ጋሰለ አረሩ አዴፓም ብአዴን ነው!

Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ባደኩበት ሰፈር አቶ አረሩና አያ አዳነ የሚባሉ ሰዎች ይኖሩ ነበር፡፡ አቶ አረሩን ኮስማናዋ እናቱ እማማ ሐብትሽ ምን እያበሉ እንዳሳደጉት አላውቅም ቁመናው የገደል ግማሽ ያኻክል ነበር፡፡ ጥምቡልዝ መልኩም የተወቀጠ ኑግ ይመስል ነበር፡፡ አቶ አረሩ የገደል ግማሽ እንደሚያህል ለመግለጥ የሰፈሩ ሕዝብ ” አረሩ ብቻውን የቤት ጣራ ተሸክሞ መሄድ ይችላል” ይለው ነበር፡፡ አያ አዳነ በተቃራኒው ቁመናዋ እንደ ስንበሌጥ የሰነነች መልኳም በቀይና በቀይዳማ መካከል ያለች ቆፍጣና ጎበዝ ነበረች፡፡ አቶ አዳነ በሰንጢ ንግግሯ እንደ አለቃ ገብረ ሃና የምትታወቅ ጠቢብ ነበረች፡፡ የአያ አዳነን የንግግር ሥስለትነት ለመግለፅ ማህበረሰቡ “የአዳነ ንግግር ያልጋለ ብረት ከመቅፅበት ይቆርጣል” ይላት ነበር፡፡

በዚሁ ሰፈር ካቶ አረሩ በተጨማሪ አረሩ የሚባል ጠብደል ጥቁር አለሌ ይኖር ነበር፡፡ አቶ አረሩ ከአለሌው ለመለየትና  አረሩ የተባለውም የተቀቀጠ ኑግ በመሰለው ቆዳው ምክንያት ስለመሰለው ባካባቢው ባልተለመደ መንገድ ስሙን ጋሰለ ወደ እሚባል ስም ቀየረና አረፈው፡፡ ይኸንን በአካባቢው ያልተለመደ የሥም ለውጥ  የተረዳ አብዛኛው የአቶ አረሩን ሥም በየቤቱ እያነሳ እየጣለ ሌላውም “ሥሙን መለወጥ መብቱ ነው!” እያለ የአንድ ሰሞን የቡና ቴራቲም ወሬ አደረገው፡፡ 

ብዙውን ጊዜ ተመንጋው ጋር የማትነዳዋ አያ አዳነ ግን የአቶ አረሩ ድንገተኛ ሥም ቅየራ የአንድ ሰሞን የቡና ወሬ አድርጋው ማለፍ አልፈቀደችም፡፡ አብዛኛው ሰው አቶ አረሩን በአዲሱ ስሙ ጋሰለ እያለ ሲጠራው አያ አዳነ ግን በሥሙ አፍሮና በማንነቱ ተሸማቆ ስም በቀየረው አቶ አረሩ በሽቃ በማያስፈልገው ቦታ ሁሉ “አረሩ” ብላ እየተጣራች አስቸገረችው፡፡ ይኸንን የአያ አዳነን ጥኑ አቋም የተመለከቱ ሽማግሌዎችም አረሩን በፈለገው ስም ጋሰለ ብላ እንድትጠራው  አያ አዳነን ቢለምኗትም “ሥምን የሚያወጣው ወላጅና እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ እናቱ እማማ ሐብትሽ ባወጡለት ሥም ነው የምጠራው” ስትል በአቋሟ ጠናች፡፡ 

ባያ አዳነ እምቢተኝነት ያልተደሰተው የድሮው አረሩ ያሁኑ አቶ ጋሰለ በበኩሉ “አዳነ ጋሰለ ብሎ ታልጠራኝ ምላሱን እቆርጠዋለሁ” እያለ በሰፈሩ ማስወራቱን ቀጠለ፡፡ ዳሩ ግን ጋሰለ የሚባል ሥም ከአያ አዳነ አንደበት እንኳን በውኑ በህልሙና በቅዠቱም አልወጣ አለ፡፡ እንዲያውም አያ አዳነ በበነነ በተነነው “አረሩ….” የሚለውን ቃል ከወትሮውም በበለጠ እያነሳች አቶ ጋሰለን ማሳቀቁንና እንደዚህ ዓይነት በራስ ተሸማቆ ሥምን የመቀየር ባህል እዳይለመድ ማስተማሩን ቀጠለች፡፡ 

አቶ ጋሰለና አያ አዳነ በእንዲህ ዓይነት ውጥረት ውስጥ ሳሉ በአንድ የሰንበት ቀን አያ አዳነ አቶ ጋሰለ ጋቢውን ተከናንቦ ድንኳን መስሎ አህያው አረሩ ሳር ከሚግበት መስክ ተቀምጦ አየው፡፡ አያ አዳነም በአቶ ጋሰለ አጠገብ ስታልፍ “ደህና አደርክ አረሩ” የሚል ሰላምታ አቀረበች፡፡ አቶ ጋሰለ ሰላምታውን እንዳልሰማ ሁሉ “ምን አልክ?” ሲል በንዴት ጠየቀ፡፡ አያ አዳነም  በሽመሉ አለሌውን አረሩን እየጠቆመ “ያኛውን አረሩ ነው!” ሲል መለሰ፡፡ 

እናቱ እማማ ሐብትሽ ያወጡለትን ስም በማንነቱ አፍሮ እንደቀየረው አቶ አረሩ ብአዴንም እናቱ ህወሀት ያወጣችለትን ሥም በማንነቱ አፍሮ በድንገት ቀየረው፡፡ በአለሌው አረሩ ሥም እንደተሰየመው አቶ አረሩ ሁሉ ብአዴንም እናቱ ህወሀት ባወጣችለት ሥምና በባርነት ግብሩ ተሸማቀቀ፡፡ ይህ የተሸማቀቀ ውርጃ ድርጅትም ሥሙን ወደ አዴፓ ቀየረና አረፈ፡፡ 

ዳሩ ግን ጋሰለ የሚለው ስም የአቶ አረሩን መልክና ምንነት እንዳልቀየረው ሁሉ አዴፓ የሚለው ሥም የብአዴንን መልክና ምንነት አይቀይረውም፡፡ አዴፓ የሚለው ስም ብአዴን ለሰላሳ አመታት በአማራ ሕዝብ የፈጠመውን ወንጀልና ክህደት እንደ እንዶድ አያፀዳውም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን የህወሀት አጋሰስ ሆኖ እየተጫነ ያዘረፈውን ሐብት አያስመልሰውም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን የአማራን ዓይን ጨፍኖ ለህወሀት ያስረከባቸውን ራያን፣ ሁመራና ወልቃይትን አይመልስም፡፡ 

አዴፓ የሚለው ማታለያ ብአዴን ከቢሮው ጣራ አልሞ ተኳሽ አንጠልጥሎ ባህርዳር ያሰዋቸውን ወጣቶች ነፍስ አይመልስም፡፡ አዴፓ የሚለው ጅል ስም ብአዴን በህወሀት አሽከርነት በድብቅ ስፍራዎች ያስቀበራቸውን፣ ያሰለባቸውን፣ ያስገረፋቸውን፣ ያስጠለፋቸውና አካለ ጎደሎ ያስደረጋቸውን ዜጎች አይታደግም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን በአምባ ጊዮርጊስ፣ በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ዳንግላ፣ ቡሬ፣ ወልዲያ፣ ማጀቴና ሌሎችም ቦታዎች ያስፈጃቸውን ዜጎች አያስረሳንም፡፡

አዴፓ የሚለው ማታለያ ብአዴን “አያገባኝም” እያለ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በጉራፈርዳ፣ በጎሬ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በሀገረ ማርያምና ሌሎችም ሥፍራዎች ያስፈጃቸውንና ያሰደዳቸውን አማሮች ታሪክ አይፍቀውም፡፡

ስለዚህ አቶ ጋሰለ አረሩ ነው፡፡ አዴፓም ብአዴን ነው፡፡ እማማ ሐብትሽ  ለልጃቸው ያወጡለት ሥም አረሩ ነው፡፡ ከአማራ መቃብር ሪፐብሊኳን ለመመስረት አጋዥ ልጆች የወለደችው ሕወሀትም ለበኩር ልጇ የሰጠችው ሥም ብአዴን ነው፡፡ 

አረሩም ሆነ ብአዴን ካለ እናቶቻቸው ፈቃድ ሥማቸውን መቀየር ክህደት ነው፡፡ አረሩ ሺ ጊዜ ሥም ቢቀይር እናቱም ሺ ጊዜ እማማ ሐብትሽ ናት፡፡ ብአዴንም ሺ ጊዜ ሥም ቢቀይር እናቱ ሺ ጊዜ ህወሀት ናት፡፡ በአፈጣጠራቸው አፍረው አረሩም ሆነ ብአዴን ሥማቸውን ቢቀይሩም እናታቸው፣ መልካቸው፣ ግብራቸውንና ታሪካቸው ዘላለማዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ መልካቸውን፣ ግብራቸውንና ታሪካቸውን በሚገልጡትና እናቶቻቸው ባወጡላቸው ሥሞች አረሩና ብአዴን ተብለው ቢጠሩ መልካም ነው፡፡ ጋሰለ አረሩ አዴፓም ብአዴን ነው፡፡  

ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

One Response to ጋሰለ አረሩ አዴፓም ብአዴን ነው!

  1. How much did you paid berhe from the Mekele group? Bereket slavery beadin is different than general Asamnew adp , though there are some .

    Avatar for Kefafay yieodem

    Kefafay yieodem
    January 5, 2019 at 11:07 pm
    Reply

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.