/

መረጃ – የነሸዋፈራው ቁማር

1 min read

የጥበብ ላይ ቁማርተኞች

ክንፉ አሰፋ

አንጋፋዋ አርቲስት አለምጸሃይ ወደጆ ወደ ሃገር ቤት ስትገባ፣ አንዲት የጥበብ ፈርጥ ሮጣ እንደ እባብ ተጠመጠመችባት። ከሌሎቹ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በተለየ ተፍለቅልቃ ነበር። አለምን አቅፋ እንደያዘቻት፣ በግራ ጆሮዋ ውልብ ያለው ቃል ግን ደስታዋን በመቅጽበት ነጠቀው። “አቆሸሸቻት” የሚል ቃል ነበር ከሕዝቡ አቅጣጫ እንደ እጅ ቦንብ የተወረወረው። ቃሉ የዚህች እህት ልብ ለሁለት ሲከፍለው ከፊትዋ ላይ ይነበባል።

በሃሳብ መንገድዋ ተጭና ወደኋላ ስትጓዝ፣ በበረከት ስምዖን መጽሃፍ ምረቃ ላይ ታሳይ የነበረው ማሽቃበጥ ትዝ ሳይላት አልቀረም። የደደቢቱ ጉዞ አጋፋሪነት በአዕምሮዋ ውልብ ማለቱ እርግጥ ነው። “ኩራዝ ሙዚየም ይገባል!” ስትል በሕዝብ ገንዘብ ከመኒ-ቴክ (ሜቴክ) ጋር አብራ የቀለደችበት ስራዋ ፊትዋ ላይ ሊደቀንም ይችላል።…. ግራና ቀኝ ሳትመለከት የተሰበረ ልቧን ይዛ ወደመጣችበት ተመለሰች። ከዚያ በኋላ በየትኛውም መድረክ ላይ አልታየችም። አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ።

አንገት የተበጀልን የኋላውን ዘወር ብለን እንድንመለከት ነው። “የሕዝብ ሃብት ነን” እያሉ መፈክር ከማሰማት ጎን ለጎን ለዚህ ሕዝብ ምን አድርጌ አውቃለሁ? ብሎ መጠየቅ በራሱ አርቲስት ሳይሆን፣ ሰው መሆንን ይጠይቃል። አንዳንዴ ዘወር ብሎ ያደፈ ጉድፍን መመልከትም የፊቱን ለማጥራት ይጠቅማል።

አንቱ ብለን የምንጠራቸው አርቲስቶቻችን ከስርዓቱ ጋር በነበራቸው ልዩ የጥቅም ትስስር ጥበብን ማርከሳቸው አንድ ነገር ነው። ከህወሃት ጋር ሲደንሱ ያቆሸሹት እድፋቸውን ሳያጸዱ፣ ከመጣው ጋር ለመጣበቅ መሞከር ደግሞ ዋጋ እንደሚያስከፍል ያቺ ክስተት ብቻ በቂ እማኝ ናት። “ማንም ሰው በቆሸሸ እግሩ በአዕምሮዬ ውስጥ እንዲረማመድ አልፈቅደም” የሚለውን የማሃትማ ጋንዲ ንግግር ያስተውሏል።

ጥበብ አንድን ሕብረተሰብ የምንለውጥባት እንቁ ሃብት እንጂ ገበያ ወጥታ እንደ ሸቀት የምንቸበችባት እቃ አይደለችም። ጥበብ በገንዘብ የምንተምናት፣ በገንዘብ የምንመነዝራትና በገንዘብ የምንለውጣት ቁስ አይደለችም። ጥበብ ከበዳዮች አትወግንም። ይልቁንም ወጀብና ነውጥን ተቋቁማ ለእውነት ትቆማለች።

በኪነ-ጥበብ መሰላል ከፍ ብለው ወጥተው ከበዳዮች ጋር የመወገናቸው ማሳያ የሚሆነው ዛሬ ሊነግሩን የሚሞክሩት ተረት-ተረት ሳይሆን በገሃድ የተገበሩት ስራቸው ብቻ ነው።

“አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” እንዲሉ አንዳንዶቹ ሜዲያ ላይ ወጥተው ሲናገሩ ምን ያህል ከእውቀት የጸዱ መሆናቸውን ያመላክቱናል። ስፓኒሾች “La ignorancia es atrevida” ይላሉ። ድንቁርና ሲበዛ ደፋር ናት እንደማለት ነው። ድንቁርና በራሱ ከልክ በላይ ሲሆን እጅግ አደገኛ ይሆናል እንጂ ለመማር ፈቃደኛ እንዳለመሆን አሳፋሪ አይደለም ይለናል ቤንጃሚን ፍራንክሊን።

አርቲስት ዝናብዙ ጸጋዬ ሜድያ ላይ ቀርቦ ሜቴኮች “እያዋከቡ ገንዘብ እንደሚከፍሉት” ሲናገር ነበር በአርቲስቶቻችን የእውቀት አድማስ ላይ ተስፋ የቆረጥነው። በዚህ ተደምመን፣ በአፋችን የጫንነውን እጃችንን እንኳ ሳናነሳ፣ ታሪክ ሰራሁ የሚሉ አርቲስቶች “ጉድ በል ጎንደር” አሰኙን።

አጥቢያ ጀግኖች ከበረሃ ሳይሆን ይልቁንም ከየማጡ ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ፤ “ከመቶ በላይ እስረኞችን አስፈትተናል” የሚሉ ድል አድራጊ አርቲስቶች ደግሞ በቴሌቭዥን ተከስተዋል። ጀግኖቹ እስረኞቹን ያስለቀቁት ልክ እንደ አሜሪካው “ፕሪዝን ብሬክ” ድራማ ይሁን ወይንም በሌላ መንገድ በውል አልገለጹልንም። እድሜ ሰጥቶን የማንሰማው የጀግንነት ጥግ የለም። “ሁሉ ሆነ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ” አሉ አበው። ጮክ ብሎ ለመናገር ከመቸኮል በፊት ጮክ ብሎ ማሰብ መቻል ጥበብን ይጠይቃል።

እረፍት አጥተው ውስጥ ውስጡን ለነጻነት ሲታገሉ ነበር አርቲስቶቹ። ይህን በቲቪ ላይ ቀርበው ሲነግሩን የአይኖቻቸው ሽፋሽፍቶች እንኳ አይከደኑም ነበር። ከንገፈቸውም አይደርቅም። እጃቸውም አይንቀጠቀጥም። በቆብ ላይ ሚዶ መሆኑ ነው። ጥበብና ትግል – ዱባና ቅል። ጥበብ ዱባ ስትሆን ትግሉ ደግሞ ቅል ነው። ዱባና ቅል ለየቅል!

ሁለቱ “አርቲስቶች” አይናቸውን እንኳ ሳያሻሹ “እስረኞችን አስፈትተናል” ሲሉ እርግጥም እየሰሩ ያሉት የአዲስ ፊልም ርዕስ ያልመሰለው ተመልካች አልነበረም። በጋዜጠኛው ጥያቄ ቃላቸውን ደገሙትና አረፍነው እንጂ። ቅጥ ያለፈው ድፍረታቸውን እና በራስ የመተማመናቸውን ነገር ያለማድነቅ አይቻልም። በዚህ ደረጃ መተርተር ያስቻላቸው ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም። ገድላቸው እውቅና ተሰጥቶት እጩ ተሸላሚ ለመሆን ፈልገው ይሆን?

አንደኛ ደረጃ የውሸት ተሸላሚ ይሆናሉ። ሳያስቡት ጥግ የሚያስይዝ ጥያቄ ሲወረወርባቸው ግዜ ትንፋሽ አጥሯቸው መዘባረቅ እንደጀመሩም ግልጽ ነው። ሙስና እግር እና እጅ አውጥቶ በሚራመድበት ስርዓት ውስጥ ዋና ተዋንያን ስለነበሩ፣ መተርተር አያሳፍራቸውም። በሚሊዮን ሲለቀቅባቸው የነበረ የሜቴክ ብር አናታቸው ላይ ወጥቶ እንዳሰከራቸው መገመት አያዳግትም። ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚያውቀውን በጸሃይ የተመታ ታሪክ ለማወላገድ መሞከር ግን ከንቀትም የመነጨ ይመስላል።

እርግጥ ነው። ሰራዊት ፍቅሬ እና ሸዋፈራው ደሳለኝ ምናባዊ ገፀ-ባሕሪ ሆነው በገሃዱ አለም የቀረቡ እንጂ ቃለ-ምልልስ የሚያደርጉ አይመስሉም። በሌላው ላይ ጣት ለመጠቆም ተደራጅተው የመምጣታቸው ሙከራ ግን አሌ የሚያስብል ነው።

ጠብ የሚል ነገር የሌለው እንቶ ፈንቶ ሰብቃቸውን በማየት ግዜ ማባከን ከልሆነ በቀር፣ በኤል ቲቪ እና በፋና ላይ ወጥተው የሚናገሩት ነገር የንቀትና ትእቢታቸውን ልክ እንደ መስታወት የሚያሳየን መረጃ ነበር።

ሀገር በቁም ስትሽጥ አልሰማንም አይሉም። በወገን ላይ የግፍ ዱላ ሲወርድበት አላየንም ሊሉም አይችሉም። የዘረፋ ማስታወቂያዎችን እያሽሞነሞኑ ሲያቀርቡ ከርመው እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ለመምሰል መሞከራቸው ሌላውን ሰው የሚመለከቱበት መነጽር እንደ ጭጋግ የደበዘዘ መሆኑን ይጠቁመናል። የራሳቸውን ጉድፍ ሳያጠሩ ሌላው ላይ የሚወረውሩት ድንጋይ በሙሉ እየዞረ አናታቸውን መቀጥቀጡም የሚጠበቅ ነው።

የድፍረት ቀበቶ ታጥቀው፣ ውሸትን ተጫምተው፣ የይሉኝታን ቆብ አውልቀውና የጥበብን ካባ ለብሰው ህዝብ ፊት ብቅ አሉ። በቴሌቭዥን። አንዴ ገባንበት … ብለው ተስፋ በመቁረጥ ካልሆነ በቀር፤ ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ጥቁር ብሎ መዘላበድ ከትዝብት አያልፍም። እንደሰው ተፈጥረው እንዳውሬ ከሚያስቡ ሰዎች ከዚህ በላይ አይጠበቅም። ጉድፍን ሸፋፍኖ፣ ስምን ለማጽዳት ተራራ መቧጠጥ ከመሞከር ይልቅ በሁለት ቃላት መገላገል ይቻል ነበር። ሕዝብን በድለናል! ይቅርታ እንጠይቃለን። ነጻ የምታወጣቸው ይህች ቃል ለምን እንደምትተናነቃቸው ግራ ይገባል።

የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ከታጠቀ ህወሃት ጋር ሞግተው፣ ሞትን መርጠው ጥበብን ሰውተው እስረኞችን እንዳስፈቱ የሚተርክ ዲስኩር ከሚነግሩን ይልቅ ይቅርታ ብለው ከዚህ ሁሉ ጭንቀት እንዲገላገሉ መካሪ እንዳጡ ያስታውቃል።

የይሉኝታን ጉዳይ ከጌቶቻቸው ወርሰዋታል። ማፈር አጠገባቸው የለችም። እውነት ርቃቸዋለች። ክህደታቸውም ማለቂያ የለውም። ታላቁ መሪን በጥበብ ስም የወርቅ ብዕር የሸለሙት የተረሳ መስሎ “አግኝቻቸውም አላውቅም” ብሎ ከመሸምጠጥ በላይ ክህደት የለም።

ሲጀምር ጫረታ ተወዳድሬ አላውቅም ይለንና፣ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ጫረታ አሸንፎ ስለሰራው የሃምሳ ሚሊዮን ፕሮጀክት ይነግረናል ሰራዊት ፍቅሬ። ድራማ የሚሰሩም ይመስላል። ድራማም ቢሆን በዘፈቀደ የሚሰራ ሳይሆን ኮንቲንዩቲ የሚባል ቴክኒክ ያለው ጥበብ ነው።

ሺፈራው ደሳለኝ ለሁለቱ ሰለተከፈለው አራት ሚሊዮን ብር ሲያወሳ ስለ አራት ሚሊዮን ሳይሆን ስለ አራት ሳንቲም የሚያወራ ነው የሚመስለው። ከክፍያዎቹ ሁሉ ትንሽዋ መሆንዋ ነው። ይህች ሃገር አጥንትዋ እስኪቀር ድረስ ስንቱ ነው የጋጣት? በዕውቀትና በልምድ የበለፀጉ የጥበብ ዋርካዎች እንዳላፈራች ሁሉ፣ ማንነትን ያመከኑ የጥበብ ሸቃዮች መፈጠራቸው እንግዳ አይሆንም። ላቡን አንቆርቁሮ ሳይሆን ዘርፎ ሃብት ያካበተ ቡድን የህሊና አይን አይኖረውም።

ከተደራጁ ሌባዎች ጋር አብረው ሲያሽቃብጡና ሲያጎበድዱ ከርመው ዛሬ ይቅርታ ማለት አንድ ነገር ነው። ያንን ሁሉ ነገር ባልሰማ እና ባለየ አልፈው በሌላ አጀንዳ ብቅ ማለት ግን ህሊና ቢስነት ይሆናል።

እንደ ፖለቲካ ነጋዴው ሁሉ የጥበብ ነጋዴም አለ። የሚጠበቀው የጥበብን ካባ ደርቦ ኮፍያ መቀየር ብቻ ነው። በነፈሰው ለመንፈስ እያኮበኮቡ ያሉ እንደዚህ አይነት የጥበብ ቁማርተኞችን ሕዝቡ ሊዋጋቸው ግድ ይላል።

2 Comments

  1. ነገሩን የበለጠ የሚወሳስበው በስነጥበብም በግል ንግድም ላይ መሳተፋቸው ይመስላል፡፡ በአገራችን ታሪክ ግን እንደዚህ የተጣመረ ግኑኝነት ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የእነዚህ ሃብት ጊዜው ሆኖ በሚሊየን መቆጠሩ ካላስደነገጥን በስተቀር፡፡ በስነጥበብ ሥራ ላይ ከተሰማራ ከመንግሥት ጋር የተገናኘ ንግድ መስራት የለባቸውም ነው? ንግዱ ሁሉ በወያኔ የተበከለ ነው፡፡ ትንሽ ለመፍረድ ያስቸግራል፡፡

    በእርግጥ ዝናብዙ የሚሉት የውሽት ጎተራ ነው፡፡ከሁሉም እንዳያጣ ሲዘላብድ ነው የተገኘው፡፡ የሽዋፍፈራ የሚሉት ደግሞ የማያስቅ፣ አገራችን በስነጥበብ አዋቂዎች ድሃ እንደሆንን የሚያስታውሰን ሰውዬ ነው፡፡ በስነጥበብ ውስጥ ችሎታው ምንድነው? ንግግሩን ለሰማም ድንቁርናም የሚያጣው አይመስልም፡፡ ሎሎች ባለሙያዎችን ክዚህ ሰው ጋር ደባልቆ ማውራትም ሃጥያት ነው፦)

  2. የኢትዮጵያን የቲያትር ጥበብ ወደመቃብር የወረወሩትና የተጠቀሱትና ብጤዎቻቸው ናቸው፡፡ ባለፉት ሁለት መንግሥታት አንድ የመድረክ ቲያትር ከአንድ ዓመት በላይ ይታይ ነበር፡፡ በኘሮግራሙ ቀንና ሰዓት የነበረው ሰልፍ ትዝ ይለኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ገና የምረቃው ዕለት በአምባሳደርና በሲኒማ አምፒር የሚከፈላቸው ወጣቶች ተመልካች ለማግኘት የሚያደርጉት ውትወታ ከታክሲ ረዳቶች ጥሪ ጋር መቶ በመቶ ተመሳሳይነት አለው፡፡ የቲያትር ጥበብ መቸ ከሙታን እንደሚነሳ መሥራት አለያም ቆሞ መጠበቅ ነው፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.