በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ከአቅም በላይ ወደመሆን እየተሸጋገረ መሆኑ ተጠቆመ

Filed under: News Feature,ጤና |

(BBN News) በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ከምንጊዜውም በላይ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተጠቆመ፡፡ የፌደራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት እንደገለጸው ከሆነ፣ በሽታው በአሁን ጊዜ በአስደንጋጭ ሁኔታ በመዛመት ላይ ይገኛል፡፡ ጽ/ቤቱ ከዚህ ቀደም ባወጣው ሪፖርት፣ ኤች አይ ቪ በብዛት ከሚሰራጭባቸው ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ መሆኗን ገልጾ ነበር፡፡ አሁን በወጣው ሪፖርት ደግሞ የገጠር አካባቢዎችም በከፍተኛ ደረጃ የበሽታው ተጠቂ እየሆኑ ይገኛሉ ብሏል፡፡

የኤች አይ ቪ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት እንደገለጸው ከሆነ፣ በአሁን ሰዓት በሽታው በብዛት እየተዛመተባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የመንገድ እና የስኳር ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች በሽታው ከአቅም በላይ እየተሰራጨ መሆኑን የገለጸው ጽ/ቤቱ፣ ለዚህም እንደ ምክንያት ያስቀመጠው በተጠቀሱት አካባቢዎች የወሲብ ንግድ መስፋፋቱን ነው፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ መንግስት የበሽታውን ስርጭት እንደገታው ሲናገር ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሽታው እንደ አዲስ በመዛመት ላይ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በሽታው በአስደንጋጭ ሁኔታ እንደ አዲስ ሊሰራጭ የቻለው በምን ምክንያት እንደሆነ በግልጽ የተነገረ ነገር የለም፡፡ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ጋምቤላ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ከሚሰራጭባቸው ከተሞች ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም ስማቸው እምብዛም የማይነሳው የገጠር አካባቢዎች አሁን ላይ ግን ስማቸው ከበሽታው ጋር ተያይዞ እየተነሳ መሆኑ፣ ሁኔታውን አስጨናቂ እንዳደረገው መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.