የሕዳሴው ግድብ በመጪው ክረምት ውሃ መያዝ ይጀምራል – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

1 min read

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ውሃ መያዝ የሚችልበት የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች በመጪው ክረምት ኃይል ማመንጨት የሚያስችላቸውን ውሃ ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብና ዓለምዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት በአሁን ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለም ብሎም የኢትዮጵያ ስጋት ቢሆንም የግድቡ ግንባታ ለአፍታም አልተቋረጠም።

የግንባታ ሥራው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባወጣው የጥንቃቄ መመሪያ መሰረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት የሚያስችላቸውን ውሃ በመጪው ክረምት ለመያዝ የሚቻልበት የግንባታ ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸው፣ “የግድቡ ኃይል ማመንጫ ዩኒት 9 እና 10 ግንባታ በፍጥነት እየተከናወነ ነው” ብለዋል።

ግድቡ ኃይል እንዲያመነጭ ከታሰበው ጊዜ በላይ ከተራዘመ አገሪቷ በየዓመቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታጣ ከማድረግ ባለፈ ለተጨማሪ የግንባታ ወጪ ትጋለጣለች ያሉት አቶ ሞገስ፤ አላስፈላጊ ወጪን ለማስቀረትም በዕቅዱ መሰረት የውሃ ሙሌት ሥራው ”ከዘንድሮ ክረምት አያልፍም” ብለዋል።

የግድቡ ግንባታው እየተከናወነ ውሃው መያዝ የሚችለውን ያህል መያዝ ካልቻለ ተጨማሪ አንድ ዓመት ሃይል ሳያመነጭ ሊያልፍ ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ክረምት ላይ ውሃ መያዝ ከቻለ ግን ከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ በኋላ ሁለቱ ኃይል ቀድመው የሚያመነጩ ዩኒቶችን በመፈተሽ ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአሁን ጊዜ የግድቡ የብረታ ብረት ሥራ 26 በመቶ ላይ ደርሷል።“ይህ አሀዝ የዛሬ ሁለት ዓመት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም በዓለምአቀፍ ጥራትና ግብዓት እንደ አዲስ እርማት ተደርጎለት ግንባታው እየተከናወነ ነው” ብለዋል።
የደን ምንጣሮን ጨምሮ ለግድቡ ውሃ ሙሌት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የሦስትዮሽ ድርድር ኮሚቴ አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው እ.ኤ.አ በ2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በመሪዎቻቸው አማካኝነት ካርቱም ላይ በተፈራረሙት የመርህ ስምምነት በሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት።

ይሁንና ግብጽ ግድቡ ውሃ መያዝ የሚያስችለው ደረጃ ላይ መድረሱን እርግጠኛ በመሆኗ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር የመርህ ስምምነቱን ለመጣስ ሙከራ በማድረግ ላይ ናት ያሉት ኢንጂነር ጌዲዮን፤ ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያንና ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን መብትና ጥቅም በጣሰ መልኩ የወንዙን ውሃ በብቸኝነት ሲጠቀሙ እንደነበርም አታውሰዋል።

ግድቡ 65 ሜትር ቁመት ላይ ሲደርስ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ለመሙላት ዕቅድ መያዙን ገልጸው ይህም በተያዘው ዕቅድ መሰረት በዘንድሮ የዝናብ ወቅት እንደሚከናወን ተናግረዋል።
”ከግድቡ መሰረት ወደ 65 ሜትር የውሃ ቁመት ከፍ ይላል የሚይዘው ውሃ አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ

ይሆናል።በሁለተኛው ዓመት ላይ ተጨማሪ 13 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ግድቡ ይይዛል። በዚህ ጊዜ የውሃው ቁመት 595 ላይ ወይም ከግድቡ መሰረት 95 ሜትር ከፍ ብሎ ይገኛል ማለት ነው። በዚያን ወቅት ተጨማሪዎቹ 11 አሸንዳዎች ውሃ ማስተላለፍ ይጀምራሉ” ብለዋል ኢንጂነር ጌዲዮን።
እንደ ኢንጂነር ጌድዮን ገለጻ የውሃ ሙሌት ስርዓቱ በየዓመቱ ደረጃ በደረጃ የሚከናወን ይሆናል።

ይህም የግድቡ ተርባይኖች ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨት የሚችሉበት ቁመት ላይ እስኪደርሱ ውሃው ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ይሞላል ብለዋል።

የግድቡን ውሃ ሙሌት በሁለት ዓመት ማከናወን ቢቻልም የግድቡን ደህንነትና የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ደረጃ በደረጃ የመሙላት እቅድ መያዙንም ኢንጅነር ጌድዮን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም በአሁኑ ወቅት 73 በመቶ መድረሱን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ ኢዜአ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.