//

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 19 ሺህ ሰው በኤች አይ ቪ እንደሚሞት ተገለጸ

1 min read

(ቢቢኤን) በኢትዮጵያ በየዓመቱ 19 ሺህ ሰዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ እንደሚሞቱ ተገለጸ፡፡ 27 ሺህ ሰው ደግሞ በየዓመቱ በበሽታው እንደሚያዝ ተነግሯል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኤች አይ ቪ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ከሰኞ ጀምሮ በአዳማ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው፣ በሽታው በአሁን ሰዓት አደገኛ ወረርሺኝ ላይ ደርሷል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በሽታው ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት ያደረሰውን ዓይነት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ1990 አጋማሽ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአስደንጋጭ ሁኔታ አልቀዋል፡፡ በወቅቱ በየዓመቱ እስከ መቶ ሺህ የሚጠጋ ሰው በቫይረሱ ይረግፍ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከ1995 እስከ 1998 ድረስ በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ወደኋለ ላይ ግን በበሽታው የሚያዙ ሰዎች መጠን ቀንሶ ተስተውሎ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ድጋሚ በማገርሸት በተለይ በአዲስ አበባ ያለው የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ወይም ወረርሺኝ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሶ ብዙዎችን እያጠቃ ይገኛል፡፡

በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው የቫይረሱ ስርጭት፣ የዓለም የጤና ድርጅት አንድ በሽታ ወረርሺን ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያረጋግጥበት ልኬት ላይ ደርሷል፡፡ በሽታው በድጋሚ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊስፋፋ የቻለው በምን ምክንያት እንደሆነ የተለያዩ መላ ምቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የአዳዲስ ከተሞች መስፋፋት፣ የውጭ ተቋማት በሽታውን ለመከላከል ለኢትዮጵያ ይሰጡት የነበረውን የገንዘብ እርዳታ ማቋረጥ፣ ከውጭ በሚገቡ ቱሪስቶች እና በመሰል ምክንያቶች በሽታው ዳግም እንደ አዲስ ተቀስቅሷል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታዎች በሚካሔዱባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎችም በሽታው በሰፊው እየተሰራጨ እንደሚገኝ ከዚህ በፊትም አሁንም ተነግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢም በሽታው እንደ አዲስ እየተቀሰቀሰ ሲሆን፣ በሽታው በአሁን ሰዓት በብዛት እየተዛመተ የሚገኘው በወጣቱ ክፍል ላይ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.