የአማራ ክልል ምክር ቤት Vs ከትግራይ የህዝብ ግንኙነትና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተሰጠ መግለጫ

Filed under: የዕለቱ ዜናዎች |

በአማራና በትግራይ ወንድማማች ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ መልካም ግንኙነት ውስጥ ልዩነት በመፍጠር ወደ ጦርነት የሚያስገባ ጸብ አጫሪነት ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው የአማራ ክልል ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

በትግራይ ክልል አመራሮች በኩል የጦርነት ቅስቀሳና የሰራዊት ዝግጅቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የአማራ ክልል ምክርቤት በአጽንዖት መክሯል፡፡

የምክር ቤቱ 5ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ከየካቲት 26 እስከ 29/2011 ዓ.ም እየተካሄደ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ የወሰናቸውን ዐበይት ጉዳዮች በተመለከተ የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው እንደተመላከተው ከትግራይ ክልል ጋር እየተፈጠረ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ምክር ቤቱ በዝርዝር ገምግሟል፡፡

ሁለቱ ሕዝቦች በታሪክ፣ በባህል፣ በኃይማኖትና ሀገርን በመገንባት ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ እንዳላቸው ምክር ቤቱ መገምገሙን አቶ አሰማኸኝ አመላክተዋል፡፡

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት፣ ጸብም ሆነ መቃቃር እንደሌለና አብረው የኖሩና የሚኖሩ መሆናቸውን ምክር ቤቱ በአጽንዖት መገምገሙንም አስታውቀዋል፡፡

ሕዝቦቹ ጥረው ግረውና ለፍተው የሚያድሩ፣ ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነታቸው ወደፊትም የሚዘልቅ መሆኑን እምነት እንዳለው ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ነው ያሉት አቶ አሰማኸኝ፡፡

በአማራና በትግራይ ወንድማማች ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ መልካም ግንኙነት ውስጥ ልዩነት በመፍጠር ወደ ግጭትና ጦርነት እንዲገቡ የሚደረግ ማንኛውም ትንኮሳ፣ ማንኛውም ጸብ አጫሪነት ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው ምክር ቤቱ መወሰኑንም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር አንዳንድ አካላት የሚያሳዩት ድርጊት በምክር ቤቱ ተቀባይነት እንደሌለውም ተገምግሟል፡፡

ከትግራይ ክልል አመራሮች በኩል የጦርነት ቅስቀሳዎች፣ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት፣ ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች ሰራዊት የማቅረብ እና አንዳንድ ፀብ አጫሪ አካሄዶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፤ ከዚህ ድርጊታቸውም እንዲታቀቡ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

በትግራይ ክልል የመሸገው፣ በተለይ በለውጡ የተገፋው፣ ስልጣኑን ያጣው፣ ዘራፊው ቡድን፣ ጦርነት ለመቀስቀስ ቢፈልግ እንኳ ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ዝም ብሎ ይመለከተዋል የሚል እምነት እንደሌለው ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው፡፡

ከእርስ በርስ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም ያለው ምክር ቤቱ የትግራይ ሕዝብ ለመሸጉትና ሕዝብን መከታ አድርገው ለሚንቀሳቀሱት ጥሪና ትንኮሳ ምንም አይነት መልስ ባለመስጠት ሰላም ወዳድነቱን በተግባር እንዲያስመሰክር ምክር ቤቱ ማሳሰቡን አቶ አሰማኸኝ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በኩልም ግጭት ከሚፈጥሩ ትንኮሳዎችና የትግራይ ሕዝብን ስጋት ላይ ከሚጥሉ ፀብ አጫሪ ንግግሮች ማንኛውም አካል እንዲቆጠብ፣ እንዲህ ዓይነት ንግግሮች ለሰላም ፈላጊው የአማራ ሕዝብ እንደማይመጥኑትና ይህን በሚያደርጉ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ምክር ቤቱ መወሰኑም ተመላክቷል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት የአማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ ሰላም ለመጠበቅ፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የአማራን ሕዝብ ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

(አብመድ) ግርማ ተጫነ

===========

ከትግራይ የህዝብ ግንኙነትና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተሰጠ መግለጫ

ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ ዋነኛ አጀንዳችን ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ነው!!

የአማራ ክልል ምክር ቤት፣ ከየካቲት 26-29/2011ዓ/ም እያካሄደው ባለው 5ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 12ኛ መደበኛ ጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አስመልክቶ፣ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ዳይሬክተር፣ የካቲት 27/2011 ዓ/ም ለአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በዚህ መግለጫ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አስተላለፉዋቸው ከተባሉት ጉዳዮች መካከል የትግራይ ህዝብና መንግስት ጦርነት ለማካሄድ እያደረጉት ካለው ቅስቀሳና ዝግጅት እንዲቆጠቡ የሚል ማስጠንቀቅያ አዘል መልእክት ተሰራጭቷል፡፡

ነገር ግን የትግራይ ህዝብና መንግስት የጦርነት አስከፊነት ስለሚረዱ፣ ዋነኛ አጀንዳቸው የሆነው ሰላም ማስፈን፣ ዲሞክራሲ ማስፋትና መልካም አስተዳደር ማንገስ እንዲሁም ፈጣንና ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ለማረጋገጥ በመታተር ላይ ናቸው፡፡ የትግራይ ህዝብና መንግስት በ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ወቅት፣ ወታደራዊ ፋሽሽት ደርግ ለመደምሰስ በተደረገው መራራ ትግል፣ የአማራ ህዝብ፣ ከወንድሙ የትግራይ ህዝብ ጎን ተሰልፎ ተገቢው መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ በመሆኑም የትግራይ ህዝብና መንግስት የታገሉለትን ህዝባዊ መሰመር አንግበዉ ወደፊት ከመገስገስ ዉጭ በወንድም የአማራ ህዝብ ላይ አፈሙዝ የሚያዞርበት አንዳች ምክንያት የላቸዉም፡፡

በመሆኑም የትግራይ ህዝብና መንግስት ባለፉት ዓመታት፣ በተለያዩ ችግሮች የባከኑባቸውን ጊዚያት ለማካካስ፣ ሁለመናቸው ያቀዱት የዲሞክራሲና የትራንስፎርመሽን ዕቅድ ለማሳካት በመሯሯጥ ላይ ናቸው፡፡ በተያያዝነው የበጋ ወቅትም ቢሆን አፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት በማሳለጥ ለ2011/2012 የክረምት ስራ ቅድመ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

ይልቅኑም ማነው በግላጭ ትንኮሳና የጦርነት አታሞ ሲጎስም የከረመው የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ ምላሹ ሰላም ወዳድ ዜጋ ምስክርነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሽፍቶች ጨምሮ የተለያዩ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች የተለያዩ የሚድያ አማራጮችን ተጠቅመው፣ ላለፉት ሶስት ዓመታት፣ ያለእረፍት ቀንና ለሊት የጦርነት ቅስቀሳና ቱንኮሳ ከማካሄድ አልፎው፣ በትግራይ ወሰኖች ሄድ መለስ ሲሉ ቆይተዋል፡፡

ትላንት የትግራይ ክልል ብሄር ተወላጆች ብቻ በመሆናቸው በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በድንጋይ ተቀጥቅጦው ሲገደሉ፣ ከ50 ሺ በላይ ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩት ሃብትና ንብረታቸዉ ተዘርፈው፣ እትብታቸው ከተቀበረበት ቀዮ ሲፈናቀሉ፣ እንዲሁም የአማራና የትግራይ ህዝብ እንዳይገናኙ አውራ መንገዶችን ዘግቶ ባይሳከለትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሻክር የተፍጨረጨረዉ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሉ ታሪክ ይቅር የማይለው በደልና ክህደት ፈፅሟል፡፡

በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብና መንግስት ነጋ ጠባ ከፅንፈኛ ሃይሎች የሚወረወርባቸዉ የቃላት ጦርነትና ትንኮሳ ከልክ በላይ ያለፈ ቢሆንም፣ ጦርነት ለየትኛውም ወገን እንደማይጠቅም አሳምረዉ ስለምያዉቁ፣ እስከ አሁን ድረስ ትዕግስትን መርጠዋል፡፡

ይህንን እውነታ ንፁህ ህሊና ያለው ፍጡር የሚያውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ ያደረጉበት ምክንያት ከዋነኛ የሰላምና የልማት አጀንዳቸው ላለመራቅ ነው፡፡ ስለሆነም ትላንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ህዝብና መንግስት ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ጦርነታቸዉ ከድህነት ጋር በመሆኑ ማንኛውም ሰላም ወዳድ ዜጋ ስጋት ሊገባዉ አይገባም፡፡

በአጭሩ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዋነኝነት የአማራና የትግራይ ህዝቦች ሰላም ተረጋግጦ የልማት ተቋዳሽ የሚሆኑት፣ በሃገራችን ሕገ-መንግስት ተከብሮ፣ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ፣ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ተጠናክሮ ሲቀጥል መሆኑ የማይታበል ሓቅ ነው፡፡

ሰለሆነም የአማራ ክልል ም/ቤት 5ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 12ኛ መደበኛ ጉባኤ በፀጥታ ጉዳዮች አስመልክቶ በትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ አስተላልፎታል የተባለው ዉሳኔ ለአማራም ሆነ ለትግራይ ህዝብ ሰለማይበጅ ጉዳይን ዳግም እንዲያጤነዉ የትግራይ ህዝብና መንግስት ጥሪአቸውን ያቀርባሉ፡፡

ዘልአለማዊ ክብር እንከን ለማይነካቸው የትግሉ ሰማእታት!!

የትግራይ የህዝብ ግንኙነትና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ-ትግራይ
የካቲት 28/06/2011 ዓ/ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.