Health: በኢትዮጵያ ያሉ የጥርስ ክሊኒኮች ከመንቀል የዘለለ አገልግሎት ባለመስጠታቸው ህዝቡ ለጥርስ ህመም ስቃይ እየተዳረገ ነው

1 min read

እፀገነት አክሊሉ

 

ሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ወጣት ሰለሞን አሰፋ ጥርሱን መታመም ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ህመሙ እንዳይነሳበት በሚል ጠንካራ ምግቦች ከመመገብ ተቆጥቧል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ መነሻው ምን እንደሆነ በማያውቀው ምክንያት በጣም ይታመማል። «የጥርስ ህመም እጅግ ከባድ ነው» የሚለው ወጣት ሰለሞን፣ የተቦረቦሩት የመንጋጋ ጥርሶቹን ማስነቀል ፈርቶ ለብዙ ጊዜ በባህላዊና ዘመናዊ ህመም ማስታገሻዎች ሲጠቀም መቆየቱን ይናገራል። ሀኪሞች የተቦረቦረው ጥርሱ እንደሚሞላ ቢነግሩትም አገልግሎቱን ለማግኘት ግን ከፍተኛ ክፍያ ተጠይቋል።

የጥርስ ህክምና የሚሰጡ የመንግሥት የጤና ተቋማት እንዳሉ ቢያውቅም፣ ከመንቀል የዘለለ አገልግሎት ባለመስጠታቸው እና የግል የጤና ተቋማት የሚጠይቁትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻሉ የተነሳም ለዓመታት በጥርስ ህመም እየተሰቃየ መሆኑን ይጠቁማል።

እንደ ወጣት ሰለሞን ገለጻ፣ ህመሙ እጅግ ስለባሰበትና መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የመጨረሻ አማራጩ ወደ አንድ የመንግሥት የህከምና ተቋም ሄዶ ማስነቀል ነበር፡፡ ይህንን በማድረጉም መፍትሔ ሊያገኝ ችሏል።

የፊት ጥርሶቹ የወለቁበት ሌላው ወጣት ሳሙኤል አርሃም በበኩሉ ለውበትም ለንግግርም በሚል ለማስተከል ቢፈልገም የሚጠየቀው ዋጋ ግን ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል፡፡ ጥርስ ማስተከል እየፈለገ ከዓመታት በፊት አንስቶ ሳያስተክል እስከ አሁንም መቆየቱን ይናገራል።

ወጣቱ እንደሚለው፤ ሁለት የግል የህክምና ተቋማት የተለያዩ አማራጭ የጥርስ ዓይነቶችን እንዲሁም የአተካከል ሁኔታዎችን አቅርበውለት ከ4 እስከ 5 ሺ ብር መክፈል እንዳለበት ጠይቀውታል። ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ ግን አሁንም ከችግሩ ጋር አብሮ ለመኖር ተገዷል፡፡

አገልግሎቱ በመንግሥት ተቋማት ያለመሰጠቱ ብዙዎች በከፍተኛ ህመም እንዲሰቃዩ እና መነቀል የሌለባቸውን ጥርሶች ለማስነቀል ጭምር እንዲገደዱ እያደረገ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ሳሙኤል፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የጥርስ ሕክምና ክፍሎቸ ተጠናክረው ከመንቀል በዘለለ መትከልን ማጠበን እንዲሁም ጥርስ ሳይጎዳ እንዴት መያዝ አለበት የሚለውን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማስተማር እንዳለባቸውም ያስገነዝባል።

ዶክተር ፍሰሃ የማነ የጥርስ ሀኪም ናቸው፡፡ በአገሪቱ ቀድሞ የጥርስ ህክምና አልነበረም ማለት ይቻላል የሚሉት ሀኪሙ፤ በመንግሥት ህክምና ተቋማት ላይም የመጀመሪያ የህክምና እርዳታን ከመስጠት የዘለለ አገልግሎትም እንዳልነበር ይናገራሉ፡፡ እንደ ዶክተር ፍስሃ ማብራሪያ፤ ከአስር ዓመት ወዲህ ትልልቅ የግል የጥርስ ክሊኒኮች ዘርፉን በመቀላቀላቸው በአሁኑ ወቅት ማንኛውም ዓይነት የጥርስ ችግር በቀላሉ እልባት ማግኘት ከመቻሉም በላይ በአውሮፓና ሌሎች አገሮች የሚሰጡ የህክምና ዓይነቶችን ሁሉ መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

በእነዚህ ክሊኒኮች ውስጥም ከትንሹ የማማከር አገልግሎት ጀምሮ እስከ ሊስተካከሉ የማይችሉትን የመንቀል፣ በከፊል ለተበላሸ ጥርስ የሙሌት ስራ በመስራት ቋሚ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ የማድረግ፣ በጽዳት ጉድለት ምክንያት የተበላሹ ጥርሶችን የማጠብ፣ በአበቃቀል ምክንያት የተበላሹ ጥርሶችን የማሰር (ብሬስ) የመስራት፣ በባክቴሪያ ተጎድተው አልያም በአደጋ የተነቀሉ ጥርሶች ሲኖሩም በተነቀሉበት ቦታ በሰው ሰራሽ መንገድ የመተካት ሥራም እንደሚከናወን ያብራራሉ።

ከ90 እና 100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለበት አገር ያሉት የጥርስ ሀኪሞች ቁጥር ውስን ነው። አገልግሎቶቹን ለመስጠት በሥራ ላይ የሚውሉት ማሽኖችም ውድ መሆናቸው እንዲሁም ብዙዎቹ ክሊኒኮች በቤት ኪራይ ላይ መሆናቸው፣ አላቂ የሚባሉት መጠቀሚያዎችም ውድ መሆን የአገልግሎት ክፍያው ትንሽ ወደድ እንዲል ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም ቢሆን ግን የእኛ አገር የጥርስ ህክምና ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ተመጣጣኝ ነው ይላሉ።

‹‹አሁን ያለው ዋጋ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ተፈታትኗል ከተባለ በተለይም በመንግሥት በኩል ለህክምናው የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ከታክስ ነፃ ሆነው የሚገቡበት አማራጭ ቢመቻች በዚህም ራሳቸው ሀኪሞቹ እንዲያስገቡ ቢደረግ፣ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በብዛት ማሰልጠን ችግሩን ሊፈታው ይችላል›› የሚሉት ዶክተር ፍስሃ፣ ከሁሉም በላይ ግን ኅብረተሰቡ የጥርሱን ጤና እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ማስተማሩ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለክታሉ።

በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የጥርስ ሀኪምና የህክምና ክፍሉ ኃላፊ ዶክተር ሀያት መሀመድ እንደሚሉት፤ ከፍተኛ ጥንቃቄንና ጽዳትን ከሚፈልጉ የሰውነት አካል ከፍሎች መካከል ጥርስ ግንባር ቀደሙ ነው ። በንጽህና ጉድለት እንዲሁም የውስጥ አካል በህመም ከመያዝ ጋር በተያያዘም ጥርስ ሊበላሽ ይችላል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉም በግል የህከምና ተቋማት በከፍተኛ ክፍያ የሚሰሩ ጥርስ መንቀል፣ መሙላት የጥርስ ስር ህክምና የተሰበረ ጥርስ መትከል የወለቁ አጥንቶችን መተካት አፍ ውስጥ የሚወጡ እብጠቶችንና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን እንደሚያክም ጠቅሰው፣ ጥርስ ማሰር (ብሬስ) እና የወለቀ ጥርስ መትከልን ግን እንዳልጀመረ ይናገራሉ።

ሆስፒታሉ በቀን በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎችን ያለምንም ሪፈራል ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ የሚናገሩት ዶክተር ሀያት፣ በተለይም ወደ ግል ህክምና ተቋማት ሄደው አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ መሆኑን ይናገራሉ።

በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ በተለይም ለህከምናው የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ቶሎ የሚበላሹና ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ግዢዎች ስለሚዘገዩም በሥራው ላይ እንቅፋቶች እንደሚያጋጥሙም ዶክተር ሀያት ይጠቁማሉ።

እንደ ዶክተር ሀያት ገለጻ፤ ሆስፒታሉ ከህክምና ባሻገር በሳምንት ሦስት ቀናት ሰኞ ረቡዕና አርብ ስለ ጥርስ ንጽህና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ይህንን የትምህርት ፕሮግራም በአቅራቢያው ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመሄድም ይሰጣል። ማንኛወም ሰው በቀን ሁለት ጊዜ ማለትም ጠዋት ከመኝታ ሲነሳና ማታ ከመተኛቱ በፊት በተገቢው ሁኔታ ከጸዳ ጥርሱን ከጉዳት መካለከል ይቻላል ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ሕክምና እና ማሰልጠኛ ክፍል ሃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን ፋንታዬ በአገራዊ የጥርስ ሕክምና ተደራሽነት ላይ የተደረገ ጥናት አለመኖሩን ጠቅሰው «በየአካባቢው የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች የጥርስ በሽታ በከፍተኛ መጠን መጨመሩንና ህጻናትም ጭምር እየተጠቁ እንደሚገኙ ያመላክታሉ» ይላሉ።
ዶክተር ወንድ ወሰን እንደሚያብራሩት፤ በአገሪቱ ዋና ዋና እና መለስተኛ ከተሞች የጥርስ በሽታ በዋናነት መታየት ጀምሯል። የአፍ ንጽህና አጠባበቅ ጉድለት፣ የአመጋገብ መቀየርና የአፍ-ጤና ንቃተ-ህሊና አለማደግ የጥርስ በሽታ እንዲስፋፋ በር ከፍተዋል።
የአፍ ጤና አጠበባቅ ሕክምና መሻሻል የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም የተሰጠው ትኩረት እያደገ መጥቷል የሚሉት ዶክተር ወንድወሰን፣ በአገሪቱ የጥርስ ሕክምና ትምህርት መስጠት የተጀመረው ከአሥር ዓመታት ወዲህ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ከመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎች በዘለለ በሦስተኛ ዲግሪ እየተሰጠ መሆኑን ለዚህ እንደማሳያ ይጠቅሱታል።
የግል የጥርስ ሕክምና አገልግሎት መወደድ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍዊ መሆኑን የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ውስን ሰዎች በሚያሰሯቸው ድርጅቶች አማካይነት ሕክምና ከሚያገኙ ዋጋውን ከፍለው መታከም ከሚችሉ ውሱን ሰዎች ውጭ አብዛኛው ሕክምና ፈላጊ የሕብረተሰብ ክፍል ደፍሮ የሚገባበት ዋጋ እንዳልሆነም ይጠቁማሉ። የመንግስት የሕክምና ተቋማት በግል መታከም ለማይችሉ አማራጭ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ከስራ ሰዓት ውጭ በሆስፒታሎች በተመጣጣኝ ክፍያ የሚሰጠው የጥርስ ሕክምና ከግልና ከመንግስት ቀጥሎ ሶስተኛ አማራጭ እየሆነ መጥቷል።
የመንግስት የጥርስ ሕክምና ማእከላት የተሟላ አገልግሎት ላለመስጠታቸው የጥርስ ሕክምና ግብአትና መሳሪያ እጥረት ዋናው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ የጥርስ ሕክምና መሳሪያዎች ጥገና ባለሙያዎች ባለመኖራቸው የሕክምና መሳሪያዎች ከጥቅም ውጭ እንደሚሆኑ እና የአገልግሎት ክፍተት እንደሚፈጥርም ይናገራሉ።
ዶክተር ወንድወሰን በቂ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት፣ በጥርስ ሕክምና መሳሪዎች በቂ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች በማፍራት የአገልግሎቱን ተደራሽነትና ጥራት ማሻሻል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የሕክምና አገልግሎት መስጠት ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ የአፍ ጤና አጠባበቅን ቅድመ መከላከልን ማእከል ባደረገ ስትራቴጂ መደገፍ እንደሚገባ ይመክራሉ። የአፍ ጤና አጠባበቅ ትምህርት በስርዓተ-ትምህርት ተካቶ ልጆች ስለአፍ ጤና አጠባበቅ እየተገነዘቡ እንዲሄዱ ማድረግ፣ ሰፊና ተደራሽ የአፍ ጤና አጠባበቅ ትምህርት በመስጠት፣ፖስተሮችን በማዘጋጀት የሕብረተሰብ ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ።

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.