ጥቂት ነጥቦች ስለ ታይሮይድ ዕጢ

1 min read


ታይሮይድ ዕጢ፣ አንገታችን ላይ ከማንቁርት በታች የሚገኝ የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ትንሽ ዕጢ ነው፡፡ ታይሮይድ ዕጢ (የእንቅርት በሽታ) በአየር ቧንቧችን ዙሪያ የሚገኙ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ጠቅላላ ክብደቱ ሩብ ግራም ገደማ ይሆናል፡፡ ታይሮይድ ዕጢ በሰውነት ውስጥ ከሚገኙት ኢንዶክሪን ተብለው የሚጠሩ አካል ብልቶችና ህብረ ህዋሳት አንዱ ነው፡፡ እነዚህ የአካል ብልቶችና ህበረ ህዋሳት ሆርሞኖችን ማለትም ኬሚካላዊ መልዕክተኞችን ይሰራሉ፣ ያከማቻሉ እንዲሁም ሆርሞኖቹ በቀጥታ ወደ ደም ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡
ታይሮይድ ዕጢ የተገነባው የታይሮይድ ሆርሞኖችን በያዘ ዝልግልግ ፈሳሽ በተሞሉ በርካታ ጥቃቅን ከረጢቶች ነው፡፡ በሆርሞኖቹ ውስጥ ከፍተኛ የአይኦዲን ክምችት ይገኛል፡፡ እንዲያውም በሰውነታችን ውስጥ ካለው አዮዲን ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በታይሮይድ ዕጢ ውስጥ ነው፡፡ አዮዲን ያለበት ምግብ ዕጥረት የታይሮይድ ዕጢ ማበጥ ወይም እንቅርት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የአዮዲን እንዳያመነጭ እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል አካላዊ፣ አዕምሮአዊና ጾታዊ ዕድገታቸው እንዲጓተት ያደርጋል፤ ይህ አይነቱ የጤና እክል ክሪትኒዝም ይባላል፡፡
ከተገቢው መጠን ያነሰ ሆርሞን የሚያመነጭ ታይሮይድ ዕጢ እርግዝናን የሚያወሳስብ ቢሆንም፣ የታይሮይድ ዕጢ ህመም ያለባቸው አብዛኞቹ ሴቶች ጤነኛ ልጅ ይወልዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ እናቲቱ የሆርሞን መተኪያ ህክምና ማግኘቷ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ጽንሱ መጀመሪያ ላይ የታይሮይድ ሆርሞን ማግኘት የሚችለው ከእናቱ ብቻ ነው፡፡
ታይሮይድ ዕጢን የሚከታተል አካል
ታይሮይድ ዕጢን የሚቆጣጠረው ሀይፓታላመስ ተብሎ የሚጠራው የአንጎል ክፍል ነው፡፡ ሀይፓታላመስ፣ በሰውነት ውስጥ የታይሮይድ ሆርሞን እንደሚያስፈልግ መልዕክት ሲደርሰው ከላይኛው ላንቃ በላይ በአንጎል ታችኛው ክፍል ላይ ለሚገኘው ፒቲዩታሪ ዕጢ ምልክት ይሰጣል፡፡
ፒቲዩታሪ ዕጢ በምላሹ የታይሮይድ ሆርሞኖች እንዲመረቱ የሚቀሰቅስ ሆርሞን ወደ ደም ውስጥ ይለቃል፤ ይህ ሆርሞን ደግሞ የታይሮይድ ሆርሞኖችን እንዲያመርት ታይሮይድ ዕጢን ያነሳሳዋል፡፡
ሐኪሞች የታይሮይድ ሆርሞኖች እንዲመረቱ የሚቀሰቅሰውን ሆርሞን መጠንና የታይሮይድ ሆርሞኖችን መጠን ከደም ውስጥ በመለካት ታይሮይድ ዕጢያችን በተገቢው መንገድ መስራት አለመስራቱንና ጤናማ መሆኑን ለይተው ማወቅ ይችላሉ፡፡ ታይሮይድ ዕጢያችን እክል ሊያጋጥመው ስለሚችል ይህ አይነቱ ምርመራ አስፈላጊ ነው፡፡
ታይሮይድ ዕጢ በተገቢው መንገድ እንዳይሰራ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል የአዮዲን እጥረት፣ አካላዊ ወይም አዕምሮአዊ ውጥረት፣ በዘር የሚወረስ ጉድለት፣ በባክቴሪያ የሚመጡ ህመሞችን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎች (አብዛኛውን ጊዜ በሽታ ተከላካይ ህዋሳት ሌሎች ህዋሳትን እንዲያጠቁ የሚያደርጉ የጤና ቀውሶች) ወይም የተለያዩ ህመሞች ከሚታዘዙ መድኃኒቶች ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጎንዮሽ ጉዳይ ይገኙበታል፡፡ የታይሮይድ ዕጢ ማበጥ ወይም እንቅርት የበሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ታይሮይድ ዕጢው ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰነው ክፍል ብቻ ሊያብጥ ይችላል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ እንቅርት ጉዳት የሚያስከትል ባይሆንም እንደ ካንሰር ያለ ከባድ የጤና ችግር መኖሩን የሚያመላክትም ሊሆን ስለሚችል ምን ጊዜም ቢሆን የህክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የታመሙ የታይሮይድ ዕጢዎች፣ ከመጠን በላይ አሊያም በጣም ትንሽ ሆርሞን ያመነጫሉ፡፡ የታይሮይድ ሆርሞኖች ከመጠን በላይ መመንጨት ሃይፐር ታይሮዲዝም ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በጣም ትንሽ የታይሮይድ ሆርሞኖች መመንጨት ደግሞ ሀይፖታይሮይድ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በጣም ትንሽ የታይሮይድ ሆርሞኖች መመንጨት ደግሞ ሀይፖርታይሮይዲዝም ይባላል፡፡ የታይሮይድ በሽታ ቀስ በቀስና ሳይታወቅ እየተባባሰ ሊሄድ ስለሚችል አንድ ሰው በሽታው ኖሮበትም ለዓመታት ላያውቀው ይችላል፡፡ እንደ አብዛኞቹ ህመሞች ሁሉ በሽታው መኖሩ ቀደም ብሎ ከታወቀ የተሻለ የመዳን አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡
በጣም የተለመዱት የታይሮይድ ህመም አይነቶች ሐሺሞቶስ ታየሮይዳይተስ እና ግሬቭስ የሚባሉት በሽታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ህመሞች የሚከሰቱት በሰውነት ውስጥ የሚገኙት በሽታ ተከላካይ ህዋሳት ሌሎች ሴሎችን እንደ ባዕድ በመቁጠር በሚያጠቋቸው ጊዜ ነው፡፡ ሴቶች ሐሺሞቶች ታይሮይዳይተስ በተባለው በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከወንዶች በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜም ይህ ህመም ሀይፖታይሮይዲዝም ያስከትላል፡፡ ሴቶች ግሬቭስ በተባለው በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከወንዶች በስምንት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ይህ ህመም ሀይፐርታይሮይዲዝም ያከስትላል፡፡
መፍትሄውስ
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የታይሮይድ ችግርን ለመከላከል ሊረዳ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ የታይሮይድ ሆርሞኖች እንዲመነጩ ለማድረግ የሚያስፈልገውን አዮዲን በምንመገበው ምግብ ውስጥ በበቂ መጠን ይገኛል? ጨዋማ በሆነ ውሃ ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎችና ከባህር በሚገኙ ሌሎች ምግቦች ውስጥ ይህ አስፈላጊ ማዕድን ይገኛል፡፡ በአትክልቶችና በሥጋ ውስጥ የሚገኘው አዮዲን መጠን እንደየአካባቢው የአፈር አይነት ይለያያል፡፡ አንዳንድ መንግሥታት፣ ከምግብ ውስጥ ሊጎድል የሚችለውን ይህን ማዕድን ለማካካስ ጨው አምራቾች በጨው ውስጥ አዮዲን እንዲጨምሩ የሚያዝ ህግ አውጥተዋል፡፡
ለታይሮይድ ዕጢ አስፈላጊ የሆነው ሌላው ነገር ሲሊኒየም ነው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ እጅግ አነስተኛ በሆነ መጠን የሚገኘው ይህ ንጥረ ነገር T4ን ወደ T3 ለመለወጥ የሚረዳው ኢንዛይም ክፍል ነው፡፡ በአትክልቶች፣ በሥጋዎችና በወተት ውስጥ የሚገኘው የሲሊኒየም መጠንም ቢሆን በአካባቢው የአፈር አይነት ላይ የተመካ ነው፡፡ ከባህር የሚገኝ ምግብ፣ እንቁላል፣ ጎመንና ቲማቲም ሲሊኒየም በብዛት ከሚገኝባቸው ምግቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በእርግጥ የታይሮይድ ችግር እንዳለብህ ከተጠራጠርክ ሐኪም አማክር እንጂ ራስህን ለማከም አትሞክር፡፡