የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በደብረ ብርሃን ከተማ አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ቅዳሜ እና እሁድ ካካሄደ በኋላ አዳዲስ አመራሮችን መርጧል

1 min read

”አብንን በሊቀመንበርነት መምራቴ የእድሜ ልክ ኩራቴና ክብሬ ነው።” ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ / የቀድሞው የአብን ሊቀመንበር

አማራ ሚዲያ ማዕከል /አሚማ
የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ

በዚህም መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው ፓርቲውን ከምስረታው ጀምሮ በሊቀ መንበርነት ሲመሩት የቆዩትን ደሳለኝ ጫኔን (ዶ/ር) አንስቶ በምትካቸው ምክትላቸው የነበሩትን አቶ በለጠ ሞላን ሊቀ መንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን፤ አቶ ዩሱፍ ኢብራሂምን ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር አድርጎ ሾሟል።

በዚህም መሰረት የቀድሞው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በቲውተር ገፃቸው በድርጅቱ ውስጥ ስለነበራቸው ቆይታና ስለተደረገው የስልጣን ሽግሽግ መልዕክት በማስተላለፍ እንዲሁም ምስጋና በማቅረብ ተሰናብተዋል።

”አብንን በሊቀመንበርነት መምራቴ የእድሜ ልክ ኩራቴና ክብሬ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን ይጀምራሉ ዶ/ር ደሳለኝ። ከዚህ በፊት በሰራሁባቸው የተለያዩ ሃላፊነቶችም ሆነ ወደፊት ላገለግልባቸው የምችልባቸው ማንኛውም አይነት ሃላፊነቶች ከአብን አመራርነቴ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም።

ምክንያቱም የአማራ ህዝብ የዘመናት መቃተት የወለደውን እና የአማራነት መንፈስ ፣ የህዝባችን ተስፋ የሆነን ንቅናቄ የመምራት ክብር አገር መምራት ሊሰጥ ከሚችለው በላይ ስሜት ሰጥቶኛል። ሙሉ ስሜቴን እና ህይወቴን ገዝቶኛል። በስብእና፣ በተሞክሮ፣ በአመለካከት፣ በእውቀት እና በክህሎት አሳድጎኛል ብለዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ በመልዕክታቸው ሲቀጥሉ ከአብን ቅድመ ምስረታ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ከታሰርንበት ጊዜ ጀምሮ ያሳለፍኳቸው ሁለት አመታት በየቀኑ በርካታ ስራ የሰራንበት፣ ተለዋዋጭ እና ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ያሳለፍንበት፣ ፈተናዎችንም ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት ያደረግንበት፣ ከስራ አስፈጻሚ እና ሌሎች አመራር ጓዶቼ ጋር ብዙ የተደሰትንበት፣ በሀሳብ ያማጥንበት፣ የተፋጨንበት እና አንዳንዴም እንባ ጭምር ያነባንበት ብዙ አጋጣሚዎችን አሳልፈናል።

አስመራጭ ኮሚቴዎች እና የትግል ጓዶቼ በድጋሜ በእጩ ሊቀመንበርነት ለማቅረብ ከፍተኛ ማግባባት ቢያደርጉም አብን ውስጥ ያደረግነው ንስራዊ መታደስ ምልኡ ይሆን ዘንድ ፣ እንዲሁም ከእኔ የተሻለ አመራር እንዲመጣ ከነበረኝ ጉጉት ጋር ተዳምሮ ራሴን ከእጩነት አግልየ በአብን አመራር ታሪክ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ምሳሌ ለመሆን ሞክሪያለሁ።

በዚህም ወንድሞቼ እና ጓደኞቼ ከዛሬ ጀምሮ በኩራት መሪዎቼ የምላቸውን ጓድ በለጠ ሞላ ጌታሁንን በሊቀመንበርነት፣ ጓድ የሱ ኢብራሂም ሽፋውን በምክትል ሊቀመነበርነት እንዲመረጡ እድል ፈጥሯል። ሁለቱም መሪዎቼ በሁሉም ነገር ከእኔ የተሻለ የፖለቲካ እውቀት፣ ክህሎት እና የመሪነት ተክለ ስብእና ያላቸው መሆኑ ደግሞ ሃሴት ፈጥሮልኛል። ከነባሩ አመራር የቀጠሉትም ሆነ አዲስ የተቀላቀሉት ስራ አስፈጻሚዎችና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላትም አብን እና የአማራ ህዝብን ወደ ድል እንደሚመሩት እተማመናለሁ ሲሉ ተስፋቸውን ገልጠዋል።

በመጨረሻም በመሪነት ዘመኔ ከጎኔ በመሆን ለደገፋችሁኝ፣ በሀሳብ እና በምክር ለደገፋችሁኝ ፣ ፍቅር እና እንክብካቤ ላሳያችሁኝ የንቅናቂያችን አመራሮች ፣ አባላጥ ደጋፊዎች፣ የብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ አባላት ፣ የምክር ቤቱ አመራሮች እና አባላት፣ በመላው አለም የምትኖሩ የአብን ደጋፊዎች እና ድጋፍ አስተባባሪዎች ፣ ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ በሙሉ ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ እና ምክር ፣ ላሳያችሁኝ ፍቅር ፣ አክብሮት እና መጨነቅ ከልብ የመነጨ ምስጋናየን አቀርባለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።”

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.