/

ጎሳዬ ተስፋዬ ቴዲ አፍሮ ጋር ሽማግሌ ላከ

1 min read

 

አሜሪካውዊው ፈላስፋና ደራሲ ኢልበርት ሁባርድ “ከችት ለማምለጥ ምንም አትስራ፡፡ ምንም አትናገር፡፡ ምንም አትሁን፡” ይላል:: ቴዲ አፍሮ እና ጎሳዬ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ታታሪ ሰራተኞች በመሆናቸው ከትችትም ከሃሰተኛ ወሬም ርቀው አያውቁም:: ቴዲ አፍሮ ከአፉ የወጣችው ብቻ ሳትሆን ሊናገር ያስባል የተባለው ነገር ሁሉ መነጋጋሪያ እንደሚሆነው ሁሉ ጎሳዬ ተስፋዬም በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ሃሰተኛ ወሬዎች ተወርቶበታል::

ከነዚህ ውስጥ ሚሚ ስብሃቱ በዛሚ ኤፍ ኤም ያስወራችበት “ሃይማኖቱን ቀይሮ ሙዚቃ በቃኝ በማለት መዝሙር ሊያወጣ ነው” የሚለው ወሬ አንዱ ሲሆን የሚሚ ራድዮ ለምን ይህን በድምጻዊው ላይ እንዳስወራበት ሌላ ተልዕኮ እንዳለው ግልጽ ቢሆንም እስካሁን አልወጣም::  የሚሚን ራድዮን ወሬ የተቀበለው እዚያው ሃገር ውስጥ የሚወጣ መጽሄትም “አሁን ዳግመኛ ተወልጃለሁ፤ ጌታ ለዚች ቀን ስለመረጠኝ ክብርና ምስጋና ለናዝሬቱ ኢየሱስ ይገባዋል፤” ሲል ጎሳዬ ተናገረ ብሎ ፎቶውን በግድንግዱ ፊቱ ገጹ ላይ ለጥፎ ተበጠረቀ::

በወቅቱ ጎሳዬ የቀረቡት ዘገባዎች ሃሰተኛ ስለሆኑ መጽሄቱም ሆነ ዛሚ ኤፍ ኤም ሬድዮ ድምፃዊውን እንዲሁም አንባቢና አድማጩን ይቅርታ በመጠየቅ እንዲያስተባብሉ  ቢጠይቅም; መገናኛ ብዙሃኑ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ግን ክስ በመመስረት የጉዳት ካሳ እንደሚጠይቅ ሊያስቦካቸው ቢሞክርም አልሰሙትም::  ጎሲ ይቅርታም አልተጠየቅም ማስተባበያም አልተሰጠለትም:: ቆየት ብሎም ሰይፉ ላይ ቀርቦ ትንሽ ተንፈስ አለ::

ማርቲን ሉተር ኪንግ ”የሚሞትለት ዓላማ የሌለው ሰው ለመኖር ብቁ አይደለም ” ያለው ቴዲ አፍሮን ለመኖር ብቁ እንደሚያደርገው ብዙዎችን ያስማማል:: አቡጊዳ ብሎ የሙዚቃ አልበሙን ካወጣ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬዋ ድረስ ለሚሞትለት ዓላማ በሙዚቃ ሥራዎቹ ሕይወቱን ሊያሳጡት የሚችሉትን ያህል መስዋዕትነት ከፍሏል:: እየከፈለም ነው::

ከነዚህ ውስጥ  ሕወሓቶች 17 መርፌ በምትለው ዘፈኑ ሕዝብ “ቅጫማም” የሚለውን ስድብ እንዲያስታውስ አድጎ በሙዚቃ ሰደበን; መለስ ዜናዊ በሚገኝበት የሚሊኒየም አዳራሽ ዝግጅት አልዘፍንም ብሎ ኮራ, በአላሙዲ ሸራተን አልዘፍንም አለ – ምን ያህል ቢንቀን ነው በሚሉ ሸፋፋ ምክንያቶች በደህንንነት መስሪያ ቤቱ በተሰራ ተንኮል ቴዲን መኪና ሰው ገጭቶ ገደለ በሚል አስረውታል:: ታስሮ ከተፈታ በኋላም ያን ቅጫማም የምትለውን ስድብ የምታስታውሰውን ’17 መርፌ’ ዘፈን አትዝፈንብን እያሉ ቢያስፈራሩትም እርሱም በሕይወቱ እየፈረደ የሕዝቡን ጥያቄ በማሟላት በየመድረኩ ሲዘፍነው – የሰሙት እነዚሁ ባለቁምጣዎች ፓስፖርቱን እየቀሙ የውጭና የሃገር ውስጥ ኮንሰርቶቹን አሰርዘውታል::

የኢትዮጵያውያንን ጤና ሲነሳ ቆይቶ ዛሬ የዓለም ጤና ድርጅትን እየመራሁ ነው የሚለው ቴዎድሮስ አድሃኖም ሳይቀር ቴዲ በአፍሪካ ሕብረት በዓል ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ እንዲዘፍን ተመርጦ እንዳይዘፍን እንዳሳገደው ሰሞኑን እንደ አዲስ እየተንሾካሾከ ይገኛል:: አንድ የቅርብ ሰው ሹክ እንዳለን ቴዲ የሞራል ልዕልናው ከፍ ያለና ለገንዘብ ግድ የሌለው ሰው በመሆኑ እንጂ ባለ17 ቁምጣዎቹ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር የተዘረጉ ኮንሰርቶች እንዲሰረዙ በማድረግና ከሃገር እንዳይወጣ በማገድ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ቢያሳጡትም በአቋሙ እስካሁን አለ:: እንግዲህ ማርቲን ሉተር ኪንግ ”የሚሞትለት ዓላማ የሌለው ሰው ለመኖር ብቁ አይደለም ” ሲል የተናገረው ለቴዲ አይነቱ ሰው ነው::

ቴዲ ለዓመታት ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኝ በባለ 17 ቁምጣዎቹ ሲከለከል ኖሮ ፍቅር ያሸንፋል እያለ ሲሰብክ ቆይቶ ከዓመታት በኋላ አሁን በመጣው ለውጥ የተነሳ ባለፈው ወር ተፈቅዶለት በአዲስ አበባ ታሪካዊ ኮንሰርት አካሂዶ ነበር:: ከዚህ ኮንሰርት በኋላ የመጡ ሃሳቦች ናቸው ጎዳዬ ተስፋዬ ወደ ቴዲ አፍሮ አማላጅ እንዲልክ ያስገደደው:: ለምን? የቅርብ ሰው ሹክ ብሎናል ሹክ እንላችኋለን – ከዛ በፊት ግን ምናልባት ያልሰማችሁት ከሆነ አንድ ሁለት መረጃ ስለጎሳዬ እንወርውር::

ጎሳዬ ተስፋዬና ቴዲ አፍሮ የሙያ ፉክክሩ እንዳለ ሆኑ የሚዋደዱ ድምጻውያን ናቸው:: ቴዲ አፍሮ በታሰረበት ወቅት ጎሳዬ በምርጥ አልበሙ አሜሪካንን እና አውሮፓን ሲዞር; በአዲስ አበባም በተለያዩ ቦታዎች ሥራዎቹን ሲያቀርብ ቴዲን ለማስታወስ እያለ በግፍ መታሰሩን ለህዝብ ለማሳወቅና ሕዝቡም ከጎኑ እንዲቆም እየጠየቀ የቴዲ ዘፈኖች በመዝፈን ኮንሰርቶቹን ይጀምር ነበር::

ቴዲ አፍሮ በወቅቱ በመታሰሩ የሚደሰቱ አርቲስቶች በነበሩበት ዘመን ጎሳዬ በግምባር ቀደምትነት ታሪካዊ ሥራ ሰርቷል:: ከዚያም በኋላ በአንድ መድረክ በዋሽንግተን ዲሲ ሲያትልና ሌሎችም ከተሞች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል:: በተለይ ከሌላ ድምጻዊ ጋር በአንድ መድረክ ኮንሰርት ብዙም የማያቀርበው ቴዲ  ከጎሳዬ ጋር በአንድ ላይ የቀረበው ለርሱ ካለው ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ነው ሲሉ ፕርሞተሮቹ በወቅቱ ሹክ ብለውን ነበር:: ግን ቴዲ ከማህሙድ ኤርትራዊው ሮቤል ጋር መዝፈኑንም እናስታውሳለን::

እናም ወደ ሹክሹክታው ስናልፍ ጎሳዬ ተስፋዬ ሰሞኑን ወደ ቴዲ አፍሮ ቤት አማላጅ ልኳል:: ሽማግሌዎቹ ልጅህን ለልጄ ሊሉ አይደለም ወደ ቴዲ ቤት የሄዱት:: ይልቁንስ ቴዲን ተረጋጋ ሊሉት እንጂ:: 

ጎሳዬ ላለፉት 12 ዓመታት የሙዚቃ አልበም አላወጣም:: በዓል በመጣ ቁጥር በየራድዮው እየቀረበ አሁን አልበሜን ጨርሻለሁ ለዚህ በዓል ይወጣል በማለት ቃል ሲገባ ቢቆይም አልተሳካለትም:: ሆኖም አሁን ግን ለገና በዓል ለማውጣት ሙሉ ዝግጅቱን ጨርሷል:: 15 ዘፈኖችን ይዟል አልበሙ:: 

አልበሙ ውስጥ  ካሉት ዘፈኖች ቴዲ አፍሮም አለበት:: የታምራት ደስታን ሥራዎች በብዛት ሲሰራ የነበረው ሃብታሙ ቦጋለን ጨምሮ ስመጥር የዜማና የግጥም ሰዎች በዚህ የጎሳዬ አልበም ተጠበውበታል:: ጎሳዬ ለገና ሕዝቡን ከዳር ዳር ሊያነቃቃው ባሰበበት ወቅት ያልታሰበ ዜና ይሰማል:: እርሱም ምንድን ነው? ቴዲ ለዓመታት የተከለከለበትንና ለመጀምሪያ ጊዜ ባለፈው ወር የሚሊኒየም አዳራሽ ላይ ያቀረበውን ኮንሰርት በሲዲ ሊለቀው እንደሆነ ጎሳዬ ይሰማል:: የቀኑ መገጣጠም; ከገበያው ሰፊ አለመሆን ጋር ተያይዞ ጎሳዬ ከዳር እዳር አልበሙ እንዲሰማለት ቴዲን ሲዲህን አሁን አትልቀቀው ይለፍህ ሲል ሽማግሌ ልኮበታል::

የቴዲ ምላሽ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በዘመናዊ መንገድ የተቀረጸው ይህ የኮንሰርት ቭዲዮ በጥራት መዘጋጀቱ ተሰምቷል:: ነገሩን ውስብስብ ያደረገው ደግሞ የጎሳዬን አልበም የገዛው ቴዲ አፍሮን በሰሜን አሜሪካ ሲያዞረው የነበረው ጌታነህ መሆኑ ነው:: ቴዲ አፍሮ ገበያውን ለሁለቱ ወዳጆቹ ይለቅላቸው ይሆን? ከቀናት በኋላ የምናየው ይሆናል::

በነገራችን ላይ አትላንታ ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጉሮሮ እየተመነጠቅ በሚላክላቸው ብር የጎሳዬን ዘፈኖች በብዛት እያስከፈቱ በውስኪና በሺሻ ሲራጩ የሚያመሹት የሕወሓት ባለስልጣናት ልጆች ሰሞኑን ከክለቦቹ እንደጠፉ ሹክ ተብለናል:: ግን በየስቴቱ ያለው የህገውጥ የዶላር ንግድ ተጧጡፎ ቀጥሏል:: ሆኖም ተደምሬያለሁ; ሃገሬ ተዘረፈች እያለ የሚቆጨው ዲያስፖራ ግን የሕወሓትን ዶላር እየመነዘሩ ኢትዮጵያን የሚያቆረቁዙትን ፎቷቸውን እና ስማቸውን በማስተላለፍ ሲያጋልጥ ስለማይታይ የጥቁር ገበያ ንግዱ ደርቷል::

ይህ ሹክሹክታ ነው!!

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.