የዐድዋ ፡ ዘላለማዊ ፡ ድል ፡ ባተራማሽና ፡ ባጥፊ ፡ ስያስ ፡ አይደብስም  – ኢ.ሀ.ሥ.አ

1 min read
ዜና ፡ መግለጫ
ለንደን ፥ መጋቢት ፡ 16 ፡ ቀን ፡ 2012 ፡ ዓ.ም. ።
በዓለም ፡ ደረጃ ፡ የተስፋፋውን ፡ እጅግ ፡ አደገኛውን ፡ የ”ኮሮኖ ፡ ተላላፊ” ፡ ወረርሽኝ ፡ ለማሸነፍ ፡ የዓለም ፡ መንግሥታትና ፡ አህጉራውያን ፡ ተቋማት ፡ በሞላ፟ቸው ፡ በሚያስደንቅ ፡ መተባበርና ፡ መናበብ ፡ በሚታገሉበት ፡ በዚህ ፡ ሰዓት ፥ በኢትዮጵያ ፡ ላይ ፡ የተንጠለጠለው ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፡ የሀገሪቱን ፡ ህልውና ፡ የሚፈታተን ፡ ባዕድ-መራ፟ሽ ፡ ተልእኮውን ፡ መፈጸሙን ፡ ቀጥሏል ።
ኢትዮጵያ ፥ ቅኝ ፡ ገዢነትን ፡ ድል ፡ ባደረገችበት ፡ በየካቲት ፡ 23 ፡ ቀን ፡ 1888 ፡ ዓ.ም. ፡ የዐድዋ ፡ ጦርነት ፡ 124ኛ ፡ ዓመት ፡ መታሰቢያ ፡ ሰሞን ፥ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ (“የኢትዮጵያ ፡ ፌዴራላዊ ፡ ዴሞክራሲያዊ ፡ ሪፓብሊክ” ) ፡ የ”ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ” ፡ የውንብድና ፡ ይዘት ፥ በሌለው ፡ ሥልጣንና ፡ የራሱን ፡ “ሕገ ፡ መንግሥት” ፡ (አንቀጽ ፡ 5) ፡ በመጣስ ፥ “በጉባኤ ፡ አጽድቄያቸዋለኹ” ፡ ያላቸውን ፡ ኹለት ፡ አጥፊዎች ፡ የስያስ ፡ ሰነዶች ፡ ይፋ ፡ አውጥቷል ። በዚህ ፡ አደራረጉ ፥ ያፈጣጠሩን ፡ ዐይነት ፣ የተልእኮውን ፡ ምንነትና ፡ የላኪውን ፡ ማንነት ፡ ለዓለሙ ፡ ዅሉ ፡ ፍንትው ፡ አድርጎ ፡ ከሥ፟ቷል ።
እንደ ፡ መግቢያ ፡ የቀረበው ፡ የመዠመሪያው ፡ የስያስ ፡ ሰነድ ፥ በትረካው ፡ ፍጹም ፡ ንኅለተኛ ፡ (“ኒኂሊስት” ) ፡ የኾነውን ፡ ያኽል ፥ የኢትዮጵያ ፡ ተማሪዎች ፡ የሀገራቸውን ፡ ታሪክ ፡ በሀገራዊ ፡ ቋንቋቸው ፡ በዐማርኛ ፡ ከመማር ፡ ከልክሎ ፥ በእንግሊዝኛ ፡ እንዲማ፟ሩት ፡ ያስገድዳል ።
ኹለተኛውና ፡ ዋነኛው ፡ የስያስ ፡ ሰነድ ፡ ደግሞ ፥ ላንድ ፡ ሺሕ ፡ ዓመታት ፡ በአንድያ ፡ መንግሥታዊ ፡ ልሳንነት ፡ ያገለገለውን ፡ ዐማርኛ ፡ አካቴውን ፡ በማስወገድ ፥ በምትኩ ፡ 5 ፡ ደባ፟ሎች ፡ የሥራ ፡ ቋንቋዎችን ፡ በ”ደባ፟ዩ ፡ መንግሥት” ፡ ደረጃ ፡ በመመደድ ፥ ርስ ፡ በርሳቸው ፡ ተፎካክረውና ፡ ተራኵተው ፡ የሚጣጣሉበትን ፡ ደበኛ ፡ የቋንቋ ፡ ስያስ ፡ አስተዋውቋል ።
የኹለቱም ፡ ስያሶች ፡ የጋራ ፡ ግብ ፥ ለዘለቄታው ፡ ዐማርኛ ፡ በኢትዮጵያና ፡ በአፍሪቃ ፡ የሚኖረውን ፡ ቦታ ፡ በመንሣትና ፡ ተስፋውን ፡ በመቅጨት ፥ በምትኩ ፥ እንግሊዝኛን ፡ አንድያው ፡ ያካባቢው ፡ የሥራ ፡ ቋንቋ ፡ ለማድረግና ፡ ኢትዮጵያዊ ፡ ሀገራዊነትን ፡ ለመደምሰስ ፡ ያለበ ፡ የ124 ፡ ዓመት ፡ ደባ ፡ ነው ።
ይህ ፡ በ”ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ” ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፡ መሣሪያነት ፡ የሚፈጸም ፡ ፀረ ፡ ኢትዮጵያ ፣ ፀረ ፡ አፍሪቃ ፡ እና ፡ ፀረ ፡ ሥልጣኔ ፡ የምልክዮሽ ፡ (የ”ኢምፔሪያሊዝም” ) ፡ ኀይሎች ፡ ድርጊት ፥ በኢትዮጵያና ፡ በመላ፟ ፡ አፍሪቃ ፡ ላይ ፡ በተለየ ፡ መመጻደቅና ፡ ተንኰል ፡ የተቃጣ ፡ የጥፋት ፡ ድርጊት ፡ ነው ። መላ፟ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ባንድነት ፡ በመቃወም ፡ ያስወግደዋል ፡ ሲል ፡ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ ሙሉ ፡ እምነቱን ፡ ይገልጻል ። በዐድዋ ፡ ድል ፡ ነጻ ፡ ለወጣው ፡ ለመላ፟ው ፡ የአፍሪቃ ፡ የብስ ፡ ሕዝብም ፡ የሐራ ፡ ኢትዮጵያ ፡ ታሪክ ፡ የሐራነቱ ፡ ታሪክ ፥ የ”ዐም ፡ ሐራ” ፡ ልሳን ፡ ዐማርኛም ፡ የነጻነቱ ፡ ልሳን ፡ ስለ ፡ ኾኑ ፥ መቼም ፡ ቢኾን ፡ መላ፟ው ፡ የአፍሪቃ ፡ ሕዝብ ፡ ከኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ጐን ፡ ይቆማል ፡ ሲል ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ያምናል ።
1 ፤ ደባው ።
የተባበሩት ፡ ያሜሪካ ፡ ኹነቶች ፡ (“ዩናይትድ ፡ ስቴይትስ ፡ ኦፍ ፡ አሜሪካ” ) ፥ በእግዝእት ፡ ኢትዮጵያ ፡ የውስጥ ፡ ጕዳይ ፡ ጣልቃ ፡ በመግባት ፥ በግንቦት ፡ ወር ፡ 1983 ፡ ዓ.ም. ፥ “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ” ን ፡ በውንብድና ፡ አገዛዝነት ፡ በኢትዮጵያ ፡ የሥልጣን ፡ ሰገነት ፡ ላይ ፡ አላግባብ ፡ ጕብ ፡ እንዲል ፡ አድርገውታል ። የውንብድና ፡ አገዛዙም ፥ ያን ፡ ጊዜ ፡ በተነገረው ፡ ዕገውጡ ፡ መመሪያ ፡ መሠረት ፥ “ዐዲስ ፡ የቋንቋ ፡ ፖሊሲ” ፡ በሚል ፡ ርእስ ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሳይጠይቅና ፡ ሳይጠ፟የ፟ቅ ፥ ዐማርኛን ፡ ከሀገራዊ ፡ ልሳንነት ፡ አውርዶ ፡ በመንግሥት ፡ የሥራ ፡ ቋንቋነት ፡ መድቦታል ። በዚህም ፡ ድርጊቱ ፥ ላለፉት ፡ 29 ፡ ዓመታት ፡ ዐማርኛን ፡ ተከታትሎ ፡ ከማድከም ፡ ጋራ ፥ ለእንግሊዝኛ ፡ ርምምድ ፡ በሩን ፡ በሰፊው ፡ ከፍቶ ፡ የግብር ፡ ከፋዩን ፡ ሕዝብ ፡ ገንዘብ ፡ ለዚህኛው ፡ ባዕድ ፡ ቋንቋ ፡ መስፋፊያ ፡ ሲያፈሰው ፡ ቈይቷል ።
ከ”ጠቅላይ ፡ ሚኒስትሩ” ፡ አንሥቶ ፡ የማወራኛውን ፡ የለፈፋ ፡ ጊዜ ፡ ባብዛኛው ፡ የተቈጣጠሩት ፡ የይዘቱ ፡ ሹመኛዎችም ፥ “እናገለግላቸዋለን” ፡ የሚሏቸውን ፡ ሀገርና ፡ ሕዝብ ፡ በናቀ ፡ ፍጹም ፡ ዕብሪት ፥ በይፋና ፡ በሥራ ፡ ንግግሮቻቸው ፡ ዅሉ ፥ በዐማርኛ ፡ ውስጥ ፡ እንግሊዝኛን ፡ እየቀላቀሉ ፡ የመናገርን ፡ ነውረኛ ፡ ልማድ ፡ እንዲያስፋፉ ፡ ይዘቱ ፡ በግልጽ ፡ ያበራታቸዋል ።
ዛሬ ፡ ደግሞ ፥ የዐድዋን ፡ ድል ፡ በዓል ፡ 124ኛ ፡ ዓመት ፡ መታሰቢያ ፡ ለክፉ ፡ ምክንያት ፡ ጠልፎ ፥ የምልክዮሽ ፡ የአእምሮ ፡ ምንደኛዎች ፡ ልንላቸው ፡ በምንገደደው ፡ ጥቂት ፡ ምሁራን ፡ ሲሰናዱ ፡ የቈዩትን ፡ የማተራመሻና ፡ የማጥፊያ ፡ ስያሶች ፡ እንሆ ፡ ይዘቱ ፡ ሊፈጽማቸው ፡ ይፋ ፡ አውጥቷቸዋል ።
2 ፤ የደባው ፡ መነሻና ፡ መድረሻ ።
ኢትዮጵያ ፡ በራሷ ፡ ሥልጣኔ ፡ በ”ሥልጡንሕዝብና” ፡ መሠረት ፡ ላይ ፡ የተከወነች ፡ እግዝእት ፡ ሀገር ፡ ናት ። በታሪክ ፡ የተከታተሉ ፡ የምልክዮሽ ፡ ኀይሎች ፡ ዅሉ ፡ ርሷን ፡ ለማንበርከክና ፡ ለመደምሰስ ፡ ቢሞክሩም ፥ የዐድዋ ፡ አንጸባራቂ ፡ ድል ፡ እንዳስታወሰን ፥ በየጊዜው ፡ ድል ፡ እየኾኑ ፡ ተባረዋል ። ዛሬም ፥ የዘመኑ ፡ የምልክዮሽ ፡ ኀይሎች ፥ በኢትዮጵያ ፡ አንጻር ፡ ዐጕል ፡ እልኽ ፡ ውስጥ ፡ ገብተው ፥ ነጻነቷን ፡ ባጐናጸፋት ፡ ሥልጣኔዋ ፡ ላይ ፡ ስለ ፡ ዘመቱ ፥ የሥልጣኔዋ ፡ መስፋፊያ ፡ ጐዳና ፡ የኾነውን ፡ ልሳን ፡ ዐማርኛን ፥ የሥልጣኔዋ ፡ መንኰራኵር ፡ የኾነውን ፡ ኢትዮጵያዊ ፡ ፊደሏንም ፡ ተከታትለው ፡ ያውካሉ ።
ዐማርኛ ፡ በኢትዮጵያ ፡ የሀገራዊነት ፡ ልሳን ፡ የኾነው ፡ ከ3000 ፡ ዓመት ፡ በፊት ፡ ነው ፤ ካ11ኛው ፡ ምእትያ ፡ አንሥቶ ፡ ደግሞ ፡ በግእዝ ፡ ምትክ ፡ የኢትዮጵያ ፡ መንግሥታዊ ፡ ልሳን ፡ ኾኗል ። በዚህ ፡ ረዥም ፡ ዘመን ፥ የተደቀኑበትን ፡ መሰናክሎች ፡ ዅሉ ፡ አንድ ፡ ባንድ ፡ እያለፈ ፡ በችሎታ ፡ ዳብሮ ፥ በተፈጥሮ ፡ በተሰጠው ፡ የመርባት ፡ ጸጋው ፡ የሰበቀለው ፡ ዐማርኛ ፥ ይህን ፡ ሀገራዊ ፡ ሟያውን ፡ በላቂያ ፣ በብቃትና ፡ ባስተማማኝነት ፡ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ውሏል ፥ ወደ ፡ ፊትም ፡ ይውላል ።
እንደዚሁ ፥ በዘመናችን ፥ እንግሊዝኛ ፥ በተመራጭ ፡ አህጉራዊ ፡ ቋንቋነቱ ፥ ለኢትዮጵያ ፡ የውጭ ፡ ግንኝቶች ፡ ኹሉ ፡ ዐያሌ ፡ አገልግሎቶችን ፡ ውሏል ፤ ወደ ፡ ፊትም ፡ ይውላል ።
የ”ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ” ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፥ ከዐማርኛ ፡ ጋራ ፡ ሌሎች ፡ የኢትዮጵያ ፡ የኅብረተሰብ ፡ ቋንቋዎችን ፥ ኦሮምኛን ፣ ትግሪኛን ፣ ሶማልኛን ፣ ዐፈርኛን ፡ (እንደ ፡ አገውኛ ፣ ሲዳምኛ ፣ ጉራግኛ ፣ ወዘተርፈ ፡ ያሉትን ፡ ቋንቋዎች ፡ በመተው) ፡ በ”ደባ፟ዩ ፡ መንግሥት” ፡ የሥራ ፡ ቋንቋነት ፡ ኰልኵሏቸዋል ። ይህን ፡ ሲያደርግ ፥ እነዚህ ፡ የኅብረተሰብ ፡ ቋንቋዎች ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ያንድነቱ ፡ ቋንቋዎችና ፡ ቅርሶች ፡ እንጂ ፥ የከፊል ፡ ሕዝብ ፡ የግል ፡ ንብረቶች ፡ አለመኾናቸውን ፡ ዘንግቶታል ። የኢትዮጵያ ፡ እግዚእ ፡ ሕዝብ ፡ የሀገራውያኑ ፡ አንድነት ፡ ነው ፤ በቋንቋ ፣ በባህል ፡ መበልጸጉም ፡ የቋሚ ፡ ሥርዐቱን ፡ ሥልጡንነትና ፡ ዐቃፊነት ፡ ይመሰክራል ። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ አሜሪካ-ሠራሽ ፡ የአፓርትሀይድ ፡ “ሕገ ፡ መንግሥት” ፡ በሐሰት ፡ እንደሚለው ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ የ”ሕዝቦች” ፡ ጥርቅም ፡ አይደለም ፤ አንድ ፡ ሀገራዊ ፡ ሕዝብ ፡ እንጂ ።
ኢትዮጵያ ፡ በርትዕ ፡ ኹነትነት ፡ ከተቋቋመችበት ፡ ከቀዳማዊ ፡ ምኒልክ ፡ ዘመነ ፡ መንግሥት ፡ ዠምሮ ፡ (982-957 ፡ ቅድመ ፡ ልደተ ፡ ክርስቶስ) ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ በግብር ፡ ስሙ ፡ “ዐም ፡ ሐራ” ፡ ወይም ፡ “ነጻ ፡ ሕዝብ” ፡ ተብሎ ፡ በአንድነቱ ፡ ይጠ፟ራ፟ል ፤ የሀገራዊነት ፡ ልሳኑም ፡ ዐማርኛ ፡ ነው ። ኢትዮጵያዊ ፡ ሀገራዊነት ፡ ራሱ ፡ ኢትዮጵያ ፡ አንድ ፡ ሀገራዊ ፡ ልሳን ፡ እንዲኖራት ፡ በባሕርዩ ፡ ያስገድዳል ። ዐማርኛም ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ በተዋሕዶው ፡ የሠራው ፡ ሀገራዊ ፡ ልሳኑ ፡ በመኾኑ ፥ ሕዝቡ ፡ በፍጹም ፡ አክብሮትና ፡ ፍቅር ፡ ወዶ ፡ ፈቅዶ ፡ ተቀብሎት ፡ ኖሯል ። “ዐማርኛ ፡ ከሀገራዊ ፡ ልሳንነት ፡ ወደመንግሥት ፡ የሥራ ፡ ቋንቋነት ፡ ይውረድልኝ ፤ 84ቱም ፡ የጎሳ/የኅብረተሰብ ፡ ቋንቋዎች ፡ እኩል ፡ የመንግሥት ፡ የሥራ ፡ ቋንቋዎች ፡ ይኹኑልኝ” ፡ የሚል ፡ ጥያቄን ፡ በየትኛውም ፡ ዘመን ፡ ሕዝቡ ፡ ጠይቆ ፡ አያውቅም ። አኹን ፡ በምንገኝበት ፡ ኹኔታ ፥ ጫናው ፡ ከምልክዮሽ ፡ ኀይሎች ፡ የመጣ ፡ የጥቃትና ፡ የጥፋት ፡ ስልት ፡ ነው ፡ ብለን ፡ ልንደመድም ፡ እንገደዳለን ።
ከምልክዮሽ ፡ ጋራ ፥ ምናልባት ፡ ለዚህ ፡ ለባዕዳን ፡ ኀይሎች ፡ የጣልቃ ፡ ገብነት ፡ ድርጊት ፡ ምክንያት ፡ ይኾናል ፡ የምንልበት ፡ አንድ ፡ ከግንዛቤ ፡ ማነስ ፡ የመጣ ፡ ስሕተት ፡ አለ ። እኛ ፡ ኢትዮጵያውያን ፥ ኢትዮጵያን ፡ “ሀገር” ፡ ስንል ፥ ከጎሳ ፡ ማንነት ፡ በላይ ፡ የኾነ ፡ የ”ሥልጡንሕዝብና” ፡ ወይም ፡ የኢትዮጵያዊ ፡ ሥልጣኔ ፡ ርትዐት ፡ የሰበሰባቸው ፡ ሀገራውያን ፥ ባንድነታቸው ፡ ከሰፈሩበት ፡ ብሔር ፡ (ምድር) ፡ ጋራ ፡ በመዋሐድ ፥ የፈጠሩትን ፡ ኹነት ፡ ወይም ፡ መንግሥት ፡ ለማለት ፡ ነው ። ለ”ሀገር” ፡ ምዕራባውያን ፡ “City” ፡ የሚሉት ፡ ቃል ፡ በትርጕም ፡ ይቀርበዋል ። ኢትዮጵያ ፥ በውልደት ፡ ወይም ፡ በነገድ ፡ ላይ ፡ የተመሠረተን ፡ ኹነት ፡ (መንግሥት) ፡ ካለፈችው ፡ 3000 ፡ ዘመን ፡ ኾኗታል ።
የሀገራዊነትን ፡ መብት ፡ ያከበረች ፡ ኢትዮጵያ ፥ በታሪኳ ፥ ከራሷም ፡ ዐልፋ ፡ በዓለም ፡ ለተጠቁ ፡ ዅሉ ፡ መጠጊያ ፡ ኾናለች ። ባ4ኛው ፡ ምእትያ ፥ በዐፄ ፡ አልአሜዳ ፡ ዘመነ ፡ መንግሥት ፡ (470-478 ፡ ዓ.ም.) ፥ በሮማዊ ፡ ምልክዮሽ ፡ ተጠቅተው ፡ የተሰደዱትን ፡ የተዋሕዶ ፡ ክርስትና ፡ ሐዋርያት ፡ ተስዐቱ ፡ ቅዱሳንን ፡ ከሮማ ፣ ከግብጽና ፡ ከሶርያ ፡ ተቀብላ ፥ ከኢትዮጵያውያን ፡ ተዋሕዶ ፡ ወገኖቻቸው ፡ ጋራ ፡ በነጻነት ፡ እንዲያመልኩ ፡ አድርጋቸዋለች ። ዛሬ ፥ የኢትዮጵያ ፡ ኦርቶዶክስ ፡ ተዋሕዶ ፡ ሃይማኖት ፡ ተከታዮች ፡ 79 ፡ ሚልዮን ፡ ደርሰዋል ።
በ7ኛው ፡ ምእትያ ፥ በዐፄ ፡ አድርዓዝ ፡ ዘመነ ፡ መንግሥት ፡ (595-615 ፡ ዓ.ም.) ፥ በመካ፟ ፡ ገዢዎች ፡ የተሳደዱት ፡ የእስልምና ፡ ተከታዮች ፥ ነቢያቸው ፡ ሙሐመ፟ድ ፡ “ወደ ፡ ኢትዮጵያ ፡ ኺዱ ፤ በዚያች ፡ ሀገር ፡ ማንም ፡ አይጨ፟ቈ፟ንም” ፡ ያላቸውን ፡ ሰምተው ፡ ቢሰደዱ ፥ ኢትዮጵያ ፡ ተቀብላና ፡ አስጠግታ ፥ ሃይማኖታቸውን ፡ በሰላምና ፡ በነጻነት ፡ የመከተል ፡ መብታቸውን ፡ አክብራላቸዋለች ። ዛሬ ፥ ካ18 ፡ ሚልዮን ፡ ያላነሱ ፡ ኢትዮጵያውያን ፡ መስልሞች ፡ በኢትዮጵያ ፡ ይገኛሉ ።
የሀገራዊነት ፡ ዕስባት ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብን ፡ መንፈስ ፡ ሠርጾታል ፥ ግዛታዊ ፡ ባህሉንም ፡ ተዋሕዶታል ። ለዚህም ፡ ማስረጃ ፥ በቅኝ ፡ ገዢዎች ፡ ተቈርሳ ፡ የነበረችው ፡ ጥንታዊቷ ፡ የኢትዮጵያ ፡ አካል ፡ ባሕር ፡ ምድር ፡ (“ኤርትራ” ) ፥ በሕዝቧ ፡ ውዴታ ፡ መሠረት ፥ በ1945 ፡ ዓ.ም. ፡ በተባበሩት ፡ መንግሥታት ፡ ውሳኔ ፡ ወደ ፡ እናት ፡ ሀገሯ ፡ ኢትዮጵያ ፡ እንድትመለስ ፡ ሲወሰን ፥ ሕዝቡ ፡ ከጠየቀው ፡ ተዋሕዶ ፡ ውጪ ፥ ለኢትዮጵያዊ ፡ አስተሳሰብ ፡ ፍጹም ፡ ባዕድ ፡ በኾነ ፥ በ”ድበ፟ላ” ፡ (“ፌደሬሽን” ) ፡ መልክ ፡ እንድትገናኝ ፡ ቢወስኑባት ፥ ካሥር ፡ ዓመት ፡ በዃላ ፥ በ1955 ፡ ዓ.ም. ፡ በባይቶ ፡ (በሕዝብ ፡ ምክር ፡ ቤት) ፡ መክራ ፡ ዘክራ ፥ በሙሉ ፡ ድምፅ ፡ በመወሰን ፡ ድበ፟ላውን ፡ ገፍታዋለች ። የኢትዮጵያ ፡ የሕዝብ ፡ ምክር ፡ ቤትም ፡ ውሳኔዋን ፡ በማጽደቅ ፥ በዚያው ፡ ዓመት ፡ 14ኛዋ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ጠቅላይ ፡ ግዛት ፡ (ክፍለ ፡ ሀገር) ፡ ኾና ፡ በዐዋጅ ፡ ተመልሳ ፡ ተዋሕዳለች ። ኢትዮጵያውያን ፥ ሕዝብና፟ቸውን ፡ በሀገራዊነት ፡ አገባብ ፡ እንጂ ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ “ባዕድ-ሠራሽ ፡ የአፓርትሀይድ ፡ ሕገ ፡ መንግሥት” ፡ እንደደነገገው ፥ በውልደቶች ፡ ክፍለት ፡ መልክ ፡ አያዩትም ።
ነገር ፡ ግን ፥ ዛሬም ፡ በዚሁ ፡ በውልደት ፡ ላይ ፡ በተመሠረተ ፡ ኹነት ፡ (መንግሥት) ፡ ደረጃ ፡ ለሚገኙ ፡ የውጭ ፡ መንግሥታት ፥ ይህ ፡ ኢትዮጵያ ፡ ጥንት ፡ ያለፈችው ፡ ደረጃ ፡ የላቀ ፡ ደረጃ ፡ ስለሚመስላቸው ፥ ኢትዮጵያም ፡ የዃልዮሽ ፡ “በውልደት ፡ ክፍለት ፡ ተከፋፍላ ፥ ዳግመኛ ፡ በደባ፟ይ ፡ (በ”ፌደራል”) ፡ መንግሥትነት ፡ አለዚያም ፡ በተዳባይ ፡ (በ”ኮንፌደራል”) ፡ መንግሥትነት ፡ እንዳዲስ ፡ ትዋቀር” ፡ ብለው ፡ በማያገባቸው ፡ ገብተው ፡ ፈቃዳቸውን ፡ በሀገሪቱ ፡ ላይ ፡ በጕልበት ፡ ሊያጸኑባት ፡ ይሞክራሉ ። ከ3000 ፡ ዘመን ፡ በዃላ ፡ በውልደቶች ፡ ድበ፟ላ ፡ ወይም ፡ ተዳብሎ ፡ (“ኮንፌደሬሽን” ) ፡ ኢትዮጵያን ፡ ለማዋቀር ፡ መሞከር ፥ ባንዲት ፡ እግዝእት ፡ ሀገር ፡ የውስጥ ፡ ጕዳይ ፡ ጣልቃ ፡ መግባት ፡ የኾነውን ፡ ያኽል ፥ ፍጹም ፡ አዘብጣጭና ፡ ውድቅ ፡ አደራረግም ፡ ነው ፤ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ እስካኹን ፡ አንዳልተቀበለው ፡ ዅሉ ፥ ወደ ፡ ፊትም ፡ ያስወግደዋል ።
ለ”ፕሮፐጋንዳ” ፡ ዐላማ ፡ በሰፊው ፡ የሚነ፟ዙ፟ትን ፡ አኃዞች ፡ ወደ ፡ ጐን ፡ ትተን ፥ በኢትዮጵያ ፡ ስለቋንቋ ፡ ተናጋሪዎች ፡ አኃዞች ፡ እውኑን ፡ ስንመለከት ፥ ኹኔታው ፡ እንደሚከተለው ፡ ነው፦
•ዐማርኛ ፡ የ110 ፡ ሚልዮን ፡ ኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ልሳን ፡ እንደ ፡ መኾኑ ፡ መጠን ፥ በመላ፟ ፡ ሀገሪቱ ፡ ይነገራል ፤ የሀገሪቱ ፡ ትምህርት ፡ ቤቶች ፡ ተማሪዎችም ፡ ይማሩታል ።
•ከዐማርኛ ፡ ጋራ ፥
‣ኦሮምኛ ፡ ተናጋሪ ፥ 15% ፡ (15.4% ፡ የኬንያን ፡ ተናጋሪዎች ፡ ጨምሮ) ፤
‣ትግሪኛ ፡ ተናጋሪ ፥ 8% ፡ (ባሕር ፡ ምድርን ፡ ጨምሮ) ፤
‣ሶማልኛ ፡ ተናጋሪ ፥ 5% ፡ (17% ፡ የሶማልያን ፣ የኬንያንና ፡ የጂቡቲን ፡ ተናጋሪዎች ፡ ጨምሮ) ፤
‣ዐፈርኛ ፡ ተናጋሪ ፥ 1.7% ፡ (2% ፡ የጂቡቲን ፡ ተናጋሪዎች ፡ ጨምሮ) ።
እነዚህን ፡ አራት ፡ የኅብረተሰብ ፡ ቋንቋዎች ፡ ከዐማርኛ ፡ ጋራ ፡ “ዐምስቱ ፡ የደባ፟ዩ ፡ መንግሥት ፡ የሥራ ፡ ቋንቋዎች ፡ ይኹኑ” ፡ ብሎ ፡ “ውሳኔ” ን ፡ ማሳለፍ ፡ ራሱ ፥ የይዘቱ ፡ “ሕገ ፡ መንግሥት” ፡ ባ5ኛ ፡ አንቀጹ፦”ዐማርኛ ፡ የደባ፟ዩ ፡ መንግሥት ፡ የሥራ ፡ ቋንቋ ፡ ይኾናል” ፡ ሲል ፡ ያጸናውን ፡ መጣስ ፡ ነው ። ከዚህም ፡ የባሰ ፥ ዐማርኛ ፡ የሀገራዊነት ፡ ልሳን ፡ በኾነበት ፡ ሀገር ፥ ይህን ፡ የመሰለው ፡ “ውሳኔ” ፥ የሀገሪቱን ፡ አስተዳደር ፡ ለማወክ ፥ እድገቷን ፡ ለማሰናከል ፥ ሀገሪቱን ፡ ከፋፍሎ ፥ በምትኳ ፡ ለዘለቄታው ፡ የተዳብሎ ፡ ሥርዐትን ፡ በአፍሪቃ ፡ ቀንድ ፡ ለማዋቀር ፥ ብሎም ፡ እንግሊዝኛን ፡ ያካባቢው ፡ አንድያ ፡ የሥራ ፡ ቋንቋ ፡ ለማድረግ ፥ “በከፋፍለኽ ፡ ግዛ” ፡ ስልትም ፡ የምልክዮሽ ፡ ኀይልን ፡ ባካባቢው ፡ ላይ ፡ ለማንፈራጠጥ ፤ ወይም ፡ ባንድ ፡ ቃል ፥ ሀገርን ፡ ለባዕድ ፡ አሳልፎ ፡ ለመስጠት ፡ ካልኾነ ፡ በቀር ፥ ስያሳዊም ፡ ኾነ ፡ ጥርየታዊ ፡ አንዳች ፡ ጥቅም ፡ አይገኝበትም ።
3 ፤ ተቃውሞና ፡ ትግል ።
የ”ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ” ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፥ የሥልጣን ፡ ተገቢነት ፡ የለውምና ፥ በኢትዮጵያ ፡ ዘላቂ ፡ ጥቅም ፡ ላይ ፡ የሚወስነው ፡ አጥፊ ፡ ውሳኔ ፡ ዅሉ ፡ በመሠረቱ ፡ ውድቅና ፡ ፉርሽ ፡ ነው ። ኾኖም ፥ እስካኹን ፡ እንደታየው ፡ ዅሉ ፥ ይዘቱ ፡ እነዚህንም ፡ የጥፋት ፡ ውሳኔዎቹ ፡ በማናለብኝነት ፡ በገቢር ፡ የሚፈጽማቸው ፡ ከኾነ ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፡ ሲወገ፟ድ ፥ ኀላፊዎቹና ፡ ተባባሪዎቻቸው ፡ በሕግ ፡ ፊት ፡ እንደሚጠ፟የ፟ቁ ፡ መታወቅ ፡ አለ፟በ፟ት ።
ዘመኑ ፡ በመላ፟ ፡ ዓለም ፡ ዅሉን ፡ ዐይነት ፡ አደጋ ፡ ያዘበዘበበት ፡ አሥጊ ፡ ዘመን ፡ ኾኗል ። ከ”ዘር ፡ ማጽዳት” ፡ ዘመቻ ፡ እስከለየለት ፡ የሥልጣን ፡ ጦርነት ፡ አደጋ ፥ ከድኽነት ፡ እስከ ፡ ረኃብ ፥ ከሙስና፟ ፡ እስከሰብኣዊ ፡ መብት ፡ ጥሰት ፥ ከሕገ ፡ ወጥ ፡ የሰዎች ፡ ዝውውር ፡ እስከ”ሕዳሴ ፡ ግድብ” ፡ ውዝግብ ፥ ካንበጣ ፡ መንጋ ፡ ወረራ ፡ እስከ”ኮሮና ፡ ተላላፊ” ፡ ወረርሺኝ ፥ ኢትዮጵያን ፡ የገጠሟት ፡ አደጋዎች ፡ ብርቱዎች ፡ ናቸው ፤ የቀረውም ፡ ዓለም ፡ ተዘርዝረው ፡ በማያበቁ ፡ አደጋዎች ፡ ተጠምዷል ። ኀላፊነት ፡ የሚሰ፟ማ፟ው ፡ ወገን ፡ ዅሉ ፡ ለማንኛውም ፡ ችግር ፡ በቅድሚያ ፡ ሰላማዊ ፡ መፍትሔን ፡ በገቢር ፡ መሻትና ፡ ሥርዐትን ፡ ማክበር ፡ ይጠበቅበታል ። ሀገር ፡ ላይ ፡ ያንዣበቡት ፡ እነዚህ ፡ ችግሮች ፡ ዅሉ ፡ በሙሉ ፡ ክሂሎትና ፡ በተገቢ ፡ ሥልጣን ፡ ብቻ ፡ የሚ፟ፈ፟ቱ ፡ ስለ ፡ ኾነ ፥ የ”ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና ፡ ፓርቲ” ፡ የውንብድና ፡ አገዛዝ ፥ ይህኑ ፡ እንዲገነዘብና ፥ ከባዕድ ፡ ኀይል ፡ መሣሪያነቱ ፡ ተላቆ፟ ፥ አላግባብ ፡ ከወጣበት ፡ የሥልጣን ፡ ሰገነት ፡ በሰላም ፡ በመውረድ ፥ ቦታውን ፡ በሥልጡንሕዝባዊ ፡ መንገድ ፡ ለሚ፟ሠ፟የ፟ም ፡ የመሸጋገሪያ ፡ መንግሥት ፡ ለማስረከብ ፡ እንዲዘጋጅ ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ዳግመኛ ፡ ያሳስበዋል ።
የማንዘነጋው ፡ አንድ ፡ መሠረታዊ ፡ እውነት ፡ አለ ። አንድ ፡ የተደራጀ ፡ አካል ፡ መንግሥታዊ ፡ ኀይልን ፡ በእጀ ፡ መናኛ ፡ ሲይዝ ፥ የሥልጣን ፡ ተገቢነት ፡ የለውምና ፥ እሥልጣኑ ፡ ሰገነት ፡ ላይ ፡ ለመቈየት ፡ ሲል ፡ ብቻ ፥ ለውጭ ፡ ኀይሎች ፡ ታዛዥና ፡ መሣሪያ ፡ ሊኾን ፡ ስኡንነቱ ፡ ራሱ ፡ ያሰላዋል ፥ ያስገድደዋልም ። የዛሬ ፡ 124 ፡ ዓመት ፡ ኢትዮጵያ ፡ የዐድዋን ፡ ድል ፡ ተቀዳጅታ ፡ እግዚእናዋንና ፡ ነጻነቷን ፡ ያስከበረችው ፥ ተፈላጊውን ፡ የሥጣን ፡ ተገቢነት ፡ ለ3000 ፡ ዓመት ፡ ባረጋገጠችበት ፡ ግዛታዊ ፡ ሥርዐቷ ፡ ተገቢ ፡ ሥልጣንን ፡ በተሠየሙ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ዳግማዊ ፡ ምኒልክ ፡ ብቁ ፡ መሪነት ፡ ነበር ። የጥንቱንም ፡ የዘመኑንም ፡ የኢትዮጵያ ፡ ታሪክ ፡ መለስ ፡ ብለን ፡ ስንመረምር ፥ አብዛኛውን ፡ ጊዜ ፡ ሀገሪቱ ፡ ለሽንፈት ፡ የተዳረገችው ፡ በውንብድና ፡ አገዛዝ ፡ ሥር ፡ በወደቀችበት ፡ የድክመት ፡ ዘመን ፡ እንደነበር ፡ እንገነዘባለን ። ዛሬም ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ እግዚእናውን ፡ ፈጥኖ ፡ በማስከበር ፥ ባዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥት ፡ ወይም ፡ ክዋኔ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ የርትዕ ፡ ኹነቱን ፡ ካላቆመና ፡ ገዢዎቹን ፡ በሥልጡንሕዝባዊ ፡ ሥርዐት ፡ ካልሠየመ ፡ በቀር ፥ አኹን ፡ ጫፍ ፡ ጫፉን ፡ የምናየው ፡ የምልክዮሽ ፡ ደባ ፡ በማንኛውም ፡ ሰዓት ፥ በተለይ ፡ ደግሞ ፡ ድንገት ፡ በሚፈጸም ፡ የክዳት ፡ አደራረግ ፥ ሀገርን ፡ ወደ ፡ ማፈራረስ ፡ እንደሚሸጋገር ፡ አያጠራጥርም ።
የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ የተደቀነበትን ፡ ጊድር ፡ ለመቋቋም ፥ ሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካሉ ፡ ለኾነው ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ በሠሪ ፡ አባልነቱ ፡ በፍጥነትና ፡ ባገር ፡ ፍቅር ፡ በማበር ፥ ተደራጅቶ ፡ ይነ፟ሣ፟ል፨
የጊዜያዊ ፡ ፈጻሚ ፡ ምክር ፡ ጽሕፈት ፡ ቤት ፥
ኢ.ሀ.ሥ.አ. ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.