ሃጫሉ ሁንዴሳ: ከሞቱ አሟሟቱ፣ ካሟሟቱ ቀብሩ፣ ከቀብሩ ሽብሩ – አሁንገና አለማየሁ

1 min read
1

ሃጫሉ ሁንዴሳ እና ማልኮም ኤክስ

መግቢያ

“ከሞቱ አሟሟቱ፣ ካሟሟቱ ቀብሩ፣ ከቀብሩ ሽብሩ”

ከሸገር ቀጥሎ ለአምቦ የተለየ ቅርበትና ፍቅር ይሰማኛል። በልጅነት እድሜ የቦረቅኩባት፣ ሌጣ ፈረስ ግልቢያ የተማርኩባት፣ በወንዝም በመዋኛ ገንዳም ውሃ የተምቦጫረቅኩባት፣ ጥንቸል አባርሬ ለመያዝ መከራዬን ያየሁባት የአምቦ ከተማና አካባቢዋ ትልቅ ትዝታ በውስጤ የተወችብኝ ናት። አዳሜ የልማት ጀግና እየተባለ በዘመነ ወያኔ የሚደረገውን ቀልድ ሳስብና በአምቦ ገና በኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ የምር የልማት አርበኛ የነበረውን መምህር ጋዲሳን ሳስብ የሚያቃጥል ቁጭት ይይዘኛል። የቀለም መምህር ብቻ ሳይሆን የተግባራዊ ኑሮና የልማት አስተማሪ የነበረው መምህር ጋዲሳ በአትክልት ልማት፣ በወተት ሀብት ልማት በእጁ ሠርቶ ገነትን የፈጠረ ሰው ነበር። የሚሠራ ሰው በመንግሥት እገዛ በማያገኝባት ሀገራችን ስንት እንቅፋቶችን እየታገለ ብዙ መልካም አርአያ ያሰቀመጠ ሰው ነበር። በኋላም በአቶ በንቲ ሙለታ አስተዳደር ጊዜ አምቦ ከአብዮቱና ከስልሳ ዘጠኝ ሽብር ተረጋግታ መልካም አስተዳደርና ሰላም የሰፈነባት ሆና ነበር። ካደግሁም ወዲህ ብዙ ጊዜ ቤተሰብ ጥየቃና በአምቦ እርሻ ኮሌጅ የሚያስተምሩ ጓደኞቼን ጥየቃ ተመላልሺያለሁ። ይሁንና አምቦ በኃይለ ሥላሴ ዘመን በጀመረችው የእድገት ጉዞ ፍጥነት አልቀጠለችም። የአምቦ ፍቅሬ ተጨማሪም ምንጭ አለው። በአዲስ አበባም እንደ አባቴ የማያቸው፣ መክረው ዘክረው፣ አብልተው አጠጥተው፣ ከልጆቻቸው ሳይለዩ ያሳደጉኝ ጎረቤቴ የአምቦ ሰው ናቸው።

እኔ እስከማስታውሰው የአምቦ አካባቢ ሕዝብ ንቁና  ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት የነበረው ነው። ዛሬ ከአምቦ ትዝታዬ ጋር የተቆራኙ ብዙ ሰዎች በሕይወት የሉም። የእድሜ እኩዮቼ ያለ ጊዚያቸው ሞተዋል። አቶ በንቲንም ወያኔ በሐሰት በኦነግ ስም ከስሳ ማስረጃ ስታጣ ደግሞ የቀይ ሽብር ተዋናይ ብላ ባልዋሉበት በስተእርጅና እድሜያቸው በእስር ቤት አንዲሞቱ አድርጋለች። ፈረስ ግልቢያ ያስተማረኝ ጋሽ በቀለ በሶማሌ ወረራ ጊዜ ሞቷል። የልጅነት ጓደኞቼ በርካቶቹ ውትድርና እየተቀጠሩ በኤርትራ ለሀገር አንድነትና ድንበር መስዋዕት ሆነዋል።

የሃጫሉን ዘፈኖች ስሰማ ያን ጊዜ የምንውልባቸው የሰንቀሌ፣ የጉደር የጊንጪ አካባቢዎች ሁሉ በዓይነ ኅሊናዬ ይመጣሉ። ከቃላቱም ይበልጥ ዜማው አጥንት ሰርስሮ የሚገባ ነገር አለው።

ሃጫሉ አሜሪካ በመጣበት ጊዜ ቤተሰቤ ሌላ ቦታ ልንሄድ የያዝነውን ትልቅ ቀጠሮ ሰርዘን ነው ከነጃምቦ ጆቴ ጋር በጋራ ባቀረቡት የሙዚቃ ዝግጅት የታደምነው።  በወቅቱ ስለአምቦ እና ስለ ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን ጥቂት ተጨዋውተን ነበር። በዚያ ኮንሰርት ላይ ያየችኝ አንድ ወዳጄ ማክሰኞ ለት ደውላ ሃጫሉ ተገደለ ስትለኝ በድን ነበር የሆንኩት። ያን ለት ስንነጋገር ስላየች የቆየ ትውውቅ ወይም የግል ዝምድና ያለን መስሏት ሊሆን ይችላል።

የሃጫሉ ግድያ እጅግ የተወገዘ ተግባር ነው። የፈሪም ሥራ ነው። ጀግና በፈሪ እጅ ሲሞት ደግሞ ሐዘንን ያከብደዋል።

ከማን ጋር ልወጣው ሐዘኔን ብዬ ሳስብ ዛሬ አንድ የአምቦ አዛውንት ጋር ደወልኩና እቤታቸው ሄድኩ። ምንም ነገር ሳይሉኝ “ከሞቱ አሟሟቱ፣ ከአሟሟቱ ቀብሩ፣ ከቀብሩ ሽብሩ” አሉኝ።

የአስከሬኑ መንገላታትና በአስከሬኑ ላይ ሲካሄድ የነበረው የፖለቲካ ቁማርን ማለታቸው መስሎኝ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ስቀባጥር እንዲህ አሉኝ።

“የትም ይቀበር የትም ይህ ልጅ የአርበኛ ቤተሰብ ነው። ራሱም ጀግና ነው። እንዴት በግብጾች ሴራ ተገድሎ በግብጽ ባንዲራ ተጀምሎ ይቀበራል?”

ቴሌቪዥኑን ዩቲዮብ ላይ ከፍተው አሳዩኝ። አስከሬኑ ላይ ጣል የተደረውን ልብስ ጠቆሙ። የኦሮሚያ ባንዲራ ነው ስላቸው። “አይ የዛሬ ልጆች! ይህንን ነው ማስተዋል የተሳናችሁ። ግብጾች እኮ ቀድመው ሥራቸውን ሰርተውብናል።”

እውነትም ነገ ግብጽ በምትከፍትብን ጦርነት በዚህ ባንዲራ ያደገ ትውልድ በምን ዓይነት ሥነ ልቡና ግብጾችን ለመዋጋት ይችላል?የተመረጠው ሰንደቅ ዓላማ ከግብጽና ከብዙ የአክራሪ እስልምና ሀገሮች ሰንደቅ ዓላማ ጋር ይመሳሰላል ሳይሆን አንድ ነው። የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ጀግኖቻችንም በገዳዮቻቸው ባንዲራ ቀለማት ተጀምለው ሊቀበሩ አይገባም። ፈርጀ ብዙውን የግብጽ ሴራ በድፍረትና በእውቀት መጋፈጥ ያስፈልጋል። በብዙ የሐሰት ድሪቶ እና ማስመሰያ ተረት የተሸፋፈኑ ጉዳዮች አሉ። ገላልጦና መርምሮ ሥር መሠረታቸውን ማወቅ ያሻል።

በሃጫሉ ሞት ተገን የተደረገው የንጹሐን ግድያ፣ የንብረት ውድመት ሃጫሉ የቆመለትን፣ የታገለለትን ዓላማ የሚያዋርድ እና የሚቀለብስ የተወገዘ የሽብር ተግባር ነው። በተሰናከለ የትምህርት ፖሊሲ አድጎ በጥላቻ ተረት ከታወረና በደም ጠማሽ የሲዖል ጭፍራ ልሂቃን ከበሮ ከሚመራ ትውልድ ግን ያልተጠበቀ ድርጊት አይደለም። መንግሥት እየሠራ ያለው የሩዋንዳዊውን  የእልቂት ቀጠሮ የማራዘም እንጂ የማምከን ሥራ ባለመሆኑ እኛ የአባቶቻችን ለነጻነት የተከፈለ መስዋእትነት በሞኝ እና ሆድ አደር ልጆቻቸው ከንቱ የተደረገብን፣ ያልታደልን ሕዝቦች መሆናችንን የሚያሳይ ነው። መንግሥትም ዛሬ በሕዝቦች ላይ እየፈቀደ ያለው የሽብር ድርጊት፣ እያደገ ሄዶ ነገ በራሱ ላይ ከቤተመንግሥት ሬሳው ተጎትቶ መውጣትን የሚያስከትል መሆኑን ሊያስተውል ይገባል።

ሃጫሉ እና ማልኮም ኤክስ

በተለያየ አህጉር የታገሉና ጨቋኛቸውን በተላያየ መሣሪያ የተዋጉ ቢሆኑም ሃጫሉንና ማልኮም ኤክስን እጅግ ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ።

ጨቋኞች ጀግኖችን እስከዘር ማንዘራቸው ለማጥፋት ይፈልጋሉ። የጀግና ልጅ ጀግና ይሆናል ብለው ስለሚፈሩ። ጣልያን የአርበኞችን ቤተሰቦች ጥርግርግ አርጎ ነበር የሚጨፈጭፈው። ሕወሃትም የአርበኞችን ልጆች ከትግራይና ከስሜን በወረንጦ ለቅማ የፈጀችበት ምስጢር ይኸው ነው። ሻዕቢያም በኤርትራ ያደረገው ተመሳሳይ ነው። የመንካዕ የምናምንቴ የሚል ሽፋን የተሰጣቸው ተከታታይ እንቅስቃሴዎች የአርበኛ ልጆችን ለቃቅሞ የማስወገድ ተግባራት ነበሩ።

ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ የሚያሳየው ሐቅ ይሄንኑ ነው። በአሜሪካ በስልሳዎቹ ትግል ውስጥ ተፈጥረው ባለም ታሪክ አንጸባራቂ ሆነው የወጡት ሁለቱም ታጋዮች ማልኮም ኤክስና ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ለእውነት ከቆሙ ደፋርና ግንባር ቀደም ወላጅና አያቶች የተወለዱ ነበሩ።

ሃጫሉ እንደማልኮም ኤክስ ሲታገላቸው በከረሙት ሰዎች የሞቱ ነገር ቢቆረጥም እሱን ለመግደል የተጠቀሙት ግን በእጅ አዙርና በገዛ ወገኖቹ እጅ ነው። ማልኮም ኤክስ በአፍሪካን አሜሪካኖች እንዲገደል እንደተቀነባበረበት።

ሃጫሉም እንደ ማልኮም ኤክስ በወያኔ ሥርዓት ምክንያት ትምህርቱን መማር ያልቻለ፣ የልጅነት ዓመታትን በወያኔ እስር ቤት ያሳለፈ ነበር።

በዚህ ምክንያት ሃጫሉም ራሱን እያስተማረ ተቃውሞውን አሳድጎ ከእስር ሲፈታ ሀገር አቀፍ አድርጎታል። ማልኮም ኤክስም በአባቱ ሞት ምክንያት ትምህርቱን ቢያቋርጥም፣ በእስር ቤት ራሱን አስተምሮ፣ ራሱን ለትግሉ አዘጋጅቶ፣  ለወገኖቹ ነጻነት ሲል ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ትግል መርቷል።

ሃጫሉና ማልኮም ኤክስን ሌላ የሚያመሳስላቸው ድፍረታቸው ነው። ማልኮም ኤክስ ተደጋጋሚ የሞት ዛቻ እየደረሰበት ፈርቶና ተደብቆ የእለት ተእለት ኑሮውን ከመምራት አልተቆጠበም ነበር። ሃጫሉም በተለይ “አራት ኪሎ ግባ፣ ላንተ አይቀርብህም ወይ?” የሚለውን ባደባባይ ካቀነቀነ በኋላ የጥላቻና የበቀል፣ የግድያ ዛቻ እንደሚደርሰው ደጋግሞ ተናግሯል።

ሃጫሉና ማልኮም ኤክስን አደገኛ ያደረጋቸው እና ለግድያ ያሳጫቸው ግን ሌላ ጉዳይ ነው። እነዚህ ሁለት ታጋዮች በየጊዜው ራሳቸውን እያስተማሩ፣ እያደጉና እየተለወጡ የሚሄዱ እንጂ ለዝና እና ለሸፍጥ ብለው ትናንት በሰሙት ብቻ የማያላዝኑ ናቸው። ማልኮም ኤክስ እሳት የሚተፋ ነገር በሚናገርበት ዘመንና ሁሉንም ነጭ ጠላት አድርጎ በሚያቀርብበት ዘመን እንዲገደል አልተፈለገም። እንዲያውም የሚናገረውን በስፋት በማስደመጥ ለመብታችን እንታገላለን የሚሉት ጥቁሮች እንደዚህ ጽንፈኞችና ደንቆሮዎች ናቸው ለማስባያ ተጠቅመውበታል። ማልኮም ኤክስ ግን በትግሉ ሂደት ራሱን እያስተማረ ዘረኝነት የጭቆና ሥርዓት እንጂ የአንድ ሕዝብ ባሕርይ አለመሆኑን ሲረዳ፣ ጭፍን ጥላቻውን ሲተውና፣ አቋሙን እና ንግግሩን እያስተካከለ ከሁሉም ሕዝቦች ውስጥ ለወገኖቹ አጋሮችን ማሰባሰብ የሚያስችል ስልት በሚከተልበት ጊዜ ዘረኞቹ ነጮች አካሄዱ አደገኛ ነው ብለው የግድያ ትእዛዝ አወጡበት። ዛሬ አስከሬን ከቤተሰብ ላይ ሳይቀር በመናጠቅ ለዚሁ ለጌቶቻቸው ትእዛዝ በባንዳነት አገልግሎት ለማበርከት ሲሯሯጡ እንዳየናቸው ጉዶች፣ ያን ጊዜም ማልኮምን ለመግደል ቃታ በመሳብ የጠላቶቻቸው ተላላኪ ሆነው የተገኙት የቀለም ወንድሞቹ ነበሩ። ስለዚህ አጫሉ የተገደለው በመንግሥት ላይ አመጽን ከመቅስቀስ፣ የግድቡን ሂደት ከማጨናጎልም በዘለለ እጅግ የፈሩትን የሃጫሉን እድገትና የብስለት ጉዞ ለመቅጨት በማለማቸው ነው። ትናንት በወያኔ ስንኩል የትምህርት ሥርዓትና ዘረኛ ቅስቀሳ ያደገና ልጅነቱን በእስር ቤት ያሳለፈ ወጣት ይህን ያህል ግዙፍ አስተዋጽኦ ማበርከት ከቻለ፥ የሰላቶን እኩይ የከፋፍለህ ግዛ መርዘኛ እንዲሁም መሰሪ ፕሮፓጋንዳ ይበልጥ እየተረዳ ሄዶ ወደፊት በግፍ እና በድህነት ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሁሉ ድምጽ እየሆነ የመምጣቱ ነገር የኢትዮጵያን ጠላቶች እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ነበር ማለት ነው።

ሃጫሉም ሆነ ማልኮም ኤክስ በጉዞ ላይ የተደናቀፉ መንገደኞች፣ በእድገታቸው የተቀጩ ተክሎች እንጂ የበሰለውን ፍሬያቸውን መስጠት የቻሉ አይደሉም። ከሃጫሉም ሆነ ከማልኮም ኤክስ ንግግሮች የተሟላ እውነት ላይ ገና ያልደረሱ እንደነበር የሚያሳዩ ነገሮች አሉ። ሁለቱም የዘረኞች ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከሆነ እና በጨለማ ከተደፈነበት ትውልድ መምጣታቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል።

በሃጫሉ የግንዛቤ ጉድለቶች የምንደነቅ ሰዎች የትምህርት ዘመኑ በወያኔ አደንቁረህ ግዛ እንደባከነበት፣ የወጣትነት ዘመኑ ደግሞ በኦነጋዊ ስብከት እና ዛሬ  በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ጥላቻና ድንቁርና በሚሰብኩ ሀገር አፍራሽ የምዕራባውያን እና የግብጾችን አጀንዳ አራማጆች ጩኸት ውስጥ ያለፈ መሆኑን ማመዛዘን ይገባናል። ይሁንና እጅግ ብልህና ወገኑን ወዳጅ ስለነበር ነገ የተሟላ ግንዛቤ ላይ ይደርስ እንደነበር አያጠራጥርም። ያንን መቅጨት ነው የተፈለገው። የሱን ጉዞ መቅጨቱ ትውልዱም አፓርታይድን ተሻጋሪ እንዳይሆን በጥላቻ በረዶቤት ተገግሮ እንዲቀር ያግዛልና። ያ ግግር ነው ሀገር ለማፍረሻ የሚፈለገው።

ስለዚህ ሀገራችን ያጣችው የምናውቀውን ሃጫሉን ብቻ ሳይሆን ገና በሙሉ ብስለት ትልቅ ፍሬ ሊያፈራ የሚችል ዛፍ፣ ትልቅ ጮራ ሊፈነጥቅ የሚችል ኮኮብን፣ የነገውንም ሃጫሉን ነው።

በመጨረሻም ሃጫሉም እንደማልኮም ኤክስ የተደረገበት ግድያ የወለዳቸውን ሕጻናት ልጆች ያለ አባት ያስቀረ ነው። የዛሬው የዓለማችን የልጆች እድገት እንኳን ካለ አባት ከአባት ጋርም ሆኖ በቀላል የማይገፋ ከባድ ፈተና የበዛበት ነው።

 

ነፍስ ይማር።

እግዚአብሄር ለቤተሰብና ለወገኖቹ ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን።

የሃጫሉን ግድያ ማባያ በማድረግ በሀገራችን በሽብርና በጭካኔ የተጎዱት፣ ንብረታቸው የወደመባቸውን ወገኖቻችንን እግዚአብሄር መጽናናትን ይስጥልን። የተገደሉትን ነፍስ ይማርልን።

ለፖለቲከኞቻችን እና ለመንግሥት ባለሥልጣናት ልቡና ይስጥልን።

የሩዋንዳዊውን እልቂት ቀጠሮ የሚያራዝሙና ቀን የሚያስተላልፉ ሸንጋዮችን ሳይሆን ያን የጥፋት ሰሌዳ ሰብረው ሰባብረው ገደል የሚጨምሩ የብሩሕ ዘመን አብሳሪ መሪዎችን ይስጠን።

በሥልጣን ጥምም ይሁን በምንዳ ወይም በጥላቻ ስካር፣ የሽብር ከበሮ የሚደልቁትን ያስታግስልን።

ከትውልዱ ላይ የተዘራበትን የጥላቻ አራሙቻ ይንቀልልን።

በፈጣሪያችን፣ በሀገራችን እና በአባቶቻችን ላይ ስለሠራነው ሁሉ ይቅር ይበለን።

ቸሩ እግዚአብሔር ይታረቀን። አሜን።

ሃጫሉ
በበሰለ ቅኔ በሚያምር ዜማ
ይገልጠው ነበረ የቀኑን ጨለማ
ሳይሞት ቢነጋለት ነገን ቢውልማ።
በእንጭጩ ቀጩት ገና በለጋ እድሜ
የሐሰት ግንባቸው እንዳይበላ ድሜ።

ገና እናለቅሳለን
አስለቃሽ በዊስኪ እቅድ እያወጣ ተቀምጦ መቀሌ
ገና እናለቅሳለን ከጋይንት አሳሳ ከወለጋ ቦሌ
ትናንት አቅም እያለ በዋዛ የተውነው ውዝፍ የቤት ሥራ
ገና ያስነባናል እያጨራረሰ በሩዋንዳ ካራ።
የምትምልበት ያ ሕገ መንግሥቱ የሲዖል ብራና
ገና ያስለቅሳል ያልተወለደ ጽንስ እንኳንስ ብላቴና።
ይተርጎም ይፈታ ስትል የከረምከው የዲያብሎስ ሰነድ
የቋያ እሳት ፍሙ/ ሀገር ሳይከስል አይከስም/ በእቶን እሳት ሳይነድ።
የእልቂት ካርታ ነው ሀገር የመበተን በደም ባሕር መንገድ

አሁንገና አለማየሁ

1 Comment

  1. “እንዴት በግብጾች ሴራ ተገድሎ በግብጽ ባንዲራ ተጀምሎ ይቀበራል?” > ግብዝ ድኩማን! ጥቁር፣ ቀይ፣ ነጭ የቀደመው የኩሽ ልጆች፣ የአባጋዳ ባንዲራ ነው! Don’t wash your dirty/ignorance linen in public! በግብጾች ለመገደሉ ምን ማስረጃ አላችሁ፣ የገዳዩን የአቢይን ማዋናበጃ ልበወልድ ከማስተጋባት ዉጪ??

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.