ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት ቱርክ የኔ ነው ስትል መናገሯ፣ ከመናገርም አልፋ በዩኔስኮ ማስመዝገቧ ተሰማ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

ኢትዮጵያ ሲባል፣ ባህሏ ሲወሳ አንዱ የሚነሳውና የሚወሳው የቡና አፈላል ስነ ሥርዓታችን እንደሆነ ይታወቃል። ቡናው ተቆልቶ፣ እየተሸተተ፣ ከዚያ ተወቅጦና ተጥዶ፣ ሲኒና ጀበናው ተደርድሮ በርጋታ ቁጭ ብሎ አቦል፣ ቶና እና በረካ ብሎ መጠጣት ለብዙ ዓመታት የቆየ ባህላችን ነው።

የቡና አፈላልና አጠጣጥ ስነ ሥርዓታችን ፣ የቡና ጉዳይ ብቻም አይደለም። እናቶቻችን የሚገናኙት፣ የሚወያዩት፣ የሚመካከሩት፣ የሚረዳዱት፣ መረጃ የሚለዋወጡት፣ ያዘነ የሚያጽናኑት፣ የታመመ የሚጠይቁት ቡና አፍልተው ነው። የቡና አፈላልና አጠጣጥ ስነ ሥር ዓታችን ፣ የሳይካትሪስት ቢሯችን ነው፣ ክሊኒካችን ነው፣ ትምህርት ቤታችን ነው ፣ የመረጃ ምንጫችን ነው፣ ቡና ለኛ ብዙ ነገር ነው።

ይህን እጅግ በርካታ ዓመታት የቆየ ባህል ታዲያ ቱርክ “ይህማ የኔ ስርዓት ነው” ብላ በአለማቀፉ የአእምሮ ንብረት መዝጋቢ የባህል ተቋም ዩኔስኮ ዘንድ ማስመዝገቧ ተሰምቷል። ቱርክ ፣ በቋንቋዋ ምን እንደምትለው ባናውቅም ፣ አቦል ቶና እና በረካ የኔ ነው፣ የቆላሁትን ቡናም የማሸትተው እኔ ነኝ ብላ እንደ ራሷ ንብረት አስመዝግባዋለች። ይህን ያደረገችውም የዛሬ 13 ዓመት ነው ተብሏል።

ቱርኮች፣ ከአጼ ሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ በአማካሪነትም በሌላም አገራችን ብቅ ጥልቅ ማለታቸው አልቀረምና ያኔ ስናፈላ አይተው ኮርጀውስ ቢሆን? እንዴትስ የነሱ ከሆነ እስከዛሬ ቁጭ ብለው የዛሬ 13 ዓመት ማስመዝገብ ፈለጉ? ምናልባት እኛ እንዳላስመዘግብነው አጣርተው ይሆን?

የነሱ ቅልጥፍና እንዳለ ሆኖ የኛ መንቀራፈፍና ቸልተኝነት ግን ወደር እንደሌለው ሁሉም ይስማማበታል። ጤፍ የኛ ሆኖ ፣ ሆላንድ የኔ ነው ብላ አስመዝግባለች፣ ግዕዝ የኛ ቋንቋ ሆኖ ሳለ፣ በትምህርት ደረጃ ዲግሪ የሚሰጠው ግን በጀርመን ነው። የሚያኮሩንን የኛ የሆኑትን ፣ ከፍ የሚያደርጉንን ሁሉ ቸል እያልን፣ የፈረንጁ ላይ መንጠልጠላችን ገና ብዙ ያሳየናል የሚሉ አሉ።

በዚሁ ከቀጠልንም ዛሬ የምናከብረውን የአድዋ ድል “የኔ ድል ነው” ብላ ጣሊያን ሌላ ታሪክ ፈጥራ እንዳትወስድብንም ማሰብ ሳይኖርብን አይቀርም።

Source:  Admas Radio

One Response to ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት ቱርክ የኔ ነው ስትል መናገሯ፣ ከመናገርም አልፋ በዩኔስኮ ማስመዝገቧ ተሰማ

  1. በዚሁ ከቀጠልንም ዛሬ የምናከብረውን የአድዋ ድል “የኔ ድል ነው” ብላ ጣሊያን ማስመዝገቧ አይቀርም ሱዳን የኔ ነው ብትልስ?

    Netsanet Mekuria
    March 5, 2018 at 4:12 am
    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<