በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው የነበሩት ግለሰብ ነፃ መሆናቸው ተረጋገጠ

1 min read

ከሰሞኑ በቢቡኝ ወረዳ ከሳዑዲ ዐረቢያ ወደ በአዲስ አበባ በኩል የገቡ አንዲት ግለሰብ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተጠርጥረው እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ግለሰቧ የካቲት 29/2012 ዓ.ም ነበር ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው የተገለጸው፡፡ መጋቢት 2/2012 ዓ.ም በበሽታው ከተጠቃች ሀገር ስለመጡ ጤንነታቸውን በሕክምና ለማረጋገጥ በመፈለጋቸው ግለሰቧ ካሉበት ወይኗ ቀበሌ ወደ ጤና ኬላ አቅንተዋል፡፡ የጤና ኬላ ሠራተኞችም የግለሰቧ የጤና ሁኔታ እና የሚታዩ ሁኔታዎችን በመረዳት አስፈላጊውን ምርመራ ካደረጉ በኋላ ስላለው ሁኔታ ለወረዳው ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ሁኔታውን እንዲያውቀው አደረጉ፡፡

የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ደግሞ ለዞኑ ጤና ጥበቃ ጥበቃ መምሪያ እና ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አሳወቀ፡፡
የዞኑ ጤና ጥበቃ መምሪያ እና የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ በጋራ የደም ናሙና በመውሰድ በተደረገው የምርመራ ውጤት መሠረትም ግለሰቧ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ግለሰቧ የራሳቸውን ጤንነት ለማረጋገጥ የወሰዱት ርምጃ የሚደነቅ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ መምሪያ እና የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ማድነቃቸውን የቢቡኝ ወረዳ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ/ አብመድ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.