በኢትዮጵያ ባለው አለመረጋጋት የተነሳ የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ተራዘመ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

 

(BBN) ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት የህዝብ እና ቤት ቆጠራ እንዲራዘም ምክንያት ሆነ፡፡ አራተኛው የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ሊካሔድ ታቅዶ የነበረው በመጪው ህዳር ወር 2010 የነበረ ቢሆንም፣ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት ቆጠራው በአራት ወራት እንዲራዘም ማስገደዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለቆጠራው መራዘም በይፋ ምክንያቱን ባያስቀምጥም፣ የመረጃ ምንጮች ግን ቆጠራው የተራዘመው በሀገሪቱ ባለው ግጭት እና አለመረጋጋት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

አምቦ በተቃሞ ላይ:: የዛሬ ፎቶ

በተለይ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ለቆጠራው መራዘም እንደ ዋነኛ ምክንያት ተወስዷል፡፡ የተቀሰቀሰው ግጭት እንደ አያያዙ ከሆነ እስከ መጪው ህዳር ወር ሊቋጭ ቀርቶ ረዘም ላለ ጊዜ ይቀጥላል ተብሎ በመሰጋቱ፣ ቆጠራው እንዲራዘም ሆኗል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ ከዚህ ቀደም ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ እና ከሀገር በሚወጡ የንግድ ምርት እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር መፍጠሩ ሲገለጽ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ግጭቱ የአራተኛው ዙር የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ እንዲራዘም መንስኤ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ለዘንድሮው የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ሲባል 3 ነጥብ 1 ቢሊዬን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ቆጠራውን ለማካሔድም የታብሌት እና ፓወር ባንኮች ግዢ ተፈጽሟል፡፡ ቁሳቁሶቹን ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት 665 ሚሊዬን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ የቁሳቁሶቹ ግዥ ተፈጽሞም ወደ ሀገር ቤት መግባታቸው ተነግሯል፡፡ ከቁሳቁስ ጀምሮ ሁሉም ዓይነት ዝግጅት ተደርጎ የተጠናቀቀለት የዘንድሮው የህዝብ እና ቤት ቆጠራ፣ በሀገሪቱ ባለው አለመረጋጋት ብቻ ለአራት ወራት ተራዝሟል፡፡ ከኢትዮጵያው ሶማሌ ክልል እና ኦሮሚያ በተጨማሪ፣ በደቡብ ክልልም አለመረጋጋት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<