ሰብ አዊ አደጋውን በጋራ እንቋቋመው! – ከአንተነህ መርዕድ

1 min read

አንተነህ መርዕድ
ማርች 2020

አሁን በመላ ዓለም የተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ አደጋ ከምንጊዜውም የከፋ ነው። በጥንካሬ፣ በአንድነትና በዲሲፕሊን ከተከላከሉት የሚቋቋሙት መሆኑን ቻይናዎች አሳይተዋል። በቢልዮን ከሚቆጠር ህዝባቸው መካከል የገባውን መቅሰፍት መንጥረው በማውጣት የተቋቋሙት ከሁሉም በላይ ህዝቡ ሆነ መሪዎቹ ዲሲፕሊን ስለአላቸው ነው። ዛሬ እነሆ የስልጣኔ ቁንጮ የሆኑት አውሮፓውያንና አሜሪካኖችን እያስጨነቀ ያለው መቅሰፍት ሊቋቋሙት ፈታኝና ጨካኝ መሆኑን አስመስክሯል።

በአንድ የበለጸገ አገር የጤና ተቋም ውስጥ እንደመስራቴ ካላቸው እውቀት፣ ሃብትና ጠንካራ ድርጅታዊ ቁመና አንጻር የአገሬን ሁኔታ ሳስብ እንቅልፍ ይነሳኛል፣ እንባ ይተናነቀኛል። ከሁሉም በላይ ተማርን ያሉ ፖለቲከኞችንና የዘረኞችን ድንቁርና በየቀኑ ሳይ ተስፋዬ ይሟሽሻል። መገናኛ ብዙሃኑ፣ ሶሻል ሚድያውና ሌላውም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሳይ ምንም አደጋ የሌለ ይመስል ጥላቻውና ወንዝ የማያሻግር፣ ህይወት የማያድን በካይ ፕሮፓጋንዳ ተሞልቶ የማየትን ያህል መራር ነገር የለም። “የጨው ተራራ ሲናድ፤ ሞኝ ይስቃል፣ ብልህ ያለቅሳል” እንዲሉ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ትንሽ ሆኖ መታየት ያዘናጋን ሚሊዮኖች ነን። ጣልያንም ሲጀምራት በጥቂቶች ነበር። ዛሬ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ ናት።

ይታያችሁ! ከአንድ መቶ አስር ሚሊዮን በላይ በድህነትና በዕውቀት ኋላ የቀረው ህብረተሰባችን በሽታው ከተማና ገጠር ከገባ ሲዎችን አይደለም ሚሊዮኖችን ሊገድል እንደሚችል እሙን ነው። በየትኛውም ጊዜ አገራችንን ከገጠሙት የውጭ ወረራዎች ሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ካለቀው ህዝብ በላይ ሊጨርስ ይችላል። ይህን ስል ጨለምተኛነት አጥቅቶኝ አይደለም። የህመሙን አደገኛነትና የህዝቤንም ቸለልተኛነት በማየት ነው።

በተለይ በመርዘኛ የዘር ፖለቲካ የተለከፋችሁና ሰውን እርስ በርስ የምታፋጁ ወገኖች ሆይ! ዘር የማይለይ፣ እናንተንም የማይምር፣ ከእናንተም የከፋ መቅሰፍት መጥቷል። ሰው በመሆናችን ብቻ ሁላችንንም እኩል የሚያጠቃን ጠላት ተጋርጦብናል። ስለሆነም ፖለቲከኞች፣ አክቲቢስቶች፣ ባለሃብቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ባለስልጣናት፣ ሁላችሁም ህዝብ ከሌለ ምንም አይደላችሁም። ለህዝቡም ለራሳችሁም ስትሉ አገር አድን ዘመቻ ጀምሩ።

በሶሻል ሚድያ በተለያዩ ቅድሚያ ልንሰጣቸው በማይገባን ጉዳዮች ላይ ያተኮራችሁ ሁሉ ስለሰው ዘር መትረፍ፣ በተለይም ሳይማር ላስተማረን ምስኪን የኢትዮጵያ ህዝብ ስትሉ ስልካችሁን፣ ኮምፒዩተራችሁን፣ ሚድያችሁን፣ ጉልበታችሁን ሆነ ጊዜአችሁን ለዚህ የተቀደሰ ሰባዊነት አውሉት።

ይህ የከፋ እልቂት በአገራችን ቢስፋፋ፣ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስ ተጠያቂዎቹ ሁላችን ነን። ይህ ህዝብ በስንት ይቀጣ? እንባውንስ ማን ያብስለት? እርሃቡንስ ማን ያስታግስለት? ሰላሙንስ ማን ይመልስለት? ፈጣሪ የማይረሳው ህዝብ ቢሆንም እኛስ በመከራው ጊዜ ልናሳውቀው፣ ልንደግፈው፣ ልናጽናናው አይገባንም? የመቅሰፍቱን አደገኛነት ሳይሸበር ማሳወቅና የሚከላከልበትን መንገድ ከእኛ የተሻለ ማን ይንገረው?

ቤት ዘግቶ መቀመጥ፣ መታጠብ፣ ጭንብል መልበስ፣ ምግብና ውሃ በቀላሉ ማግኘት በሚቻልባቸው አገሮች ችግሩ ካስጨነቃቸው አገራችን ሲደርስ የሚያስከትለውን እልቂት ቆም ብለን እናስብና እንንቀሳቀስ።

እንደዛሬ አንቲባዮቲክ በቀላሉ በማይገኝበት፣ ትንንሹ ህመም ሁሉ በገነነበት በጨለማው ዘመን ከተስቦና ልዩ ልዩ ወረርሽኝ አያቶቻችንና ቅድመአያቶቻችን ራስን በማግለልና በመራዳዳት ከሞት ተርፈው እኛን ያሳደጉን፣ ያስተማሩን የዛሬ ትውልድ ከነሱ ተሽለን መገኘት ይኖርብናል። አገርን በአንድነት በማቆየት፣ በሽታን ተባብሮ በመመከት ለዚህ አብቅተውናል። የአገር ህልውናና የህዝብ ደህንነት እኛ ላይ ሲደርስ አደጋ ላይ ሊወድቅ አይገባውም።

ከተማ ውስጥ ያለው ህዝብ የተሻለ ኝዛቤ ከመገናኛ ብዙሃን ያገኛል። የገጠሩ ህዝብ ግን ምን ማድረግ እንዳለበት በዘመቻ መልክ ሊቀሰቀስ ያስፈልጋል። በማህበር፣ በለቅሶ፣ በሰርግ፣ በገብያ፣ በእምነት ተቋማት፣ የሚያደርገው መሰባሰብ ለበሽታው መስፋፋት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጾ ለማስገንዘብ ዘመቻ ካልተጀመረ አደጋው የከፋ ይሆናል።

ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ወ ዘ ተ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰራተኛ ማህበራት፣ የመንግስት ተቋማት፣ ወ ዘ ተ የመጀመርያ ዘመቻቸው ህዝቡን ስለወረርሽኙ አደገኛነትና መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ ማሳወቅ ሲሆን በተጓዳኝ አደጋው ቢስፋፋ መደረግ ያለባቸውን የተግባር ቅደም ተከተሎች መንደፍና መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። “እየየም ሲዳላ ነው” እንዲሉ ትኩረታችን ሁሉ ህዝብንና ራስን ማዳን ላይ ይሁን። በዚህ ሰዓት የጥላቻ እሽኮለሌ የሚጫወት ሁሉ የአገርና የህዝብ ብሎም የራሱ ጠላት ነው።

ሰብአዊ አደጋውን በጋራ እንቋቋመው!

1 Comment

  1. Some of the young generations siblings are already fighting over inheritance by arguing at elders neighborhood bars over the wills of their parents, all these while currently the parents are alive and well, with legal courts shut down many are claiming they are on the will , most of the elders donot really know who is on the will and who is not since some are even claiming to be born out of the marriage who are waiting for the pandemic to hit so they inherit whatever they assume is theirs ,it seems the neighborhood elder bar/courts are going to be overloaded with such cases to the point where it spirals out of control without a doubt .

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.