//

”ትራንዚት” ድራማ አጭር ቅኝት | ክንፉ አሰፋ (አምስተርዳም)

1 min read

“ስለ ህይወት መጻፍ ከመጀመርህ በፊት ህይወትን መኖር ይገባሃል።” ይላል ስመ ጥሩ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ፣ እርነስት ሄሚንግዊይ። በመኖር እና በመስማት መካከል ትልቅ ጅረት አለ ሊለን ፈልጎ ነው። የህይወትን ክፉም ሆነ ደግ ገጽ ሊለይ የሚችለው፤ ያለፈባት ብቻ ነው። መራራም ትሁን ጣፋጭ፤ የስደትን ጣዕም ጠንቅቆ የሚያውቃት የቀመሳት ብቻ ነው።

የ ”ትራንዚት” ድራማ ደራሲ እና አዘጋጅ ቢንያም ወርቁ ስደትን ኖሮባት አያውቅም።  ስለ ስደት ጽፎ ያዘጋጀው ድራማ ግን የተመልካቹን ስሜት የሚቆጣጠር ነበር። መድረክ እና ተመልካች ሳይላቀቁ የሚያልቀው ተውኔት፤  የእርነስት ሄሚንግዊይን “የኖሩበትን መመስከር” አባባል ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ታላቁ መጽሃፍ “ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው።” ይላል። እርግጥ ጥበብ የገሃዱ አለም ነጸብራቅ ናት። ይህችን የስደት አለም ሳይኖሩባት የሚጽፉትን ከማድነቅ አልፈን ምን ልንላቸው እንችል ይሆን?

የስደትን እውነተኛ ገፅታ ወለል አድርጎ ባያሳየንም፤ ቢነገር እና ቢፃፍ የማያልቀው የስደት ችግር በማንኪያ ጨልፎ፣ ታሪክን ሰድሮ፣ ቃላቶችንም ቀምሮ በኮሜዲ ዣነር አቅርቦታል።

ስደት አስቸጋሪ እና አድካሚ ነው። በእያንዳንዱ የስደት ምዕራፍ ውስጥ የህይወት ስንክሳር አለ። በተለይ ከሚወዱት ባህል፣ ከሚያፈቅሩት ቤተሰብና እትብታቸው ከተቀበረባት ሃገር ወጥቶ እና ርቆ ለመኖር መወሰን በህይወት ላይ ትልቁ ውሳኔ ነው። ማንም ሰው ካልተገፋ በቀር እንዲህ አይነት ህይወት ውስጥ ሊገባ ፈጽሞ አይፈቅድም።

ከዚህ የስደት ህይወት ስንክሳር ውስጥ ጉድፎችን እንደ ሰበዝ እየመዘዙ አውጥቶ፣ ስሜትን መኮርኮር መቻል በራሱ ጠለቅ ያለ ጥበብን ይጠይቃል።

በድራማው አራት ተዋንያን ይሳተፉበታል።  ሁለቱ ስደተኞች ፤ ሁለቱ ደግሞ ስደተኛ ለመሆን የሚግደረደሩ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች። ለትራንዚት ካረፉባት ጣልያን ከተማ ላይ ይገናኛሉ። ስደተኛ በነበሩት እና ለመሆን በሚጥሩት መሃል የሚፈጠር የሃሳብ ፍጭት፣ የአመለካከት አንድነት እና ልዩነቶችን በ “ትራንዚት” ድራማ እናያለን።

በብሄራዊ ፍቅር እና በቤተሰባዊ ፍቅር የሚነሱ የሃሳብ ፍጭቶችን በስሜት ሳይሆን በአመክንዮ ያሳየናል። መሰደድ የሚፈልገውም፤ ስደትን የሚጠላውም፤ እያንዳንዱ የየራሱ ምክንያት አለው። በስደት እና ሃገርን በመክዳት ትርክት መካከል ያለውን ብዥታ የሚያጠራው፤ በስደት ላይ እንኳ የማይጠፋው የነደደ የሃገር ፍቅር ስሜትም በመድረኩ ተሸክኗል።

አንዱ ስለ አገር አደራ ይጨነቃል፤ ሌላው ስለ ቤተሰባዊ ፍቅሩ። ስደት ላይም ሆኖ የሃገሩን ብሄራዊ ድል የሚመኝ፤ በማንነቱ የሚኮራ እና በሃገር ፍቅር ስሜት የሚቃጠል ዜጋን ታሪክ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል ትራንዚት።

አራት የጥበብ ፈርጦች ይተውኑበታል። ሃና ዮሃንስ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሳምሶን ታደሰ እና ተሻለ ወርቁ።  ድራማው አዝናኝና ቁምነገር አዘል ቢሆንም፤  በውስጡ ያሉ አንዳንድ ጥርስ የማያስከድኑ ቀልዶች የበለጠ ስሜት የሚሰጡት ለኖረበት እና ችግሩን ለተቋደሳት ብቻ ነው።

”ትራንዚት” የመድረክ ድራማ ስደትን ላልኖረበት ተመልካች ትርጉም ላይሰጠው ቢችል አይገርምም።  በውስጡ የሚነሱ ስደት ነክ እውነታዎችን ለማያውቋቸው ሰዎች ስሜት አልባ ሊያደርጋቸው ይችላል። በውስጡ ስሜትን የሚኮረኩሩ የስደት አለም ብቻ የሚከሰቱ እውነታዎች አሉበት። አንዳንዶቹ ዲያሎጎች ተመልካችን በስሜት ሰረገላ ወደ ኋላ ይመልሱና የትዝታ ማዕበል ውስጥ ይጨምራሉ። ይህ አይነቱ ቴክኒክ በራሱ የተመልካችን ስሜት የመያዝ ጥበብ ይሁን እንጂ ስደትን በማያውቁ ተመልካቾች ላይ ላይሰራ ይችላል።

የስደት ምክንያቶችን ከሁሉም ጠርዝ ይዳስሳል። ከበጎ ጎኑ ፈቀቅ ብሎ እፉ ገጽታ ላይ በማመዘኑ ምክንያት ትንሽ የመጋነን ነገር ቢታይበትም፤ መጋነኑ በራሱ ጥበብ እንጂ ከገሃዱ አለም እውነት የመውጣት ነገር ተደርጎ ሊታይ አይገባም።  በመጨረሻ ግን የድራማውን እይታ ከትራጀዲ ወደ አስቂኝ አውድ ለመቀየር የሄደበት መንገድ ከገሃዱ አለም እውነታ አርቆታል።

ጥቅል መልዕክቱ፤  የሃገር ፍቅር እና ብሄራዊ ክብር፣ ከቤተሰብም ይሁን ከራስ ችግር ሁሉ ይበልጣል የሚል ነው።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.