News Feature

ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ማእከላይ ኮሚቴ ባለ 10 ነጥብ ድርጅታዊ መግለጫ አወጣ

ከዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ማእከላይ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ከተመሰረተበት 2000 ዓ/ም ጀመሮ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን ለማከናወን ህጋዊ እውቅና ያገኘ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርጅታችን በትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ትግል ትልቅ ሚና እየተጫወተና በመጫወት ላይ የሚገኝ ሰላማዊ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለሰላማዊ ትግል የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ሁሉ እየከፈለ የመጣና በመክፈል ላይ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ብዙ አባላቶቹና ደጋፊዎቹ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ብቻ በሂወት እንዳይኖሩና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዳይመሩ የሚያደርግ አሰቃቂ እና ፀረ ህገመንግስታዊ ዓፈና እየደረሳቸው ይገኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአባላቶቻችን የደረሰ ግድያ፣ ድብደባ፣ እስርና ሌሎች አካላዊና ስነ አእምራዊ ጥቃቶችንና ግፎች ቆመው ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲከበር እናሳስባለን፡፡

ድርጅታችን ዓረና ክልላዊ ራዕዩና ዓላማው ለማሳካት እንዲሁም ሀገራዊ መልክ ለማስያዝ ከሌሎች የሃገራችን ድርጅቶች በመሆን መድረክ የሚባል ግዙፍና ጠንካራ ሀገራዊ ግንባር አቋቁሞ መስራት ከጀመረ ዓመታት አልፏል፡፡ መድረክ በሀገር ደረጃ የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሞች የሚያስከብርና እንዲከበሩ እየታገለ የሚገኝ ትልቅ የሀገራችን ድርጅት ነው፡፡ ይሄም በሀገራዊ ማንነት፣ በዜጎችና ህዝቦች እኩልነት፣ እንዲሁም ፍትህና ርትዕ ለማረጋገጥ አፅንኦት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ፖለቲካዊ ቀውስ አጋጥሟት በሚገኝ ወቅት የዓረና ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ የዓመቱ እቅድ አፈፃፀም፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴው፣ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎችን ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡
ድርጅታችን ባለፈው ዓመት የሰራቸው ስራዎች ገምግሟል፣ እንዲሁም ሀገራችን ያለችበት ፖለቲካዊ ቀውስ በመገምገም ፖለቲካዊ ቀውሱ እንደሚያሳስበው ለመግልፅ ይወዳል፡፡
የዚህ ምክንያት ደግሞ ለሰዎስት አስርት አመታት ገደማ የታጀለ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ አፈና የወለደው መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ፖለቲካዊ ምክንያት፡

የቀውሱ ፖለቲካዊ ምክንያት ስናይ የኢህአዴግ ስርዓት ፖለቲካዊ ምህዳር እያጠበበና በእሾህ እያጠረ፤ የዴሞክራሲ ተቋሞች እያጠፋና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቃኝቶ እየተካ፣ ነፃ መገናኛ ብዙሐን እንዳያቆጠቁጡ እየቀጠፈና እያጠፋ፣ ነፃ የሞያ ማህበራት ( ስቪክ ማህበራት) እንዳይኖሩ ለራሱ በሚያገለግሉ ማህበራት እየተካ አሁን ወዳለንበት የቀውስ ደረጃ አድርሶን ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች ወይም የራሳቸው ነፃ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች በጅምላ ወሀኒ ላይ የታጎሩበትና ለሞትና ለስደት ሰለባ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ውጤቱም ምክንያታዊና ሰላማዊ ፖለቲካ ጠፍቶ የዓመፅና የጉልበት ትግል እየተካው ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ለብዙ የሂወት መጥፋት፣ የሰላማዊ ዜጎች ንብረት ውድመት እያስከተለ ከመሄዱም በላይ ሀገራችን ልትወጣው ወደማትችለው የፖለቲካ አረንቋና ስርአት አልበኝነት እያሰፈነ ይገኛል፡፡

በአንድ አገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ነፃ፣ ፍትሀዊና በመራጩ ህዝብ ተኣማኒ ምርጫ እንደሚያስፈልግ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ ሆኖም ግን የኢህአዴግ ስርአት በሚፈፅማቸው ያፈጠጡ ያገጠጡ ወንጀሎች የህዝብ ድምፅ እየተሰረቀ የሀገራችን ስርዓት በአንድ ድርጅት እጅ እንዲወድቅ አስገድዶታል፡፡ የ 2007 ዓ/ም የምርጫ ሂደት ለማየት ስንሞክር ኢህአዴግ “100% በህዝብ ተመረጥኩ” ብሎ ያወጀበት አገባብ ስርአቱ አይን ያፈጠጠ ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑ የተጋለጠበት አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ በዓለም የዴሞክራሲ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፣ እውነተኛ የሀገራችን ምስል የማይወክል ከመሆኑም በላይ ብዙ ዜጎች በሰላማዊ ትግል የነበራቸው ደካማ እምነት ጨርሶ ያጠፋ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡

ከዚህ በላይ የከፋ ነገር የክልልና የፌዴራል ወንበሮች በአንድ አምባገነን ድርጅት መዳፍ ስር መውደቃቸው ብቻ አይደለም፡፡ የከፋው ነገር ይሄንን ተከትሎ የተሸረሸረው የዜጎች ህገ መንግስታዊ እምነት፣ የመጣው ፖለቲካዊ ውጥረትና ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ለመቆጣጠር በመንግስት የተወሰዱ አውዳሚና ያልተመጣጠኑ እርምጃዎች ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል፡፡ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ልዩነቶች በድርድር ምትክ ጥይጥ፤ በዲፕሎማሲና በሰላማዊ ውይይት ምትክ በጉልበት ለመፍታት መሞከሩ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች የተፈጠረው ፖለቲካዊ ጥያቄ በግዜውና በአግባቡ ስላልተመለሰ ዘግናኝና አስደንጋጭ ውጤት አምጥቶ ይገኛል፡፡
በየክልሉ እየጠፋ ያለው የዜጎች ሂወት፣ ከሶማልያና ኦሮሚያ የተፈናቀሉ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ወገኖች፣ ከ ጎንደር፣ ባህርዳርና ሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ ተጋሩ ኢትዮጵያውያን፤ ከቤኑሻንጉልና ሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ፤ እንዲሁም ከተለያዩ የደቡብ ክልል ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ወዘተ የቀውሱ ደረጃ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳያ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ስርዓት በትግራይ ፤ የኢህአዴግ ስርዓት ደግሞ በሀገር ደረጃ የሚታይ ሀገራዊ ቀውስ መፍትሔ እንዲያገኝ ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ ሀይሎች የሚሳተፉበት ቦታ ሊፈጥሩ ይገባል፡፡ ይህ ቀውስ ባለው የይምሰል ፖለቲካ ከቀጠለ አደጋው ከባድ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ስርዓት ሀቀኛ መፍትሄዎች ከማፈላለግ ይልቅ በተሃድሶና “በከፍታ ዘመን” የሚሉ ነገር ግን ምንም የአስተሳሰብ ለውጥ የማያመጡ አሰልቺና የተለመዱ ውሳኔዎች መጠመዱ ችግሩን እያባባሰ ይገኛል፡፡

የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ “የትግራይ የበላይነት” በሚል የፖለቲካ ውስልትናም ተወያይቷል፡፡ ቁጥራቸው የማይናቅ ፖለቲከኞች በተለይ ደግሞ የመንግስት ስልጣን የጨበጡ የኢህአዴግ ድርጅቶች “የትግራይ የበላይነት” በሚል ውስልትናና ዘመቻ ከፍተው በንፁሃን ተጋሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ቆይቷል፡፡ ይህ ፀረ ሰባኣዊ መብትና ፀረ ዴሞክራሲ ከመሆን አልፎ የሀገር አንድነትና ህልውና የሚያፈርስ እኩይ ተግባር ስለሆነ አጥብቀን እንኮንነዋለን፡፡
ይህንን ደግሞ የሁለት ትልቅ ሀይሎች ውጤት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በአንድ በኩል የህወሓት መሪዎች ሊያስቆማቸው የሚያስችል ፖለቲካዊ አስተሳሰብና በራስ መተማመን ስለሌላቸው “ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” እያሉ በትግራይ ህዝብ ብብት ስር ሲደበቁ ይታያሉ፡፡

ህወሓት “ ትግራዋይ ሲጠቃ ወደ ህወሓት ይጠጋል” የሚል የተሳሳተ አመለካከቱ አርሞ ህዝብ እንደ ማስያዣና እንደ ቁማር መጫወቻ መጠቀም እንደስልት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፅንፍ የፖለቲካ ተቃውሞ የሚያራምዱ ፖለቲከኞችና ከህወሓት እልህ የተጋቡ የኢህአዴግ ድርጅቶችን “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” እያሉ በንፁሀን ተጋሩ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
በአንፃሩ ግን ህዝባችን ከህወሓት ታማኞችና መሪዎች የሚስተካከል ኑሮና ሀብት ሊኖሮው ይቅርና መሰረታዊ ፍላጎተቹ አማልቶ መኖር በማይችልበት የድህነት አረንቋና ፋታ በማይገኝበት የጦርነት ቀጠና ይገኛል፡፡

ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያቶች 
የሀገራችን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ በከፋ ደረጃ ይገኛል፡፡ በተለይ ደግም የትግራይ ምጣኔ ሀብት እጅግ በጣም በሚያሳስብ ደረጃ ይገኛል፡፡ በትግራይ የግል ኢንቨስትመንት አይበረታታም ብቻ ሳይሆን ዘርፉ ትላልቅ አፈናዎችና ተፅእኖዎች የተጫኑበት ነው፡፡ በትእምት ( EFFORT) ፍፁማዊ የበላይነት የተያዘ ንግድና የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት የፈጠረው አሉታዊ ተፅእኖ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ተቀፍድዶ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ክልላችን በሀገራችን የድህነት ወለል ተርታ ትገኛለች፡፡ ይህንን የወለደው የተማረና ወጣት አምራች ሀይል እግሩ ወደ መራው ስደት እየተንከራተተና የዓሳ እራት፣ ለአሸባሪዎችና ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን እየተጋለጠ ይገኛል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የትግራይ ህዝብ በውሸት ዘገባ በሀብት ላይ ሀብት ያከማቸ እንደሆነ ተደርጎ በድርጅቱ ሚድያዎች እና በመንግስት ሲዘገብ የሌላ ክልል ተወላጆች ጥያቄ እስከሚያነሱ እና የተሳሳተ ምስል እንዲጨብጡ ከተደረገና ጉዳት ካደረሰ በኋላ “ ዋሽተን ነው” የሚል ኑዛዜ ማቅረባቸው ነው፡፡

በመጨረሻም የትግራይ ህዝብ ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና በዝቶበትና መሮት አልገዛም ማለቱ ገሀድ ሀቅ ነው፡፡ በተመሳሳይም የኢህአዴግ ስርዓት በተለመደው አገባብ ሊገዛ በማይችልበት ደረጃ መድረሱ ግልፅ ሆኗል፡፡ እንደ መፍትሔ የተወሰዱ “ጥልቅ ተሀድሶ፣ የከፍታ ዘመን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ወዘተ የሚሉ ጭንቀትና ቀቢፀ ተስፋ የወለዳቸው እርምጃዎች ስለሆኑ ምንም አይነት መፍትሔ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡
በዚህ መሰረት የአረና ማእከላይ ኮሚቴ የ 10 ነጥብ አቋሞቹ ይገልፃል፡

1) ወደ ግጭትና ጦርነት የሚያመሩ ሁሉም ፖለቲካዊ ውሳኔዎችና እርምጃዎች የሚቆሙበት፤ ሀገራዊ መግባባት እና ሀገራዊ አንድነት የሚገነባበት መንገድ እንዲፈለግ እናሳስባለን፡፡

2) በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተገደሉ፣ የታሰሩ፣ የተደበደቡና የተንገላቱ ዜጎች ያለምንም ልዩነት ፍትህና የሞራል ካሳ እንዲያገኙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

3) በኦሮሚያ ፣ በሶማልያ ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች በፖለቲካዊ አቋማቸው እና በብሄራቸው ምክንያት በንፁሃን ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት መውደም እና መፈናቀል እንዲቆምና ወንጀለኞች ወደ ህግ እንዲቐርቡ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

4) የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ጉልበትና አፈሙዝ በህግና ፍትህ ተተክተው ሀገር ከቀውስ የምትወጣበት ፖለቲካዊና ህጋዊ ቦታ እንዲስተካከል እናሳስባለን፡፡

5) መንግስት በሀገር ደረጃ የተጀመረው የፖለቲካ እስረኞች መፍታት በትግራይ ባለመታየቱ ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ያለው ልግምተኝነት እና ውሱን ተነሳሽነት እንዲያስወግድ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

6) የትግራይ ህዝብ በፖለቲካዊም ሆነ በሌሎች ህጋዊ አደረጃጀቶች በነፃ ፍላጎቱ ተደራጅቶ ጥቅሙና ደህንነቱ የሚያረጋግጥበት ቦታ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ ደግሞ በመሬት ላይ ያሉ ፖለቲካዊ እንቅፋቶች እንዲነሱ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

7) የገዢው ፓርቲ መሪዎች በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያደርጉት ዘረፋ እንዲቆም፤ የአርሶ አደሮች መሬት ወረራና ማጭበርበር እንዲቆም፤ እንዲሁም በህዝብ ስም የሚደረግ ማወናበድ እንዲቆም ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

8) የአንድ ድርጅት ጠቅላይነትና ፍፁም የበላይነት ቀርቶ ህገ መንግስት ወደ ትግባር የሚመነዘርበትና ሁሉም ዜጎች በነፃነት የሚሳተፉበት የፖለቲካ መህዳር እንዲመቻች እና የሀገራችን ሰላም ወደ ተለመደው እንዲመለስ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

9) ፍትህ፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያብብ አስፈላጊ የሆኑ የዴሞክራሲ እሴቶች ( ነፃ መገናኛ ብዙሀን፤ ስቪክ ማህበራት) እና ሌሎች ተቋሞች እንዲመሰረቱ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡

10) በህወሓት አፋኝ ተግባር የተነሳ በንፁሃን ሰላማዊያን ተጋሩ እየተፈፀመ ያለው ግድያ፣ ዘረፋ ኣጥብቀን እንኮንናለን፡፡

የዓረና ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ
ጥር 28/2010 ዓ.ም
መቐለ

5 Comments

5 Comments

 1. ጳውሎስ

  February 8, 2018 at 3:54 pm

  ይድረስ ለዓረና ትግራይ!
  በቅድሚያ በመግለጫችሁ ላይ እንደምታስቀምጡት በኢትዮጵያ ውስጥ 27 ዓመት መሉ የኢትዮጵያን ህዝቦች እየመጠመጠ የኖረው ኢህአዴግ ሳይሆን የትግራይ ነጻ አዉጭ ድርጅት ትነአድ/ህወሃት ነው። ኢሕአዴግ የሚባለው አቶ አስገደ እንዳሉት ህወሃት በሚባለው ስሙ ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደማይችል እና የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ እንደማያገኝ የተረዳው የትግሬ ነጻ አውጭ ድርጀት የፈበረከው ጭንብል ነው ኢህዴግ። ስለዚህ እናንተም ራሳችሁ ምንም እንዳልተቀየራችሁ አመላካች ነው። የህወሃት የበላይነት ነው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተንሠራፋው የሚለውን ለመቀበል ሲተናነቃችሁ ይታያልና። ስለዚህ ለዚህ የህወሃት የበላይነት ማረጋገጫው በዚህች አጭር ግጥም ላይ የሠፈረችውን እባካችሁ አንብቧት አረናዎች። የግጥሟ ርዕስ ….ሓጎስ ሓጎስ ይላል ግድግዳና አጥሩ ትላለች። ግጥሟን ያገኘኋት ከኢትዮ ፓትርዮትስ ነው።

  ሁሉም አንድ ሆነሳ፣ ስም ጠፋ ወይ ባገር
  ቋንቋው አንድ ሆነብኝ፣ ሁሉም ሰው ሲናግር
  ሃሰትም አይደለም፣ ስሙ እስቲ ስናገር
  ሰው ባዕድ ይሆናል፣ ባደገበት አገር
  በሄድኩበት ስፍራ፣ ሁሉም ሃጎስ ነበር።

  ከመከላከያ፣ ጎራ ብል ደርሼ
  ከበታች መኮነን ፣እስከላይ ዳስሼ
  ይወታደሩን እዝ፣ ሁሉንም አምሼ
  ከሐጎስ በስተቀር፣ ስላጣሁ ነቅሼ
  በወሰደኝ እግሬ፣ ወጣሁ ተመልሼ።

  በለመድው እግሬ፣ ደህንነት ገብቼ
  የተሻለ ይሆናል፣በማለት ገምቼ
  ማጣራት ጀመርኩኝ፣ መዝገቤን አውጥቼ

  ግና ምን ይሆናል፣ አልሆነም ያስብኩት
  የተለዬ ነገር፣ አገኛለሁ ያልኩት
  ሁሉም ሃጎስ ሆኑ፣ ጭራሽ ያልጠበቁት።

  ለምናልባት ብዬ፣ ከጉምሩክ ብገባ
  ይገኙ እንደሆነ፣ ተገኝ እና ሮባ
  ካንዱ ቢሮ ወደ አንዱ፣ ብወጣ ብገባ
  ሁሉም ሃጎስ ብቻ፣ ሞክቶ የሰባ
  ምኑን አሳየኽኝ፣ ጆሮም ልብስ ዳባ
  ተስፋዬ በቀለ፣ የሚል ስምየት ገባ።

  ከቤተ ክህነቱ፣ አየር መንገድ ብሄድ
  ከሃጎስ በስተቀር ፣ አይታይ በመንገድ
  ትምህርት ምኒስቴር፣ ማረሚያን ጎብኝቼ
  ከሃጎስ በስተቀር፣ ሌላ ስም አጥቼ
  እስቲ ለምናልባት ፣ወጥቼ ከምድሩ
  አየር ተሳፍሬ ፣ ብዞር በየሃገሩ
  ይገኙ እንደሆነ፣ ቶሎሳና ፍቅሩ
  በር በማንኳኳት፣ ኢምባሲ መዞሩ
  የሚፈታ መስሎኝ፣ የሃጎስ ምስጢሩ
  ከታችኛው ሎሌ፣ እስከ አምባሳደሩ
  እንኳን አምባሰደር ፣ ዘበኛው የበሩ
  ሃጎስ ሃጎስ ይላል፣ ግድግዳና አጥሩ
  ካሳሁን በለጠ፣ ዲማና መገርሳ የሉም በሃገሩ።
  ታዛቢው
  December 24/ 2017

 2. እምቢ ለዳያስፖራ ድርጅቶች

  February 8, 2018 at 6:09 pm

  የትግሉ በተለይም የሰፌው አማራ ህዝብ ዎና ጥያቄ የሆነውን ሁሉን ያካፈለ የሽግግር መንግስት ጥያቄ ማንሳት ፈራችሁ??????

 3. destatwins

  February 9, 2018 at 12:25 am

  በየትኛውም ከተማ ትገሬ ከሆንክ ተጠቃሚ ነህ፡፡ ሌላው ብሄር ተገሎና ተዘርፎ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ በዚህ በኩል ሲታይ የአረና መግለጫ አንድ እምርታ ነው፡፡ ያልተነሳው ነገር ቢኖር በጎንደርና ወሎ መሬት ላይ የሚታይ የግዛት ማስፋፋትን መቃወም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁንም በሀገሩ ሆኖ በስሙ እየተነገደበት ያለው ህዝብ የህወሀት ስልጣን ከኢትዮጵያ ሲያበቃ ነገ ጥሩ መሬት ይዘናልና ትግራይ ትገንጠል አኛም የዘረፍነውን እዚች ሀገር ላይ ነግሰን እንበላለን ስልጣናችንም እንዲሁ በአረመኔያዊ አያያዝ ትግራይ ህዝብ ላይ ማቆየት እንችላለን ከማለት ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም፡፡ ሌላው ምክንያት የግዛት ማስፋፋት ጥያቄ ሆን ተብሎ ትግራይ ህዝብ ከነሱ ጋር እንዲወግን የሚሰራ የፖለቲካ ስራ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡

 4. Tesfa

  February 9, 2018 at 6:37 am

  የፓለቲካ ውስልትናን የተቃመሱ አንዳንድ ሾተላዮች እንደሚሉት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ያለ ትግራይ ህዝብ ሙሉ አይሆንም። የትግራይ ህዝብ በተለያዪ ዘመናት ሃበሳውን የቆጠረ ህዝብ ነው። ከረጅሙ ሃበሳው የሚከፋው በወያኔ የደረሰበትና እየደረሰበት ያለው ግፍ ነው። በወያኔ በስሙ እየተነገደበት ያለ ህዝብ። ከሌላው የሃገራችን ህዝብ ጋር እንዲጋጭ ወያኔ የሚለፈው የተንሻፈፈ የፓለቲካ ምህዳር አሁንና ቆይቶ የሚያስከትለው ቆርሾ የትግራይን ህዝብ በነሲብ እንዲጠላ አድርጎታል። ለምሳሌ በቅርቡ በመቀሌ በተደረገው የቡጢ ቀረሽ የወያኔ ስብሰባና እንደ አመቻቸው የወያኔ መሪዎች በየመድረኩ በሚለፉት ፍሬ ቢስ የፓለቲካ ንፋስ እንደ አቶ መስፍን ስዮም ያሉት የትግራይ ህዝብ ለትግል እንዲነሳ እንዲታጠቅ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያደረጉት ጥሪ አፍራሽና በውስልትና የተለወስ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ አይጠላም። ዘራፊዎችንና በስሙ የሚነግድበትን ግን አምርሮ ይጠላል።
  አረና ትግራይ ከላይ የሰጠውን መግለጫ ልብ ብሎ ላነበበ ህዝባችን ምን ያህል ከዘሩ፤ ከቋንቋው ይልቅ አንድነቱን እንደሚወድ መረዳት አያዳግትም። አሥሩም የአቋም መግለጫ ነጥቦች ለእኔ ይስማሙኛል። በአንድ ወቅት የትግራይ ክልል አለቃ የነበሩት ገብሩ አስራት አርቆ አሳቢና የሃገር ፍቅር የሚያቃጥላቸው ግለሰብ እንደሆኑ በጎናቸው ያሉና የነበሩ ሹክ ብለውኛል። ለዛም ነው ከወያኔ የገበጣ ጫዋታ የተባረሩት። እውቁ የሰው መብት ተከራካሪና ጸረ ወያኔ አቋም ያለው ወንድማችን አብርሃ ደስታ የሃገር የወገን ፍቅር የሚያቃጥለው የወያኔ ቡጢና እስራት ያለማቋረጥ የወረደበት፤ የግል ሃብቱና ንብረቱን በወያኔ ካድሬዎች የተዘረፈ ለኢትዮጵያ አንድነትና ህዝብ ራሱን ለመከራ ያሰለፈ ጀግና ነው። በወያኔ ግፍ ሃገራቸውን ለቀው በየዓለማቱ የተበተኑ ሌሎችም ሃገር አፍቃሪ የትግራይ ልጆች አሉ። በአንጻሩ ደግሞ የዛሬን እንጂ የነገን የማያዮ ከዘረፈ ጋር ዘርፈው፤ ከገደለ ጋር ገድለው፤ በትግራይ ህዝብ ስም የናጠጡ ከበርቴዎች የሆኑ የትግራይ ልጆች ሞልተዋል። ግን ትርፍ የላቸውም። አወዳደቃቸው እንደ ሮም አወዳደቅ ነው የሚሆነው። መጠጊያችን ህዝባችን ሃገራችን እንጂ በግፍ ያካበትነው ንዋይ ሊሆን አይችልም። በመሰረቱ ለሃገሪቱ የወደፊት እድል ፈንታ የሚበጃት አንድ ነገር ነው። ወያኔን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መፋቅ አይቻልም። ታሪካቸው የትግራይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ነው። ታሪክ የከፋውንም ሆነ የለማውን መዝግቦ ለትውልድ ያስቀምጠዋልና። ይህም በመሆኑ ወያኔ ያጠፋውን ለመበቀል ራስን ከማዘጋጀት ይልቅ ያለፈን ረስቶ፤ ራስን ከህዝብ ጋርና ከራስ ጋር አስታርቆ፤ ህዝብ ለመረጠው ሰው ሥልጣን በማስረከብ ህዝባችን በሰላምና በነጻነት ክልል ሳይበጅለት የሚኖርበትን ሃገር እንፍጠር። የአረና ትግራይና የአቶ ለማና ድርጅታቸው መግለጫ እንዲሁም በውጭ ያሉት የኦሮሞና የሌሌችም ሃይሎች አቋም የሚያንጸባርቀው የህዝባችን አንድነትና አብሮ ኗሪነትን ነው። እንበርታ! የህዝባችን ሰቆቃ ማብቂያ ጭላንጭሉ ይታየኛልና!!

 5. ጳውሎስ

  February 9, 2018 at 1:02 pm

  Tesfa
  ቂ ቂ ቂ ቂ እባክህ እባክህ በማይቀልድበት ጊዘ አትቀልድ ። ከፈለግህ ሰሞኑን ቆራጡ ኢትዮጵያዊ አቶ ገብረ መድህን አርዓያ ስለ እነ ገብሩ አስራት የጻፉትን በጎልጉል ላይ ሂድና ተመልከተው። አብርሃ ደስታ ደግሞ አዎ ታስሮ ነበር ግን የታሠረው እስረኞችን እስር ቤት ሆኖ እንዲሰልል ነበር። መርፌም አልወደቀችበትም በ አብርሃም ደስታ ላይ። በሌሎቹ የደረስውን ግን ራሳቸው እየተናገሩ ነው። አብርሃ ደስታ ማለት ዳዊት ከበደ ማለት ነው። ዳዊት ከበደ እስኪጋለጥ ድረስ በነፃ ሚዲያ ስም ጛዜጠኛ ነኝ ብሎ፡ ከቅንጂቶችም ጋር ታስሮ እስከ መሸለም የደረሰ ነበር ። ግን ዛሬ ሰልፉ እማ ጋ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። ከትግሬው ወያኔ ጋ ተሰልፎ ህዝብ እያጠቃ ነው። ለዚያዉም ከሚወደቀው የማፊያ ወንበዴ ጋር ወግኖ። ከርሱ ጋ ታስራ የነበረችው ብርቱካን ሚደቅሳማ ምን እንደደረሰባት አይተናል።
  እናም ተስፋ እባክህን እየቀለደክ መሠለኝ:: እየቀለደክ ከሆነ አሁን ጊዜው የመቀለጃ ሳይሆን የእነ ገብሩ አስራቱ የትግሬ ወያኔ አንድ እግሩ ወደ ጉድጉድ ገብቷልና፤ በዚያው ወደ መቃብሩ ለመክተት እየተረባረብ ነዉና ከህዝብ ጋር መቀላቀሉ ነው የሚያዋጣው እንጅ እየወደቀ ካለው ከእነ ገበሩ አስራት የማፊያ ቡድን ጋር አይደለም

  God Bless Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

To Top