ይድረስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት:    ድምፃችሁ ሕወሀትን ወይስ ኢትዮጵያን ለማዳን?

Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |

ከበድሉ በዛብህ

ለዚህ ፅሁፍ  መነሻ የሆነኝ የሰሞንኛው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄዬ አጥጋቤ ምላሽ ለማግኘት ባለመቻሌ ነው :: በመሰረቱ ሀገርን እመራለሁ ብሎ በሚልዮናች የሚቆጠሩ የአገሪቷ ሕዝቦች መፃኢ ዕድል ላይ በመወሰን ላይ የሚገኘው መንግስት ከስልጣኑ በላይ ለህዝቡ ማሰብ አለበት :: በእርግጥ መንግስት የህዝቡንም  ሰላም እና የሀገሪቱን ፀጥታ የማስከበር ግዴታ እንዳለብት አይካድም :: ሆኖም  ታድያ በአሁኑ ሰዕት በሚንስትሮች ምክር  ቤት የተላለፈው የኣስቸኳይ ግዜ ኣዋጅ የህዝቡን ደህንነት እና የሀገሪቷን ፀጥታ ለማስከበር  ነው? ሀገራችንስ ከገባችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ የሚያግዝ መፍትሄ ነው ? ወይስ ሕውሀት አጥልቆ ወደ ቆፈረው ጉድጏድ ለመግባት አፋፍ ለይ በመድረሱ የቀረችውን ጭላንጭል ተስፋ ሰንቆ ነብስ ለመዝራት  የህዝቡን ጥያቄ በለመደው አካሄድ በሀይል ለመጨፍለቅ እንዲያግዘው ነው ?

በአሁኑ ሰዓት እየተወሰደ ያለውስ እስረኞችን የመፍታት እርምጃ  ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ሀገራችን የተጋረጠባትን አደጋ ለመታደግ ከሆነ ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን ነው ያለበት ? ከሚመለከታቸው አካሎች ግር ውይይት ማድረግ ነው የሚሻለው  ወይስ  የመሰብሰብ እና የመናገር መብትን በማፈን ሀገራችንን እያናወጠ የሚገኘው ማዕበልን በሀይል ለማስቆም በሚደረገው  የተሳሳተ እርምጃ ሀገሪቷ ወደማትወጣበት አዘቅት ውስጥ እንድትገባ ነው የሚፈለገው ?

ሁላችንም በቀላሉ እንደምንረዳው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝቡ ብሶት ገደቡን ጥሶ በመውጣቱ ሕዝቡ ፍርሀትን አሸንፎ አልገዛም በቃ በማለት የለውጡን ማዕበል  መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ለማድረስ ቆርጦ በመነሳቱ ሕወሀት ደግሞ  ስልጣኑን  ለማስጠበቅ በሚወስደው እርምጃ  ነገሮች በፍጥነት እየተቀያየሩ በመሄዳቸው  ሀገራችንን በውቅያኖስ መሀል ላይ ማዕበል እንደሚያንገላታት መርከብ እየተናወጠች ትገኛለች:: ታድያ በዚህ ሰዓት  የህዝብ ተወካይ የምክር ቤት አባሎች “የሕዝብ” የሚለው በትምህርተ ጥቅስ ይቀመጥ እና    ሕወሀትን ወይስ ኢትዮጵያን ለማዳን ንው እየተዘጋጃችሁ ያላችሁት ?

እኔ ግን የማስበውን እና የሚታየኝን እንዳጋራችሁ ጆሮአችሁ እንድትከፈቱልኝ በኢትዮዽያ ስም እጠይቃለሁ :: ኢህአደግ  ድርጅቱ ለገባበት አዘቅት ሆነ በአገራችን ለተፈጠሩት ችግሮች በተጠያቂነት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ   እራሱን አጥፍቶ አገሪቱን ለማጥፋት የሚሂድብትን መንገድ ቆም ብሎ በመፈተሽ  በእራሴ መንገድ ብቻ መፍትሄ አመጣለሁ ብሎ 27 ዕመት ሲደክርበት የነበረውን የሀይል አማራጭ በመተው ከእንቅልፉ ነቅቶ ጆሮውን እና አይኑንም በመክፈት የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝበትን መድረክ ቤያመቻች ለድርጅቱም  ሆን ለሀገራችን የሚበጀው  ብቸኛ አማራጭ  ይመስለኛል :

ኢህአድግ የደርግን ስርኣት  አስወግዶ ሀገሪቱን በጠመንጃ አይል ከተቆጣጠረብት ከ 1983 ዓም ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት ለማትረፍ እና ሀገሪቷን በዴሞክራስያዊ  መንገድ ወደ ተሻለ ቦታ ለማድረስ በእጁ ላይ ያለውን እድል ከመጠቀም ይልቅ በተቃራኒው ከህዝቡ በየጊዜው ለሚነሱ ጥያቄዋች ጆሮ ባለመስጠት መቀበርያ ጉርጎድ መቆፈር የጀመረው ገና ስልጣን በያዘ ማግስት ጀምሮ ነው ::

ወደሗላ መለስ ብለን ኢህአድግን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያሳጣው እና በማንአለኝበት የፈፀማቸውን ታሪክ ይቅር የማይላቸው ዋና ዋና ስህተቶችን ብንመለከት :-

 • በኤርትራ የመገጠል ጉዳይ ለይስሙላ የተደረገውን ባርነት ውይስ ነፃነት የሚል አማራጭ ለመቀበል ለማስፈፀም ቁጥር አንድ መሆኑ:: ይህም የሆነው በወቅቱ ከኤርትራ የሚመጣበትን ጫና የመቋቋም ሀይል ስሌለለው ስልጣኑን ላለማጣት ብቻ በማሰብ ያደረገው ውሳኔ በመሆኑ እንደ አንድ ሀገር መንግስት  ሪፈረንደሙ ዓለምአቀፋዊ ህግን  በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ አንኳን አቋም መውሰድ አልቻለም
 • የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ ይገባት አይገባት ውሳኔው በዓለም አቀፉ ችግር አፈታት መወሰን እንዳለበት ሆኖ ኢሀአዲግ ግን እንደ ሀገር መሪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብር  መልኩ የይገባኛል ጥያቄውን በህጋዊና በመረጃ በተደገፈ ሁኔታ ከማቅረብ ይልቅ የአስብ ጉዳይ ኢትዮጵያ አያገባትም ብሎ ለሀገራችን ኢኮኖሚ እና ፀጥታ ቁልፍ ሜና መጫወት የሚችለውን ወደብ ኣሳልፎ በመስጠት ሀገሪቷን ወደብ አልባ በማድረጉ
 • ኤርትራ ነፃነትዋን ካወጀች በኃላ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እና ሌሎች ጥቅሞችን በሚጎዳ መልኩ  በማን  አለብኝነት  አንደፈለገች በሀገራችን ላይ አንድትፈነጭ  ኢሕአድግ መፍቀዱ
 • ሀገራችን አላስፈላጊ የባድሜ ጦርነት  ውስጥ እንድትገባ ማድረጉና በአስር ሺዋች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን መስዋዕት የከፈሉበትን ጦርነት ኢህአድግ በዕውቀት ማነስ በሰራው ስህተት ባድሜን ለኤርትራ አሳልፎ እንዲሰጥ ከማድረጉም በላይ አይኑን አፍጦ ሕዝቡን መዋሸቱ
 • ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ስልጣን ላይ ሊያቆየኝ ይችላል በሚል የተሳሳተ  ፖሊሲ በብሄር ብሄረሰብ ህዝቡን በመከፋፈል የህዝቡን  በነፃነት ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብቱን በመገደብ  የብሂራዌ አንድነትን በሚያደፈርስ መልኩ  በቋንቋ ላይ የተመስረተ አፍራሽ ፖለቲካ በሀገሪቷ ላይ መጫኑ  እና ያለ ምንም ሀፍረት በተቆጣጠረው የህዝብ መገናኛ አውታሮች ከኢትዮዽያዊ ባህል ውጪ በየቀኑ እየዋሸ ህዝቡን አይንህን ጨፍንን እና ላሞኝህ የሚለው አካሄድ ነው ኢህአድግን ገና ከጅማሬው ከህዝብ ጋር ሆድ አና ጀርባ ያደረገው

ምንም እንኳን በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ተታለውም ቢሆን  ለቆሙለት ዓላማ የደርግን ስርዓት ለማስወገድ ውድ የህይወት መስዋዕት ለከፈሉት  የኢህአድግ ታጋዮች  ክብር ሊሰጣቸው  ቢገባም ሕይወታቸውን ለነፃነት ለእኩልነት እና ለሰላም ብለው አሳልፈው በሰጡት ታጋዮች ደም እና አጥንት ላይ ተረማምደው ስልጣን የጨበጡት ሹሞምንቶች ከደርግ በማይተናነስ መልኩ በጉልበት እና በጠመንጃ አፈሙዝ ህዝቡ ላይ የጫኑትን ቀንበር ህዝቡ መሸከም የማይችልበት ደረጃ ደርሷል

ለዚህም ጥሩ ማሳያ  በ1997 ዓ.ም የተደረገው የምርጫ ውጤት ህዝቡ ለኢሀደግ ቀይ ካርድ ያሳየበት እና በሗላም በሀይል እርምጃ ውጤቱ ወደ  ቤጫ ካርድ የተቀየረበት ክስተት ነው::  ያም ሆኖ ኢህአድግ ክስተቱን  እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ቆምብሎ በማሰብ አካሄዱን ከመፈተሽ እና የህዝቡን ድምፅ ከመስማት ይልቅ የመድፍና የሞርታሩን ድምፅ መስማትን በመምረጡ እና ከሕዝብ ቁጥር ይልቅ የወታደሩ እና የታንኩ ቁጥር ገዝፎ ስለታየው  ህዝቡን በጠመንጃ አፈሙዝ ማነጋገር በመምረጥ  በሰልጣን ላይ ሊያቆየኝ ይችላል ብሎ ያሰበውን  የሀይል አርምጃ በመውሰድ  ጉድጎዱን ይበልጥ አጥልቆ እና እና አስፍቶ በመቆፈር እነሱ ብቻ ሳይሆኑ አገሪቱንም ይዘው ለመስመጥ ገደሉ አፋፍ ላይ ደርሰዋል::

ሰሞኑን ያለምንም ጥፋታቸው በእስር ሲማቅቁ ቆይተው የተፈቱትን የህሊና እስረኞች የታሰሩበትን ምክንያት እንኳን ብንመለከት የኢሀድግ  ችግር ምን ያህል የሰፋ እና ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሚነሱትን ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄዋች ከውይይት ይልቅ በህይል እና በህይል ብቻ በማሰር እና በማስፈራራት መልስ ለመስጠት መምረጡን በግልፅ ያሳያል ለምሳሌ አንዳንዶቹን ብንመለከት :-

 • ከመሬታችን ያለ አግባብ ለምን እንፈናቀናለን በማለት ከኦሮምያ ክልል የተነሳው ጥያቄ
 • የወልቃይት የማንነት ጥያቄ
 • ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት  ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ይደረግ የስበአዊ መብት እና ዲሞክራሲ ህገመንግስት በሚፈቅደው መልኩ ይረጋገጥ
 • የሙስሊም መፍህትሂ አፈላላጊ ኮሚቴዋች ሀይማኖታችን ነፃነት ይከበር  መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባ የዋል ድባ ገዳም መናኩሳት የገዳሙ ቅርስ እና የገዳሙን መሬት በልማት ስም አይፍረስ
 • የመከላከያ አባላት የሀገር ዳር ድንበር ለማስከበር እንጄ ለአንድ ፖርቲ መወገን የለብንም

በዚህ ባለንበት በሰለጠነ ዘመን  በውይይት መፈታት የሚገባቸው ጥያቄዋች  17 ዓመት በላይ በትግል ከ26 ዓመ በላይ በስልጣን የቆየ ድርጅት ዓለማችን በፍጥነት እየተጏዘችበት ያለችበትን ሁኔታ ማገናዘብ ሳይችል ቀርቶ ከ40 እና 50 ዓመታት በፊት ጨቋኝ መንግስታት ይጠቀሙበት የነበረውን የሀይል እና ከፋፍለህ ግዛ መርህን  በመተግበር 100ዓመት ስልጣን ላይ ለመቆየት ህልም ማለሙ የድርጅቱ መሪዋች በጭንቅላታችው ሳይሆን በጡንቻቸ  ብቻ እንድሚያስቡ ነው የሚያስረዳው :: ለዚህም ነው በሕዝብ አመፅ እና አልገዛም ባይነት እንዲሁም የምዕራብውያን ተፃሳፅ የኢህአድግ ጡንቻ መዛል በመጀመሩ የህሊና እስረኞች መፍታት የጀመሩት   ይህ ጥሩ ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥር እርምጃ ቢሆንም ኢሕአድግ እራሱን ለመሰረታዊ ለውጥ ለማዘጋጀት  ሞራላዊ ብቃቱ ግን አሁንም ስለሌለው  ጡንቻውን ለማጠንከር ጊዜ መግዛቱን እና ከድርድር ይልቅ ድብድብን የመረጠ ይመስላል

ማንኛውንም ጤነኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ከህሊና እስረኞች መለቀቅ  በሗላ  በተስፋ የሚጠብቀው ኢህአድግ ከተቃዋሚ ፖርቲ ዋች  ከሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች የሀገራቸው ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ አካላት ጋር  በጋራ በመምከር ሀገራችንን ከአደጋ ለመታደግ የሚያስችል መፍትሄ በማፈላልግ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ  ይሰጣል የሚል ነበር :: ኢህአድግ  ግን ተቃራኒውን ነውእያደረገ ያለው ድርጊቱም ምንም  የተጠናበትም አይመስልም እስረኞን በለቀቀ ማግስት የእስራት እና ግድያ  አዋጅ ማስነገር ህዝብ የመፍትሂው ኣካል እንዳይሆን እንዳይሰበሰብ እና እንድይይነጋገር መከልከል እውነት ሀገሪቷ ለገጠማት ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል?  የኣስቸኳይ ጊዜ አዋጁስ የህዝቡን ደህንነት እና የሀገሪቷን ሰላም ለማስከበር የታለመ ነው ? ወይስ ጠቅላይ  ሚኒስትሩ በህወሀት ቡራኬ የተደረበላቸው ካባ ስለወለቀ የስልጣን ክፍተት ተፈጥሯል በሚል ነውጥ ተነስቶ  ስርኣት አልበኝነት እንዳይነግስ ታስቦ ነው መልሱን ለኢሀደግ ሳይሆን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቶች እተወዋለሁ ::

ኢህአድግ ግን  ከእንቅልፉ ቢነቃ እና  ሕዝቡ ቀድሞት እንደሄደ ቢያውቅ ሀገራችንን ለመታደግ አና ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት መፍትሄው ቀላል ይሆናል::  ሰሞኑን አንድ ጥሩ አባባል ሶሻል ሚዲያ ላይ አንብቤ ነበር ከሲም ካርዱን ነው እንጂ ከቀፎው ጉዳይ የለንም የሚል ማብርራያ ሰለማያስፈልግው በዚሁ ልለፈውና: የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለው እና ተከባብሮ የሚኖር ከበቀል ይልቅ ይቅርታን የሚያስቀድም ታጋሽ ህዝብ ነው ::  ምንም እንኳን ሕወሀት ሀላፊነት በጎደለው መልኩ በተለይ በኦሮምያ በመካሄድ ላይ የነበረው የህዝብ አመፅ መልኩን ቀይሮ ያልተገባ አቅጣጫ እንዳይዝ አስተዋይነት በተሞላው አስተሳሰብ ነገሮች ከተረጋጉ በሗላ  የስልጣን መልቀቁን ዜና ማወጅ ሲገባቸው እሳት ላይ ቤንዝል በማርከፍከፍ አድማው መልኩን ቀይሮ   ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ ለማድረግ የታቀደ በሚመስል መልኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን መልቀቅን ዜና ቢናገሩም ‘ነገሩ የስራ  መልቀቂያ  እንጁ የስልጣን አይደለም” መጀመርያውኑ ስልጣን ስላልነበረው ሆኖም ግን ህዝቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቅ በላይ ከእስር የተፈቱት ጀግኖቹን ለመቀበል አመፁን አቋርጦ የተዘጉ መንገዶችን በመክፈት ሰላማዊነቱን ነው ያረጋገጠው ::

ህዝቡ ለሚያነሳቸውን ጥያቄዋች  በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ በመውጣት ያለምንም ረብሻ አንድም ኩሽታ ሳይሰማ ብሶቱን ማሰማት  ነው የሚፈልገው አገዛዙ ግን ህዝቡ ጥያቄውን እንዳያሰማ የሚያደርገው ዕንቅፋት  ወደ አላፈላጊ ብጥብጥ እና ረብሻ  ህዝቡን እየከተተው ያለው:: ምንም እንኳን  የህዝቡን ጥያቄ በሀይል ለማፈን መሞከር ምንም መፍትሄ እንደማይሆን የከዚህ ቀደሙ ተሞክሮው እራሱ ኢህአድግም በተግባር ያየው ቢሆንም አሁንም ኢህአድግ ከለመደው ቅኝት መውጣት ባለመቻሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስም የስልጣን ዘመኑን ሊያራዝምልኝ ይችላል ብሎ የሚያስበውን የሀይል እርምጃ ለመሙስድ እያመቻቸ  እና ዕቅዱን ለማስፈፀም እንዲረዳው የህዝብ ተወካዮችኝ ቡራኬ እየጠበቀ ይገኛል::

እኔ እንደምገነዘበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገበት ሞክንያት በዋናነት የህዝቡ እምቢተኝነት እና አልገዛም ባይነት መነሻው ይሁን እንጂ መድረሻው ግን በኢህአድግ አጋር ድርጅቶች በተለይ በኦህዲድእና በብአዲን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ  የመጣው ለህወሀት አልታዘዝም እና የህውሀትን አጀንዳ አናስፈፅም የሚል አቋም ነው :: በተለይ በቅርቡ ከኦህዲድ መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው የህዝቡ አመፅ ተገቢነት እንዳለው እና ህዝቡ ችግሩን  በሰላማዊ መንገድ  እስገለፀ ድረስ ያልተመጣጠነ የሀይል እርምጃ መውሰድ አግባብ እንዳልሆነ  የተላለፈው መልእክት እና በአማራ ክልልም ምንም እንኳን የብአድን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሕወሀት ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ ባለመውጣቱ እንደ  ኦህዲድ በግልፅ የወጣ ባይሆንም  በቅርቡ በወልዲያና በአካባቢው በተነሳ እመፅ እጋዚዋች የውሰዱትን  ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃን በተመለከተ ሕወሀት ከአማራው ክልል የገጠመው  ቀላል የማይባል ተቃውሞ ሕወህትን ያስደነገጠ ነው :: በተጨማሪም የኦሮምያና የአማራው ክልል ፀጥታ ሀይሎች ለህዝቡ ወገንተኝነት ማሳየታቸው ለሕውሀት ሌላው ዕንቅልፍ የነሳው ጉዳይ በመሆኑ  ነው::

በዚህም ምክንያት በተለይ የኦሮሚያና የአማራው አንድነት መጠናከር እና ለህዝቡ እምቢተኝነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ ማድረጋቸው ህዝቡን በይበልጥ ለአመፅ ያበረታታል የህዝቡንም የፍራቻ ድንበር ሙሉ በሙሉ ይበጥስ እና ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል በሚል በሕውሀት በኩል ትልቅ ጫና እየፈጠረ መሆኑ ግልፅ ነው:: ከጥቂት ወራቶች በፊትም እንደታየው የፀጥታ ምክር ቤት በሚል ስልጣኑ እና ዓላማው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ጋር ብዙም የማይለያይ ኮሚቴ በማቋቋም ሕውሀት የሁሉንም ክልል ፀጥታ ሀይሎች በአንድ ዕዝ ስር በማድረግ በኦሮምያና በአማራ ክልል የሚደረግገውን  ማንኛውንም ዓይነት  ተቃውሞ  በመከላከያ ሰራዊቱ እና በደህንነቱ ለመጨፍለቅና ለማፈን ጥረት ያደረገበት አካሄድ ምንም እንኳን ከሁለቱ ክልሎች በገጠመው ተቃውሞ ዕቅዱ ሳይተገበር ቢቀርም አካሄዱ የዚህ ማሳያ ነው

መግቢያው ላይ እንደተገለፀው የዚህ ፅሁፍ መነሻ የአስቸኳይ ጊዜው አዋጅ እንድምታው “ሕውሀትን ወይስ ኢትዮዽያን ለማዳን ነው የሚለውን ጥያቄ”  ለተከበሩት  የሕዝብ ተወካይ የሚለው በትምህርተ ጥቅስ ይቀመጥ እና ትምህርተ ጥቅሱ ተነስቶ ለተከበሩት  የሕዝብ ተወካይ የምክር ቤት አባላቶች ተብለው እንዲጠሩ ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ሰርተው ለማለፍ የታሪክ አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት ለመጠቆም ነው :: የሀገራችን መፃኢ ዕድል በእጃችሁ ላይ ነው ያለው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በደማቅ ቀለም ለመፃፍ ወይም የመረጣችሁን ሕዝብ በአደባባይ ደሙ እንዲፈስ በመተባበር ታሪክ የማይሽረው ጠባሳ ትቶ ሀገራችን ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ በማስገባት ታሪክን ለመደለዝ ምርጫው በእጃችሁ ላይ ይገኛል::

ሕውሀት የቀረችውን አንድ ዕድል በመጠቀም ሀገሪቷን በወታደራዊ ቁጥጥር ስር አድርጎ በሙስና በበለፀጉት የመከላከያ እና የደህንነት ሹመምንቶቹ ጡንቻ በመተማመን ከህዝቡ ጋር የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ እየተፍጨረጨረ ስለሚገኝ   በቃህ በማለት የህዝቡን ሰቆቃ የምታስቆሙበት ጊዘው አሁን ነው :: የተከበሩ የአቶ ለማን አባባል ልዋስና ፅሁፌን ልቋጭ “ ሀገር ከስልጣን አይበልጥም “ ስለዚህ የህዝቡን የነፃነት ጥያቄ ሊያቆመው የሚችል አንዳችም ሀይል እንደማይኖር ተገንዝባችሁ ክህዝብ ጋር ቆማችሁ ያለ ምንም ደም የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ውድቅ በማድረግ ሕውሀት ወደ ድርድር ጠረዼዛ እንዲመጣ የማድረግ ትልቅ ሀላፊነት ተጥሎባችሗል

ኢትዮዽያ በብሔር ብህሔረሰቦቿ ደምቃ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር

Bedilu Bezabih

bbzabih1997@gmail.com

Gondor Ethiopia

3 Responses to ይድረስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት:    ድምፃችሁ ሕወሀትን ወይስ ኢትዮጵያን ለማዳን?

 1. Siltan kehager aybeltim tebilo yinebeb essachewu yalut endezi new

  Workineh dagim
  February 28, 2018 at 2:13 am
  Reply

 2. This time, there is extremely serious call to members of parliament, they have to look at it differently than ever, They are not representative of the butchers of TPLF Generals ( Ye Weyane Generaloch ). But, representative of peoples ( Ye hizb twekayoch ). MPs need to stand with the nation at least by voting big NO. while our youth Qeero & Fanoo paying their life.

  Amlak Ethiopian yitebikat.

  Ahmed
  February 28, 2018 at 5:18 am
  Reply

 3. Thank you for the comment. Sirty for the typing mistake. Yes it is true that Ato Lemma Megersa says Sultan ke Hager aybelyim new. Please correct it while you are reading. The editor.

  Bezabih
  March 1, 2018 at 7:23 pm
  Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<