በአምቦ እና ሻሸመኔ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሔዱ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

በዛሬው ዕለት በአምቦ እና ሻሸመኔ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሔዱ፡፡ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የህወሓት አገዛዝ እንዲያከትም እና ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት የሚጠይቁ የፖለቲካ መፈክሮች በስፋት ተስተጋብተዋል፡፡ በአምቦ ከተማ የተካሔደውን ሰልፍ የተከታተሉ ታዛቢዎች፣ ሰልፉ ፍጹም ሰላሚዊ እና የተሳካ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአምቦ ከተማ በየጊዜው እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ህዝቡ በአገዛዙ ምን ያህል እየተማረረ እንደመጣ ያሳያል ብለዋል-ታዛቢዎቹ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም በሻሸመኔ በተካሔደው ሰልፍ ላይ፣ የከተማዋ ነዋሪ የህወሓትን አገዛዝ ሲያወግዝ ተስተውሏል፡፡ ‹‹ውድቅት ለወያኔ›› የሚሉ እና መሰል መፈክሮች በተስተጋቡበት የሻሸመኔው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ፣ በርከት ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ በአደባባይ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ የከተማዋ አውራ መንገዶች ለተወሰኑ ሰዓታት ተዘጋግተው እንደነበር ከስፍራው የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ በሁለቱም ከተሞች በተካሔዱት ሰልፎች ላይ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የሚጠይቁ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኘው አገዛዝ የሚደረግበት ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ክብር እና ሞገስ ሳያገኝ 26 ዓመታትን በስልጣን ላይ የቆየው የህወሓት አገዛዝ፣ ‹‹አስተዳድረዋለሁ›› በሚለው ህዝብ ፊት አንድም ቀን ሲመሰገን ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ በተለይ የአምቦ ህዝብ ህወሓት በ1983 ወደ አዲስ አበባ ሲያደረግ የነበረውን ጉዞ መንገድ በመዝጋት ጭምር ሲያሰናክል እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እስካሁን ድረስም አምቦ የህወሓት ብርቱ ተቃዋሚ ሆኖ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎችም ምንም ዓይነት ቦታ የሌለው ህወሓት፣ አንድም ቀን ክብር ሳያገኝ ዕድሜው እያለቀ ነው ይላሉ-ታዛቢዎች፡፡(ቢቢኤን)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<