፋለመም ነው፤ በዚህም ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወጣቶችና አረጋዊያን የአጋዚ ጦር ሰለባ በመሆን ምትክ የሌለውን ክቡር ህይወታቸውን ሰጥተዋል ፤ ህወኃት/ኢህአደግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ አድርጎ የፓለቲካና የሂሊና እስረኞች መኖራቸውን ለመጀመሪያ ግዜ አምኖ እስረኛ ለመልቀቅ ለዓለምም ጭምር ቃል በገባበት ማግስት አሁን በሰሞኑ በሰሜን ወሎ ወልዲያ ፣ ቆቦና መርሳ መላው ህዝብ የተሳተፈበት ህዝባዊ እምቢተኝነት ጥያቄ ሳቢያ እየተካሄደ ያለው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ግድያና ይህንን ተከትሎ ቀውሱና ህዝባዊ  እምቢተኝነቱ እየሰፋ እንዳለ ይህንንም ተከትሎ ፣ መንግስታዊ ስራ ፣ የትምህርትና ንግድ አገልግሎት መቋረጡን ተመልክተናል ፤ በአገራችን በርካታ  አካባቢዎች ተነስተው የነበሩ የመብትና የማንነት ጥያቄዎች ወደ ፓለቲካ ጥያቄነት ከመሸጋገራቸውም በሁሉም አካባቢ  ሰብዓዊ መብቱን የነፈገው የጋራቸው የሆነው ብቸኛው እርስ በርስ አጋርነት የመግለፅ ህዝባዊ ምላሾችን ከምን ጊዜውም በላይ ጎልተው ወጥተዋል፤ በቀደመው  በጎንደርና ባህር ዳርም በኦሮሚያ ወገኖቹ ላይ የደረሰውን ግድያና ጭፍጨፋ የአወገዘ  የአጋርነት መልዕክቶች ከወትሮው ጎልተው መታየታቸው ለአገዛዙ የህዝቡ አንድነት እንደ ከፍተኛ ስጋትም ታይቷል ፤  በኦሮሚያና በአማራ ክልል ፕሬዝደንቶች በህዝቡ መካከል አንድነቱን ለማጠንከር የተወሰደው እርምጃ ከህወኃት/ኢህአደግ እውቅና ወጪ መሆኑ ለአገዛዙ ስጋት ቢሆንም የህዝቡን ትግል  ወደ አንድ ማዕከል በማምጣቱ ረገድ ስጋትንና ጥርጣሬን መቅረፉ ለትግላችን አንድ እመርታና ትልቅ አቅምም ሰጥቷል ማለት ይቻላል ።

በዚህም በኩል  በመላ አገራችን ላይ የህወኃት/ኢህአደግ አገዛዝ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ አፈና በብሔራዊ ደረጃ አጉልቶ የአወጣ ህዝባዊ ማዕበል በበርካታ የአገራችን ማዕዘናት ሲቀጣጠልና በኃይልም ሲታፈን ነበር ይህም ከዓመታት በላይም ያስቆጠረው መራር ህዝባዊ እምቢተኝነት እጅግ ተጋግሞ እየተከሰተና ተመልሶ እየተዳፈነ የዕልፍ አዕላፍ እምቢኝ ያሉትን ዜጎኝ ክቡር ህይወት እያስከፈለ ዛሬም በተመሳሳይ በአንድ ድምፅ ከመብትና የማንነት ጥያቄ አልፎ መንስኤው የሆነው ሥርዓቱ እራሱ ስልጣን ለህዝብ እንዲያስረክብ እየተጠየቀ ነው! በሥርዓቱም ውስጥ በምሶሰነት ኢህአድግ የተባለውን ከመሰረቱት አንዳንዶች በህወኃት የበላይነት መቀጠል እንደማይቻል በመግለፅ ለፌደራሉ ሥርዓት መሸርሸርና በዋነኝነትም ለህወኃት የበላይነትና አልፎም ለህልውናው ትልቅ አደጋም ወደ መሆን ተደርሷል።

ለአንባቢያን ማሳየት የተፈለገው አሁን አገሪቱ የምትገኝበትን ፖለቲካዊ ግለትና እመሬት ላይ ከወትሮው በሰፋ መልኩ የሚታየውን ህዝባዊ እምቢተኝነት አስፈሪ ድባብ ለማሳየት እንጅ ይህ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ በተለያዬ የአገሪቱ ክልሎች እየተከሰቱንና በኃይል እርምጃ የተዳፈኑትን ፤ የህዝባችንን እጅግ ሰላማዊ የመብትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአገዛዙ በኃይል የተጨፈለቁት ፣ በወላይታ አረካና በወጋ ጎዳ ሳቢያ በግፍየታሰረ የተገደሉትን ፣ የአኝዋክን ህዝብ ጨምሮ በጅምላ የተጨፈጨፉ ንፁኃንን ፣ በደኖ በአማራ ወገኖቻችን በጅምላ ጭፍጨፋ ፣ በአኙዋክ ህዝብ ላይ የደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋና በዚሁም ሳቢያ የአኝዋክን ህዝብ አስተባብራችኃል በመባል በሽብርተኝነት ስም ለበርካታ ዓመታት በየወይኒ ቤቱ የታጎሩትን ፣ እንደዚሁም እስከ ዛሬም  የሞስሊሙ ወገኖቻችን  በአነሱት እጅግ ሰላማዊ የመብት ጥያቄዎቻቸውም ምላሽ ሳያገኙ  ፣ መሪዎቻቸው ማለትም የሞስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ዛሬም ቢሆን ጥቂቶች ሲለቀቁ አሁንም ብዙዎች በግፍ ታስረው ይገኛሉ ፤ ስለሆነም በጥቅሉ ቤት ይቁጠረው እንጂ  በዚህ አጭር ጽሑፍ ወስጥ ሁሉንም ማጠቃለል ፈጽሞ አይቻልም ፣

በኦሮሚያ ውገኖቻችን ላይ የሃያ ስድስት ዓመታት የደረስው ግፍ ወሰን የለውም ለአብነትም በአንድ ወቅት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመጽሐፋቸው በቃሊቲ የእስር ቆይታቸው የታዘቡትን በእስር ቤቱ የኦሮምኛ ተናጋሪው ቁጥር ምን ያህል እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በአግራሞት ሲገልፁ በተመሳሳይም በጊዜው ዋና አሳሪ የነበሩት ከፍተኛ የህወአት አመራር አባል አቶ ስዬ አብርሃ  በተራቸው ቃሊቲ ወርደው በእስር ቆይታቸው የታዘቡት የኦሮሞ ተናጋሪዎች ቁጥር  እጅግ ከፍተኛ መሆኑን እንደዚሁ በመጽሐፋቸው ላይ መግለጻቸው ምን ያህል ኦሮሚኛ ተናጋሪውና ሌሎችም ዜጎቻችን በገፍ በበርካታዎች ትላልቅ እስር ቤቶች ታጉረው እንደሚገኙ አመልካች ነው።

ክፍል ሁሉት መፍትሔ አቅጣጫውን የሚያካትተው  ይቀጥላል!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top