ኢትዮጵያዊቷ ፊቷ ላይ አሲድ ተደፋባት – ደፍቷል ተብሎ የተጠረጠረው ሌላው ኢትዮጵያዊ ተይዟል

Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |

(አድማስ ሬዲዮ)  ነገሩ የሆነው አሜሪካ፣ ሜሪላንድ ግዛት ባለፈው ፌብሩዋሪ 28/2018 ነው። ሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን እና ሌሎችም የዜና ምንጮች ከሥፍራው እንደዘገቡት በክሪ አብደላ የተባለው ኢትዮጵያዊ ወጣት ፣ በደባልነት (ሩም ሜት) አብራው ትኖር የነበረችው ሰላማዊት ተፈራ ፊት ላይ አሲድ በመድፋት ተሰውሮ ከቆየ በኋላ ሊያዝ ችሏል ብለዋል። ሰላማዊትና በክሪ ምን ያህል ጊዜ በደባልነት አብረው እንደኖሩ ዜናው አይገልጽም፣ ለምን ይህን ወንጀል በክሪ እንደፈጸመም ገና በምርመራ ላይ ነው።

 

የዜና አውታሮች እንደሚሉት አሲድ የተደፋባት ሰላማዊት ተፈራ፣ ቀድሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ ሆና ትስራ ነበር። አሜሪካ ከመጣች ገና ሁለት ዓመት እንደሆናትም ተነግሯል።

ሰላማዊት ጥቃቱ እንደደረሰባት፣ ከቤቷ በሩጫ በመውጣት ለጎረቤቶች የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማቷም ታውቋል። በኋላም ፖሊስ ደርሶ ወደ ሆስፒታል ወስዷት ህክምናዋን በመከታተል ላይ ስትሆን፣ ለህክምናዋ ወጪ መሸፈኛ እንዲሆን የቅርብ ጓደኞቿ በጎ ፈንድ ሚ የርዳታ ማሰባሰብ ሥራ መጀመራቸውም ተሰምቷል።

የዜና አውታሮች ፣ ጎረቤቶችን ጠቅሰው እንደዘገቡት፣ የ28 ዓመቱ ወጣት በክሪ አብደላ ፣ ብዙ ጊዜ ጮክ እያለ ለብቻው ሲያወራ እንደሚያዩትና ጸባዩ ለየት ያለ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል። በክሪ ወንጀሉም መፈጸሙን እንዳመነ ፖሊስ ያስታወቀ ሲሆን፣ በመጪው ማርች 27 ክሱ መታየት ይጀምራል ተብሏል።

አሜሪካን አገር ሰዎች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ከደባል (ሩም ሜት) ጋር አብሮ መኖር የተለመደ መሆኑን የሚናገሩ ባለሙያዎች፣ ነገሩ ያ ቢሆንም፣ አብሮን ውሎ አብሮን የሚያድረው ሰው ምን ዓይነት እንደሆነ ለማጣራትና ለማወቅ መሞክር ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። አንዳንድ ሰዎች ጠዋት ሩም ሜት እፈልጋለሁ የሚል ማስታወቂያ አይተውና ደውለው፣ ከሰዓቱን ዕቃቸውን ይዘው እንደሚገቡ ይታወቃል።
(Pic. Bekri and Selamawit)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.