የሀጂና ኡምራ ተጓዦች እንግልት እና የመጂሊስ ገንዘብ ዝርፊያ

Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |
162 Shares

ቢቢኤን ነሐሴ 05/2009 – በህወሀት መራሹ መንግስት የሚመራው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ (መጂሊስ) ከአመት ወደ አመት ወደ ሳውድ አረቢያ መካ ለሀጅና ኡምራ ጉዞ የሚያደርጉትን ምዕምናን ምንዛሬ ጨምሯል በሚል ከፍተኛ ገንዘብ በማስከፈል ተጓዦችን እያጉላላ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል በዘንድሮው የሀጅና ኡምራ ጉዞ ከመጀመሩ ከሶስት ወራት ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ (መጂሊስ) ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከዚህ አመት ጀምሮ ወደ ሀጂ ጉዞ የሚያደርጉ ሀጃጆች በቅድሚያ የነጃሺን መቃብር ዘይረው እንዲሄዱ እንደሚደረግ በመግለጫው አስፍሮ ነበር፡፡ በአሁን ሰዓትም የነጃሺ የቀብር ዝያራ የሚለዉ አዲሱ የመጅሊሱ መመሪያ መተግበር መጀመሩን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሀጃጆቹ ወደ መቀሌ በሚያደርጉት የጉዞ ወጪ ሙሉ ለሙሉ የሚሸፈነው በራሳቸው ሲሆን ለአሮፕላን ትኬት ለአንድ ሰው ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር እንደከፈሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ወደ መካ ለሚያደርጉት ጉዞ ደግሞ ለእያንዳንዱ ሰው ሰባ ዘጠኝ ሺ ብር እንዳስከፈሏቸው ታውቋል፡፡ ከክፍያው በተጨማሪም መንገደኞቹ የጉዞ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከሀጅ በኃለ የሚመለስ በሚል በመጅሊስ የባንክ አካውንት ውስጥ መቶ ሺ ብር እንዲያሲዙ እንደሚደረግ በደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ (መጂሊስ) መረጃ መሰረት አጠቃላይ ለሀጅ ጉዞ የሚሄዱ የተጓዥ ብዛት ስምንት ሺ እንደሆነ ነው የተገጸው፡፡ አፍሪካ ኒውስ የተሰኘ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ ደግሞ አጠቃላይ ለሀጅ ከኢትዮጵያ የሚሄዱት የሰዎች ብዛት አስራ አምስት ሺ መሆኑን በዘገባው አስፍሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የነጃሺን ቀብር ዝየራ በሚል ወደ መቀሌ የተጓዙት ሀጃጆች ከፍተኛ መጉላላት እዳጋጠማቸው ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡ ከጅማ ሀጅ ለማድረግ ከተጓዙት ውስጥ አንድ ህፃን ልጅ ከቤተሰቡ ጋር አብሮ ያለ ሲሆን መጉላላትና እንግልት እየደረሰበት መሆኑን ከስፍራ በተላከልን መረጃ መሰረት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሀጅ እና ኡምራ የጉዞ ሂደት ማድረጊያ ቦታ ላይ የፌደራል ፖሊስ እና ደህንነቶች ከነ መኪናቸው እንደነበሩ ታውቋል፡፡ ፌደራል ፖሊስ እና ደህንነቶች ሀጃጆች ጋር ምን ያደርጋሉ እዚህ የጦር ሜዳ አይደል የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ መንግስት ከሀጅ እና ኡምራ ተጓዦች ከመጅሊስ ጋር በመሆን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ (መጂሊስ) መረጃ መሰረት አጠቃላይ የሀጅ እና ኡምራ ተጓዦች የከፈሉት ክፍያ ስድስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው፡፡ መንገደኞቹ ከፍተኛ ገንዘብ የከፈሉ ቢሆንም መካ ከደረሱ በሃላ የሚያርፉት በአንድ ክፍል ውስጥ በአማካኝ ስድስት ሰዎች በአንድ ላይ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በቂ የሆነ ምግብ እና ውሀ እንደማይዘጋጅላቸውም በተደጋጋሚ ሀጃጆች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ለጉዞው የሚፈጀው አጠቃላይ ወጪ ከሰላሳ አምስት እስከ አርባ ሺ ሲሆን መጂሊስ ቢያንስ ከሀጃጆች ከአንድ ሰው ሰላሳ አምስት ሺ ብር እንደሚዘርፍ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ቢቢኤን ሬዲዮ በሰራው ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ (መጂሊስ) ሀላፊዎች በሀጅ እና ኡምራ ወቅት በየአንዳንዱ የቤተሰባቸው አባል አበል በሚል ሰላሳ አምስት ሺ ብር እንደሚወስዱ በማሳስረጃ አስደግፎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም መጂሊስ የሀጃጆች ቁጥር መቀነሰ የፈለገው የሚያገኘውን ገንዘብ እንዳይታወቅ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በየአመቱ የሚሄዱትን የተጓዥ ብዛት በግልፅ ስለማያሳውቅ በአረፋ ተራራ ላይ ከሁለት አመት በፊት የደረሰው አይነት አደጋ ሲከሰት የተጎጂዎቹ ቁጥርን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ካለፉት አስር አመታት ጀምሮ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሀጂ እና ኡምራ በግላችን ማለተም በጉዞ ወኪሎች በኩል ማድረግ እንፈልጋለን የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ (መጂሊስ) እና መንግስት አይሆንም የሚል ምላሽ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከሙስሊሙ ጋርም ቅራኔ ከፈጠሩት ጥያቄዎች ውስጥም አንዱ ነው፡፡

መጅሊስ ለሀጅ እና ኡምራ አድራጊዎች በማስታወቂ በማስደገፍ በገለጸው ማሳሰቢያው ላይ ማንኛውም ተጓዥ ለመሄድ ተመዝግቦ በተለያዩ ምክንያቶች ሀጅ መሄድ ባይፈልግ የአገልግሎት ክፍያ የሚያሰከፍል መሆኑን የገለጸ ሲሆን ተጓዡ ቪዛ ከተመታለት በኃላ በአጋጠመው ችግር የሚቀር መሆኑን አስቀድሞ አሳውቆ ገንዘቡ እንዲመለስለት ቢጠይቅ ሙሉ ገንዘቡ እንደማይመለስለት አስታውቋል፡፡

በዚህ አመት ሀጅ የሚያደርጉ ከጅማ የመጡ ሀጃጆች መካከል አንድ የኦሮመኛ ተናጋሪ የሆነ ግለሰብ ለቢቢኤን በሰጠው አስተያየት ‹‹ከጅማ እንደመጣ፤ አብረውን የሚሄዱ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ መቼ እንደምንሄድ አናቅም፡፡ ዝም ብለው ነገ እያሉ ነው፡፡ እነዚህ የመጅሊስ ሰዎች በጣም ሰው ያስቸግራሉ፡፡ አላህ እነዚህ ሰዎች ካላነሳቸው በስተቀር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ እነዚህን ሰዎች በሙሉ ገንዘብ አስከፍለው በሰው ይጫወታሉ፡፡ ምንም ነገር የለም ብር ከመብላት ውጪ›› ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡

ለማስያዣ የተያዘው መቶ ሺ ብርም ሀጃጆች ከሀጅ ከተመለሱ በኃላ ብሩን እንዲመለስላቸው ቢጠይቁ የሀጅ ኮሚቴው እስኪመለስ እንዲጠብቁ እንደሚነገራቸው ባለፈው አመት ሀጅ ካደረጉ ሰዎች ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ የሀጅ ኮሚቴው ሁሉም ሀጃጆች ተመልሰው ብዙ ሳምንታት ከቆዩ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡ ያን ሁላ ቀናት የሚያስቆያቸው ጉዳይ ምን እንደሆነ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል በየአመቱ የሳዑድ አረቢያ መንግስት በየአመቱ ከሚሄዱት ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆን ለኢትዮጵያ መሻይኮች እና ለአቅመ ደካሞች የነፃ እድል የሚሰጥ ሲሆን የመጅሊስ ሰዎች ግን የነፃ ኮታውን ለራሳቸውና ለዘመድ አዝማዳቸው የተረፈውን ደግሞ ለሽያጭ እንደሚያውሉት ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድም በየአመቱ ለሀጅ ተጓዦች ከሀምሳ በላይ የሚሆን ነፃ የበረራ ትኬት የሚሰጥ ሲሆን መጅሊሶች ለግላችው እንደሚጠቀሙበት የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *