‘ሥርዓት የማፍረስ እና ሥርዓት የመገንባት ሂደት ውጣ ውረድ!’ | ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና 

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ ባላደገ ከተናጠል ፍላጎት በላይ የኾነ የጋራ ፍላጎት፤ ከጋራ ፍላጎት በታች የኾነ ነጠላ ፍላጎት ልዩነት በሌለው በሥልጣን ፖለቲካ አስተሳሰብና አመለካከት ቅኝ በተገዛ – በእምነቱ፣ በእውቀቱና በድርጊቱ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ባሕሪያዊ መገለጫው አፍርሶ መገንባት – ነገሮችን ከዜሮ የመጀመር ሥነ ልቦናዊና ተግባራዊ የአካሄድ መመሪያ መኾኑ እሙን ነው፡፡

በዚህ ረዥም የጊዜ ልምድና ተሞክሮ ውስጥ ካሉ ቁልፍ መንገዶች የማፍረስ እና የመገንባት ሂደት በዓለም የቅኝ ግዛት እና የርስ በርስ ጦርነት ላይ የተደረጉ ኹለንተናዊ ትግሎች ታሪክም ኾነ ነባራዊ ኹኔታ ሁለት ዐበይት ምዕራፎች ማሳያ ናቸው፡፡

እነዚህም፡-

  1. ሥርዓት ማፍረስ
  2. ሥርዓት መገንባት

አብዝሃ ሕዝብ እንደሕዝብ አልያም የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ከሚደርስበት፣ ደረሰብኝ እና ሊደርስብኝ ይችላል ከሚለው የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ እጦት፣ የደኅንነት ስጋት፣ ጭቆና፣ የፍትህ መነፈግ፣ የነጻነት(የሃይማኖት፣ የከባቢ፣ የባሕል፣ የዕሴት) አለመከበር፣ ራስን በራስ ያለማስተዳደር፣ የሕዝብ አልያም የሕብረተሰቡ መናቅ፣ መራብ፣ መጠማት፣ መታረዝ፣ መሰደድ፣ መታሰር፣ ግርፋት፣ መቁሰል፣ መሞት፣ የሕዝብ ታሪክ አለመታወስ፣ መድሎና መገለል፣ መሐይምነት፣ ድንቁርና፣ ድህነት፣ ኃላቀርነት፣ አለመሠልጠን፣ የዲሞክራሲ አለመኖር፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ – – – በጥቅሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹለንተናዊ አስከፊ የትላንትና ዛሬ ኹኔታዎች ብሎም የነገ ስጋቶች እልህና ቁጭት የፈጠረባቸው አካላት መበራከት በሀገራዊ፣ ከባቢያዊ፣ ሃይማኖታዊም ኾነ ርዕዮተ ዓለማዊ አመክንዮ በመነሣት ሥርዓት ማፍረስ የሚሹ ኃይሎች በግለሰብ፣ በቡድንና በድርጅት ደረጃ እንዲነሡ ያደርጋል፡፡

ለኹሉ ኹለንተናዊ ችግር መፍትሔው እንዳላቸው ነባራዊ ምቹ ኹኔታ ተመስርተው ትጥቃዊ አልያም ሰላማዊ ትግልን ያደርጋሉ፡፡ ይህም ሂደት በዋናነት በተለይ እንደኛ ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ ባልተሻገሩ ሀገራት ሥርዓት ከማሻሻል ይልቅ ሥርዓት የማፍረስ ትግል ያደርጋሉ፡፡

በዚህም ሂደት የሚታገሉትን ሥርዓት አስከፊነት በእጅጉ በማንሣት እየተራቡ፣ እየተጠሙ፣ እየታረዙ፣ እየተሰደዱ፣ እየቆሰሉ፣ ኹለንተናዊ መስዋዕትነት (የሕይወት፣ የአካል፣ የስሜት፣ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የእውቀት) እየከፈሉ፣ ሕዝብን በትግሉ ሂደት እያሳተፉ (እያነቁ፣ እያደራጁ፣ እየመሩና እየታገሉ/እያታገሉ)፣ በኹለንተናዊ መንገድ (በአስተምህሮት፣ በሚድያ፣ በፕሮፕጋንዳ፣ በኢኮኖሚ፣ በስለላ፣ በጦር) ቀን ከለሊት በመትጋት – – – ይታገላሉ፡፡

ለዚህም ሥርዓት የማፍረስ ሂደት በባሕሪውና በጠባያቱ ሥርዓት መገንባትን መነሻውና መዳረሻው ያደርጋል፡፡ ሊያደርግም ግድ ይለዋል፡፡ የሥርዓት ማፍረስን አስፈላጊነት ከሥርዓቱ ኹለንተናዊ አስከፊነት ከማስቀመጥ ባሻገር ሥርዓት የመገንባት ሂደት፣ ፍላጎት፣ ህልምና ተስፋን ደግሞ ያስቀምጣሉ፡፡ “ከምንታገለው ሥርዓት የተሻለ ለመታገል ምክንያት የኾነንን ነባራዊ ኹለንተናዊ (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ኹኔታ/ዎች በመሠረታዊነት የሚቀይር ሥርዓት እንገነባለን” ብለው ፍቅርን በማሳየት፣ እምነት እንዲጥሉባቸው በማድረግ ተስፋቸው እጅጉን የላቀና የታመነ እንዲኾን ያደርጋሉ፡፡

ኾኖም ግን በብዙ ከቅኝ ግዛትም ኾነ በርስ በርስ ጦርነት ትግል ውስጥ ያለፉ ሕዝቦች ነባራዊ ኹኔታ የሚያሳየን ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) ቢኖር ሥርዓት በማፍረስ የተሳካላቸው ሥርዓት በመገንባት ሂደት ግን እምብዛም ከወሰደው ጊዜ አንጻር ከውጤታማነት አንጻር የተሳካላቸው አለመኾኑ በታሪክ የታየና በመኖር የምናውቀው ነው፡፡ ይሄ ለምን ኾነ ብለን ከኃይሎቹ አንጻር ብቻ ያለውን ከሌሎች ኹለንተናዊ የውስጥና የውጭ ፈተናዎች – ተያያዥነታቸውንና ተመጋጋቢነታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ከብዙ በጥቂቱ ለውይይት መነሻ ይኾን ዘንድ የሚከተለውን ሰንጠረዥ እንመልከት፡፡

በብዙ የትላንትና ዛሬ ሥርዓት ከማፍረስ ወደ ሥርዓት መገንባት በሚደረግ ሽግግር የሚዘነጉ ዐበይት ነጥቦች፡-

  1. ከሥርዓት ማፍረስ ወደ ሥርዓት መገንባት ለሚደረግ ሽግግር ያሉን ዲሲፕሊን፣ ዕሴቶች (ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ የመንፈስ መግባባት፣ መረዳዳት፣ መተዛዘን፣ የባለቤትነት ስሜት)፣ አስተምህሮ፣ ሥርዓት፣ የመታገያ ስልቶች፣ የአሰራር ሂደት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የመንፈስ መግባባት፣ የስራ ክፍፍል – – – እንዴት ከኹኔታዎች ጋር እናጣጥማቸው? የሥርዓት ማፍረሻ ባሕሪያትና ጠባያትን ከሥርዓት የመገንባት ባሕሪያትና ጠባያት ጋር እንዴት እናጣጥማቸው በማለት ጥልቅ፣ ረቂቅ፣ ሰፊ ጊዜ የሚወስድ፣ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ ሥራ አለመስራት፤
  2. ሥርዓት በማፍረስ የትግል ሂደት ትልቅ መሣሪያ የኾነውን የማንቃት፣ የማደራጀትና የመምራት ተግባር ትርጉም ባለው መንገድ ሥርዓት በመገንባት ሂደት ውስጥ ማንቃት፣ ማደራጀትና መምራትን ትኩረት አለመስጠት፤ ለአብነት፡- ለዚህ ቁልፍ መሣሪያ ከኾኑ ጉልህ ነገሮች አንዱ በዚህ ዘርፍ የሚመደቡ አመራሮችና አባላት ድርጅቱ/ፓርቲው አሉኝ የሚላቸው/የሚሏቸው ሲኾኑ ልክ ሽግግር ሲደረግ እነዚህ ጠቅልለው ቢሮክራሲ ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው በሀሳብ ድህነት ውስጥ እንዲዘፈቁ ከማድረጉም በላይ የመንፈስ መግባባታቸውን የቢሮክራሲ የራሱ ባሕሪያትና ጠባያት እንዲበላው አድርጓል፡፡
  3. ለትምህርት፣ ባሕል እና ታሪክ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ሥርዓት በማፍረስ ሂደት ውጤታማ ይኾኑና ሥርዓት በመገንባት ሂደት ይህን ይዘነጉታል፡፡ ለአብነት፡- እንደድርጅት የባሕል ክፍል ትልቅ የመታገያ ማዕቀፍ ለትግሉም ቢኾን የላቀ አስተዋጽዖ ያደረገ ክፍል ልክ ሥልጣን ሲይዙ ድርጅቱ የባሕል ክፍል አልባ ይኾናል፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ብሎም እጅግ ረቀቅ ካለ ዓላማን መዘንጋት ነው፡፡

የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት፤ ህ.ግ.ደ.ፍ (ሻዕቢያ) ከህ.ወ.ሃ.ት (ወያነ) በብዙ ነገሮች ከግብር አንጻር መመሳሰሎች ያሉዋቸው ቢኾን እንኳ ለማነጻጸር ያስቸግራሉ፡፡ ቢኾንም ህ.ግ.ደ.ፍ ከህ.ወ.ሃ.ት በእጅጉ ከሚበልጥበት ትልቅ መገለጫ አንዱና ዋነኛው በትግሉ ወቅት ህ.ግ.ደ.ፍ ሥርዓት ለማፍረስ የተጠቀመበትን የባሕል ክፍል እንዳለ በፓርቲም ይኹን በመንግሥት መዋቅር እንዳለ ይዞ ሥርዓት ለመገንባት ሂደት ከራሱ የሥልጣን ፖለቲካ ጥቅም አንጻር ሕብረተሰብን ለማነጽ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ (ልክ ነው/ ልክ አይደለም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡) በአንጻሩ ህ.ወ.ሃት ፍጹም ዘንግቶታል፡፡ የመዘንጋትንም ዋጋ ሀገር እንደሀገር በኹለንተናዊ መልኩ እየከፈለች፣ እየከፈልንና እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

  1. ሥርዓት በማፍረስ ሂደት የአመራርና አባላት – አመራረጥና አመላመል ሂደት እጅግ ትኩረት ተሰጥቶት የሚካሄድ ሲኾን ሥርዓት በመገንባት ሂደት ግን አመራረጡና አመላመሉ እጅጉን እንዝህላልነት በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ መንሰራፋት፤ የዚህ ማሳያ “እኔ ልሙትልህ” ተብሎ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ትግል አቅምና ብቃት እንደሌላቸው ለብዙ ዓመታት በተግባር ያስመሰከሩ አመራሮች ሥልጣን ላለመልቀቅ የሚያደርጉትን ፍትጊያ ብሎም “ከኔ እከሌ ይሻላል” ብሎ ሥልጣን በቃኝ! የሚል ማየት የማይታሰብ ሊባል በሚያስችል ደረጃ እንዲኾን አድርጓል፡፡
  • ሥርዓት በማፍረስ ትግል ለመሞት የተዘጋጁለት ርዕይ፣ ግብና ዓላማ የነበራቸው ሥርዓት በመገንባት ሂደት ቢያንስ ሥልጣን በቃኝ፣ ሥልጣን የሚለቁበትና ሥልጣን የሚያስተላልፉበት ርዕይ፣ ግብና ዓላማ ሳይኖራቸው ይቀራሉ፡፡
  1. በሥርዓት ማፍረስ ሂደት በኹለንተናዊ መንገድ ቁጭት የመፍጠር ሂደት ወሳኝ የትግሉ አካል ሲኾን ሥርዓት በመገንባት ሂደት ትኩረት አለመስጠት፤ በትግል ለአሳቢያን ትልቅ ቦታ መስጠት ብዙዎች ሥልጣን የያዙ አካላት በተለይ በሲቪል ሰርቪሱ በቀስቃሽነት፣ በአስተማሪነት፣ በአንባቢነት፣ በጸሐፊነት – – – የሚታወቁ ሲኾኑ ሥርዓት በመገንባት ሂደት በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ ድርጅቱ እንደድርጅት ስለድርጅቱ የትላንት፣ የዛሬና የነገ ኹኔታ ከቢሮክራሲ ነጻ ኾነው የሚያስቡ አካላት አለመኖር፤ – – –

ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች እጅግ ውስን በኾነ መልኩ ዋና ዋናዎቹን ብቻ በማዕቀፍ ደረጃ (የሀገር ውስጥና የውጭ ኹነቶችን ታሳቢ በማድረግ) ስንመለከት የምናገኛቸው ሲኾኑ እነዚህ በመዘንጋታቸውም የብዙ ታዳጊ ሀገራት ገዥዎች – ምላሳቸው ሕዝባዊ (socialist) አ‘‘ራቸው ካፒታሊስታዊ (capitalist)፤ ጽሑፋቸው ኮሙኒስታዊ (communist) ልባቸው ኢምፔሪያሊስታዊ (imperialist)፤ ሥርዓት ሲያፈርሱ selfless ሥርዓት ሲገነቡ selfish ይኾናሉ፡፡

እውነታውም (Reality) በአንድነት ታግለህ መለያየት፤ በሕብረት ታግለህ መከፋፈል፤ በመንፈስ ተግባብተህ ታግለህ በመንፈስ የማትግባባ፤ በፍቅር ታግለህ በጥላቻ መተያየት፤ በርዕይ ታግለህ ርዕይ አልባ መኾን፤ በአስተምህሮት ታግለህ ትርጉም ያለው አስተምህሮት አልባ መኾን፤ በዲሲፕሊን ታግለህ ዲሲፕሊን አልባ መኾን፤ በዕሴት ታግለህ ዕሴት አልባ መኾን፤ ለእውነት ታግለህ ሃሰተኛ መኾን፤ ለነጻነት ታግለህ ነጻነት ነፋጊ፤ ለዲሞክራሲ ታግለህ ጸረ ዲሞክራሲያዊ፤ ለፍትህ ታግለህ ኢ-ፍትሃዊ፤ ለአብዘሃ ጥቅም ታግለህ የጥቂቶች ጠቃሚ፣ በጽናት ታግለህ ልፍስፍስ መኾን፤ በመስመር ታግለህ ከመስመር መውጣት፤ ሳታንቀላፋ ቀን ከለሊት ታግለህ አንቀላፊ መኾን፤ የሕዝብ በደል ቁጭት ፈጥሮብህ እያነባህ ታግለህ የሕዝብ መበደል ምንም የማይመስልህ መኾን፤ በዳይን ታግለህ ጭራሽ ራስህ በዳይ መኾን፤ ስለሕዝብ ታግለህ ሕዝብን መዘንጋት፤ ሕዝብን አክብረህ ታግለህ ሕዝብን መናቅ፤ ቃል ገብተህ ቃልን አለመፈጸም፤ እታመናለው ብለህ ታግለህ አለመታመን፤ ለአንድነት ታግለህ ከፋፋይ ከኾንክ፤ ለሕዝባዊነት ታግለህ ግላዊ፤ ለሶሻሊስትነት ታግለህ ካፒታሊስታዊ፤ ለኮሚንስታዊነት ታግለህ ኢምፔሪያሊስታዊ ከኾንክ፤ ብዙዎች አብረውህ አንተን አምነው ሕይወታቸውን፣ አካላቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን ኹሉ ዋጋ ከፍለው ያመጡትን – በኹለንተናዊ መስዋዕትነት የተገኘን ውጤት – የተከፈለለትን ዋጋ ፍሬ አለማስገኘት ጭራሽ ከግብርህ የተነሣ “ለዚህ ነው እንዴ የታገሉት!” ከተባልክ – – – ዕውነት በዕውነት ስለዕውነት “ኹለተኛ ሞት ነው!” እንዲህ አይነት ተርዕዮዎች በብዙ የዓለማችን ክፍሎች የተስተዋለና አብዛኛው ከቅኝ ግዛት ትግል፣ በመፈንቅለ መንግሥትም ኾነ እንደኛ በርስ በርስ ጦርነት የታገሉ ሕዝቦች የኖሩበትና እየኖሩበት/እየኖርንበት ያለ ያደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

ተቃርኖን እንደግለሰብ፣ እንደቡድንና ተቋም በእምነት፣ በእውቀትና ድርጊት ደረጃ አለማስተካከል ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የመጡበትን መንገድ መርሳት የቁም ሞት ነው፡፡ ትውልድ ላይ ያልተገባ ነገር መፈጸም – ያልበላን በልቷል፣ ያልጠጣን ጠጥቷል፣ ያልለበሰን ለብሷል፣ ያልዳነን ድኗል፣ ያልተጠየቀን ተጠይቋል፣ ያልተመቸውን ተመችቶታል፣ ያልተቀበለን ተቀብሏል፣ ያላገኘን አግኝቷል፣ ያልተሰራን ተሰርቷል – – – በተለይ ሕዝብን እንደሕዝብ እንደዛ ማለት ታላቅ ጥፋት፣ ታላቅ የሞራል ዝቅጠት፣ በህሊና የሚያስወቅሰ፣ በታሪክ የሚያስጠይቅ፣ በሕግ የሚያስጠይቅ፣ በፈጣሪ ፍርድን የሚያሰጥ፣ በትውልድ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ታላቅ የጥፋቶች ኹሉ ታላቅ ጥፋት ብሎም ከበደሎች ኹሉ የላቀ ታላቅ በደል ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ማግኘት የሚገባውን ከማጣቱና ከማሳጣቱም በላይ የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይኾን የትውልድ ትውልዶች ላይ ጠባሳው ትልቅ ነውና፡፡

በረሃ ያስወጣህን ብዙ ዋጋ ያስከፈለህን የሕዝብ ድህነት፣ የሕዝብ ደኅንነት አለመረጋገጥ፣ የፍትህ ማጣት፣ የሙስና መንሰራፋት፣ የሀሰት ሪፖርት፣ ግላዊነት በሕዝባዊነት ላይ መሠልጠን፣ መገለል፣ የዲሞክራሲ እጦቶች፣ አድሎ፣ አድርባይነት፣ የነጻነት መነፈግ፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ (አለመከበር)፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ – – – ሥርዓት በማፍረስ ሂደት የታገልከው አካል ሲያደርገው የነበረውን በእምነት፣ በእውቀትና በድርጊት ደረጃ እንደግለሰብ፣ እንደቡድንና እንደተቋም ራስህ አሸናፊ ኾነህ ሥርዓት በመገንባት ሂደት ከፈጸምከው ልዩነትህ ታድያ ምንድነው? መታገልህ ፋይዳው ምኑ ላይ ነው? ልዩነት መፍጠር ካልቻልክ መኖርህ ጥቅሙ የት ላይ ነው?

ምቹ ኹኔታን ጥለው ስለሕዝብ የታገሉ፣ እየተራቡ፣ እየተጠሙ፣ እየታረዙ፣ እየተሰደዱ፣ እየታሰሩ፣ እየቆሰሉ፣ ኹለንተናዊ ዋጋ እየከፈሉ (የሕይወትና አካል) – – – ሥርዓት ማፍረስ የቻሉ ኃይሎች – ስለምን እጅጉን ጠግበው፣ ጠጥተው፣ ለብሰው፣ ሳይሰደዱ፣ ሳይቆስሉ፣ ኹለንተናዊ ዋጋ የሚከፈለው ከሕይወትና ከአካል በታች ኾኖ – – – በአንጻራዊ መልኩ ‘ተመች~ቸው’ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ብሎም ሕያው ሥርዓት መገንባት እንዴት ያቅታቸዋል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ቢኾንም እኖራለው ብሎ ለሕዝብ መታገል እሞታለው ብሎ ከመታገል እጅግ የከበደ፤ ራስን የትግል አካል ማድረግትግልን የራስ አካል ከማድረግ በላይ የላቀ፤ ራስን ከራስ በላይ ላለ ርዕይና ዓላማ አስገዝቶ መታገልሌላውን ከራስ ርዕይና ዓላማ በታች አድርጎ ከማየት እጅጉን ታላቅ የሀሳብ ልዕልና ባለቤት የመኾን ዕውነትን (Truth) መረዳት አስፈላጊነት ይጠይቃል፡፡

ሥርዓት ማፍረስ የምትታገለው ሥርዓት ሲፈርስ ይቆማል፡፡ ሥርዓት መገንባት ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የማይቋረጥ ሂደት ነው፡፡ በሥርዓት ማፍረሻ አስተሳሰብና አመለካከት ሥርዓት ለመገንባት መሞከር ኃላቀርነት ነው፡፡ ሥርዓት በማፍረሻ ባሕሪያትና ጠባያት ትርጉም ያለው ሥርዓት መገንባት ከቶ አይቻልም፡፡ ሥርዓት ማፍረስም ኾነ ሥርዓት መገንባት የየራሱ ባሕሪያት/ቶችና ጠባያት/ቶች አሉት፡፡ የእያንዳንዱን ነባራዊ ኹነት በኹለንተናዊ መንገድ በጥልቀት መፈተሽ፣ መመርመር፣ መረዳትና ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ሥርዓት ማስወገድ ሥርዓት ለመገንባት ግብ አልያም መሣሪያ /means/ ነው፡፡ ሥርዓት መገንባት በራሱ ርዕይ ሲኾን ሥርዓት መገንባት ባለርዕይ መኾንን የግድ ይላል፡፡ በርካታ በዓለም ሀገራት የተካሄዱ ሰላማዊና ትጥቃዊ ትግሎች ግን በአንጻሩ ሥርዓት ማፍረስን እንደ’ርዕይ’ በመውሰድ በመንፈስ አንድ ኾነው እንዲሁም ሕዝብን በመንፈስ አንድ አድርገው ሥርዓት ለማፍረስ በቅኝ ግዛትም ኾነ በርስ በርስ ጦርነት የታገሉና ያታገሉ ኃይሎች ሥርዓት በመገንባት ሂደት ግን እን£ንስ ሕዝቡን ራሳቸውን እን£ በመንፈስ አንድ ማድረግ ያቅታቸዋል፡፡

ስለኾነም ሥርዓት ለማፍረስ ያነሣሣህ ኹለንተናዊ ነገር ሥርዓት በመገንባት ሂደት አንተ ላይ ከመጠን፣ ከአይነትና ከአድማስ አንጻር ካለ ጠባያዊ ልዩነት ውጭ ባሕሪያዊ ልዩነት ከሌለ ሌሎች ሥርዓት ለማፍረስ ቢነሱ የሚገርም አይኾንም፡፡ የሥርዓት ባሕሪያት/ቶች ልዩነት እንጂ የሥርዓት/ቶች ጠባያት/ቶች ልዩነት በግለሰብ፣ በቡድንና ተቋም ደረጃ የገዥዎችና ጨቋኞች ጠባያት/ቶች መቀያየርና መለዋወጥ ያለ ግለሰባዊ፣ ቡድናዊም ኾነ ተቋማዊ ባሕሪያት/ቶች መቀያየርና መለዋወጥ ፈጽሞ መሠረታዊ ለውጥ እንደማያመጣ – ሊያመጣም እንደማይችል አመክንዪ፣ ታሪክም ኾነ አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<