ነፃ አስተያየቶች

ኦሕዴድ የለጋት ኳስ የት ታርፍ ይሆን?


(ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ በፌስቡክ ገጹ ከጻፈው የተወሰደ)

ድርጅቱ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማስተናገደ የሚፈልግ ይመስላል። ጋባዥ ምልክቶችን እያሳየ ነው። ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፣ ኦሕዴድ እያደረገ ያለውን ለውጥ ችላ ማለት አይቻልም። ድርጅቱ ፖለቲካውን የሚገልጽበት መንገድ በግልጽ ተቀይሯል፤ ቢያንስ በአማርኛ በምንሰማው፣ በኦሮሚኛ የሚባለውን አላውቅም። ነገሩ ከቋንቋም አልፎ የፖለቲካ ትንተናና አረዳድ ለውጥን እያካተተ መምጣቱን በአድናቆትም፣ በትዝብትም፣ በጥርጣሬም እየተከታተልን ነው።

ተሳካላቸውም አልተሳካላቸውም ራሳቸውን ከህወሓት ዓይነ ጥላ ለማላቀቅ እየሞከሩ ነው። ሙከራው ራሱ እውቅና ሊቸረው የሚገባ ነው፤ በተለይ የመጣንበትን መንገድ ወደኋላ ዞር ብለን ስናየው፣ እንዲሁም ከፊታችን ያለውን አደጋ በዐይነ ሕልና ስንቃኘው። ለማ መገርሳና ቡድኑ፣ በቃል ከነገሩን አንኳር ጉዳዮች ለግማሾቹ ታማኝ ሆነው ከዘለቁ አገር ይጠቅማሉ። የሚጠብቃቸው ፈተና ግን ከህወሓት ብቻ አይሆንም። ብዙም ሳንቆይ እንደምናየው ሌላ ብሔረሰብን ካልኮነነና በጠላትንት ከሶ ደም ካላፈሰሰ ፖለቲካ የሠራ የማይመስለው ግሪሳ ይነሣባቸዋል። ይህ ለእነ መረራም የሚቀር አይደለም። ይህን በዋናነት በብሶት ትርክት የሚመራ ቡድን ለማስደሰት ብለው የተወሰኑ ስሕተቶችን መፈጸማቸው እንደማይቀር ብጠረጥርም፣ የኦሕዴድን ጅምር ንሸጣ ሳላበረታታ አላልፍም። ንሸጣ ሲከሽፍ ቱሽሽሽ ብሎ ይከስማል፣ ሰለሞን ዴሬሳ እንደሚለው።

የኢትዮጵያን ያለፈ ፖለቲካ በጨቋኝ-ተጨቋኝ ብሔረሰቦች ትንተና ከሚያሰላው የህወሓትና መሰል ድርጅቶች ባህል በማፈንገጥ፣ ጭቆናው መደብ ተኮር ነበር የሚለው መግለጫ ትኩረት የተቸረው ሆኗል። ለእኔ ትልቁ ነገር የመደብ ትንተና ትክክል ከመሆን አለመሆኑ ላይ አይደለም። ቁልፉ ለውጥ፣ የብሔር ጭቆና ትንተናና ትርክት ዴሞክራሲን ለመመስረት ቀርቶ አብሮ ተማምኖ ለመኖርም እንደማያስችል ግንዛቤ መወሰዱ ነው። የመደብ ትንተናውን ሳያስገቡት፣ የብሔር ጭቆና ትርክቱን አሁን ካለው የፖለቲካ ትንተና ቋንቋቸው ማስወጣታቸው በራሱም በበቃ ነበር። ትልቅ ለውጥ ነው። ጤናማ የፖለቲካ አየር ባለበት አገር ቢሆን፣ ኦሕዴድ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን ቦታ የሚያስጠይቅ ሁሉ ነው።
የፖለቲካ ትንተናቸውንና ግባቸውን “ጨቋኝና ጠላት ብሔረሰብ አለብን/አለልን” ከሚል መነሻ የቀመሩት ህወሓትና ሌሎቹ ቡድኖች ይህን አጀንዳ ለጊዜው ካልሆነ ዝም ብለው እንደማያልፉት መገመት ይቻላል። ከመቀሌም ይሁን “ከሚኒሶታ” ቢያንስ የክህደት ክስ መሰማቱ አይቀርም። እናያለን።

በእግር ኳሷ ጋዜጠኞች ቋንቋ፣ ኦሕዴድ ኳሷን ጥሩ አድርጎ አሻምቷታል ልንለው እንችላለን። ኳሷ አሁንም ያለችው በኢሕአዴግ ሜዳ ነው። ኳሷ በመጨረሻ ረድፍ በሚቆመው፣ ጨዋታውን የሚመጥን ቴክኒካዊም ሆነ ስነልቦናዊ አቅም በሌለው ህወሓት እግር ስር ነች። መልሶ ወደ ኦሕዴድ እንደሚለጋት መጠበቅ ነው። ብአዴን ቀድሞ ላገባ ነው። የኅይለማርያም ድርጅት ኳስ አይወድም፤ አይጫወትም፣ አያይም። እንግዲህ ጨዋታውን እናያለን፤ ለኢትዮጵያ የሚያተርፈው ነገር እንዳለ።

2 Comments

2 Comments

 1. Ewunet

  February 8, 2018 at 3:35 am

  Mesfin Negash, Yared Tibebu, Tekle and other TPLF sympathisers are out on social media to vent their anger and frustration following the current episodes.

  Their critics is mixed with their emotions that they couldn’t hide but say it loud. They pretends to appease the ongoing public momentum and at the same time tried to underestimate its outcome.

  Even in this article Mesfin (wedi Negash) recognize the unprecedented stance of OPDO towards apartheid minority regime that was smashing existing Lord to slave relationship between TPLF and OPDO but at the same time he didn’t feel any shame to tell us they wouldn’t achieve anything meaningful.

  TPLF sympathisers like Mesfin and other fail to understand that the current measures taken by OPDO are reflections of desires and aspirations of the people of Oromo that was denied by the Tigre gov for over two decades.

  Wedi Negash don’t worry about any sort of violence targeting ethinicity because that is not a TPLF revolutionary democracy or federalism that engulfed the entire country and claims millions of lives of Amhara and Gambellas. Their political principle OPDO has pursued is totally opposite to Tigre TPLF. On this occasion I would like to remind you that Obo Lemma Megersa has scraped disclosing ethinicity on ID card only Ethiopianism. I know you got sick when you have heard that .. ……cont

 2. Mekonnen

  February 8, 2018 at 6:02 am

  የትንታኔው ርዕስ ትክክል ይመስለኛል። ኳስ ስለተለጋች በአየር ላይ ነች ፡ ነገር ግን ሜዳው በኢህአዲግ ታጥሯል። የብሄር ጭቆና አልነበረም የሚሉ ወገኖች ኳሷን ያገኗት ይሆን (ከኦሆዲድ ጋር ይተባበሩ ይሆን?) ወይስ የብሄር ጭቆና ነበር አሁን ግን ፈትቼዋለሁ የሚለው ህወሃት ቀልቧት መልሶ ይለጋት ይሆን? ወይስ የብሄር ጭቆና ነበረ አሁንም መልኩንና ጨቋኙን ቀይሮ ቀጥሏል የሚሉት ጋር ኳሷ ትደርስ ይሆን? እነሱስ እንዴት ያደርጓት ይሆን?

  በመደብ ጭቆናም ሆነ በብሄር ጭቆና ነበረ/አለነበረም አሁንስ አለ የለም ጉዳይ ላይ መቶ በመቶ መስማማት ላይኖር ይችላል።
  ሁላችንም የየራሳችን ግንዛቤ ላይ የሚመሰረት አቋም ሊኖረን ይችላል: ከመቀራረብና ከመወያየት ልዮነትን ማጠበብ ይቻል ይሆናል። ነገር ግን አንድን ወይም ሌላውን ወገን ስድብ ያዘለ ትችትና ፍረጃ ማድረግ የሚበጅ አይመስለኝም፡ ጋዜጠኛ መስፍን “ብዙም ሳንቆይ እንደምናየው ሌላ ብሔረሰብን ካልኮነነና በጠላትንት ከሶ ደም ካላፈሰሰ ፖለቲካ የሠራ የማይመስለው ግሪሳ ይነሣባቸዋል” በማለት ሰውን ወይም ቡድንን ግሪሳ ማለቱ ከጋዜጠኛ ስነምግባር ውጪ ነው።

Leave a Reply

Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top