News Feature

የአጼ ቴዎድሮስ ሃውልት ዛሬ በደብረታቦር ከተማ ተተክሎ ተመርቋል


[ቴዲ አትላንታ]

የአጼ ቴዎድሮስ ሃውልት ዛሬ በደብረታቦር ከተማ ተተክሎ ተመርቋል። ከዚህ በፊትም በጎንደር እንዲሁ ሃውልታቸው ቆሟል። በቅርቡም እንዲሁ በናዝሬት ከተማ ለአትሌት ዋሚ ቢራቱ ፣ ለአርቲስት አሊ ቢራ መንገድ በስማቸው የተሰየመ ሲሆን፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ እዚያው ናዝሬት ከተማ እንደ አፄ ገላውዲዮስ ት/ቤት ፣ደጀኔ ስሜ ት/ቤት ፣ ሀይለማሪያም ማሞ ሆስፒታል እንዲሁም ሌሎች ስማቸው ተለውጦ በሌላ መተካቱም ተነግሯል።

ለታዋቂዎቻችን እና ለጀግኖቻችን መታሰቢያ መሰራቱ ግሩም ተግባር ሆኖ ሳለ፣ እነዚህ ሰዎች ጀግንነታቸውም ሆነ ታዋቂነታቸው ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሆኖ ሳለ፣ መታሰቢያቸው ሁሉ “በክልል” ብቻ እየሆነ ከመጣ ክብራቸውን ያሳንሰዋል እንጂ ከፍ አያደርገውም።

አንድ ሰው በተወለደበት መንደር መታሰቢያ መሰራቱ የትም ዓለም ያለ ቢሆንም፣ ይበልጥ እነሱንም ከፍ የሚያደርጋቸው፣ እኛንም በአንድነት ገመድ የሚያስተሳስረን፣ ለዋሚ ቢራቱ በሲዳሞ፣ ለዳግማዊ ሚኒልክ በወለጋ፣ ለድምጻዊ አሊ ቢራ በጎንደር፣ ለደጃች ሃይለማርያም ማሞ በናዝሬት፣ ለአጼ ቴዎድሮስ በሐረር፣ ለአጼ ዮሃንስ በኢሊባቡር፣ ለወይዘሮ ሸዋረገድ ተክሌ በጅማ፣ ለአትሌት ፋጡማ ሮባ በመቀሌ….. ወዘተ. ሃውልትና መታሰቢያ ቢሰራላቸው ነው።
በናዝሬት ማርያም ሰፈር የሚባለው አካባቢ ያለ ጎዳና “በላይ ዘለቀ መንገድ” ይባል ነበር፣ ዛሬ ስሙ ተቀይሯል ተብሏል። ይህን መንገድ ቀይረን “ደራርቱ ቱሉ መንገድ” ብንለው ወይም “ጥሩነሽ ዲባባ መንገድ” ብንለው፣ የጥሩዬና የደራርቱን ክብር አይጨምርም፣ እንዲያውም ከኢትዮጵያዊነት አሳንሶ የአንድ ጎሳ ብቻ ያደርጋቸዋል።

ላይ ላዩን ስናይ፣ ውስጥ ውስጡን የልዩነት አጥር የመስራቱ ነገር እየጠበቀ እንዳይሄድ ብናስተውል መልካም ነው። ከሃውልትና ከመታሰቢያም እንኳን አልፈን፣ መጋቢ ሓዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እንደሚሉት “የአንድነታችን ጉዳይ በርግጥ የሚያሳስበን ከሆነ፣ የወለጋው ጎረምሳ የሲዳሞ ቆንጆ፣ የሃረሩ ጉብል የጉራጌ ቆንጆ፣ የትግሬው ወጣት፣ የጎጃሟን ቆንጆ፣ ጎንደሬው ሸበላ የአፋሯን ውብ …ወዘተ…. ነው ፈልጎ ማግባት ያለበት”

ሰዎች የአንድነታችንን ቋጠሮ ፈቱት እያልን እየወቀስን፣ እኛ ከሥር ከሥር እንዲህ እያደረግን ካልቋጠርነውና እንዲቋጠር ካልገፋፋን፣ ሌላውን መውቀስ ብቻ ምን ዋጋ አለው?

2 Comments

2 Comments

 1. በለው!

  February 6, 2018 at 3:25 pm

  ..ቴዲ እጅ ይባርክ!
  “መጋቢ ሓዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እንደሚሉት “የአንድነታችን ጉዳይ በርግጥ የሚያሳስበን ከሆነ፣ የወለጋው ጎረምሳ የሲዳሞ ቆንጆ፣ የሃረሩ ጉብል የጉራጌ ቆንጆ፣ የትግሬው ወጣት፣ የጎጃሟን ቆንጆ፣ ጎንደሬው ሸበላ የአፋሯን ውብ …ወዘተ…. ነው ፈልጎ ማግባት ያለበት”አጼ ምንይልክን ለማድነቅ የሸዋ ሰው..ምሩጽ ይፍጠርን ለማድነቅ ትግሬ…ቀነኒሳ በቀለን ለማድነቅ ኦሮሞ መሆን? ለምን? የሰፈር ጀብደኛ ሳይሆኑ ሀገራዊ ጀግና ልናደርጋቸው ይገባል!ተጋድሎው ለነገዱ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገሩ ነውና።

  “አንድ ሰው በተወለደበት መንደር መታሰቢያ መሰራቱ የትም ዓለም ያለ ቢሆንም፣ ይበልጥ እነሱንም ከፍ የሚያደርጋቸው፣ እኛንም በአንድነት ገመድ የሚያስተሳስረን፣ ለዋሚ ቢራቱ በሲዳሞ፣ ለዳግማዊ ሚኒልክ በወለጋ፣ ለድምጻዊ አሊ ቢራ በጎንደር፣ ለደጃች ሃይለማርያም ማሞ በናዝሬት፣ ለአጼ ቴዎድሮስ በሐረር፣ ለአጼ ዮሃንስ በኢሊባቡር፣ ለወይዘሮ ሸዋረገድ ተክሌ በጅማ፣ ለአትሌት ፋጡማ ሮባ በመቀሌ….. ወዘተ. ሃውልትና መታሰቢያ ቢሰራላቸው ነው።”
  መጋቢ ሓዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እንደሚሉት “ድብልቅልቅ ብለን ለጠላት እንዳንመች!” ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!

 2. Haileleul Kassa

  February 7, 2018 at 12:43 pm

  ባይተዋሩ ልዑል!

  ባይተዋሩ ልዑል ÷ ሰው አልባው ሰው የለው
  እርሙን ያወጣው ÷ ካገሩ ያለ ሰው
  መቼም ባይሸሽገው ÷ መቼም ባይደብቀው
  ውለታው ከባብዶ ÷ በዓለም ያልመለሰው።
  ሐዘን ወመከራ እንደ ተጫጫነው
  በሩቅ ወጥቶ የቀረው ÷ የሚያሳዝነው ሰው
  ይህን ዓለም አየው! እያሠቀያየው
  የውስጥ ስሜቱን ÷ ማንም ሳይጠይቀው።
  እናት እንደ ሌለው ÷ አባት እንደ ሌለው
  ሰማይ በላዩ ላይ ÷ ወዲያ ቢደፋበት
  ወዲህ እኮ ነበረው ÷ ፍቱን መድኃኒት
  ባይተወሩ ልዑል! ሕመሙን ቢያውቁለት።
  ትዝታ ከብረት ÷ እንደ በረታበት
  ናፍቆት ከእግር ብረት ሲጠነክርበት
  ተስፋ ባይነፍጉት
  ወዲህ መዳረሻ ÷ ቀኑም አያጥርበት
  ያኔ በልጅነት።
  ግና ያባት ዕዳ ÷ ኾነና ለልጅ
  ባልዋለበት ውሎ ÷ ወደቀ ሰው ደጅ።
  እናት እንደ ሌለው ÷ አባት እንደ ሌለው
  ወደቀ ሰው ደጅ
  ባይተዋሩ ልዑል የመሳፍንት ልጅ
  ሕልሙ ሳይቋጭ።
  ሀገር እንደ ሌለው ÷ ወገን እንደ ሌለው
  ወደቀ ሰው ደጅ
  ባይተዋሩ ልዑል በባይተዋር እጅ
  እርሙን ላይበጅ።
  ወርቅ አበድሮ ጠጠር!
  በኖረበት ሀገር ÷ ተረስቶ ኹሉው ነገር
  ባይተዋሩ ልዑል የጥሩዬ ዘር
  እንደ ምን ይቀልለው ÷ ያገሩስ አፈር?
  በእናቱ በኵል ጥሩ የሚባል
  ክብሩም ‘ማይዋልል
  አባቱም በውል ÷ የማይታበል
  የኢትዮጵያ ባል!
  ለዳዊት መንግሥት ÷ ለሰሎሞን ዘር
  ቀናዒ አድርጎት፤
  የየሩሳሌም ውሽማም ቢሉት
  ስሙ ቢያኮራት፤
  ካሣ ቀርቶበት ÷ ለፅዮን ታቦት
  ሕይወቱን ሰጣት።

  ኃይለ ልዑል ካሣ
  አ/አ
  ታሕሣሥ 5 / 2009 ዓ/ም ተጻፈ
  ከሀገሩ ወጥቶ ለቀረው
  ለልዑል ዓለም አየሁ ቴዎድሮስ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top