በአሜሪካ አትላንታ ከተማ ኢትዮጵያዊቷ ባለማወቅ የገጨቻት ህጻን ህይወቷ አለፈ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |


(አድማስ ሬዲዮ አትላንታ) አንዳንድ ጊዜ ከቤት ስንወጣ ምን እንደሚያጋጥመን አናውቅም፣ አባቶቻችን በቀኝ አውለን የሚሉት ለዚህ ነው። በዚህች ኢትዮጵያዊት እህታችን የደረሰውም ይኸው ነው።

የሁለት ልጆች እናት (Single mother) የሆነችው እህታችን ፣ እዚህ አትላንታ ነዋሪ ነች። Feb. 16 አርብ ጠዋት ላይ ልጆቿን ትምህርት ቤት ለማድረስ ከቤቷ ትወጣለች። በመንገድ ላይ እንዳለችም፣ የትራፊክ መብራት ቀይ በርቶ ያስቆማታል፣ ትቆማለች፣ ወዲያው አረንጓዴ ሲበራ መንገድ ትጀምራለች። ከፊት ለፊቷ በሌላው መንገድ የትምህርት ቤት አውቶቡስ (ስኩል ባስ) ነበር፣ እሷ እንደምትለው አውቶቡሱ ለመቆም እያቀዘቀዘ ነበር፣ ግን የ”ቁሙ” ምልክት አላሳየም።
ለማለፍ ሞከረች ፣ መጥፎ ዕድል ሆኖ ወደ አውቶቡሱ ለመግባት አንዲት ህጻን ሮጣ ትገባለች፣ እናቷም መሮጣን አይታ ሊሆን ይችላል፣ ተከተለቻት፣ በመካከል የኔፓል ዜጎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚገመቱት እናትና ልጅ ተገጩ፣ የዜና አውታሮች እንደሚሉት የ 8 ዓመት ዕድሜ ያላት ህጻን እዚያው ህይወቷ ሲያልፍ፣ እናት ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸውም ተነግሯል።

ይህችው አደረሰች የተባለችው እህታችን፣ ከሌላ ከተማ ቀይራ መጥታ ሦስት ዓመታት በአትላንታ የኖረች ሲሆን፣ ያለ አባት የምታሳድጋቸው ሁለት ልጆች አሏት። ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የትራፊክ አደጋ አጋጥሟት አያውቅም፣ ፖሊስ ወጣቷን እስር ቤት ከወሰዳት በኋላ ፣ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግ አሳውቆ ፣ ወደ ቤቷ መልሷታል። ይህ ነገር ያጋጠማት ይህችው ወጣትም፣ ጠበቃ ይዛ ጉዳዩን ትከታተላለች ማለት ነው።

ልጃቸውን ላጡት ቤተሰቦች መጽናናትን፣ ለህጻኗ ህይወት ማለፍ የተሰማንን ታላቅ ሃዘን እንገልጻለን። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ይህ መጥፎ አጋጣሚ የገጠማትን ብቸኛ እናት እንደ ማህበረሰብ ፣ እንደኢትዮጵያዊ ልንረዳት፣ ልናማክራት፣ ልናጽናናትና በምንችለው ልንደግፋት ይገባል እንላለን። ይህ ማንም ላይ ሊያጋጥም የሚችል መጥፎ አጋጣሚ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<