የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ደጋፊዎች እና ቤተሰቦች (የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ)

1 min read

 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የተሰጠውን አደራ ተቀብሎ ውጥን የልማት ሥራዎቹን ለማስጀመር እና የገጠመንን ያልታሰበ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሀገራችን ላይ ሊያመጣ ከሚችለው ጉዳት ሕዝባችንን ለመታደግ ሙሉ ጊዜውን እና እውቀቱን በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ደፋ ቀና በሚልበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፤ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ትረስት ፈንዱ የሰበሰበውን ገንዘብ አላግባብ ጥቅም ላይ አውሎ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም የተሳሳተ ዘገባ መቅረቡ በእጅጉ አሳዝኖናል።

ውድ ለጋሾቻችን !

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል  ለማድረግ ብክነትን፣ ገንዘብን አለአግባብ መጠቀምንና ስርቆትን ለመከላከል እና ለማመላከት የሚያስችል የአሠራር እና የመቆጣጠርያ ስልት በማበጀት የሚንቀሳቀስ ግልፀኝነት እና ተጠያቂነትን መርሁ ያደረገ ተቋም ነዉ። ለወደፊቱም በዚሁ ዓላማዉ ጸንቶ የሚቆም መሆኑን ለባለድርሻ አካላት እያረጋገጥን እስከዛሬ ድረስ ምንም አይነት ገንዘብ አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ልንገልፅላችሁ እንወዳለን።

በዚህ አጋጣሚ በመገናኛ ብዙኃን ስለተነሱት አንዳንድ ጉዳዮች እውነታዉን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስገንዝብዎ።

  • የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የፋይናንስ አሠረር እና ደንብ ያልተከተለ ምንም አይነት የገንዘብ አያያዝ ግድፈት እንዳላጋጠመው እና ለወደፊቱም እንዲህ ያለ ክፍተት ሊኖር እንደማይችል ያረጋግጣል፡፡ ወጪና ገቢያችንን የሚያሳይ መረጃ በድረ-ገፃችን ለሁሉም ዕይታ ክፍት ሆኖ መቀመጡ የአሠራራችንን ግልፅነት የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው።
  • ለወገን ደራሽ ከሆነው የዳያስፖራ ሕብረተሰብ መካከል በቅድሚያ ከተሰለፉት ከ25 ሺህ በላይ ለጋሾቻችን የተሰበሰው $6.36 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ለመዋጋት ለተላለፈው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ $1.173 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መስፈርት መሰረት የህክምና ዕቃዎች ተገዝተዉ ወደ ሀገር ቤት ተልከዋል። ከዚህ ውጪ ለሌላ ፕሮጀክት ትግበራ ይሁን ለአስተዳደረዊ ጉዳዮች ዳያስፖራ አባሎቻችን ካዋጡት ገንዘብ ውስጥ ምንም ዓይነት የገንዘብ ወጪ አለመደረጉን እናረጋግጣለን።
  • በልማት ሥራዎች ከተሰማሩ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ በትረስት ፈንዱ የምዘና መስፈርት ለገንዘብ ድጋፍ ብቁ የሆኑ አምስት(5) ፕሮጀክቶች በዳይሬክተሮች ቦርድ ፀድቆላቸዉ ከድርጅቶቹ ጋር የመግባባያ ሰነድ ተፈርሟል። አስራ ሰባት (17) ተጨማሪ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት እንዲቻል የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች እና መመዘኛዎች የማሟላት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ ይጠበቃል፡፡
  • ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በሀገር ልጆች ድጋፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የኮቪድ መስፋፋትን ለመቋቋም የሚያስችል  ከ$1.173 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ለወገኖቻችን መድረስ መቻላችን ትንሽ እፎይታ ቢሰጠንም፤ ወረርሽኙ በጤናችን እና በዕለት ተዕለት አኗኗሯችን ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የሚያደርሰው አደጋ ፈታኝ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ለመደገፍ የጀመርነውን ውጥን እዳር ሳናደርስ እረፍት እንደማይኖረን ለሁሉም አባሎቻችን እናረጋግጣለን። ሚያዝያ 26 ቀን 2012 በወጣው ጋዜጣዊ መግለጫችን የተዘረዘሩትን የህክምና የግል መከላከያ መርጃ ዕቃዎች በተመለከተ በድረ-ገፃችን ላይ የሰፈረውን ሪፖርት እንዲያነቡ እንጋብዛለን።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ነሐሴ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. መቋቋሙ ይታወሳል። ይህ ቀን ዳያስፖራው ሀገር ቤት ላሉ ወገኖቹ በወል አለኝታነቱን የገለፀበት እና በረዥሙ ታሪካችን ዉስጥ በፋና ወጊነቱ ሲዘከር የሚኖር ነዉ።  ትረስት ፈንዱ ምንም አይነት ልዩነት ሳያደርግ በመላዉ ዓለም ያሉትን የዳያስፖራ አባላት የአላማዉ አጋር በማድረግ ወገኖቻችንን ለመርዳት ትልቅ ራዕይ የሰነቀ ተቋም ነው።

በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ እና በሀገራችን ውስጥ አስፈላጊ የህክምና መሳሪያዎችን እና እንደየአስፈላጊነት ሌሎች ቁሳቁሶችንም ለማቅረብ የምናደርገው ተጨማሪ መዋጮ ወገናችንን እንደሚደግፍ ሙሉ እምነት አለን።

የተከበራችሁ የባለድርሻ አካላት እና የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሙሉ!

ወገኖቻችንን ለመርዳት ዓለም አቀፋዊ ጥረታችንን ስለተቀላቀሉ ከልብ እያመሰገንን፤ ከሁሉም በላይ ታማኝነት እና ግልፅነት የትረስት ፈንዱ የማይናወጥ ልዩ መገለጫችን እና የመርሀችን ምሰሶ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.