/

ዛሬ በአርባምንጭ ከባድ የመኪና አደጋ ተከሰተ፣ አደጋውን ያደረሰው አሽከርካሪ በፀፀት ህይወቱን አጠፋ!

1 min read
1

 

በአርባምንጭ ከተማ ዛሬ ጠዋት በደረሰ የመኪና አደጋ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ በቦታው ከነበሩ አይን እማኞች በተገኘ መረጃ መሰረት አደጋው የተፈጠረው በፍጥነት ሲያሽከረክር የነበረው የሲኖ ትራክ አሽከርካሪ ባለ 3 እግር ባጃጅን ለማትረፍ የቀኝ መስመሩን ትቶ ወደ ግራ በመታጠፍ ፒካፕ መኪናን በመግጨት ከመስመር ያስወጣው ሲሆን፣ በእግረኛ መንገድ ስትጓዝ የነበረች የ13 ዓመት ሕጻንን ጨምሮ በፒካፕ መኪናው ውስጥ የነበሩ 3 ተሳፋሪዎች ሕወታቸው አልፏል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ም/ኢንስፔክተር አባሃጅ ጉጆ እንደገለጹት ዛሬ የካቲት 19/2011 ዓ.ም ጠዋት 2 ሰዓት ላይ በአርባምንጭ ከተማ ወዜ ቀበሌ ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ በነበሩ መኪናዎች በተፈጠረ አደጋ የ5 ሠዎች ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡ በሆስፒታል ጉዳት ደርሶባቸው እየታከሙ ያሉ ስላሉ የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ከስፍራው እየተነገረ ነው፡፡ ይሕ በእንዲህ እንዳለ ለአደጋው መንስኤ የነበረው የሲኖ ትራክ አሽከርካሪው በፀፀት ራሱን ከመብራት ታወር ላይ በመጣል ሕይወቱ ማለፉን ም/ኢንስፐክተር አባሃጅ ገልጸው በአደጋው ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

አሽከርካሪዎች ከተፈቀደ ፍጥነት ወሰን በላይ ባለማሽከርከር በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ እንደሚጠበቅባቸው የከተማው ፖሊስ አዛዥ ም/ኢ/ር አባሃጅ ጉጆ አሳስበዋል ሲል የጋሞ ዞን ህዝብ ግንኙነት አስታውቋል፡፡