ወረርሽኙ ከሚያደርሰው አካላዊ ጉዳት በተጨማሪ ሥነ ልቦናዊም ጫና እንዳለው እየተነገረ ነው

1 min read

ኮሮናቫይረስ ዓለምን የማያባራ መጠራጠር ውስጥ ከትቷል። ስለ ቫይረሱ የሚወጡ መረጃዎች ማብቂያ ያላቸው አይመስልም። ይህ ሁሉ የሰዎች ስነልቦና ጤና ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ቀላል አይደለም።

በተለይም ቀድሞም የአእምሮ ጭንቀት ያለባቸው ላይ። ስለዚህም በዚህ ፈታኝ ወቅት ሰዎች እንዴት የአእምሮ ጤናቸውን ይጠብቁ?

ስለ ኮሮናቫይረስ የሚወጡ ዜናዎችን ሁሉ በትኩረት መከታተል የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም ይህ ግን የአእምሮ ጭንቀት ላለባቸው ከባድ ጫና ነው።

እንደዚህ ባሉ ሁኔታዎች መጠራጠርን እና ፍርሃትን መቋቋም አለመቻል የተለመደ የአእምሮ ህመም ባህሪ እንደሆነ የአእምሮ ጤና ባለሙያዋ ኒኪ ሊድቤተር ይናገራሉ።

እኚህ እንግሊዛዊ “ብዙ ጊዜ የጭንቀት ህመም ገና ባልተፈጠረና ባልታወቀ ነገር ላይ ይሆናል ብሎ አብዝቶ በመጨነቅ የሚመጣ ነው። ከዚህ አንፃር ኮሮናቫይረስ ከባድ ነገር ነው” ይላሉ።

የምትከታተሉትን ዜና መቀነስና የምታነቡትን መጠንቀቅ

ስለ ኮሮናቫይረስ በርካታ ዜናዎችን ማንበብ ቀድሞም ጭንቀት ያለባቸውን የሁለት ልጆች አባት በተደጋጋሚ ለሚመላለስ የልብ ህመም እንደዳረገ ይናገራሉ ባለሙያዋ።

“ስጨነቅ ልቆጣጠረው በማልችል መልኩ እጅግ መጥፎ የሆነ ነገር እንደሚመጣ አውጠነጥናለሁ” በማለት ኮሮናቫይረስ ቤተሰቦቼን እና የማውቃቸውን አዛውንት ሰዎች ይጎዳል በማለት እንደሚጨነቁ ተናግረዋል።

ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ጭንቀት ቀስቃሽ ነገሮችን ማስወገድ

ለተወሰኑ ጊዜያት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲሁም የዜና ድረ ገፆችን አለመመልከት ከእንዲህ ያለ ጭንቀት እንደሚገላግል ይነገራል።

ማህበራዊ ሚዲያ ለአንዳንዶች ጭንቀት አምጭ ነገር ነው። በማንችስተር ከተማ ኗሪ የሆነቸው 24 ዓመቷ አሊሰን ጭንቀት ያለባት ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያ የምታያቸው ነገሮች ምን ያህል እንደሚረብሿት ትናገራለች።

“ከአንድ ወር በፊት ትዊተር ላይ ሃሽታጎችን እየተከታተልኩ ያነበብኳቸው የሴራ ትንታኔዎች በጣም ረበሹኝ፤ ተስፋም አስቆረጡኝ” በማለት ማልቀሷንም ጭምር ትናገራለች።

ከዚያ በኋላ ግን የምትመለከታቸውን ዜናዎች በጥንቃቄ መምረጥ መጀመሯን ትገልፃለች። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምታጠፋውን ጊዜም እንደቀነሰች ትናገራለች።

ከልክ በላይ እጅን አለመታጠብ

እጃችሁን በተደጋጋሚ ታጠቡ የሚለውን የጥንቃቄ መልእክትን በተደጋጋሚ መስማት ጭንቀት ላለባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጫና ነው።

እነዚህ ሰዎች ሌሎች በተደጋጋሚ እጃቸውን ሲታጠቡ ወይም በሳኒታይዘር እጃቸውን ሲያፀዱ መመልከትን ከህመም ጋር ያያይዛሉ።

በተላላፊ በሽታ እያዛለሁ የሚል ከፍተኛ ስጋት የበርካታ የአእምሮ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ባህሪይ እንደሆነ የምትናገረውና በዚህ ጉዳይ መፅሃፍ የፃፈችው ሊሊ ቤሊ የእጃችሁን ታጠቡ ተደጋጋሚ መልእክት የእነዚህን ሰዎች ጭንቀት ቀስቃሽ ነው ትላለች።

ሊሊ ቤሊ ራሷ ጭንቀት ህመም ያለባት ሰው ነች።

ለእንዲህ ያለ አጋጣሚ እንዲሁ በተደጋጋሚ እጃችሁን ታጠቡ ማለት ሳይሆን በቀን ይህን ያህል ጊዜ ወይም በዚህ ጊዜ ልዩነት ውስጥ እጃችሁን ብትታጠቡ የቫይረሱን ስርጭት ትገታላችሁ ቢባል መልካም እንደሆነ ታስረዳለች።

ራስን ነጥሎ መቀመጥም እንዲህ ያለ ችግር ላለባቸው ሰዎች ትልቅ ችግር እንደሆነ “ቤት እንድንቀመጥ ከተገደድን ብዙ ለማሰብ ጊዜ አለን ፤ እንደበራለንም” በማለት ትገልፃለች።

ከሰዎች ጋር መገናኘት

ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለሆነ ሰዎች ከአጠገብ ቢርቁ እንኳ በስልክና በኢሜል ለመገናኘት ትክክለኛ የሰዎችን የስልክ ቁጥሮችና ኢሜል አድራሻዎች መያዞን ያረጋግጡ።

በዙሪያዎ ካሉ ሰዎች ጋር ሁሌም ግንኙነት ይኑርዎ። በለይቶ ማቆያ ካሉ ቀን በቀን በመደበኝነት ከሚያደርጓቸው ነገሮች ባሻገር እያንዳንዱ ቀን የተለየ ተግባር እንዲኖረው ያድርጉ።

ይህ ከሆነ በለይቶ ማቆያ የሚኖርዎት ቆይታ ውጤታማና ይሄን ሳደርግ ነበር የቆየሁት የሚሉበት ሊሆን ይችላል። አንዱ መፅሃፍ ማንበብ አንዱ ሊሆን ይችላል።

ድካም መቀነስ

የእረፍት ጊዜ አስፈላጊ ሲሆን የሰው ልጅ አእምሮ እንደ ፀሃይ ብርሃን ያሉ ተፈጥሯዊ ነገሮችን በዘላቂነት ማግኘትን ይመርጣል። ስለዚህም ማረፍ ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ መመገብ እና በቂ ፈሳሽ ማድረግ ወሳኝ ነው።

BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.