Sport: የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ

Filed under: News Feature,ስፖርት |

ዳግም ከበደ

የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ሊጀመር ቀናቶች ቀርተውታል። አምስት ሳምንታት እና 39 ቀናቶች የቀሩት ይህ አጓጊ የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ስፖርት በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ነው። በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ለአንድ ወር በዘለቀ የውድድር ቀናት አጓጊ ትዕይንቶች ይስተዋሉበታል ተብሎ ይጠበቃል። ያልተጠበቁ የእግር ኳስ ውጤቶች፣ ቀልብን የሚስቡ የደጋፊ ትዕይንቶች፣ ለጆሮ ያልተለመዱ፤ ለእይታ እንግዳ የሆኑ ወሬዎች እና ድርጊቶች በዚህ ውድድር ላይ እንደሚከሰቱ የሚጠበቅ ነው።


የዓለም ዋንጫን ከሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች ለየት የሚያደርገው የተለያየ ባህል፣ ቀለም እና ማንነት ያላቸው የስፖርቱ ቤተሰቦችን ከእግር ኳስ ውድድሩ በተጨማሪ በሌሎች ዝግጅቶች እና ትዕይንቶች ረዘም ለሚሉ ቀናት በበጎ ጎን ማስተሳሰር መቻሉ ነው። በዝግጅቱ ላይ ስፖርታዊ ወድድር ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅ አገራት ባህል ይዳሰሳል። የቱሪዝም መስህቦች በታዳሚዎች ይጎበኛሉ። በዓለም ዋንጫው ላይ ከተለያዩ አገራት የመጡ ደጋፊዎች ድንበር የሚሻገር ጓደኝነት የሚፈጥሩበት፣ ከዚያም በዘለለ በጋብቻ የሚተሳሰሩበት አጋጣሚዎች ተፈጥረው ያውቃሉ። ለዚህም ነው ዓለም ዋንጫ ከእግር ኳስ ውድድር በላይ ፋይዳው ጉልህ እንደሆነ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የሚነገረው።

ስፖርት ወዳዱ ህብረተሰብ ከዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገራት አንድ ጉዳይ በተለየ መልኩ ይጠብቃል። የመክፈቻ ዝግጅት። ላለፉት ጊዜያት አገራት ውድድሩን ለማዘጋጀት ቃል ሲገቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ያለውን ድባብ ያማረ እና ስኬታማ ከማድረግ ባሻገር አንድ ቃል የሚገቡት ነገር አለ። ይኸውም የመክፈቻ ዝግጅቱን ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተለየ መንገድ ደማቅ እና ልዩ ለማድረግ ከዓመት በላይ ዝግጅት ማድረግ ነው። በዚህ የመክፈቻ ዝግጅት ላይ አዘጋጇ አገር የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ አቅም ለማሳየት ከመቻሏም በላይ ለስፖርታዊ ውድድሮች የምትሰጠውን ትኩረት አመላካች ይሆናል። በተለይም ባህል እና ወግ ብሎም አገራዊ ማንነት በመክፈቻ ዝግጅቶቹ ላይ ጎልተው እንዲታዩ ይደረጋል።

ስፖርት በተለይም እግር ኳስ የዓለምን ህዝብ እያዝናና አንድ የማድረግ ኃይል እንዳለው በተግባር የሚያሳዩ ትዕይንቶች ይቀርባሉ። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ሙዚቃ እና እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ላይ አንድ ሆነው የምናገኛቸው። በዛሬው የዕሁድ ስፖርት አምዳችን ላይ ስለ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት ዳሰሳ እያደረግን ነው። ጥቂት ሳምንታት የቀሩት ይህ ተጠባቂ የእግር ኳስ ውድድር ተወዳጅ ጨዋታዎችን እና እልህ አስጨራሽ ፉክክሮች እንደሚከናወንበት ከወዲሁ ይገመታል። ሆኖም ለዛሬ በዝግጅታችን ለመቃኘት የፈለግነው ከውድድሩ ጎን ለጎን የሚካሄዱ እና የጨዋታው ድምቀት የሆኑ ሁነቶችን ነው። ይህን ስንል ደግሞ አንድ ጉዳይ በቶሎ በህሊናችን ላይ ይከሰታል፤ ሙዚቃ።

ስምንት ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ስናስታውስ ደግሞ አፍሪካዊቷ «ደቡብ አፍሪካ» ያሰናዳችው የዓለም ዋንጫ በትዝታ መልክ ተቀምጦ እናገኘዋለን። ይህም ብቻ አይደለም የመሰናዶው ምልክት እና ማስታወሻ የሆነውን «ዋካ ዋካ» ወይም ይህ ጊዜ የአፍሪካ ነው የሚለው ማጀቢያ ዘፈን በቅድሚያ በትውስታችን ውስጥ መከሰቱ አይቀሬ ነው።

ሙዚቃ እና ስፖርት በተለይ በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ላይ መተሳሰር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሁለቱ የመዝናኛ ዘርፎች ዓለምን አንድ የማድረግ ኃይል እንዳላቸው የተገነዘቡ ግለሰቦች እና ተቋማት በዝግጅቶቻቸው ላይ በጋብቻ እንዲተሳሰሩ በማድረግ ጣፋጭ ጊዜያትን ይፈጥራሉ። ለዚህም ነው መለስ ብለን የተለያዩ የውድድር ጊዜያቶችን ስናነሳ ታሪካዊ ዘፈኖች እና አርቲስቶችን የምናነሳው። እስቲ ለዛሬ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ ዝግጅቶች ላይ የነበሩትን ማጀቢያ የሙዚቃ አልበሞች እና አርቲስቶች እያስታወስን በሩሲያው ውድድር ላይ ምን እንጠብቅ የሚለውን እንመልከት።

ሁለት አስርት ዓመታት መለስ ብለን የዓለም ዋንጫ ዝግጀትን እናስታውስ። 16ኛውን የዓለም ዋንጫ በአገሯ በማሰናዳት በእግር ኳስ ችሎታ ጫፍ ደርሶ የነበረውን የብራዚል ብሄራዊ ቡድን 3ለ0 በሆነ ውጤት በፍፃሜው ጨዋታ በመርታት ፈረንሳይ ዋንጫውን ማንሳቷ ይታወሳል። ይህን የውድድር ዘመን ደግሞ በስርቅርቅ ድምፃቸው መቼም እንዳይዘነጋ በማድረግ ያዜሙ ሙዚቀኞች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል በ1990ዎቹ በዓለም ላይ ትልቅ ስም እና ዝናን አትርፎ የነበረው ፖርቶሪካዊው አርቲስት «ሪኪ ማርቲንስ» አንዱ ነበር። ይህ አቀንቃኝ የወቅቱን ዋንጫ ይፋዊ የሙዚቃ አጃቢ ነበር። የ1998ቱን ውድድር እና የብራዚልን ያልተጠበቀ ውጤት የሚያስታውስ ማንም የስፖርት ቤተሰብ « The Cup of Life» ወይም የህይወት ዋንጫ በማለት ያቀነቀነውን ተወዳጅ ማጀቢያ ሊዘነጋ አይችልም። ውድድሩን ከተለያየ ክፍለ አገራት ለመከታተል በፈረንሳይ ከትሞ የነበረው የስፖርት ቤተሰብም በዚህ ሙዚቃ አንድ ወር ከመዝናናቱም ባለፈ የስፖርትን እና የሙዚቃን ትስስር በማይረሳ መንገድ ለትዝታው ቋት ገብይቶ ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ 2002 የተደረገው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ይወስደናል። ይህ የዓለም ዋንጫ በብዙ መንገድ ልዩ የሚያደርጉትን ታሪካዊ ክስተቶች አስተናግዷል። ከእነዚህ መካከል በኤሺያ አገራት ተዘጋጅቶ የማያውቀውን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያዘጋጁት። ከዚህም ሌላ ለ16ጊዜ የተደረጉት ውድድሮች የተዘጋጁት በአንድ ሉዓላዊ አገር ብቻ ነበር። ሆኖም 17ኛው የዓለም ዋንጫ በልዩ ሁኔታ በሁለት አገራት ጣምራ ሊዘጋጅ ችሏል። በዚህም የዓለም እግር ኳስ ማህበር «ፊፋ» ውድድሩን ሁለት ጎረቤት አገራት በጋራ ማሰናዳት እንደሚችሉ የሚያሳይ ልምድ አግኝቶበታል።

ሌላኛው ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ ደግሞ ለዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን ያደረግነው የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ ሙዚቃ ነበር። በዚህ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት በ2000ዎቹ በፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝነት ዝናን አትርፋ የነበረችው አናስታሲያ በረስት የጃፓኑን እና የደቡብ ኮሪያውን ውድድር ደማቅ አድርጋው ነበር። «ቡም» የሚል መጠሪያ የነበረው ይህ ማጀቢያ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነትን በማግኘቱ ከ«ቫንጀሊክ» መዝሙር ጋር በጋራ ሲዘመር እና ሲቀነቅን ቆይቷል። ተወዳጁ የእግር ኳስ ውድድርም በዝነኛ አቀንቃኞች እንዲታጀብ እና ባህል እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የ2006ቱ የጀርመን የዓለም ዋንጫ ነው። በዚህ ዝግጅት ላይ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኞቹ ኢል ዲቮ እና ቶኒ ብራክስተን በማጀቢያነት ማቅረባቸው ሙዚቃ እና ዓለም ዋንጫ እንደማይነጣጠሉ ያመላከተ ነበር።

የ2010 የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት ከመካሄዱም በላይ በማጀቢያ ሙዚቃ የተለየ ትውስታ ኖሮት በደማቅ ሁኔታ አልፏል። ከተዘጋጁት የማጀቢያ ሙዚቃዎች ውስጥ ደግሞ የሻኪራ «ዋካ ዋካ» ሁሉንም የስፖርት ቤተሰብ ከማዝናናት ባለፈ «ጊዜው የአፍሪካ» ነው የሚል መልዕክት ያስተላለፈ ነበር። ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን በብዛት የማታዘጋጀው አፍሪካም በሻኪራ ዋካ ዋካ ለአንድ ወር ፈንጠዝያ ውስጥ ቆይታለች። ተወዳጇ አቀንቃኝም ከሌሎች ዘፋኞች በተለየ ለስፖርቱ በተለይ ለእግር ኳስ ቅርብ መሆኗን አሳይታበታለች። ሻኪራ የውድድሩን ዋንጫ መሳም ከቻለው የስፔን ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ተጫዋች ጄራርድ ፒኬ ጋር ትዳር መስርታ ልጆችን ማፍራት የቻለችበትን የፍቅር አጋጣሚ መሰረት ያስያዘችበት የዓለም ዋንጫ ሆኖም ይታወሳል።

በደቡበ አፍሪካ በተሰናዳው ተወዳጁ ውድድር ላይም ከቀድሞዎቹ ዝግጅቶች በተለየ ታዋቂ እና ስኬታማ አቀንቃኞች ተሳትፈው ነበር። በዚህ የፊፋ ይፋዊ አልበም ላይ ከኮሎምቢያዊቷ አርቲስት ሻኪራ ጋር ክላውዲያ ሊት፣ የአር ኤንድ ቢ አቀንቃኙ አር ኬሊ፣ የሂፕ ሆፕ ተጫዋቹ ፒት ቦል እንዲሁም ጃፓናዊቷ የዘፈን ደራሲ ሚሲያ በተባባሪነት ሠርተዋል። በፍፃሜው ጨዋታ ስፔን ኔዘርላንድን በመሀል ሜዳው ጥበበኛ አንድሬስ ኢኒዬሽታ የተጨማሪ ሰዓት ግብ 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን ስታነሳ ዓለም ደግሞ በተወዳጁ ሙዚቃ «ዋካ ዋካ» ጣፋጭ አንድ ወርን አጣጥሟል።

ሌላኛው እና ከእግር ኳስ የትውስታ መዝገብ ውስጥ የማይፋቀው የሙዚቃ አሻራ ሻኪራ ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ የሙዚቃ ሥራዋን የለቀቀችው ነው። ይህ ሥራ ከሌሎቹ ሙዚቃዎች ለየት የሚያደርገው በቪዲዮ ክሊፑ ላይ ሊዮኔል ሜሲ፣ ጄራርድ ፒኬ እና ኔይማር ማሳተፉ ነው። እነዚህ ተወዳጅ የዓለማችን የእግር ኳስ ጥበበኞች ኮሎምቢያዊቷ የሙዚቃ ኮከብ ሻኪራ ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ የሚሆን አዲስ የሙዚቃ ሥራ «ላ ላ ላ» በሚል መጠሪያ ይፋ ስታደርግ በጋራ ሠርተዋል።

በሙዚቃ ሥራው የቪዲዮ ክሊፕ የባርሴሎናውን ኮከብ ባለቤቷን ጄራርድ ፒኬን፣ ሊዮኔል ሜሲን፣ ኔይማር እና በዓለም ዋንጫ የማይሳተፈውን ኤሪክ አቢዳል ብሎም ልጇ ሚላንን በማሳተፏ የዝግጅቱ ድምቀት ነበር። በተጨማሪም አርጀንቲናዊው ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ራዳሜል ፋልካዎ ተሳትፈዋል። በውድደሩ ወቅትም የዓለማችን ታላላቅ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ይህን ሙዚቃ ሲያጫውቱት ከርመዋል። ስፖርቱም በሙዚቃው ታጅቦ በድምቀት ተጠናቋል። ሙዚቃው የአዘጋጇ አገር ብራዚል የሳንባ የሙዚቃ ምት እንዲኖረው ብራዚላዊውን ካርሊኖሆ ብራውን በፊቸሪንግ ተሳትፎበት ነበር። በተለይ ሻኪራ በ2010 የዓለም ዋንጫ «ዋካ ዋካ» በሚል መጠሪያ የሠራችው የደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ማጀቢያ ሥራ በበርካቶች ዘንድ መወደዱ በዚህኛውም ሥራዋ ላይ በጉጉት እንድትጠበቅ አድርጓት ነበር። የሻኪራ «ላ ላ ላ» የተሰኘው ማጀቢያ የጄነፈር ሎፔዝና ፒት ቡል «ኦላ ኦላ» ጋር ተደምሮ ሙዚቃ በስፖርት ላይ ሞገስ እና ፍቅር እንደሚጨምር ማሳየት ችሏል።

ሩሲያ 2018

የፊፋ የዓለም ዋንጫ በሩሲያ አስተናጋጅነት በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከሰኔ 14 እስከ ሀምሌ 15 2018 እንዲካሄድ መርሐ ግብር ተይዞለታል። በጉጉት የሚጠበቀው ውድድር ሊጀመርም አምስት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል። ፊፋ ከውድደሩ ጅማሮ አስቀድሞ ለሦስት ጊዜያት የዓለም ዋንጫው በተመረጡ ሃገራት እንዲዘዋወሩ አድርጎ ነበር። በተመሳሳይ ለአራተኛ ጊዜ በበርካታ አገራት ዋንጫው ተዘዋውሯል። የፊታችን ግንቦት አንድም በሩሲያ ማጠናቀቂያውን ያደርጋል።

ፊፋ ዋንጫው እንዲጎበኛቸው የመረጣቸው አገራት 51 ሲሆኑ፤ 91 ከተሞች ላይ ተዟዙሯል። ይህ ዕድል ለኢትዮጵያም ደርሷታል። ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ዕድሉ ለኬንያ ሲደርሳት በ36 ከተሞች በአድናቂዎቹ አቀባበል ተደርጎለታል። የዓለም ዋንጫም ከስፖርቶች ሁሉ በስፋት ተወዳጅነትን ያተረፈ ለመሆን በቅቷል። ለዚህም ነው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሚጀመረው የሩሲያው ዝግጀት ላይ የሚቀርቡ ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎች በተመሳሳይ በጉጉት የሚጠበቁት። እውቅ አቀንቃኞቹ ሻኪራ፣ አናስታሲያ፣ ሪኪ ማርቲን ላለፉት ጊዜያት ዓለም ዋንጫን በዜማ አድምቀዋል። አሁን በ2018ቱ የሩሲያ ዝግጅት የትኛው ዘፈን ተወዳጅ ይሆናል የሚለው ጥያቄ ደግሞ እልህ አስጨራሽ ከሆነው የብሄራዊ ቡድኖች ፍትጊያ ውጪ ተጨማሪ ጉጉትን ፈጥሯል።

በርከት ያሉ የማስታወቂያ ድርጅቶች ከወዲሁ የዓለም ዋንጫን መምጣት እያበሰሩን ይገኛሉ። ልክ እንደ አዲስ ዓመት መባቻ ሁሉ ለዚህ ውድድርም ከወዲሁ «እንኳን አደረሳችሁ» የሚል መልዕክት በእነዚህ የማስታወቂያ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ለስፖርት ቤተሰቡ እየተላለፈ ይገኛል። ሆኖም በዓሉን እነዚህ ማስታወቂያዎች ብቻ አይደሉም የሚያደምቁት። ላለፉት ዓመታት ስፖርቱ ደማቅ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስዱት ተወዳጅ አቀንቃኞች ጭምር ናቸው።

የዓለም እግር ኳስ ማህበሩ «ፊፋ» እና አጋር ደርጅቶቹ እግር ኳሱ ያለ ተወዳጅ ሙዚቃ ደማቅ እንደማይሆን ያለፈው ልምዳቸው ስላስገነዘባቸው ጥሩ የሚባል የማይዘነጋ ትዝታን ለመጣል ከወዲሁ እየተሯሯጡ ይገኛሉ። ሙዚቃውን ሲሰሙ የዓለም ዋንጫን፤ የዓለም ዋንጫን ሲያስቡ ተወዳጁን ሙዚቃ በጭንቅላታቸው የሚያሰላስሉ የእግር ኳስ ወዳጆችም ጉዳዩን በትኩረት እየጠበቁ ናቸው። በዚህም የተለያዩ አቀንቃኞች ከወዲሁ ተወዳጅ ሙዚቃ እና ይፋዊ የዓለም ዋንጫ መዝሙራቸው ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተገምቷል።

ጄሰን ዱሩሎ

አሜሪካዊው ተወዳጅ አቀንቃኝ እና የዘፈን ደራሲ ጄሰን ዱሩሎ በሩሲያው የዓለም ዋንጫው ላይ ድምቀት ሆኖ ብቅ ያለ አቀንቃኝ ነው። «ከለር» የተሰኘው ሙዚቃው በኮካኮላ የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ እንዲሆን ተመርጧል። ይህ ሙዚቃ አብሮነት እና ከዘረኝነት የፀዳ አዲስ ዓለም ምን ያህል ውብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ሙዚቃው በጉጉት ለሚጠበቀው ዓለም ዋንጫም ልዩ ምልክት እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው። የማህበራዊ ድረ ገፅ በሆነው የምስል ማጋሪያ «ዩቱይብ» ከ14 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተመልክተውታል።

ጄሰን ዱሩሎ መጋቢት 9 «ከለር» የተሰኘውን ዘፈን ለዓለም ዋንጫ መልቀቁን ተከትሎ በቲውተር ገፁ «ሁላችሁም አገራችሁን ወክሉ፤ ባንዲራችሁን ወክሉ፤ በመጣችሁበት እና ባላችሁ ማንነት ኩሩ» በማለት ዘፈኑን በይፋ ለውድድሩ መልቀቁን አስታውቆ ነበር።

ጥቂት ስለ ዓለም ዋንጫ ታሪክ

ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1930 ነው። እግር ኳስን በበላይነት ለመምራት እና ተወዳጅነቱን ለማስፋት ጉልህ ሚናን የተጫወተው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር «ፊፋ» በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የዋንጫ ውድድር ያደረገው። የያኔው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ሪሜት እግር ኳስን በዓለም ዋንጫን ማዕቀፍ ስር በማድረግ ከኦሎምፒክ ስፖርቶች ነጥሎ ለማድረግ የተገደደበት አንድ አጋጣሚ ነበር።

የኦሎምፒክ ስፖርት አዘጋጆች በ1932 በአሜሪካ ሎስአንጀለስ በሚካሄደው ውድድር ላይ ከስፖርታዊ ክንውኖች መካከል እግር ኳስን ለማካተት ፍላጎት በማጣታቸው ማህበሩ ለብቻው ተገንጥሎ የራሱን ውድድር ለማድረግ ውሳኔ አሳለፈ። ይሄ አጋጣሚ እግር ኳስ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን እንዲያተርፍ የዕድል በሩን ከፈተ እንጂ ጭርሱኑ እንዲጠፋ አላደረገውም።

በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ 13 አገራት ብቻ ተሳትፈዋል። ውድድሩ አሀዱ ብሎ ሲጀምር አሁን የደረሰበት የተወዳጅነት ልክ ላይ ይደርሳል የሚል ግምት አልነበረም። ለዚህም ነበር ከጅምሩ 13 አገራትን ሊያውም 7ቱ ከአዘጋጅ አገሯ ከኡራጋይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙት የደቡብ አሜሪካ አገራት የተሳተፉበት። የእግር ኳስ ማህበሩ አባላቱን በተለይም አውሮፓውያኑ ቡድናቸውን ወደ ኡራጋይ ልከው ውድድር እንዲያካሄድ አድርጎ ነበር። ሆኖም እውሮፓውያኑ አትላንቲክ ኦሽንን አቋርጦ በደቡብ አሜሪካዋ አገር ላይ ውድድሩን ማድረግ ከርቀቱና ከሚያስወጣቸው ከፍተኛ ወጪ አኳያ ሊቀበሉት አልቻሉም ነበር። በዚህ የተነሳም 13 አገራት ብቻ ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚያ ዘመን አንስቶ ውድድሩ በዕድገቱ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ መርሀ ግብሮቹን እያሰፋ እና ተወዳዳሪ አገራትን እየጨመረ መጥቷል። በዚህም አሁን 32 አገራት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ 200 የሚሆኑት ደግሞ ሁለት ዓመት በሚፈጀው የማጣሪያ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።

ጥቂት ስለ መወዳደሪያ ስታዲዮሞች

በታኅሣሥ መጀመሪያ በሞስኮ በወጣው የምድብ ድልድል በወርሀ ሰኔ ጅማሮውን ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ አገራት የምድብ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለወራት ተፋልመው ለታላቁ ውድድር የተሳታፉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ታዲያ ሩሲያም እንግዶቿን ተቀብላ በስኬት ውድድሮችን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን በተለያዩ የመገናኛዎች ሲዘገብ ቆይቷል። ዝግጅቱን በዋናነት ያደምቁታል ተብለው የሚጠበቁት ደግሞ አዳዲስ እና በጥሩ ሁኔታ በድጋሚ የታደሱት ስታዲየሞቿ ናቸው። አገሪቷ32ቱ ቡድኖች ሰላማዊ ፍልሚያ ያደርጉበታል ያለቻቸውን 13 ስታዲየሞች ይፋ አድርጋለች። ከዚህ ቀደም በስፋት ስለስታዲዮሞቹ የነገርናችሁ ቢሆንም በጥቂቱ እናስታውሳችሁ።
«ሉዙኒኪ ስታዲየም» በሩሲያ ግዙፉ ስታዲየም ነው። በዋና ከተማዋ ሞስኮ ይገኛል። 81ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። «ኦቲሪቲ አሬና» ይህ ስታዲየም እንደ ሉዚኒኪ ስታዲዮም በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ ይገኛል። የፍፃሜ ጨዋታ ከሚያስተናግደው ዋናው ስታዲየም በግማሽ ያህል ቀንሶ 45ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ተገንብቷል። «ካዛን አሬና» በካዛን ከተማ ውስጥ ይገኛል። 45 ሺ 379 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ታዋቂው የሩሲያ እግር ኳስ ክለብ ሮቢን ካዛን ንብረት ነው። በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ከተመረጡ ውስጥ በሦስተኝነት ተካቷል።

ከላይ በጥቂቱ ያነሳንላችሁ ስታዲዮሞች በተወዳጅ እና ታዋቂ ሙዚቀኞች፤ የአገራቸውን ብሄራዊ መዝሙር በሚያቀነቅኑ ውብ ደጋፊዎች ደምቀው ይሰነብታሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በሩሲያ የሚካሄደውን «ታላቁን ዋንጫ» ማን ያነሳው ይሆን? ጥያቄ ከሁሉም ነገር በላይ ገዝፎ በእግር ኳስ አፍቃሪዎች መካከል ጥያቄ ሆኖ ይቆያል። ዓለም ዋንጫ 5 ሳምንታት ቀርተውታል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.