ወንጀለኛን ወንጀለኛ ለማለት የሚደፍር ትዉልድ እስኪነሳ ድረስ ሀገር ብዙ ዋጋ እየከፈለ ይቀጥላል:- የጸረ ዲሞክራሲያን የጠቅላይ ሚኒስቴር ምርጫ ቅስቀሳ እንደ ማሳያ ሸንቁጥ አየለ

Filed under: ነፃ አስተያየቶች |

ኢህአዴግ/ወያኔ/ብአዴን/ደኢህዴን/አቢይ/ደመቀ/ሽፈራዉ ሽጉጤ ሁሉም ወንጀለኛ እና ጎሰኞች ናቸዉ::የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር የከፋፈሉ::የጎሳን ፖለቲካ በኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ የዘሩ:: የወያኔን የጎሳ ፖለቲካ ከማንም በተሻለ አሳምረዉ የተጫወቱ::
ኢትዮጵያዊነት ከጎሳ ማንነት በታች እንዲወርድ እና በእግር እንዲረገጥ የሰሩ::ኢትዮጵያዉያንን በቅኝ ገዥና በቅኝ ተገዥ ማህበረሰብ የከፋፈሉ::የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ የካዱ::ለሃያ ሰባት አመታት ሲገሉ: የእኔጎ ጎሳ አይደለም የሚሉትን ሲያፈናቅሉ: ህዝብ ሲያስለቅሱ: በአምባገነንነት ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አጥታ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ብቻ እንድትሆን ኮረጆ ሲገለብጡ እና ሲያስገለብጡ የኖሩ ናቸዉ:: በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሊወዳደሩ የገቡ ፓርቲዎችን/መሪዎችን/አባላትን እንዲሁም ጋዜጠኞችን እና ሰበአዊ መብት ተሟጋቾችን ሲያሳድዱ : ሲያሳስሩ እና ሲቀጠቅጡ ብሎም ከሀገር ሲያባርሩ የነበሩ ናቸዉ::
ዛሬ ምድረ ጸረ ዲሞክራሲያዉያን አቢይ ይመረጥ: ደመቀ ይመረጥ ወይም ሽፈራዉ ሽጉጤ ይመረጥ እያሉ ዳንሱን ያቀልጡት ይዘዋል::በምን መስፈርት?በዬትኛዉ ዲሞክራሲያዊ ሂደት?በማን ፈቃድ? የኢትዮጵያ ህዝብ ከምርጫ ሳይካተት: ተቃዋሚ ሀይላት ከሀገር ቤት እስከ ዉጭ ሀገር ተሰብስበዉ ለምርጫ ሳይቀርቡ: አስተማማኝ ተቋማት ተገንብተዉ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት ሳይፈጠር እከሌ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሁን ማለት እጅግ በጣም ጸረ ዲሞክራሲ መሆኑን ግን ልባቸዉ ሳያዉቅ የሚቀር አይመስለኝም::ወያኔ/ኢህአዴግ ህገወጥ አምባገነን መሆኑን እያወቁ ለዚህ ሀይል ህጋዊ መሰረት ለመስጠት ከዉጭ ሀገር ድረስ በወያኔ ድርድር ተማርከዉ እየተንኳተቱ ወደ ሀገር ቤት ለመግባትም የሚግደረደሩ ሞልተዋል::


በሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን እየኖሩ ስለ ዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ እና የሀገር አጠቃላይ ድህነት ለማንሰላሰል እሳት ዉስጥ እንደገባ ጥቁር ድንጋይ ልባቸዉን ያደነደኑ ጸረ ዲሞክራሲያን ዋና ግባቸዉ የጎሳቸዉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ መመረጡን እንደ ግብ ይዛዉታል:: ወያኔስ ከዚህ የተለዬ ምን አደረገ? የሁሉም ጸረ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አይኑን ጨፍኖ የራሱን ጎሳ ለማስመረጥ መሆኑ ነዉ:: እንዲህ አይነት ጭፍን ልብ እና እይታ ያላቸዉን ስብስቦች የሚያፈራ ማህበረሰብ እዉነትም ለርዥም ጊዚያት ሳይቀጣ አይቀርም::
ህዝቡ ብዙ ደክሞ እና በአደባባይ ተቃዉሞዉን ገልጾ ወያኔን ለድርድር አምጥቶት ሳለ: ምድረ ጸረ ዲሞክራሲያዉያን ግን ጎሳቸዉን ለማስመረጥ እና የወያኔ/ኢህአዴግ ስልጣን እንዲደላደል የየጎሳቸዉን እዉራን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንዲያሸንፉላቸዉ ቅስቀሳዉን ተያይዘዉታል:: ሀገር እንዴት በጥቅል ትድናለች ብሎም ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትስ እንዴት ትሸጋገራለች ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ የእኔ ጎሳ በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስከሆነ ድረስ ወያኔ/ኢህአዴግ ብትቀጥል ደስተኛ ነኝ የሚሉት እዉራን መብዛታቸዉ ብቻ ሳይሆን የሚደንቀዉ አንድ ሰሞን ተቃዋሚ ይመስሉን የነበሩ ሁሉ ድንገት ሰሞኑን ወያኔአዊ/ኢህአዴጋዊ መንፈስ የተጠናወታቸዉ ሆነዉ እያስተዋልናቸዉ ነዉ::
ወንጀለኛን ወንጀለኛ እስካላልከዉ ድረስ ጎሳህን እየቆጠርክ ብታሽሞነሙነዉ አንድ ቀን ዋጋ መክፈልህ አይቀርም::ወይ ሀገር ያሳጣሃል: አለዚያም ጎሳህን እራሱን እርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ይመስግልሃል ሲገፋም አንተን እራስህን ህይወትህን ያሳጣሃል::ጎሳዉን እየቆጠረ ሳይሆን እዉነትን ብቻ ተንተርሶ ወንጀለኛን ወንጀለኛ ለማለት የሚደፍር ትዉልድ እስኪነሳ ድረስ ሀገር ብዙ ዋጋ እየከፈለ ይቀጥላል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<