የፌደሬሽን ም/ቤት ከፍተኛ ፍ/ቤት በእነ ዶ/ር መረራ የክስ መዝገብ ለህገ መንግስት ትርጉም በላከው ነጥብ ላይ ትርጉም አያስፈልገውም ሲል መልስ ሰጥቷል

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት የተገኘ ዜና

በ2009 ዓ.ም ለ10 ወራት ተጥሎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የአዋጁን መመሪያና የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ላይ የተደነገጉ አንቀጾችን በመጥቀስ የተለያዩ ክሶች በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ካቀረቧቸው የክስ መቃወሚያዎች መካከል የአቃቤ ህግ ምስክሮች ዝርዝር ማንነት እንዲገለጽላቸው የሚጠይቀው መቃወሚያ ላይ ጉዳዩን የሚያየው ችሎት ለህገ መንግስት ትርጉም ለፌደሬሽን ም/ቤት መላኩ ይታወሳል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 06/2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት እንደገለጸው የፌዴሬሽን ም/ቤት በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና የክስ መዝገብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ዝርዝር ለተከሳሽ ይገለጽ ወይስ አይገለጽ በሚለው ጉዳይ ላይ፣ ‹‹የምስክሮች ማንነት ለተከሳሽ አለመገለጽ ከምስክሮች ጥበቃ አዋጅም ሆነ ከጸረ ሽብር አዋጁ አንጻር ሲታይ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 20(4) ላይ ከተመለከተው ጋር የሚጣረስ ነጥብ ስለሌለው የህገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው አይደለም›› ሲል መልስ ለፍ/ቤቱ መላኩ ተጠቅሷል፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት የምስክሮች ዝርዝር ለተከሳሽ ከማይደርስባቸው አግባቦች መካከል የቀረበው ክስ ክብደት ታይቶ ሊወሰን እንደሚችልም አመልከቷል፡፡ በዚህም ጉዳዩን የሚያየው ፍ/ቤት በእነ ዶ/ር መረራ ላይ የቀረበውን ክስ ከባድ ወንጀል ብሎ ውሳኔ ላይ ስለደረሰበት የምስክሮች ዝርዝር ለተከሳሽ ሊደርስ/ሊገለጽ አይገባም በማለት የተከሳሹን መቃወሚያ ውድቅ አድርጎታል፡፡

በመሆኑም ቀደም ብሎ ውሳኔ የተሰጠባቸውን መቃወሚያዎች ጨምሮ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቧቸው የክስ መቃወሚያዎች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደርገዋል፡፡ የመቃወሚያ ብይን መጠናቀቁን ተከትሎም ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡

‹‹በክሱ ላይ የተመለከቱ የወንጀል ተግባራትን ፈጽመዋል ወይ›› ተብለው በመሀል ዳኛው የተጠየቁት ዶ/ር መረራ ‹‹ወንጀሉን አልፈጸምሁም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም›› በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሹ ክደው ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎም አቃቤ ህግ እንደክሱ አቀራረብ የሚያስረዱልኝ ምስክሮቼ ቀርበው እንዲሰሙልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ ችሎቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለጥቅምት 24/2010 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው ወደ ፍርድ ቤት ሲመጡ በካቴና እየታሰሩ መሆኑን በመግለጽ፣ ደንበኛቸው ካለባቸው የጤና እክል አንጻርና እድሜያቸውም ታይቶ በካቴና እንዳይታሰሩ እንዲታዘዝላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጠበቆቹ ደንበኛቸው ዶ/ር መረራ በታሰሩበት እስር ቤት የጠያቂ ገደብ እንደተጣለባቸው በመግልጽ እንዲስተካልላቸው ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱ በበኩሉ ተከሳሹ አለኝ የሚሉትን አቤቱታ በጽሁፍ እንዲያቀርቡ አሳስቧል፡፡

በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና የክስ መዝገብ ከ1ኛ ተከሳሽ ዶ/ር መረራ ውጭ ያሉት ሁሉም ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.