ሁለት የራያ ቆቦ ወረዳ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ህግ በማስከበር ላይ እያሉ ሕይወታቸው አለፈ

1 min read

በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ እና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍን እና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ሞላ ዛሬ ሕይወታቸው ያለፈው ሕግ ለማስከበር ጥረት በማድረግ ላይ በነበሩበት ጊዜ መሆኑን ሰምተናል።

ድርጊቱ የተከሰተው ዛሬ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ከሮቢት ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኝ መንጀሎ በተባለ ቦታ እንደሆነም አብመድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኃላፊዎቹ ለሥራ ከቆዩበት ወልድያ ወደ ቆቦ ከተማ በመመለስ ላይ እያሉ አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍና ለኮሮና ወረርሽኝ በሚያጋልጥ መልኩ ስድስት ሰዎችን አሳፍሮ ሲያጓጉዝ ተመልክተው ሕግ ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር የወረዳው መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስማማው አምባው ተናግረዋል። ባጃጇ ታርጋ እንደሌላትና አሽከርካሪውም ለመቆም ፈቃደኛ እንዳልነበረ መረጃ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ነጋ ድንበሩ ለአብመድ እንደገለጹትም ከሮቢት ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው መንጀሎ ላይ አሽከርካሪው ባጃጇን በማቆም ከአካባቢው ወዳለ ሰርግ ቤት ከተሳፋሪዎች ጋር መቀላቀላቸውን፣ ቀጥሎም የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሕይወት እንዲያልፍ መደረጉን ነው የተናገሩት።

ተሽከርካሪዋ በቁጥጥር ሥረ መዋሏ እና ተጠርጣሪዎችም መታወቃቸው ተገልጿል። በቁጥጥር ሥር ለማዋልም ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

አብመድ ሕይወታቸውን ላጡት የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ለኅብረተሰቡ መጽናናትን ይመኛል።

ዘጋቢ፦ አቢብ ዓለሜ-ከቆቦ/ አብመድ

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.