መላኩ ፈንታ እና “ሙስና”

Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |


ጌታቸው ሽፈራው

ሕንፃ በቁሙ ጠፋ በሚባልበት ሀገር፣ 77 ቢሊዮን ብር ድራሹ ጠፍቶ ኃላፊ የተባለው በማይጠየቅበት ኢትዮጵያ አቶ መላኩ “የሳሙና ባዝ” ወስደሃል ተብሎ በሙስና ክስነት ቀርቦበታል። ሌሎች አሳዛኝ ጥቃቅን ክሶችም ቀርበውበታል። ይህ አቶ መላኩ ላይ የቀረበ ክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለስልጠናት የሚፈፅሙትን ዘረፋ የማይገልፅ ከመሆኑም በተጨማሪ በሰውዬው ላይ የቀረቡት ክሶች፣ ምስክሮችና የቤተሰብ ሁኔታ በፖለቲካ ምክንያት የሙስና ሰይፍ ያረፈበት ነው የሚያሰኝ ነው። በተለይ አቶ መላኩ ከመታሰሩ ጥቂት ጊዜ በፊት ከእየ ክልሉ ቤት ንብረታቸው እየወደመ የሚባረሩት አማራዎችን በተመለከተ ጠንካራ አስተያየት ሰጥቶ እንደነበር የሚገለፅ መሆኑ ያረፈበት የ”ሙስና” ሰይፍ በማንነቱ ላይ የደረሰ ጥቃት ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ሆኗል። አቶ መላኩ የቀረበበት ክስ ዝርዝር፣ የቤተሰብ ኑሮ ሁኔታና የምስክሮች ሁኔታ ስንመለከት መላምቱን እውነታ ያደርገዋል።

እንዲያው ለምሳሌ ያህል!

አቶ መላኩ ፈንታ ከታሰረ በኋላ ደሕንነቶች አንድ ጥቆማ ይደርሳቸዋል። ጥቆማው አቶ መላኩ ፈንታ ለታናሽ ወንድሙ ” G+1″ ቤት ሰርቶለታል የሚል ነበር። ደሕንነቶቹ ወደ መላኩ ወንድም ይሄዱና ይጠይቁታል። በእርግጥ ያገኙት ይህን የመሰለ ቤት ያለው ሰው የሚሰራው ስራ ላይ አልነበረም። እንጨት እየሸጠ ነበር።

ሆኖም ደህንነቶቹ “ወንድምህ G+1 ቤት ሰርቶልሃል?” ብለው ሲጠይቁት መልሱ “አዎ” ነበር። ይህን ቤት ሊያሳያቸውም ወደሚኖርበት ሰፈር ወስዷቸዋል። ያሳያቸው ቤት ግን ያልጠበቁት ነበር። በእርግጥ G+1 ነበር። አንደኛው ደረጃው ነው። ሁለተኛው (የላይኛው የቤት ክፍል) ደግሞ ጣራው ላይ ድንጋዮች የተጫኑበትና ከደረጃው ብዙም ያልራቀ በርካታ ድሃዎች ዝናብ ችለው የሚኖሩበት “ቤት” አይነት ነው። ሚሊዮን ብሮች ወጥቶበት ተሰርቷል በሚል ጥቆማ የደረሳቸው ደሕንነቶች ይህን ቤት አይተው አዝነው እንደተመለሱ የአቶ መላኩ የቅርብ ሰው ይናገራሉ።

አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት ለዘመዶቻቸው በተማሩበት ዘርፍ ስራ ይፈልጉላቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው በሙያው ብዙም አይከበርበትም፣ አይከብርበትም። በመሆኑም ባለስልጣናት ዘመዶቻቸውን በሙያቸው የፈለጉት መስርያ ቤት የማስቀጠር እድል ቢኖራቸውም፣ ተቀጥረው እንደማይከበሩም፣ እንደማይከብሩም ያውቁታል። ስለሆነም ከG+1 ቤት የተሻለ የንግድ ተቋምም በስማቸው ይከፍቱላቸዋል። አቶ መላኩ በዚህ ስርዓት ውስጥ ሆኖ ለወንድሙ ቤት ቢሰራ አይገርምም። ደሕንነቶችም ማረጋገጥ እንደቻሉት አልሰሩም እንጅ።

አቶ መላኩ ይህን ወንድሙን አስተምሮታል። ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ፣ “ስራ አስገባኝ” ብሎ አቶ መላኩ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ይነገራል። በመሆኑም ደሕንነቶቹ G+1 ቤት ተሰርቶለታል የተባለውን ለማጣራት ሲሄዱ እንዳገኙት እንጨት ይሸጣል። ሌላኛው የአቶ መላኩ ወንድም ደላላ ሲሆን፣ እህቱም ሊፈርስ ከደረሰው የቤተሰቦቹ ቤት ትኖራለች ተብሏል።

በሌላ በኩል፣ አቶ መላኩ ላይ የቀረቡ ምስክሮች በፍርድ ቤት የሀሰት ምስክር መሆናቸውን እስከመግለፅ እንደደረሱም ይነገራል። “አንዷ ፍርድ ቤት አልቅሳለች፣ ለምን ታለቅሻለሽ ተብላ ስትጠየቅ መላኩ በሀሰት ስመሰክርበት ምን ይለኝ ? ብላ ተናግራለች። ከዛም ከችሎት ወጥታ እንድትረጋጋ ከተነገራት በኋላ ለ30 ደቂቃ ያህል ውጭ ቆይታ ተመልሳ መስክራለች” ሲል አንድ የቅርብ ሰው አጫወቶኛል። ሌሎች የሀሰት ምስክሮች እንደነበሩም እንዲሁ!

ነገ የካቲት 27/2010 ዓም አቶ መላኩ ፋንታ ለፍርድ ተቀጥሯል።

One Response to መላኩ ፈንታ እና “ሙስና”

  1. ሊፈታ ነው ገብረዋህድ ጭምር ሀሉም ባለሃብቶች ይፈቱ

    ፍቃዱ
    March 6, 2018 at 10:40 am
    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.