‹‹የደም ካንሰር›› – ዝምተኛው ገዳይ በሽታ!

Filed under: News Feature,ጤና |

 

በርካቶቻችን እንደካንሰር አይነት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እኛን ሳይሆን በምቾት የተጨናነቁ ምዕራባዊያንን የሚያጠቁ በሽታዎች አድርገን እናስባቸዋለን፡፡ በአገራችን የተደረጉ ጥቂት ጥናቶች ከዚህ የተለየ እይታ አላቸው፡፡

እመቤት ስሜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን የሃያ አንደኛ ዓመት ልደቷን ካከበረች ጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው ያለፈው፡፡ በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ ከሆነው የፍቅር ጓደኛዋ ጋር በአንድ ወቅት ስለ ካንሰር ያወሩት ነገር በተደጋጋሚ ትዝ እያላት ትረበሻለች፡፡ በተለይ ‹‹በጡት ውስጥ የሚከሰት እብጠት የካንሰር ምልክት ነው›› ብሎ የነገራት ነገር መሰረት አድርጋ ጡቶቿን ስትደባብስ በጡቷ ውስጥ እብጠት ነገር መኖሩ ለከፍተኛ ፍርሃት እና ጭንቀት ዳርጓታል፡፡

‹‹ካንሰር ይሆን እንዴ?›› የሚለው ፍርሃቷ ከሷ አልፎ ለቤተሰቧ እና ፍቅረኛዋ ተርፏል፡፡ ካንሰር ‹‹መድሃኒት አልባ›› ገዳይ በሽታ ነው የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤዋ የአዕምሮ እረፍት ሲነሳት ነው፤ ተበረታታ ወደ ምርመራ የቀረበችው፡፡ ‹‹ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን›› ትላለች እመቤት ‹‹ነፃ›› በሚለው የምርመራ ውጤት ተደስታ፡፡ እመቤት ‹‹ዛሬም ስለ ካንሰር ሲወራ ፍርሃት ይወረኛል›› ትላለች፡፡ ስለ ችግሩ ያላት ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ደግሞ የፍርሃቷ መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ትገምታለች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት በቀረበ አንድ ጥናት እንደ እመቤት ሁሉ በርካቶች ስለ ካንሰርም ሆነ ስለሌሎች ተላላፊ ስላልሆኑ በሽታዎች መንስኤ እና መፍትሄ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ካንሰር በመላው ዓለም ትልቅ ስጋት ነው፡፡ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡

በአገራችን በካንሰር የተጠቁ ሰዎችን በተመለከተ የተብራራ መረጃ ባይኖርም ለምሳሌ በአሜሪካን አገር በያዝነው ዓመት የወጣ ሪፖርት እንደሚያመላክተው ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል፡፡ ካንሰር በርካታ አይነት ቢኖረውም የሣንባ እና የጡት ካንሰር ግን በርካቶችን በማጥቃት ግንባር ቀደም ነው፡፡

በአሜሪካ የካንሰር ማህበር ከፍተኛ የካንሰር ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዴቪድ ብላተን ካንሰር ‹‹ከቁጥጥር ውጪ በሆኑ የሴሎች መራባት የሚከሰት እና ከመቶ በላይ የሆኑ ህመሞች አጠቃላይ መጠሪያ ነው›› ብለው የበሽታውን ምንነት በአጭሩ ያስረዳሉ፡፡ ከቁጥጥር ውጪ የሆነው የሴሎች ዕድገት የችግሩ መንስኤ ሲሆን ጤናማ ባልሆነ መንገድ የሚፈጠሩ ሴሎች መደበኛውን የሰውነታችንን ስራ በማስተጓጎል ለችግር ያጋልጡናል፡፡ እንግዲህ ለዓመታት በተደረገ ጥናት ጤናማ ያልሆነ የሴሎች ዕድገት የካንሰር መንስኤ እንደሆነ ቢታወቅም፤ ጤናማ ያልሆነ የሴሎች ዕድገት ለምን እንደሚከሰት ከመላ ምት የዘለለ መረጃ እንደሌለ ዶ/ር ዴቪድ ብላንት ይናገራሉ፡፡ በመላ ምት ደረጃ ያሉትን መረጃዎች ሲዘረዝሩም ‹‹ሲጋራ ማጨስ፣ ለከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን መጋለጥ፣ የተዛባ የአመጋገብ ስርዓት እና በዘር በመተላለፍ ሊከሰት ይችላል›› ይላሉ፡፡

በካንሰር ህመም ዛሬ በአገራችን የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በተለይ ሴቶች በጡት እና በማህፀን በር ካንሰር በብዛት ይጠቃሉ፤ በአንፃሩ ወንዶች በስፋት በሳንባ ካንሰር ይጠቃሉ፡፡ በተለይ በገጠር ከግል እና አካባቢ ጤና ጥበቃ መስተጓጎል ጋር በተገናኘ እና በጊዜ መዳርን ተከትሎ ሴቶች በብዛት በማህፀን ካንሰር ሲጠቁ ይስተዋላል፡፡ በተዛባ የአመጋገብ እና የአኗኗር ልማድ የተነሳ ደግሞ በከተማ ሴቶች ላይ የጡት ካንሰር እንደሚከሰት የዳሰሳ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ጥናቶች እንደ እመቤት ሁሉ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ስለ ካንሰር ምንነት፤ መንስኤ እና ምልክት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ስለሆነ ወደ ሆስፒታል የሚመጡት ችግሩ ከተባባሰ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

የካንሰር ተመራማሪው ዶ/ር ዴቪድ ብላንት በቢቢሲ ድረገፅ የጤና አምድ ላይ ባቀረቧቸው ተከታታይ ፅሑፎች ላይ የሚከተሉትን የካንሰር መከሰት ጠቋሚ ምልክቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ በቆዳ ላይ የተለየ ነጠብጣቦች መታየት፣ በጡት እንዲሁም በሌላ የአካል ክፍል ላይ አንዳንዴ ጠጠር ሌላ ጊዜ ደግሞ ላላ ያለ እብጠት መታየት፣ በቀላሉ የማይድን የጉሮሮና አካባቢ ህመም፣ የምግብ መፈጨት ችግር መከሰት፣ በአንጀት እና በኩላሊት ላይ የሚታይ ህመም፣ በድንገት ክብደት መቀነስ እና ድንገተኛ የደም መፍሰስ ችግር መከሰት በማለት፡፡ እንግዲህ እነዚህ ምልክቶች የካንሰር መከሰት ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡

እመቤት ባደረገችው የካንሰር ምርመራ ‹‹ነፃ›› ነሽ፤ ብትባልም እስካሁን ፍርሃት አለባት፡፡ በካንሰር ላለመያዝ ፈጣሪዋን ‹‹አንተ ጠብቀኝ›› ትላለች ዘወትር፡፡ ዶ/ር ዴቪድ ግን ከፀሎቱ ጎን ለጎን እመቤትን ጨምሮ በርካቶቻችንን ከካንሰር ለመጠበቅ የሚከተሉት አማራጮች አጥብቀው ይመክራሉ፡፡

ከሲጋራ እና ሺሻን ከመከሳሰሉ የትንባሆ ውጤቶች ከመጠቀም መቆጠብ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ከቅባታማ ምግቦች ይልቅ አትክልትን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማዘውተርም ካንሰርን መከላከል ይቻላል፡፡ አደገኛ ከሆኑ ጨረሮች መቆጠብም ሌላኛው የካንሰር መከላከያ መንገድ ነው፡፡

ነገር ግን ከዚህም በዘለለ ሁኔታ ካንሰር መከሰት እና አለመከሰት በየጊዜው ከባለሞያ ጋር በመነጋገር በቶሎ መከላከል እንዲቻል ማድረግ ይቻላል፡፡ ኤም.አር.አይ፣ ሲቲስካንና አልትራሳውንድን የመሳሰሉ ዘመን አመጣሽ የህክምና መሳሪዎች ደግሞ ካንሰርን በዘመናዊ መንገድ የሚመረምሩበት መንገድ እንደሆነ ዶ/ር ዴቪድ ይናገራሉ፡፡

እንደ እመቤት ሁሉ በርካቶች ካንሰር ‹‹የማይድን›› ህመም አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ዶ/ር ዴቪድ ግን ይህ አመለካከት የተሳሳተ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ካንሰርን በቀዶ ጥገና ሙሉ በሙሉ ማከም ይቻላል›› ይላሉ፡፡ በመጀመሪያ በካንሰር የተጠቁ ሴሎችን ለከፍተኛ ጨረር በማጋለጥ ማከም ሌላኛው አማራጭ ሲሆን ኬሞቴራፒ ወይም ብዛት ያሏቸው መድሃኒቶችን እንደየአስፈላጊነቱ በአንድ ጊዜ ወይም በተለያየ ሁኔታ በመጠቀም በካንሰር የተጠቁ ሴሎች በመግደል ማከምም ይቻላል፡፡ በሆርሞን ቴራፒ እና ባዮሎጂካል ቴራፒም ካንሰርን ሙሉ ለሙሉ ማከም ይቻላል፡፡

‹‹የደም ካንሰር››

ከቀን ወደ ቀን የሰውነቱ ክብደት እየቀነሰ መምጣት በቅርብ የሚያውቁኝ ጓደኞቼ ‹‹ኧረ! ታምራት ስኳር ሳይዝህ አይቀርም፡፡ እስቲ ተመርመር›› ሲሉኝ ነው ወደ ሆስፒታል የሄድኩት፡፡ እዚያም አጠቃላይ የስኳር፣ የጉበት፣ የኩላሊት እንዲሁም የጣፊያ ምርመራ አደረግኩ፡፡ ውጤቱ ግን አስገራሚ ነበር፡፡ የስኳርም ሆነ የጉበት፣ የኩላሊትም ሆነ የጣፊያ ችግር ሳይሆን የነበረብኝ በከፍተኛ ሁኔታ የነጭ ደም ሴል በመብዛት ችግር የሚገለፀው የደም ካንሰር ነበር የተገኙብኝ ይላል ተወዳጁ እና አንጋፋው አርቲስት ታምራት ሞላ የደም ካንሰር ተጠቂ መሆኑን ያወቀበት አጋጣሚ ሲያስታውስ፡፡ አርቲስቱ በአንድ ወቅት በአንድ ታዋቂ ጋዜጣ ላይ በቃለ ምልልሱ እንደጠቀሰው በወቅቱ ‹‹ከስኳር በሽታ›› ነፃ መሆኑ ደስታን ስለፈጠረበት አለብህ ስለተባለው የደም ካንሰር ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠ ያስታውሳል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ባደረገው ምርመራ ግን በደሙ ውስጥ ያለው የነጭ ደም ሴል ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ‹‹ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺ አካባቢ መድረሱ ተነገረኝ፤ በሁኔታው ደነገጥኩኝ፡፡ በሽታው እኔ ሳላውቅ በውስጤ ለዓመታት ስለቆየ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም በምርመራ ተረጋገጠ፡፡ ከዚያ ነው እንግዲህ መድሃኒት መውሰድ የጀመርኩት›› ይላል፡፡

በአገራችንም ሆነ በበርካታ ታዳጊ አገሮች የተደረጉ ጥናቶች የደም ካንሰርን በተመለከተ ያለው ዕውቀት አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ የደም ካንሰር ከካንሰር አይነቶች መካከል አንዱ ሲሆን በደም ውስጥ ከኖርማሉ ሴል ውጪ የሆነ እና በከፍተኛ ፍጥነት የሚራባ የካንሰር ሴል መፈጠር ሲሆን፤ የካንሰር ሴሎች ኖርማል ባለመሆናቸው፤ ከኖርማል ሴሎች የሚጠበቀውን ተግባር በማስተጓጎል ሰውነታችን በአግባቡ ስራውን እንዳያከናውን ያደርጋል፡፡

እንደሚታወቀው ደም የተለየ የሰውነታችን ክፍሎች የሚያስፈልጋቸው ንጥረ ምግብ የሚጓጓዝበትን ቆሻሻ ደግሞ የሚወገድበት እጅግ አስፈላጊ ፈሳሽ ነው፡፡ በደም ውስጥ የተለያየ ተግባራትን የሚከናውኑ የሴል አይነቶች ይገኛሉ፡፡ እነሱም፡- ነጭ፣ ቀይ የደም ሴል እና ፕላትሌት ሴሎች ናቸው፡፡ እንግዲህ የደም ሴል ከደም ውስጥ ከሚገኙ ሴሎች መካከል አንዱ የሆነው ነጭ የደም ሴል ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ መራባት ነው፡፡ በአንድ ጤነኛ ሰው አካል ውስጥ ያለው ደም ከሶስት ሺ እስከ አስር ሺ የሚደርስ የነጭ ደም ሴል ክምችት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በደም ካንሰር ሲጠቃ ግን በደሙ ውስጥ ያለው የነጭ ደም ሴል ቁጥር እስከ ግማሽ ሚልዮን ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህን ያህል መጠን ያለው የነጭ የደም ሴል በደማችን ውስጥ ሲገኝ በሽታን የመከላከል ተግባሩ የሆነውን የነጭ ደም ሴል ተግባር ያስተጓጉላል፡፡

እንደ ሁሉም የካንሰር አይነቶች የደም ካንሰርም ለምን እንደሚከሰት በትክክል አይታወቅም፡፡ የተወሰኑ ነገሮች ግን በመላምትነት እንደ መንስኤ ይጠቀሳሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የክሮሞዞሞች መዛባት ሲሆን ለተለያየ አደገኛ ጨረሮች መጋለጥም ይህንን ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአደገኛ ኬሚካሎች፣ በቤንዚን እና በፀረ ተገባይ መድሃኒቶች መመረዝም ሌላኛው የደም ካንሰር መንስኤ ተብሎ ይገመታል፡፡ የተለያዩ ቫይረሶች እና ለሌላ አይነት የካንሰር ህመም የሚወሰዱ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ውጤትም ሊሆን ይችላል፡፡ በመግቢያችን ላይ የተመለከትነው የአርቲስት ታምራት ገጠመኝ እንደተጠቀሰው በምርመራ እስከሚደረስበት ድረስ በዚህ በሽታ እንደተጠቃ እንኳ አያውቅም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የደም ካንሰር መከሰት ጠቋሚ ምልክቶች በርካታ ሲሆኑ የቆዳ መንጣት፣ ዝም ብሎ መድከም፣ የልብ ምት ጤናማ አለመሆን እና የጆሮ መጮህ ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ በደም ውስጥ ከሚገኙ ሴሎች መካከል አንዱ የሆነው ፕላትሌት ተግባሩ ደም ያለ አግባብ እንዲፈስ ማድረግ ሲሆን የነጭ ደም ሴሎች ቁጥር በፍጥነት ሲያድግ የእነዚህ ሴሎች ቁጥር ይቀንሳል፡፡ ይሄን ነው እንግዲህ የድድ መድማትና ነስር እንዲሁም ሰውነታችን ላይ በሚያሳድሩት ተፅዕኖ ሳይሆን ተፅዕኖውን ለማድረስ የሚፈጀው የጊዜ ርዝማኔ መሰረት በማድረግ የደም ካንሰር በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ጊዜ የማይሰጥ የደም ካንሰር አይነት በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊከሰት ይችላል፡፡ ከሴቶች በበለጠም ወንዶችን በብዛት ያጠቃል፡፡

ወደ ህክምናው ስንመጣ ለደም ካንሰር ችግር የሚሰጠው ህክምና በዓይነቱ እና በሚገኝበት ደረጃ ይወሰናል፡፡ አንድ ሰው በዚህ ችግር እንደተጠቃ ሲታወቅ የመጀመሪያው እርምጃ ታማሚው ለደም ማነስ፣ አለአግባብ ለሆነ የደም መፍሰስ እና ለተለያየ በሽታዎች እንዳይጋለጥ ህክምና ይሰጠዋል፡፡ በመቀጠል ነው እንግዲህ ወደ መሰረታዊው ህክምና የሚገባው፡፡ በዚህም መሰረት ብዙ የጎንዮሽ ጉዳት ቢኖራቸውም መድሃኒቶች እና የኬሞ ቴራፒ ህክምናን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ የደም ካንሰር ችግር ያጋጠመው ሰው ከቅርብ ዘመዶቹ በቂ ደም በመውሰድ በውስጡ ያለው ደም እንዲቀየር ሊደረግም ይችላል፡፡ በጨረር ጤናማ ያልሆኑ ሴሎችን መግደልም ሌላኛው የደም ካንሰርን ማከሚያ መንገድ ነው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<