ኢትዮጵያ በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት በሩዋንዳ ተሸነፈች

Filed under: News Feature,ስፖርት |

ሃትሪክ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው

በወርሀ ታህሳስ ሞሮኮ በምታስተናግደው የ2018 ቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዳግመኛ እድል ያገኙት ዋልያዎቹ በሜዳቸው የ3-2 ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ዋልያዎቹ በ 4-1-4-1 አሰላለፋ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተለይም በመሀል ክፍል የመስዑድ መሀመድ እና የሳምሶን ጥላሁን ጥምረት የተሳካ ነበር፡፡ በአንጻሩ ተጋጣሚያቸው ሩዋንዳ ቡድን ኳስን ተረጋግቶ በመጫወትን እና ያገኛቸውን የጎል እድሎች በመጠቀሙ ረገድ የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡

በ18ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ በግራ አማካይ ክፍል ለሚገኘው አስቻለው ግርማ ያሻገረለትን ኳስ የሩዋንዳ ግብ ጠባቂን በማለፍ የመጀመሪያ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከጎሉ መቆጠር አንድ ደቂቃ በኀላ ሳምሶን ጥላሁን የሞከራት ኳስ የጎሉን አግደሚ ታኮ ሊወጣ ችሏል፡፡ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በኢትዮጵያ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን የአቻነቷን ጎል ለማስቆጠር 10ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገዷል፤ አበባው ቡታቆ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን ቅጣት ምት ሩታንጋ ኤሪክ ወደ ጎልነት በመቀየር አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኃላ ዋልያዎቹ ተጭነው በመጫወት ጎል ለማግኘት ጥረት ሲያደረጉ በ68ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ በመግጨት ዋልያዎቹ ዳግመኛ የሚመሩበትን እድል ፈጥሯል፡፡

ዋልያዎቹ መሪነታቸውን ከያዙ በሀላ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ለአለም ብርሀኑ በሰራው ስህተት የተገኘችውን የጎል አጋጣሚ ሃኪዚማኒ ሙሃዲሪ በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል፡፡

የጎልዋን መቆጠር ተከትሎ የስሜት መቀዛቀዝ ውስጥ የገቡት ዋልያዎቹ ሶስተኛውን ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል :: ጨዋታውም 3-2 በሆነ ውጤት በሩዋንዳ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኀላ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን የሰጡት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በተከታታይ ለደረሰብን ሽንፈት ህዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ ብለዋል። አስቻለው ታመነን ለምን የቀኝ ተከላካይ አድርገው እንዳጫወቱት የተጠየቁት አሰልጣኙ አማራጭ ስላልነበረን ተቸግረን ነው ብለዋል። ሄኖክ አዱኛን እንደ አማራጭ መጠቀም አይቻልም ነበር ወይ ተብለው ሲጠየቁ ፓስፖርት አልወጣለትም ከአርብ ጀምሮ ስንጠብቅ ነበር በማለት መልሰዋል።

የመልሱ ጨዋታ ከ1 ሳምንት በኀላ ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ የሚደረግ ሲሆን በድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆነው ብሔራዊ ቡድን የሞሮኮ ቲኬቱን መቁረጡን ያረጋግጣል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.