ሱፐር ቦል 52 – በኢግልስ አሸናፊነት ተጠናቋል – አስገራሚነቱ ግን ያ ብቻ አይደለም

Filed under: ስፖርት |

(አድማስ ስፖርት)

ሦስት ጊዜ ለሱፐር ቦል መቅረብ የቻለው ኢግልስ ለመጀመሪያ ጊዜ 41-33 አሸንፏል። በሱፐር ቦል ታሪክ 33 ነጥብ አስቆጥሮ በመሸነፍ ደግሞ ፓትርየትስ ታሪክ ሰርቷል። 6ኛውን ሱፐር ቦል በመውሰድ ታሪክ ለመስራት የቋመጠው ቶም ብሬዲ አልተሳካለትም።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀር የኢግልሱ ዛክ ኢርትዝ ያገኛት ተች ዳውን ነፍስ የዘራች ነበረች፣ ከሷ በላይ ደግሞ ብራንደን ግራሃም የቶም ብሬዲን ውርውራ ባለቀ ሰአት ማምከኑ ሌላው የድል ጠቋሚ ነበር። የአሜሪካኖቹ ፉት ቦል በ7 ነጥብ እየመሩም ቢሆን እንኳን በአንድ ሰከንድ የጨዋታው ውጤት ሊቀየር የሚችልበት ነው። በዚህ ውድድርም የመጨረሻዋ ውርወራ በተችዳውን ብታልቅ ኖሮ ውጤቱ ሊቀየር ይችል ነበር።

የኢግልሱ ኒክ ፎልስ፣ 373 ያርድ ያህል በመወርወር, ሶስት ተች ዳውን ያስገኙ ኳሶችን በመወርወር እና አንድ ተች ዳውን ሊሆን የሚችል ኳስ በማምከን ኮከብ ተጫዋች ሆኗል። ከዚያም በላይ ራሱ ወርውሮ ፣ ራሱ ተቀብሎ ተች ዳውን በማድረጉ፣ በስፖርቱ የፍጻሜ ውድድር ታሪክ የመጀመሪያው ተብሏል።

ጨዋታው ፈጣን በመሆኑም ሁለቱም ቡድኖች በጠቅላላው 1151 ያርዶችን ሮጠዋል፣ ይህም በስፖርቱ ታሪክ የመጀመሪያው ሆኗል።

በዚህ የ2018 ሱፐር ቦል ፍጻሜ ውድድር፦
– ፓትርየትስ 600 ያርድ ያህል ወደፊት ደጋግሞ በመሄድ አጥቅቶ ሲሸነፍ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል።
– ኢግልሶች 33 ነጥብ ተቆጥሮባቸው በማሸነፍ ፣ የመጀመሪያ ቡድን ሆነዋል።
– ላጋርቲ ብለንት ሁለት ሱፐር ቦሎችን በተከታታይ በማሸነፍ ታሪክ ሰርቷል፣ አምና ለፓትርየትስ ተጫውቶ፣ ዘንድሮ ለኢግልስ ተጫውቶ።
– በስቴዲይሙ ውስጥ በመገኘት የተመለከተው ሰው ብዛት 67 ሺ 612 ነበር። ባለፉት 52 ሱፐርቦሎች በጠቅላልላላ 4 ሚሊዮን ሰዎች ስቴዲየም ገብተው ጨዋታዎቹን ተመልክተዋል።
– ከአራት ወር በፊት ከማያሚው ዶልፊን ተገዝቶ የመጣው የኢግልሱ ጄይ አጄ የሮጠው 57 ያርድ ብቻ ነው፣ ቢሆንም ግን የሱ ቡድን ሻምፒዮን በመሆኑ ዕድለኛ ተብሏል።

አንዳንድ በዚሁ ሱፐር ቦል የተከሰቱ ነገሮችም አነጋጋሪ ነበሩ። ኤን ቢ ሲ ቴሌቪዥን ለ 30 ሰከንድ ያህል መጥፋቱ፣ ለስፖርቱ ተመልካቾች ዓለም የተገለበጠ ያህል ነበር የሆነባቸው፣ ነገሩ የቴክኒክ ብልሽት ሆኖ ተገኝቷል። ..ማስታውቂያዎቹስ? አንዳንዶቹ ጥሩ ነበሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ተተችተዋል፣ ለምሳሌ “ራም ትራክ” የማርቲን ሉተር ኪንግን ንግግር በማስታወቂያው መጠቀሙ ተተችቷል። እኛስ አገር? የአድዋ ድላችንን እና የጀግኖቻችንን ታሪክ ለቢራ ማስታወቂያ የሚጠቀሙ፣ የቤተክርስቲያን በዓላትና መዝሙራትን ያለቦታቸው ለሸቀጣ ሸቀጥ ማስታወቂያነት የሚጠቀሙ የሉም? ተቆጣጣሪው ማነው?

ሌላው በእንደዚህ ዓይነት የአሜሪካኖቹ ትልቅ ስፖርት ፣ ላይ በርካታ ህጻናት ሜዳ ውስጥ ገብተው እንዲሳተፉ ይደርጋል፣ የቀድሞ ታዋቂ የፉትቦሉ ተጫዋቾችም ስማቸው እየተጠራ፣ ሜዳ ውስጥ ገብተው ይዘከራሉ። እኛ ለምን እንደዚያ አናደርግም? ቡናና ጊዮርጊስ ለፍጻሜ ሲጫወቱ፣ የቀድሞ የቡድኖቹም ሆነ ሌሎች ለብሄራዊ ቡድን ያገለገሉ አንጋፋዎች ሜዳ ውስጥ ገብተው፣ ስማቸው እየተጠራ ለምን አይዘከሩም? የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ እንዲል ቴዲ አፍሮ ….

ኢግልሶች በቅርቡ ደንብ ነውና ኋይት ሃውስን ይጎበኛሉ – አንዳንዶቹ ግን ካሁኑ አንሄድም ብለዋል።

በመጨረሻም ፣ መጪው የ2019 ሱፐር ቦል ውድድር የሚካሄደው በአትላንታው መርሰዲስ ቤንዝ ስቴዲየም መሆኑን ያውቃሉ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<