ነፃ አስተያየቶች

በለውጥ ማእበሉ የኦህዴድ ሚና!

በለውጥ ማእበሉ የኦህዴድ ሚና!

መስቀሉ አየለ

በምርኮኛ ስብስብ ይመራ የነበረው ኦህዴድ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የአዲሱ ትውልድ ፈርጥ በሆኑ ወጣኒያን ከተተካ ወዲህ በዚህች አገር መጻኢ እጣ ፋንታ ላይ የተስፋ ጭላጭል ታይቷል። በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ዘጠኝ ትንንሽ አገር ለመፍጠር ሲባል በቋንቋው የሚያስብ ትውልድ ለመገንባት በተደጋጋሚ አፈር እየላሰ የተነሳው የትግራዩ ገዥ ጉጅሌ ዛሬ ክልሎቹ ጡንቻቸው ሲፈረጥም ከሩብ ምእተ አመት በፊት ሰፍቶ በሰጣቸው አንቀልባ ተጠርንፈው እንደማይቀሩ ማሳየት ሲጀምሩ ይህ “የባርነት በቃን” ዘመቻ በኦህዴድ ብቻ ላለመቆሙ ገዥ ለጉጅሌው ዋስትናውን ውሃ በልቶበታል።ዛሬ ጉጅሌው ከውጥና ከውጭ ነቅዞ በሁሉም ዘርፍ የፖለቲካ ሞት ሞቶ፣ አቅፈውና ደግፈው እዚህ ያደረሱት መንግስታት ሳይቀር ጀርባቸውን በሰጡበትና ከምንም በላይ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው ህዝባችን ዘር፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ እድሜና የትምህርት ደረጃ ሳይለይ በነቂስ እየወጣ በአንድ ድምጽ ከትከሻችን ላይ ውረድ ከማለት አልፎ አገዛዙን አውርዶ ለመፈጥፈጥ የህይወት ዋጋ ሳይቀር መክፈል በጀመረበት;የአፍሪካ ቀንድ የሃይል አሰላለፍ ተለውጦ ለሁለት አስርተ አመታት በማእቀብ ድሜ ሲበላና በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ ውሻ ሲንከላፈት የኖረው ሻቢያ ዛሬ በእንብርክክ የሚለመን እስትራቴጅካል አጋር ሆኖ በወጣበት በዚህ ሰአት “በመልኬ ጠፍጥፌ ሰርቸዋለሁ” ብሎ እግሩን ዘርግቶ የተኛበት ኦህዴድ የዘውግን ቁማር በማራገፍ ብሄራዊ አጀንዳ ይዞ ሲመጣበት መሽቶ በነጋ ቁጥር በደመነፍስ የሚዘወረው ወያኔ እውነታውን ላይቀይረው የንጹሃንን ደም በከንቱ ከማፈሰስ ውጭ የኦህዴድን አካሄድ የሚይዝበት ልጏምም ሆነ በየአቅጣጫው የፈነዳውን ህዝባዊ ሱናሜ የሚያስቆምበት አቅጣጫ የሚያሳይና የቀድሞውን አፈ ሊቅ የሚያስረሳ አንድ መሰሪ ቸግሮት፣ ይልቁንም ተደምረው አንድ ሰው በማይሞሉ ደናቁርትና ሴሰኛች ተተብትቦ የእለት የእለቱን ብቻ ይኖራል።

ኦህዴድ በአስረኛው ጠቅላላ ጉባዔ መግለጫው ላይ እንዳስታወቀው

፩ ለሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ላሉ ተቀዋሚዎች ጊዜው ፈታኝ መሆኑን በማስታወስ ከስሜት በራቀ መልኩ መደማመጥ እና አብሮ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ እና ለዚህም ዳግም ቃል መግባቱን።

፪ የኦሮሞ ህዝብ ለእኩልነት ፣ለነፃነት እና ዘመናው ሀገር ለመገንባት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ፍሬ ማፍራት መጀመሩን በማስታወስ ትግሉ በሴረኞች እንዳይቀለበስ ነቅቶ መጠባበቅ እንዳለበት አሳስቦ በማከልም ጥላቻን በጥላቻ ፤ጥፋትን በጥፋት መመለስ የኦሮሞ ህዝብ ባህል አለመሆኑን እና ከመላው የኢትዮጵያ ወንድም ህዝብ ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር የዘመናዊ ሀገር ግንባታውን እውን እንዲያደርግ ጥር አቅርቧል።በተለይ የኢትዮጵያዊያን አብሮነት በምንም መልኩ እክል እንደይገጥመው የኦሮሞ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዘብ እንዲቆም በአደራ ጭምር ለህዝቡ ጥር አቅርቧል።

የኦሮሞ ህዝብ ካለው ወርድና ቁመና አንጻር ለሩብ ምእተ አመት ያህል “ነፍጠኛ የህዝብ ጠላት ነው” ከሚል ቋንቋ ውጭ ሌላ ዜማ በማያውቅ የአንድ አናሳ ቡድን ተለጣፊ በመሆን ለዚህች አገር ትልቅ የስጋት ምንጭ ሆኖ የኖረውን ያህል ዛሬ ግን ወያኔ ካሰመረለት ሃዲድ (ፕላትፎርም) በመውጣት እንደገና ኢትዮጵያዊነትን ከመዘከር ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ እንደሌለን ከማስፈር አልፎ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ድርጅቱን ለአመታት ጠርንፈው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ ባሪያ አድርገውት ከነበሩ የውስጥ ባንዳዎች እራሱን እያጸዳ በሌላ በኩል ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ሲጀምር ለኢትዮጵያ ትንሳኤ እውን መሆን የሚጫዎተው ሚና ቀላል አይደለም።

በልበ ብርሃን ትንታጎች የተገነባው አዲሱ የኦህዴድ አመራር ከልብ የተገነዘበው እውነት
-ወያኔ ይዞት የመጣው አገርን በዘር የመከፋፈል ፖሊሲ በተለይ ከኦሮሞ ህዝብ አሰፋፈር አንጻር ምን ያህል እብደት መሆኑን፣

-በሚሊዮን የሚቆጠሩና ከሌላው ዘር ጋር ተጋብተውና ተዋልደው የሚኖሩ ኦሮሞዎች እጣ ፋንታ አደጋ ውስጥ የሚወድቅ መሆኑ፣ በ አስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ዛሬ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በሰየመው ክልል ውስጥ መኖራቸው ተግባራዊነቱ ላይ የሚኖረው አደጋ፣

-የተጠመደው አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የተባለ ፈንጅ በማንኛውም መልኩ በየትኛውም ክልል ተግባራዊ መሆን ቢጀምር ከትግራይ ውጭ አንጋፋ ከሚባሉት ሁሉም ብሄሮች ጋር የወሰን ድንበር የሚጋራ እንደመሆኑ ወያኔ የሚችለውን ያህል ገድሎና ዘርፎ ሲመሽበት “ለኦሮሚያ እና ለሱማሌ ክልል ነጻነታቸውን ሰጥቻለሁ” ብሎ ወደ ደደቢት ዋሻ ሲመለስ ወያኔ ያሰመራቸው የኦሮሚያ ድንበሮች እንደ ቸክና ስሎቫኪያ ኬክ እየቆረሱና ሽማፓኝ እየረጩ መሪዎቹ ተጨባብጠው በሰላም የሚካፈሉት ድንበር አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ህዝብ እስከ እለተ ምጻት ድረስ በእያንዳንዷ የምንጭ ውሃና የግጦሽ መሬት ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀትን እንደሚጠይቀው ሰሞኑን በኦጋዴን የታየው በአስር ሽህዎች ለሚቆጠሩ ሞትና ወደ ሚሊዮን ለሚጠጋ የኦሮሞ ህዝብ መፈናቀል መጭውን አደጋ ፍንትው አድርጎ አይቶታልና በመሰሪዎች ተጠምቆ የዋኾችን ላሰከረው የብሔር ፖለቲካ ጀርባውን ለመስጠት ተገዷል።
በመግለጫው ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በግማሽ ምእተ አመት የተካሄደውን የአገሪቱን የፖለቲካ ትግል የብሄር ጭቆና ከሚለው ከስታሊን የተወሰደውን የደደቢት ሃይማኖት “የኛ ታሪክ እንደማንኛውም የሰው ልጆች ታሪክ የመደብ ትግል ትሪክ ነው” በሚለው ማርክሳዊ ትንታኔ መተካቱ ኦህዴድ በቀኖና ለውጥ ላይ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

ዛሬ ኦህዴድ በውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙት ተቃዋሚዎች ሳይቀር ላቀረበውን የተባብረን አገራችንን እናድን ጥሪ በነ ዶር ዲማ ነጎ የሚመራው ኦዲኤፍ በመርህ ደረጃ አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን በተለይም ኦዲኤፍ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋራ ከመሰረተው ጥምረት አንጻር እንደ ክህደት ያዩት ሰዎች መኖራቸውን እያየን ነው። ሆኖም ግን አንድን ነገር በመርህ ደረጃ መቀበልና ወደ ተግባራዊነት በመግባት መካከል ያለው ክፍተት በጣም ሰፊ በመሆኑ እርምጃው ሊኮንን አይገባውም። ነገር ግን እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ከወረቀት መግለጫነት ባሻገር ስጋና ደም ለብሰው ወደ ፍሬ ክብር እንዲደርሱ ኦህዴድ ገና መውጣት ያለበት እረጅም ተራራ፣ መፍታት ያለበት ብዙ ትብታብ ከፊት ይጠብቀዋል። በዚያ ላይ የገጠመን መሰሪ ጠላት ያለ ብዙ ዋጋ ይኽንን የተሃድሶ ጅማሬ እንዴት ማሰናከል እንደሚችል ሃሳቡ በርቶለት ያደረ ቀን ሂደቱን ለማኮላሸት የሞት የሽረቱን መንፈራገጡ እንደማይቀር ይታወቃል። ነገር ግን ኦህዴድ በስሜት ሳይወጠርና በጨለምተኞች ሳይወናበድ በዚያው ልክ ደግሞ ህወሃት በየመንገዱ እየተከለ የሚያልፈውን እሾህና ጋሬጣ በማስተዋልና በዘዴ እየነቀለና በህዝብ ትግል እየታገዘ የተወሰነ እርቀት መሄድ ከቻለ የተስፋው ጭላንጭል ዛሬ የሚይዝ የሚጨብጠውን ላጣው ብአዴን መትረፉ አይቀርም። እውቀት ደግሞ ብርሃን ነውና አንድ ግዜ በብርሃን ፍኖት መጏዝ የጀመረ አካል ተመልሶ ወደ ጨለማ ጉድጏድ ለመግባት የሚፈቅድበት አመክንዮ የለምና ያን ግዜ የህወሃት ፍጻሜ ይሆናል።

በዚያው ልክ እራሱን ኦዲኤፍ ን ጨምሮ ማንኛውም በጸረ ወያኔ ትግል ውስጥ ያለ የምር የሆነ ድርጅት ሁሉ ኦህዴድ መሻገር ያለበትን ውጣ ውረድ ገና ሳይሻገር የእንተባበር ጥያቄ ስላቀረበ ብቻ ዘው ብሎ ቢገባ አድፍጦና አፉን ከፍቶ ለሚጠብቀው ዘንዶ እራስን አሳልፎ መስጠት በመሆኑ በዚህ በኩል ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግን የግድ ይላል። ነገር ግን በዚያው ልክ ዛሬ ኦህዴድ ለጀመረው አገራዊ ጥሪ ቀና በመሆን፣ ለዚህ አመራር የፖለቲካና የሞራል ድጋፍ በማድረግና በመሳሰሉት በማገዝ በመላ ኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት እያስተባበሩ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተጀመረውን በነፍጥ የታገዘ ትግል ጨምሮ በሁሉም አቅጣጫ ትግሉን ወደፊት በመግፋት የወያኔን ግብዓተ መሬት ማፋጠን የማይቻል አይደለም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ ጽሁፎች

Zehabesha - Latest Ethiopian News

Copyright © 2018 Zehabesha - Latest Ethiopian News Provider. All rights reserved.

To Top