አሸባሪው ወያኔ እያደረሰ ያለውን ገደብ የለሽ የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ለማፋጠን ያወጀውን የዘር ማጥፊያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውገዝ ከቅዱስ ሲኖዶስ የወጣ መግለጫ

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ” ገላ 5:1

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን።
በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ለምትኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ፤

(PDF) በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ከሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራችን በኢትዮጵያና በሕዝባችን ላይ አሸባሪው ወያኔ እያደረሰ ያለውን ገደብ የለሽ የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ለማፋጠን ያወጀውን የዘር ማጥፊያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውገዝ የወጣ መግለጫ፤

ቅዱስ ጳውሎስ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ” ገላ ፭፣፩ በማለት በአወጀው የሰው ልጆች የነጻነት መብት አዋጅ ነጻነት ለሰው ልጅ ሁሉ ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጠ የተፈጥሮ ስጦታ ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ንጹህ አየር የመተንፈስ፤ በተወለደበት ሀገር በነጻነት ተረጋግቶና ዘና ብሎ የመኖርና ሐሣቡን በጽሁፍ የመግለጽ መብት እንዲኖረው ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጠው የተፈጥሮ ስጦታው ነው። እነዚህን በተፈጥሮ ያገኛቸውን ነጻነቶች ሲያጣ ሲታፈንና ሀብቱን ሲነጠቅ የአስተዳደር በደል ይፈጸምበታል። የአስተዳደር በደል ሲደርስበት ደግሞ ሰላም ያጣል፤ ተስፋ በመቁረጥም የሚወዳትን ሀገሩን ጥሎ ሰላምና ነጻነት ፍለጋ ስደትን ይመርጣል። የሕዝባችንም ዋናው ችግር የመልካም አስተዳደር ማጣቱና ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጠውን ነጻነት መነጠቁ ነው። በዚህም ምክንያት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ከባድ የሆነ የታሪክም የሰው ሕይወትም ጥፋት እየተፈጸመ ለችግሩ መፍትሔ ሳይገኝለት እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋና እየባሰ ስለመጣ የኸውና 27 ዓመታትን አስቆጥሯል።

ስለሆነም ለዚህ መቆሚያ ለሌለው ከባድ ችግርም ተጠያቂው የትግራይ ነጻ አውጭ ወያኔ መሆኑ ግልጥ ነው። ከአባታችን ከአዳም ታሪክ እንደተማርነው ሰው በነፍሱ በባርነት ቀንበር የሚወድቀው፤ እንዲሁም በሥጋው በሰው እጅ ተይዞ በእሥር የሚማቅቀው ትእዛዝ አፍራሽ ወንጀለኛ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው።ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ከኃጢአት ባርነት ነጻ የወጡ ምእመናን ዳግመኛ ከባድ የበደል ቀንበር በላያቸው እንዳይጫንባቸው ኃጢአትን የሚፈሩ የመንግሥትንም ሕግ የሚያከብሩ እንዲሆኑ ትመክራለች፤ ክርስቲያናዊ ግብረ ገብነትንም ታስተምራለች። ከዚህ በተቃራኒው ግን መብቱንና ግዴታውን አውቆ ነጻነቱን ጠብቆ እና ሀይማኖቱን አክብሮ በሚኖረው ሕዝባችን ላይ የእብሪተኞች የባርነት ቀንበር ሲጫንበት፤ ሀብቱን ሲቀማ፤ ለብዙ ጊዜ ከኖረበት ከቤቱ ከቦታው ሲፈናቀል፤ ልዩ ልዩ ሰቆቃ ሲፈጸምበትና በላዩ ላይ የተጫነበትን ግፍና በደል መሸከም አቅቶት አንገቱን ሲደፋ፤ ቤተ ክርስቲያን ለሕዝቡ ጠበቃ በመሆን “ባርያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ” ገላ 1:27፤ እያለች ድምጿን ከፍ አድርጋ እኩልነትን ለሰው ልጆች ሁሉ ታውጃለች። በጉቦና በሙስና እየተጨማለቁ ያሉትን የትግራይ ነጻ አውጭ ወያኔዎችን “ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” ትላለች፤ እንዲሁም በሕዝቧ ላይ ልዩ ልዩ በደል በመፈጸም የሚደሰቱትን የወያኔን ባለሥልጣናት “በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም በሀሰት አትክሰሱ” ሉቃ 3:14 እያለች በወንጌል ቃል ትመክራለች ትገስጻለች። ይህን ማድረግ ካልቻለች ግን የግፍ ቀንበር የተጫነበት፤ በየቀኑ እየተበደለ ያለውና ቀን የባሰው ትውልድ ከጨቋኝና ከገዳይ መደብ ጋር የተባበረች አድርጎ ይመለከታታል፤ እምነቱንም ይጠላል።

በሀገር ውስጥ የሚኖሩት የሀይማኖት መሪዎች የሚባሉት አባቶችም በዘር በሽታ በጽኑእ ከታመመው ከወያኔ ጋር ተባባሪዎች ስለሆኑና የሕዝባቸው በደልና ግድያ ሰለማይገዳቸው የኃዘን ስሜት እንኳን አይታይባቸውም። አንድ አንድ አረጋውያን አባቶች ቢኖሩም በወያኔ የአፈና ቀንበር ውስጥ የወደቁ መሆናቸውን በብፁእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሚመራው ሕጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠንቅቆ ያውቃል።

ስለዚህም ላለፉት 27 ዓመታት ለነጻነት ከሚታገሉ ወገኖች ጎን በመቆም የታፈነው ሕዝባችን ነጻ እንዲወጣ ያለማቋረጥ ድምጹን በማሰማት ላይ ይገኛል። የሀገራችን ኢትዮጵያና የባለ ታሪኩ ሕዝባችን ህልውና በአሁኑ ሰዓት በከባድ አደጋ ላይ ይገኛል። ሕዝባችን የተሰጠውን የተፈጥሮ ስጦታ የታፈነ፤ ርሥቱን የተነጠቀ፤የዜግነት መብቱን የተገፈፈ፤ የመኖር ዋስትና እና ሀገር የሌለው ሕዝብ ሆኖአል።

የኢትዮጵያ መልክና ስም እንጂ ሰብአዊ ርህራሄ የሌላቸው አረመኔዎች የትግራይ ነጻ አውጭዎች ከሚያደርሱበት ልዩ ልዩ መከራና በቃላት ሊገለጹ ከማይችሉ ስቃዮች በላይ እርስ በርሱ በጎሳ ተከፋፍሎ እንዲገዳደልና ምድሪቱ የደም ምድር እንድትሆን አረመኔው ወያኔ ከበረሀ ጅምሮ እስካሁን ድረስ በጽኑእ የተያዘበትን የማይድንና መድኀኒት የሌለው የዘር በሽታ ምክንያት አድርጎ የጥፋት አዋጅ አውጆበታል።ሕዝባችንም ከወያኔ የመከራ ጽናት የተነሳ የሚወዳትን ሀገሩን ትቶ ስደትን መርጡዋል፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በባህር ሰጥመው ሕይወታቸው አልፋለች። ከባድና መሪር የሆነውን የወያኔን የግፍና የባርነት ቀንበር አንሸከምም ያሉና በሀገር ውስጥ ሆነው ለነጻነት የሚታገሉ ወገኖቻችን በየቀኑ በጥይት እየተገደሉ ይገኛሉ፤ ታሪካዊው ሕዝባችን ተዋርዶ በዓለም መዘባበቻ ሆነናል።

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ሁሉ መከራ ይጋራል ከሚደማው ሕዝባችንም ጋር በስሜቱ እየደማ ይገኛል።

የንጹሐን ወገኖቻችን ደም ሱሰኛ የሆነው ወያኔ ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎት ከዚህ ቀደም ሲያስር ሲደበድብ ሲገድል የኖረውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማፋጠን የጭቆናና የአገዛዝ ቀንበሩን ለማራዘምና የጀመረውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለመፈጸም እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ያወጀውን የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ የዘር ማጥፊያ አዋጅ በብፁእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያወገዘ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1. ለኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረበ የማስጠንቀቂያ ጥሪ፤

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስም የሚነግደው ዘር አጥፊው ወያኔ የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ለማፋጠን ለሁለተኛ ጊዜ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ የዘር ማጥፊያ አዋጅ የዓለም መንግሥታትና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅቶች አጥብቀውና አጠንክረው በይፋ ተቃውመውታል።እናንተም ለተወከላችሁበት ዓላማ የወከላችሁ ድምጹን የታፈነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጻችሁን እንድታሰሙለት ለመጀመሪያ ጊዜ እየጠየቃችሁ ይገኛል፤ ስለሆነም በዚህ ከባድና ፈታኝ ወቅት ከወከላችሁ ሕዝብ ለቀረበላችሁ ጥያቄ ይህን አጋጣሚ ሳትጠቀሙበት በከንቱ እንዳያልፍና እናንተም በታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ይህን የሁለተኛ ጊዜ የዘር ማጥፊያ የአስቸኳይ ጌዜ አዋጅ ተቀብላችሁ እንዳታጸድቁ ብቻ ሳይሆን አጥብቃችሁ እንድታወግዙትና ከሕዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል።

2. ለትግራይ ተወላጆች ወገኖቻችን የቀረበ የመጨረሻ ጥሪ፤

የትግራይ ተወላጆች ወገኖቻችን! ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር መሆኗን በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የሁላችን ወገኖች መሆናቸውን እንደምታውቁ ተስፋ እናደርጋለን። እንዲህ ከሆነ በአንዲት ሀገር ኢትዮጵያ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል አንዱ ተጠቃሚ፤ ሌላው ጦም አዳሪ፤ አንዱ ስደተኛ፤ አንዱ ነጻነት ያለው ምርጥና ኩሩ ዜጋ፤ ሌላው ባሪያ ሆኖ መኖር ይችላል ብሎ የሚያምን ቢኖር ትናንት የነበረበትንና ነገ የሚኖረውን የማያውቅ፤ ማንነቱን የረሳ ነው። የሕዝብ ማዕበል ታምቆ ሲፈነዳና የመከራው ዘመን ሲያዘነብል የሚደሰቱ፤ የሚስቁና የሚሳለቁ፤ የሚያለቅሱበት ጊዜ እንደሚመጣ ካለፈው የረጅም ጊዜ ታሪክ መማር ያስፈልጋል። ከአማራና ከኦረሞ በጠቅላላም ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተዘረፈና እየተነጠቀ በሚወሰድ ሀብትና ንብረት ተድላ ደስታ እያደረጉ መኖር የወገንን መከራና ስቃይ መርሳት ተገቢ ስላልሆነ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብም ችግርና መከራ፤ኃዘንና ስቃይ የናንተም ጭምር መሆኑን፤ የሕዝባችን ሰላምና እረፍት ደስታም፤ የእናንተም መሆኑን አምናችሁ በእናንተ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግደውን ዘር አጥፊ ቡድን በቃህ፤በኛ ስም ሀገር አትሽጥ፤ ዘርንም አታጥፋ በማለት በየቀኑ እየተገደለ ከሚገኘው ሕዝባችሁ ጎን እንድትቆሙና የዘር አጥፊውን የወያኔን የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንድታወግዙ ቅዱስ ሲኖዶስ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ጥሪውን ያቀርባል።

3. ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለፖሊስ አባላት የቀረበ ጥሪ፤

በዓለም ታሪክ እንደሚታወቀው ሁሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት የሀገር ዳር ደንበር በውጭ ጠላት ወራሪ እንዳይደፈር የሀገሩን ዳር ደንበር ያስከብራል፤ የዜጎችንም ሰላምና አንድነት ይጠብቃል፤ ሰለሆነም ይህ የዘር አጥፊው ሥርዓት ያልፋል፤ ይሻራልም፤ እናንተም ለሕዝባችሁና ለወገናችሁ ስትሉ፤ ላራሳችሁም ቀጣይ ሕይወት በማሰብና በመጠንቀቅ ለዘር አጥፊው ለወያአኔ መሳሪያ በመሆን ወገናችሁን ከመግደል እንድትቆጠቡና ከሕዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል።

4. ለፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች የቀረበ ጥሪ፤

ለኢትዮጵያ ሀገራችን ክብር በግፍ እየተጨፈጨፉ ለሚገደሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የምትቆረቆሩ የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ የቆማችሁ ወገኖቻችን በሙሉ በዚህ እጅግ በጣም ከባድና ፈታኝ በሆነ ወቅት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ያለምንም መሪና አስተባባአሪ ለሀገራቸው ክብር ለወገናቸው ነጻነት ራሳቸውን አደራጅተው መተኪያ የሌለውን ውድ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው የሞት ሽረት ትግል እየታገሉ በሚገኙበት በአሁኑ ሰዓት እናንተም ልዩነታችሁን በአስቸኳይ አጥፍታችሁ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ወንድማማችነት ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ክብርና ለአንድ ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት ከሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጎን በመሰለፍ በአንድነትና በህብረት እንድትሠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ የአስቸኳይ ጊዜ የአደራ ጥሪውን ያስተላልፋል።

5. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበ ጠሪ፤

እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ሀገራችን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር በመውደቋ በከፍተኛ አድጋ ላይ መገኘቷና ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም በአረመኔውና በከሀዲው በወያኔ አረመኒያዊ አገዛዝ የሚደርስባችሁ በደል የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን በእጅጉ አሳዝኖናል። ሕመማችሁ ያመናል፤ በግፍ የሚፈጸምባችሁ ግድያና ጭፍጨፋ ያስለቅሰናል፤ በጋዳማት የሚገኙ የቅዱሳን አጽም በመታረሱ፤ መነኮሳቱ የምንኩስና ልብሶቻቸውና ቆቦቻቸው ተገፈው መታሠራቸውና መደብደባቸው፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በሚታወቁና በማይታወቁ የጨለማ እሥር ቤት ታፍነው የሚደርስባቸው ድብደባና ሥቃይ በጣም ያመናል፤ ይህን መሪር የሆነውን የወያኔ የአገዛዝ ቀንበር ቸሩ ፈጣሪያችን እድሜውን እንዲያሳጥረው በጸሎትና በምልጃ ዘወትር ከናንተ ጋር መሆናችንን ስንገልጥ በመሪር ኃዘን ነው።

ስለሆነም ስለነጻነቱ የሚሞት ሕዝብ ምንጊዜም አሸናፊ ስለሆነ የታሠሩት መነኮሳትና በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎቻችን እስከሚፈቱ ድረስ፤ የዘር አጥፊው የወያኔ አገዛዝ ተወግዶ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደቀደመ ክብሯ ተመልሳ፤ ዜጎቿም የዜግነት መብታቸው ተክብሮ በሰላምና በጸጥታ የሚኖሩባት የሰላም ሀገር የበረከት ምድር እስከምትሆን ድረስ በምንም በምን ሳትለያዩ በአንድ ልብ በአንድ ሐሣብ ሁናችሁ የጀመራችሁትን የነጻነት ትግል በድል አድራጊነት እስከምታጠናቅቁ ድረስ የአንድነት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው ወደኃያሉ እግዚአብሔር መጮህ ለሀገራችን ሉዓላዊነት ለሁላችንም ለጀመራችሁት የጻነት ትግል ፍጻሜ የሚጠቅም መሆኑን ከታላቅ አደራ ጋር እያሳሰብን፤ ጥሪያችንን በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ ቃል እናጠናቅቃለን።

በመሆኑም “ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለጋኔን” “ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያብሎስን (ወያኔን) ግን ተቃወሙት”ያዕቆብ 4፡7 በተባለው ቃል መሠረት ያደረጋችሁ እንደሆነ ኃያሉ አምላካችን ከከሀዲውና ከዘር አጥፊው ከወያኔ አረመኔያዊ አገዛዝ ነጻ ያወጣችኋል።በታሪክ መዝገብ ውስጥ ኢትዮጵያንም የሰላም፤የአንድነትና የተስፋ ሀገር እንድትሆንና ለትውልድ እንድትተላለፍ ታደርጋላችሁ። የኢትዮጵያ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የጨለማውን አገዛዝ እድሜውን እንዲያሳጥረው፤ ለሀገራችንም ቅን መሪን እንዲተካ፤ በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሚመራው በስደት ላይ የሚገኘው ሕጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዘወትር በጸሎቱ ያስባችኋል።

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ሕዝባችንንም ይጠብቅልን! አሜን።

Address: 15521 Orchard Run Drive, Bowie, MD20715, Tel: 403-266-1178, Email:abunemichael@live.ca 4 Mailing address: 2515 Edmonton Trial NE, Calgary, Alberta, Canada T2E 3M9

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

<