ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ክልሎች፤ እና የምስኪኖች ሰቆቃ – ልጅ ወንድወሰን ተሸመ፤ ኢጆሌ ነጌሌ፤ ከዲሲ

1 min read

ተወልጄ ያደግኩት አርሲ ነጌሌ፤ ነጌሌ አርሲ ነው፡፡ ይሄንን ነገር ለመጻፍና ላለመጻፍ ከራሴም ከሰውም ተሟግቻለሁ፡፡ ባንድ በኩል ነገር ማባባስ መሰለኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሀን ደማቸው ደመከልብ ሲሆን ዝም ማለት ተባባሪነት ወይም ግዴለሽነት ሆነብኝ፡፡ በሁለት አስጨናቂ ጥያቄዎች ተፋጠጥኩ፡፡ የማከብረው ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ፤ “ልጅ ወንድወሰን ይሄንን ባትጽፍ ነው ስህተቱ፡” አለኝ፡፡ ቢያንስ ሳንጨማመር እውነቱን ብንጽፍ ግን የሚመለከታቸው ሁሉ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ይሄ የተጻፈው፤ ለማስተማሪያ ነው፡፡ ለቂም በቀል አይደለም፡፡ ለጊዜው ተበቃይ አላህ/እግዚአብሄር ነው፡፡

ፍጹም ባረገው አብሮ አደጋችን ነው፡፡ ለፍቶ፤ ጥሮ ግሮ ያደገ ልጅ ነው፡፡ ደግ፤ ርህሩህ ነው፡፡ በመጨረሻም ደግነቱ አስገደለው፡፡ ማክሰኞ፤ ሰኔ 23 ቀን፤ የተወለደበት፤ እትብቱ የተቀበረበት ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለ፡፡ የደሜን አስከሬን ለማዳን ብሎ፡፡ ደሜ፤ ጎንደሬ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለአመታት አረቄ ነግዶ ባፈራው ሀብት ነው ቢዝነሱን የገነባው፡፡ አለም ምግብ ቤት፡፡ ቢዝነሱ፤ በአመጸኞች ባንድ ቀን ወደመ፡፡ ንብረቱ ጦሱን ይዞ ቢሄድ ጥሩ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ የሱንም የወንድሙንም ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ቀጠፉት፡፡ በገጀራና በመጥረቢያ ከትክተው፡፡ የደሜን አስከሬን ምድር ለምድር ሲጎትቱ ሲመለከት፤ አብሮአደጋችን ፍጹም ባረገው “ተዉ እንጂ፤ ገደላችሁት ምናለ አሁን አስከሬኑን እንኳን ብትተዉት” ብሎ ጠየቀ፡፡ በመጥረቢያ ጭንቅላቱን ብለው የገደሉት፡፡

ቤተሰብ ከመፍራቱ የተነሳ፤ የልጃቸውን ግድያ በአጥር፤ በቀዳዳ አጮልቆ ከመመልከት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ ወደኋላ ላይ፤ የነጌሌ ጎረቤት ከተሞች፤ አባወራዎች፤ ሚስቶቻቸውንና ልጆቸውን ጥለው ሲሸሹና ከኋላቸው ሲገደሉ እንመለከታለን፡፡ ለወትሮው፤ በጦርነት ሰዓት እንኳን፤ ሴትና ሕጻን አይገደልማ፡፡ የኦሮሞም፤ የአማራም ባህል አይደለማ፡፡ በነጌሌና በዙሪያዋ የሆነው ግን፤ ከባህልም፤ ከሕግም፤ ከሀይማኖትም ያፈነገጠ ነው፡፡ የሩዋንዳ ቅምሻ፡፡

ፍጹም እሱን እንደማይነኩት እርግጠኛ ነበር፡፡ ምክንያቱም የተወለደበት፤ ያደገበት፤ ቤተሰቦቹ የገነቧት ከተማ ነቻ፤ ነጌሌ አርሲ፤ አርሲ ነጌሌ፡፡ ይገድሉኛል አይደለም፤ ይቆጡኛል ብሎ አላሰበም፡፡ እነሱ ግን፤ ስልጣኔ ያልጎበኛቸው አረመኔዎች ናቸው፡፡ ገዳዮቹን ማለቴ ነው፡፡ አይን የላቸውም፡፡ ከመካከላቸው አንዱ እጅ አያሳርፍ፡፡ ካሳረፈ፤ አበቃ፡፡ ሌሎቹ ሳያገናዝቡ፤ ሳይጠይቁ ይሰፍሩበታል፡፡ ይሄን የፈጸሙት፤ ከተማው ውስጥ ታይተው የማታወቁ ባእዶች ናቸው፡፡ ይሄን ኦሮሞ አይፈጽምም፡፡ እነዚህ ኦሮሞዎች አይደሉም፡፡ በምግባራቸው፤ በፈቃዳቸው ከኦሮሞነት ተገንጥለው ወጥተዋል፡፡ ስለዚህ ፍጹምን ገደሉት፡፡ መግደልም ብቻ አይደለም፤ እንደሰማሁት ከሆነ አስከሬኑን በገመድ ጎተቱት፤ ስልክ እንጨት ላይም ሊያንጠለጥሉት ታገሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የተከሰተው ነጌሌ አርሲ ነው፡፡ የቀድሞው ምስራቅ ሸዋ ዞን፤ ምእራብ አርሲ ተብሏል አሁን፡፡

አስጨናቂ፤ ከሰውነት ጎዳና ወጥቶ፤ አተላ አገላብጦ ከብት ቀልቦ፤ እንደምንም ተሟሙቶ ቢዝነስ ከፈተ፡፡ ድርጅቱን እንዳለ አቃጠሉበት፡፡ አባቱንም ከአመታት በፊት በዚህ ሁኔታ እንደገደሉበት ሰምቻለሁ፡፡ እነሆ ነገሌ፤ ረቡእ ሰኔ 25 በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ 4 ሰዎች ቀበረች፡፡ ከተማው አዘነ፡፡ እንደራሄል እንባውን ረጨ፡፡ መጽናናትን ግን አላገኘም፡፡ የሚያጽናናው መንግስት፤ የሚተማመንብት ሕግ የለም፡፡ የክልሉም፤ የፌደራሉም ሕገ-መንግስቶች እንደጉድ ተጣሱ፡፡ መጽሀፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርአን ተጣሰ፡፡ የሰማዩም የምድሩም ሕግ ከተጣሰ፤ ሰው በምን ይጽናናል?

ንብረታቸው የተቃጠለው የትየለሌ ናቸው፡፡ ይሄ በነጌሌ ብቻ የተከሰተው ነው፡፡ በጎረቤት ከተሞች የተከሰተው ግድያ እጥፍ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ አብሮአደጌ የነገረኝ ታሪክ እንዲህ ነው፡፡ የነጌለሌው መንግስቱ ቀጸላ፤ ኢትዮጵያን ከ30 ያገለገሉ ቆፍጣና ወታደር ነበሩ፡፡ ትንሽዋ ልጃቸው ጸሀይ መንግሰቱ ከባሏና ከሁለት ልጆቿ ጋር አዳሚቱሉ ላይ የግብርና ቢዝነስ ከፍታ፣ መኖሪያቸውን ደግሞ ዘዋይ አድርገው ይኖሩ ነበር፡፡ እሷንም፤ ባሏንም፤ ልጆቿንም፣ የዘመድ ልጅም ገደሏቸው፡፡ አረዷቸው፡፡ ሊትራሊ፤ አረዷቸው፡፡ የ31 አመተቱ ሳሙኤል፣ የ28 አመቷ ነፃነት ታረዱ። በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኘው የአጎት ልጃቸው፤ ዋሲሁን ታረደ።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.