‹‹የተወሰደው እርምጃ አግባብነት የሌለው ነው››-የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

1 min read

አብዱልቃድር መስጂድ ላይ የተወሰደው እርምጃ አግባብነት የሌለው ነው ሲሉ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱላዚዝ ወጉ ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ትናንት በአብዱልቃድር መስጂድ የተፈጠረው ችግር ከከተማ አስተዳደሩ እውቅና ውጭ ነው ብሏል።

ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት አካባቢ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሚገኘው አብዱልቃድር መስጂድ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሰዎች ላይ ለሶላት ሲጠቀሙበት የነበረውና ለዓመታት በይዞታ እንዲጠቃልለት መስጂዱ ጥያቄ አቅርቦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉዳዩ ተይዞ በማጣራት ላይ ባለበት ሁኔታ የፖሊስ ደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች “ቦታውን ልቀቁ” በሚል እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ20 ዓመት በላይ ያስቆጠረው መስጂድ ከቦታ ጥበት አንጻር የማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጠው ከሶስት ዓመት በፊት መስጂዱ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውሰዋል።

መስጂዱ ጥያቄውን ካቀረበ በኋላ የአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ለቢሮ ማስፋፊያ ግንባታ ቦታውን እፈልገዋለሁ በማለቱ ምክንያት መስጂዱና ወረዳው ክርክር ውስጥ በመግባታቸው ጉዳዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተይዞ እየተጣራ እንደሆነም አመልክተዋል።

ይህ የይግባኝ ክርክር ባለበት ሁኔታ “ፖሊስ ቦታው ላይ ህገወጥ ግንባታ አድርጋችኋል” በሚል በወቅቱ በቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ነው የሚናገሩት።

“በተወሰደው እርምጃም” በነበሩ ሰዎች ላይ የመቁሰል ጉዳት መድረሱንና የታሰሩ ምዕመኖችም እንዳሉ ጠቅሰዋል ።

መስጂዱ ለሶላት በሚጠቀምበት ቦታ ላይ ምንም አይነት ህገ ወጥ ግንባታ እንዳላካሄደም ገልጸው ቦታው በይገባኛል ክርክር ላይ ያለ በመሆኑ የሱን ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በክርክር ላይ ባለ ቦታ ምክንያት “የተወሰደው እርምጃ አግባብነት የሌለው ነው” በማለት ነው ምክርቤቱ የሚገልጸው።
ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢጠየቅም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

የከተማ አስተዳደሩ እንዳስታወቀውም ትናንት በአብዱልቃድር መስጂድ የተፈጠረው ችግር ከከተማ አስተዳደሩ እውቅና ውጭ እንደሆነ ነው።

ከመስጂዱ ጋር በተያያዘ የከተማው አስተዳደር ለአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ቦታው ለቢሮ ግንባታ ይሰጥ የሚል ምንም አይነት ውሳኔና ትዕዛዝ እንዳላስተላለፈም ገልጿል።

ምንም ዓይነት ጥያቄ ቢኖር በመነጋገር መፍታት እየተቻለ አላስፈላጊ ጉዳት ወደሚያደርስ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ከየትኛውም አካል የማይጠበቅ ተግባር አንደሆነም ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉዳዩ ከዕውቅናው ውጪ እንዴት እንደተፈጸመና በቀጣይ መጣራት የሚያስፈልጋቸው ነገሮችን በሙሉ በመፈተሽ በመዋቅሩየማስተካከያ እርምት እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.