ዘረኛነት። – ዳዊት ዳባ

1 min read

ዳዊት ዳባ።

Saturday, January 29, 2019

 

ዘረኛነት ምንድን ነው?። ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይ?። ካለ ዘረኛው ማነው?። ዘረኛነት ላይ ኢትዬጵያዊ አረዳዳችን ከሌላው ዓለም የተለየ ነው። ይህ ለምን ሆነ?። ማን፤ ለምንና እንዴት? አገሬውን ማሳሳት ቻለ። ከእውቀት ማነስ ወይስ እያወቁ?። “ዘረኛነት” ላይ ህፀፅ በሆነው አገራዊ አረዳዳችን ምክንያት ሰላማችን፤ መልካም ግንኙነታችንና አንድነታችን ላይ የጋረጠውስ አደጋ?፤ እንዲሁም አገራዊ ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ላይ መፍትሄ ፍለጋውን ማወሳሰቡን። ይህ አገራዊ ህፀፅ ማስተካከያ እንዴት ይበጅለት?። ከዛስ ትክክለኛውን ዘረኛነትና ዘረኞችን እንዴት? እንታገላቸው። እነዚህና ተዛማጅ የሆኑ ጥያቄዎችን ከግምት አስገብቶ ነው ይህ ፅሁፍ የተፃፈው። ስለዘረኛነት ስፅፍ የመጀመርያዬ አይደለም። ለስለስ ባለ በተለያየ ጊዜ ክላይ የዘረዘርኳቸውን ሀሳቦች ግምት ውስጥ ባስገባ ሀላፊነት ለራሴ ሰጥቼ እኮረኩር ነበር። ዛሬ ዘረኛነት ምንድን ነው? ዘረኛውስ ማነው? የሚለው ጥያቄ ጎልቶ እየመጣ ነው። በሚያስደንቅ ሁኔተ እራስን በራስ ማስተዳደር፤ የራስን ባህል ማሳደግና የክልል ጥያቄ እኩል በአገር ደረጃ ዘረኛነት ምንድን ነው የሚለው በተገቢው ይቀመጥ የሚለው አንድ የመብት ጥያቄ ሆና እየወጣ ያለበት ሁኔታ ሁሉ ይታያል። ያም ሆኖ ለዘመናት ተቀጥቅጦ የተሰራበት የማህበረሰብ አስተሳሰብ ስለሆነ የተሳሳተውን አተያይ ማሸነፉ ቀላል አይደለም።

 

አገሬ “ዘረኛነትን” ሊካሄድበት በሚችልበት ከፍተኛ የመጠበብ ደረጃ የምታካሂድ አገር ነች። ለዚህ ዘረኞች በተገላቢጦሽ የዘረኛነት ተጎጂዎችን “ዘረኛ” አድርጎ ማስቆጠር፤ ማሸማቀቅና ማስወቀስ የቻሉበት ሁኔታ ነው ያለው፤ መንግስት፤ ቤተ አምነቶች፤ ጥበብና መገናኛዎች በማህበር ያራመዱትና በማወቅ ቀጥቅጠው የሰሩበት ስለሆነ “ዘረኛነት” ሊደርስ የሚገባው የምጥቀት ድረጃ ላይ አደርሰውታል። በዚህ ደረጃ የሚገለፅ ነውር ይዘንና- ህፀጽ እንደአገር ተሸክመን አለን ከሚል እነሳለው። በሀሳቡ አለመስማማት ይቻላል። ቁምነገሩን እንደገና ለመመርመር ቀናነቱም ቢኖር መራር እውነት ስለሆነ ለመቀበል በጭራሽ ቀላል እንደማይሆን ግምቱ አለኝ። ዋናው ነገር ቁምነገሩን አግባብ ባለው ደረጃም ተረዳነውም አልተረዳነውም “ዘረኛነት” “ዘረኛነት” ማለታችን ግን አልቀረም። ይህ አቀራረብ ጥግ የያዘ ነው እስከጭራሹም ችግርም ስህተትም አለው ብለን ብናስብም መከራከሪያውን ማንበብ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሁሉ ግድ ይላል ለማለት ነው። ለምን ለሚለው በተጨማሪነት። አገራችን ህልውና አደጋ ላይ ነው ይባልና “ዘረኛነት” ከሚጠቀሱ ከዋንኞቹ ምክንያቶች ውስጥ አንድ ነው። እንደ አንድ አገር ህዝብ የእርስ በእርስ መተላለቅና ፍጅት ተጋርጦብናል ይባልና አሁንም “ዘረኛነት” ቀንደኛ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኖ የሚቀርብበት አገር ነው እና ያለን።

 

“ዘረኛነት” ላይ ያለንን አገራዊ አረዳዳችንን ማስተካከሉና አውነተኛውን ዘረኛነት እና ዘረኞችን መታገል የጀመርን ጊዜ በትንሹ 10% የሆነውን አገራዊ ፖለቲካዊ ችግር አስወግደናል። ሰላማዊ መፍትሄ ለመስራት ሰላማዊ መንገዶችንና ጥረቶችን ምቹ ከማድረግ አኳያ ጠቀሜታው ከዚህም የጨመረ ነው ባይ ነኝ። አሁንም ጠቀሜታውን እዚህ ደረጃ አካብጄ ነው የማየው። ይህም ብቻ አይደለም አላኗኗር አላቻችል ያለን ልዩነት የተለያየ ብሄርሰብ፤ቋንቋና እምነት…ወዘተ ስላለን አይደለም። በነገሮች ላይ ያለን አረዳድ በሁሉም ነገር ላይ በሚሰኝ የተለያየ መሆኑ ነው። ከነዛ ውስጥ ዋናው “ ዘረኛነት ምንድን ነው” ”ዘረኛውስ ማነው” የሚለው ነው። በነዚህ ምክንያቶች ተነስቼ በምኞት ደረጃ የሰላም ሚንስትርን መስራቤት ትኩረት ይስባል ብያለው፤ የተከበሩ ወ/ሪ ሙፈርአት ከማል አስቤያቸዋለው፤ አገራዊ ሰላምን የሚያግዝ ሀሳብ ካላችሁ ወዲህ በሉ ሲሉ ሰለሰሟሗቸው አምኛቸው ይሆናል። ከፅሁፍም በዘለለ በዶክመንተሪ መልክ ታስቦኛል። እድሜ ለፌዴራላዊ ስርዓቱ ዛሬ ፊኒፊኔ ላይ ብቻ አይደልም የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ትምህርት ቤቶች ያሉት በየክልሉ ከአንድም በላይ አለ። ትኩረታችሁን ይፈልጋል ስል አሳስባለው። የክልል መንግስታት ዜጎቻችሁን ከተከፈተባቸው ስነልቦናዊ ጦርነት በህግ አግባብና በፖለቲካዊ ሜዳ ላይ በሁሉም አግባብ ዜጎቻቸውን መከላከል ዋንኛ ሀላፊነታችሁ ነው ባይ ነኝ።

 

አለም።

 

ዘረኛነት ረጅም እድሜ ያለው ውስብስብ ማህበራዊ ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ “ዘረኛነት” ምንድን ነው? የሚለው ላይ ሌላው አለም ያለው ግንዛቤ ግልፅና ቀላል ነው። ወጥነትም አለው። የዚህ ዘር አልያም ብሄረሰብ አገርም መንደረም ወይም ሞያ ሊሆን ይችላል ብቻ ስለሆንኩ የተሻልኩ የበለጥኩ ነኝ። አልያም እነዛ ከኛ በሰውነታቸው ያነሱ ናቸው ብሎ ማመን ነው።

 

 

አሳብያዊ ነው። በማንነታቸው ምክንያት የተወሰኑ የማህበረስብ ክፍሎችን መበደል ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችንና መብቶችን መከልከል ነው። የዚህ ሁሉ የመጨረሻ ግብ የራስን የበላይነት ማስፈን ነው። ይህንን ዓይነት የተሳሰተ እምነት ተይዞ ወደተግባር በተገባ ጊዜ ዘር በማጥፋት፤ በባርነት፤ ሙልጭ ባለ ቀማኛነት፤ በዝባዥነት፤ ቅኝ ገዥነት፤ በጭካኔ፤ ማህበረሰቡን በማሰጠንና አድሏዊ በሆነው እኩይ ግብሩ ይለዩታል። እነዚህ ዘግናኛ የሆኑ የሰው ልጆች ላይ በዘረኞች ሲፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎች ናቸው ብሎ አለም ያምናል። መዝግቦም ይዟል። እነዚህን አይነት ወንጀሎችን ተፈፃሚ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ የሚዘረጋው እቅድ፤ ህግ፤ አሰራር፤ አደረጃጀት፤ ብለሀት፤ አተራረክ፤ ማህበረሰባዊ ግንዛቤና በይልጥም ጥበብና መገናኛ ጭምር “ዘረኛ” አድርገው ይወስዱታል።

 

ዘረኛነትን በተለያየ ይዘት ይገልፁታል።

 

ሀ- ውስጣዊ {ግለሰባዊ}- ግለሰቦች በማንነታቸው የሚያፍሩበትና አልፈውም በማንነታቸው ጥላቻ የሚያሳድሩበት ሁኔታ ነው። ቋንቋቸውን ባህላቸውን ሁሉንም አይነት ማንነታቸውን የሚጠየፉበት ሁኔታ ነው። ቢችሉ ሊደብቁት አልያም ሊያጠፉት ድረስ ያለ ፍላጎት ነው።

 

ለ- ተጓዳኝ፤- ይህ በሁለት ቡድኖች መካከል አንዱ የሌላኛው ማንነት ላይ የሚኖረው ዘረኛ አመለካከት ነው።

 

ሐ- ተቋማዊ፤- በማወቅ መንግስታዊና ህጋዊ ሽፋን ኖሮት እንደሁኔታው በፖሊሲ ተደግፎ የሚደረግ ዘረኛነት ነው።

 

መ- መዋቅራዊ፤- ዘረኛነት መፈፀም ተፈልጎ ወይ ታስቦ ሳይሆን ስራ ላይ የዋሉ ህጎች፤ ፖሊሲዎች፤ አስራሮች እና አስተዳደራዊ ልምዶች ውጤታቸው ዘረኛ ሲሆን ነው። አድሏዊ ሲሆን ማለት ነው። በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እኩል ተሰሚነት እኩል ተጠቃሚ ማድርግ ሳይችሉ ሲቀር ነው።

 

በውጪው አለምም ስለዘርኛነት በተነሳ ቁጥር አብዝታችሁ ከሚመስሏችሁ ትጋባለችሁ፤ ታመልካላችሁ፤ ትጓደኛላችሁ… ስለዚህም ሁላችንም ያው ዘረኛ ነን አይነት መከራከሪያ ለማቅረብ የሚሞክሩ ጥቂት ሰገጤዎች አሉ። የበዛው ዜጋ ግን ይህ ከዘረኛነት ጋር ምንም እንደማየገናኝ ይገባዋል። አያቶቻቸው የሰሩትን አስነዋሪና ዘግናኝ ወንጀል የተቀደሰ ስራ ሊያደርጉት ሲሞክሩ አይታዩም። ዘረኛነት ምንድን ነው? የሚለውም ላይ ሆነ አስከፊነቱ ላይ ብዥታ እምብዛም የለም። በተወሰነ ደረጃ ዘረኛነትን በተመለከተ አከራካሪ የሆነው ተዛማጅነት ያለው “ prejudice” {የሌላውን ሰው አልያም ቡድን እምነት፤ስሜትና ሀሳብ ቀረብ ብለን ጊዜ ሰጥተን ለመረዳት በማንችልበት ሁኔታ ወይ ሳንችል በችኮላ የምንደርስበት ድምዳሜ አልያም የምንወስደው ግምት “ዘረኛነት” ነው አይደለም? የሚለው ክርክር ነው።

 

ለምሳሌ፤- አንድ ነጭ ሴት ከጥቁር ጎረምሳ ጋር አሳንሱር ውስጥ አልያም ኮሪደር ላይ ስትገናኝ የሚታይባት ምቾት ማጣትና ከፍራቻ የሚመጣ የጥንቃቄ እርምጃዎች “ዘረኛነት” ነው ብለው የሚከራካሩ አሉ። አይደለም የሚሉት ይሄን አይነቱ ባህሪ ከጥንት ካፈጣጠር ጀምሮ የሰው ልጅ ከነበረ ልምድና መረጃ ተነስቶ እራስን ከአደጋ ለመከላከል እያሳደገው የመጣ ክህሎት ነው ይላሉ። ለዚህ ጥቁርም ሴት ሆነች፤ ጥቁር ሽማግሌ፤ አልያም ጥቁሯ አሮጊት በተመሳሳይ ሁናቴ ውስጥ እንደነጯ ሴት ተመሳሳይ ባህሪ ያሳያሉ ሲሉ ይከራከራሉ። ጎረምሳው ተመሳሳይ እድሜ፤ አለባበስና አረማመድ እስከለው ለምሳሌ ንቅሳታም ከሆነና ሱሪውን ከፍ አድርጎ ያልታጠቀ እስከሆነ ጎረምሳው ነጭም ቢሆን አሁንም ነጫዋ ሴትዮም፤ ጥቁሩም ሽማግሌ ሆነ፤ ጥቁሯ ሴትዬ ተመሳሳይ ባህሪ ማሳየታቸው አይቀርም ብለው ይከራከራሉ። ለኔ ይህ ዘረኝነት አይደለም የሚለው ክርክር የተወሰነ እውነትነት አለው። ያም ሆኖ ቁምነገሩ ከምሳሌው በላይ ነው። ብዙዎቹ እነሱ ወንጀለኞች ናቸው እኛ ግን ብዙዎቻችን ወንጀል አንሰራም ከሚል እሳቤ ስለሚነሳ እሳቤው ውሎ አድሮ አንድን ሰው ወይ ማህበረሰብ ላይ አድሏዊና ዘረኛ ማድረጉ አይቀርም።

 

“ዘረኛነትን” እንደኛ አገር ከማንነት ጋር በጭራሽ አይደባልቁትም። የዘረኛነት ሰለባ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ዛሬ ላይ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች፤ ምርጫ የሚያደርጓቸውን አደረጃጀቶችና የመብት ጥያቄዎች መነሻ መሰረታቸው በደል ፤ እኩልነት፤ ማጣትና ፍትህ ማጣት እነደሆነ በተገቢው መንገድ መረዳቱ አላቸው። በጭራሽ “ዘረኛነት” አድርገው አይወስዱትም። በአሜሪካ ጥቁር አሜሪካዊያን ወይ ነባር ህንድ አሜሪካዊያን ዘረኛ አይደሉም። በሳውዝ አፍሪካም እንዲሁ። እዚህ ላይ መሳሳት የሌለብን ከነዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ደረሰብን ከሚሉት በደል ተነስተው የመረረ ስሜት ንዴት ይዘው የሚኖሩ ዜጎች የሉም አይደለም። ይህ እራሱን የቻለ ሌላ ማህበረሰባዊ ችግር ቢሆንም “ዘረኛነት” ግን አይደለም።

 

 

“ዘረኛነትን” ከማንነት ጋር የማይደባልቁና ልዩነትን የሚቀበሉ የሚያበረታቱ አገራትና ህዝቦች ይህ አተያያቸው የዲሞክሪያሲያዊነታቸው መሰረት ነው። የሰው ልጆን መብት ለማክበራቸው መሰረት ነው። ከመላው አለም የሚኖሩ ህዝቦች አገራቱን ለኑሮ የተመቹና ምርጫቸው አድርገው እንዲሰደዱባቸው ምክንያት ነው። ለሰላማቸውና ልብፅግናቸው መሰረት ነው። እሩቅ መሄድ አያስፈልግም የዚህን አይነት አገራት ውስጥ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን “ዘረኛነትን” “ከማንነት” ጋር እንደማያቆራኙት እኛው ጥሩ አስረጅ ነን።

 

ኢትዮጵያዊነታችንን በአገራቸው በነፃነት እንኖረዋለን። ምን አልባትም አገራችን ውስጥ ክምንኖረው የተሻለ። በሚገርም ሁኔታ እኛ በአገራችን መብታቸውን የከለከልናቸው የመሀበረሰባችን ክፍሎች ሳይቀሩ በነዚህ አገራት ማንነታቸውን በነፃነት ይኖሩታል። እምነታችንን አምልኳችንን በነፃነት እናካሂዳለን። ቋንቋችንን በነፃነት እነጠቀማለን፤ እስከጎበዝን ለልጆቻችን ቋንቋችንን እናስተምራለን፤ ያበረታቱናልም፤ በህላችንንና በዓለቶቻችንን በነፀነት እናከብራለን እናካሂዳለን። እነሱ አገር ላይ እየኖርን ለአገራችን ህዘብ ነፃነትና ዲሞክሪያሲያዊ መብት እንታገላለን፤ ከቁጥር አኳያ ኢትዬጵያዊ ተወካይ ለህዘብ ተወካይነት በአገራቱ ማስመረጡ ላይ እየተጀመረ ያለ ቢሆንም ሁል ጊዜ ፖለቲከዊ እይታችን እየኖርንበት ያለው አገር ተጠቃሚ ይሆናል አይሆንም ከሚል ስሌት ሳይሆን አገራችን ተጠቃሚ ትሆናለች አትሆንም ከሚል ነው። በይበልጥም አንባገነኖቻችንን ከመታገል አኳያ የተሰላ ነው። ሰርተን አገራችን ላይ መዋለ ንዋይ እናፈሳለን። ለተለያየ ምከንያት ወደ አገራችን የምንልከው የውጪ ምንዛሪ አገሪቷ ወደውጪ ከምትልከው ምርት ከሚያስገኘው የውጪ ምንዛሪ በላይ ነው ይባላል ይህን ያውቃሉ ይህ ሁሉ ሆኖ “ዘረኞ” አላስባለንም። የሚገርመው ብዙዎቹ የዚህን አይነት ነገሮች በመንግስታቸው የሚበረታቱና የሚደጎሙ ናቸው። በሗላ እራሱን ችዬ ብዙ የምልበት ቢሆንም ይህንን ለሚያውቅና ለኖረው ሰው በአገራችን ዜጎችን “ዘረኛ” የምናደርጋቸው ምን አደረጉ ብለን እንደሆነ ሲታስብ ማስተዋሉና ፍታዊነቱ ላለን ያስለቅሳል። አንድን የማህበረሰብ ክፍል ስላልወደድነው ወይ ሰላፈራነው ብቻ ከመሬት ተነስተን ዘረኛ የሚባለን ትልቅ ስድብ እላዩ ላይ እንለድፍበታለን።

 

ሌላው አንድ ሰው ዘረኛ የሚሆነው “ዘር” የሚባለው ነገር የሰው ልጆች ትክክለኛው በመሀላቸው ያለውን ልዩነት መግለጫ አድርጎ በተሳሳተ መንገድ በመውሰዱ ነው የሚል መከራከሪያ የሚያነሱ ኣሉ። ለምሳሌ ሲያስረዱ የተለያዩ የወፍ የንብ “ዘር” አንልም “ዝርያ” ብለን ነው የምንገልፀው። በተመሳሳ የሰው ልጆች መሀል ያለውን ልዩነት “ዝርያ” ነው መባል ያለበት ልክ በሌሎች እንሰሳት መሀል እንዳለው የሚል አይነት መከራከርያ ነው። ሲጀመር ይህ ገዥ ሀሳብ አይደለም። ሁለተኛ ልዩነቱን አፈጣጠራዊ አድረጎ የበለጠ ነገር ከማወሳሰብ ውጪ “ዘረኝነትን” ከመከላከል አኳያ ፋይዳ የለውም። የሰውን ልጅ የነጭ የጥቁር፤ የቀይ ዝርያ ያለው ብለን ብንከፍለውም በተጨባጭ ያለው እዛው የነጭ ዝርያ ውስጥ የሰው ልጆች ያመኑባቸውና የተቀበሏቸው የሚታዩ ብዙ ልዩነቶች መኖራቸው ነው። ለኛም ሁሉም ነጭ አንድ እንዳልሆነ ውስብስብ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ሳይገባ አካላዊ ቅርፃቸውን አይቶ ልዩነት ማድረግ በቀላሉ ይቻላል። የሁሉም አፍሪካዊ አካላዊ ቅርፅም አንድ አይነት አይደለም። ለማንኛውም ይህ አንድ አይነት አተያይ ሆኖ አለ፤ ገዥ የሆነ ሀሳብ ግን አይደለም።

 

እኛ።

 

“ዘረኛነት” በኛ አገር አረዳድ “ጥሩ” ያልሆነ ተብሎ የተወሰደ “ማንነት” ነው። ይህንን ማንነት ለማንጓጠጥ እንዳለህ የፍላጎትና የጥላቻ ደረጃ ብሔረሰብ፤ ጎሳ፤ ጎጥ፤ ዘውጌ፤ መንደርተኛ አድርገህ ልትገልፀው ትችላለህ። ጠቅለል ባለ በአገሪቷ ውስጥ ገዥ የሆነው አስተምሮም ሆን አረዳዱ ግን “ዘረኛነት” ማንነት ነው። በሌላ አገላለፅ “ማንነትና” “ዘረኛነት” ፍፁም ተዋህደዋል። ማንነት ዘረኛነት ሆኗል። ዘረኛነት ማንነት ሆኗል። ያም ሆኖ ሁሉም ማንነቶች ድግሞ ዘረኛነት አይደሉም። ለምሳሌ- ኢትዮጵያዊ ማንነት ዘረኛነት ተደርጎ ሲገለፅ አይሰማም። እንዲሁ የአማራ ማንነት ብዙም ክዘረኝነት ጋር ሲዛምድ አይታይም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን እንጂ አለም ላይ ያሉ መዓት ብሄር ብሄረሰቦች ጎሳዎች እንበላቸው በቤተሰብ ደረጃ የሚደርሱ ብዙ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶች ከዘረኛነት ጋር አቆራኛተን አናያቸውም። ኬኒያዊ ማንነት ዘረኛነት አይደለም፤ የመሳይ ወይ የኩኩዩ ማንነት በዘረኛነት አንፈርጅም። አገራችን ውስጥ ያሉ ብሄረሰቦችን ከዘረኛነት ለማዛመዳችን አንዱ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ከሚችሉት ውስጥ ። “የአዲስ አበባ ልጅ ዘር የለውም። ስለዚህ ዘረኛ አይደለም”። የሚለው ነው። ዘር ካለህ ዘረኛ ትሆናለህ ማለት ነው። በኛ አገር ዘረኛነት ማንነት መሆኑ ወይም ሁሉም ማንነቶች ደግሞ ዘረኛ አለመሆናቸው ብቻ ግን አይደለም አስገራሚው። እነዚህ ማንነቶች ዘረኛ ተደርገው የሚገለፁበት ደረጃም አላቸው። መስፈርቱ ግልፅ ባይሆንም የአፋር ህዝብ ዘረኛነት ከትግሬ ህዝብ ዘረኛነት ያንሳል። የኦሮሞ ህዝብ ዘረኛነት ከትግሬም ህዝብ በልጦ በአንደኛ ደረጃ ያለ ኢትዬጵያዊ “ዘረኛነት” ነው። ከኦሮሞ ህዘብ ዘረኛነት የወለጋ አካባቢ ኦሮሞ ዘረኛነት ያየለ ነው።

 

 

“ዘረኛነት” ጥሩ ያልሆነ ማንነት ነው ብለናል። “ጥሩ ያልሆነ” ለሚለው መስፈርቱ ምን እንደሆነ ብትክክል ማስቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም። አንድ ወጥ ምክንያትም ያለውም አይደለም። መጤ ተድርጎ መታሰብ፤ ኢትዬጵያዊነት ላይ ያላቸው ቅሬታና የተለየ የታሪክ አረዳድ፤ በነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ስም የሚንቀሳቀሱ ነፃ አውጪ ድርጅቶች መኖራቸው፤ ምን አልባትም እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ጠቅለል አድርጎ አቅማቸውን አይቶ ከፍረሀት የሚነሳም ይሆናል። የነዚህን አይነት ሌሎች ምክንያቶች ድምር ውጤት “መጥፎ” ተደርጎ የተወሰደ “ማንነትን” የፈጠረ ይመስለኛል። በተገቢው እንየው ካልን አይደለም ሌላው “የመገንጠል ፖለቲካ” ማራመድ ከዘረኛነት ጋር የሚያገናኘው ነገር ግን አልነበረም። ባንተ መጎዳት እኔ ብቻ ተመችቶኝ ልኑርና አብሮነታችን ሚዛን አልጠበቀም እንፋታ አንድ አይነት አይደሉም። አንተ ብትጎዳም እኔን ስለተመቸኝ ዘረኛነት ነው። በአንፃሩ ለምሳአሌ የኤርትራዊያንን የነፃነት ትግል በጭራሽ በዘረኛነት መፈረጅ አይቻልም።

 

እንግዳና ፍፁም ህፀፅ በሆነው አገራዊ አረዳዳችን ምክንያት ቀላል ቁጥር የሌለው እንደውም የበዛው የአገሪቷ ዜጋ ዛሬ ላይ “ዘረኛ” ተድርጓል። ዘረኛ የተደርገው ጥቅል ማንነቱ ብቻም አይደለም ። የማንነቱ መገለጫዎቹም ጭምር ነው ። ቋንቋው፤ ባህሉ፤ አኗኗር፤ ዘረኛና ጎጂ ተደርጓል። ፖለቲካዊ ጥያቄዎቹ፤ ፍላጎቶቹ፤ አተያዩና አረዳዱ ብቻ ሁሉ ነገር ዘረኛ ተደርጓል። በዚህ የተነሳ ከመቼውም ጊዜ በአየለ ዜጎች እጅጉኑ ግራ ግብት ብሏችዋል። “እረ እኔ በቋንቋዬ አወራው፤ ዘፈንኩ፤ የባህሌን ልብስ እኮ ነው የለበስኩት! መብቴን ነው የጠየኩት! እነዲህ ማሰብ እንዴት ነው ዘረኛ የሚያደርገው?። እረ እኔ ዘረኛ አይደለሁም!” የሚመሳስሉ የጭንቀት መልሶችን ሲያሰሙ መስማት የተለመደ የሚያሳዝን የሚያናድድም ሆኗል። ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ በሚመለከት፤-

 

“እኛ ኦሮሞዎች ዘረኞች አይደለንም” “እኛ ኦሮሞዎች አቃፊ ነን” “ እኛ ኦሮሞዎች አማራን እንወዳለን፤ እኛ ኦሮሞዎች ትግራዊያንን እንወዳለን፤ እኛ ኦሮሞዎች ወላይታውያንን እንወዳለን………… እኛ ኦሮሞዎች ሁላችሁንም እንወዳለን” ሲሉ

 

አደባባይ ላይ ለሰልፍ በወጡ ቁጥር መፈክር ያሰማሉ።ይህን እንዲሉ የተገደዱበት ምክንያት “ዘረኞች” ናችሁ ተብሎ ያለአግባብ የሚወርድባቸው ወቀሳና ዘለፋ ምክንያት ነው ። ይህን አይነቱ የወጣቶቹ ጥረት ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሆን ተብሎ በማውቅ የሚራመድ ማሸማቀቅና በዋናነትም “ አንደኛ ደረጃ ዘረኛነት” ስለሆነ አመለካከቱን ከመዋጋት አኳያ ብዙም የሚፈይድ ግን አይመስለኝም። እንደውም “ለዘረኞች” የልብልብ ሆኗል።

 

ሄኒ ዘማን የሚባል የፊኒፊኔ ኦሮሞ በፌስ ቡክ ገፁ ካሰፈረው።

 

ለማንነት መቆርቆር ዘረኛነት አይደልም!።

 

“በሶሻል ሚዲያ የምናያቸው አክስቲቪስቶች ኦሮሚያ ምድር ላይ ተወልደውና አድገው የኦሮሚኛ ቋንቋ ሳይለምዱ ከዛም አልፈው እራሳቸውን የአማራ ህዝብ ጠበቃና ተሟጋች አድርጋው ቆጥረው ሲማገቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ የሚል ማእረግ ይሰጣቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ ፊንፊኔ ውስጥ እናትና አባቶቻችን ተወልደው በኖሩበት ምድር ላይ ማንነታችንን በመውደዳችን ብቻ “ዘረኛ” የሚል ማእረግ ይሰጠናል። ማነው ታዲያ የተመታ አስተሳሰብ ተሸካሚ? አማራነትን ማክበርና መውደድ ኢትዬጵያዊነት እንዲሆን የፈቀደው?። ኦሮሞነትን መውደድና ማክበር ዝረኛነት እንዲሆን ያፀደቀው?”። ሲል ይጠይቃል።

 

ሌላው ስሙን ያልያዝኩት እዛው ሶሻል ሜዲያ ላይ

 

“የራስን ምንነት መውደድ ዘረኛነት አይደለም። የራስን ባህል መውደድ ለሌሎች ማሳየት ዘረኛነት አይደለም። በራስ ማንነት መኩራት ዘረኛነት አይደለም። ዘረኛነት ማለት የራስን ማንነት እየወደድ ያሌላውን መጥላት ማጥላላት ነው። ዘረኛት ማለት የራሱን ባህል እያሳዩ የሌሎችን መደበቅ ነው”። ይላል።

 

የኦሮሚኛ ዘፈን አቀንቃኙ የሙዚቃው ንጉስ ሐጫሉ ሁንዴሳ “ ዘረኛ” ነህ ወይ ተብሎ ተጠይቆ የሰጠው መልስ አንድ ሰሞን አነጋጋሪ ነበር። “ዘር አለህ ከሆነ እንግዲህ እንጉዳይ አይደለሁም? አዎ ዘር አለኝ!። “ኦሮሞ ነኝ!” ዘረኛ ነህ ወይ? ከሆነ ግን ምን አድረጌ ጠየቅሽኝ። ለማንኛውም አይደለሁም” የሚል ነበር። በነገራችን ላይ ከመነሻው ሀጫሉ “ዘረኛ’ ነህ ተብሎ የተጠየቀው የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ ስለሆነ ነው። ይህን አይነት ጥያቄ የቀረበለት እሱ ብቻ አይደለም። ዛሬ ላይ ኦሮሞ የሆኑ ሰዎች በሙሉ የሚቀርብላቸው የመጀመርያ ጥያቄ ይሄ ሆኗል ። በቀጥታም ባይሆን ዘረኛ አለመሆናቸውንና

 

 

ኢትዬጵያዊ መሆናቸውን በየ-ቃለ መጠይቁ ምለው መግለፅ ይጠበቅባቸዋል። ሀጫሉን የጠየቀችው ኦሮሞ ስለሆነች ትክክለኛው ዘረኛነት መሆኑን አያስቀረውም።

 

ከላይ እንደገለፅኩት ዘረኛነት ምንድን ነው? ዘረኛው ማናው? በአገር ደረጃ ማስተካከያ ይበጅለት የሚለው ዛሬ ላይ ዋናው የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ሆኗል። አንድ አገራዊ የመብት ጥያቄ እየሆነ ነው እንድል ያደረገኝም ይህው ነው። እራስን በራስ ከማስተዳደር ጥያቄ እኩል መዋቅራዊ በሆነ መንገድ አንድ የመብት ጥያቄ አድርጎ የሲዳማ ህዘብ እየጠየቀው ነው። “ዘረኛነት ምንድን ነው?” “ዘረኛው ማነው?”። ይህን በአገር ደረጃ በተገቢው ሲብራራ በህዘብ ዘንድ ቅቡል ሲሆን ከሰላም አደፍራሽነት፤ ከአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ጠንቅነት፤ ስልጡን ካለመሆን፤ ጠይ፤ እራስን ባቻ ወዳድ ተደርጎ ከመገለፅ … ከመሳሰሉት ፍረጃዎችና በዋናነትም “ስድቦች” የሚገለፁና የሚዛመዱ ማንነቶች ያኔ እረፍት ያገኛሉ። ትክክለኛ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው ባይ ነኝ። ዘረኝነት ምንድን ነው!!!? ዘረኛው ማነው!!!?።

 

ማንነት ዘረኛነት ነው። ዘረኛነት ማንነት ነው። የሚለው አተያይ መንግስታዊም ነው። ቤተ ክርስትያንያዊ ነው። የአገራቀፋዊ ፖለቲካ አራማጆች { አሁን የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነን የሚሉ} ሁሉ ጉዳዩ ላይ ያላቸው አረዳድ ነው። የመንግስትም ሆነ የበዙት የነፃ ሜዲያዎች አረዳድ ነው። የፊኒፊኔ ምሁራን፤ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ፀሀፍት አረዳድ ነው። ጠቅለል አድርጎ የከተሜ ነን ባዮች አረዳድ ነው ማለት ይቻላል። ይህን ማለት ግን ቁምነገሩ ላይ በመንግስት ደረጃ አንዳቸው ከሌላቸው ሻል ያለ አረዳድ አልነበራቸውም ማለት ግን አይደለም። በተመሳሳይ በተቀናቃኝ ፓርቲዎችም ሆነ ምሁራን ወይ ፀሀፍት ከጅምላው በተለየ የሚረዱትና የሚገልፁት ሊኖሩ አይችሉም ማለት አይደለም። በይበልጥም ቁም ነገሩ ላይ አንዳቸው ከአንዳቸው ፍፁም ጨካኝ ክሆነው ሻል ያለ አተያይ የላቸውም ማለት አይደለም። ይህን አይነቱን ሗላ ቀርና ስድባዊ ጠቅለል ሲደርግ እራሱ “ዘረኛ” የሆነ አመለካከት ለመታገል ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ ሜዲያዎችም መኖራቸውንም ከግምት ማስገባት ይቻላል። በኢትዬጵያችን “ዘረኞች” ተበዳዩን ምን ዘረኛ ብለው መልሰው ማሸማቀቅ ማቻላቸው ግን እውነት ነው። “ማሸማቀቁን” አገራዊ እንዲሆን ማስደረግ መቻላቸውም እውነት ነው። እንዴት ቻሉ?። ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው። ከለይ የጠቀስናቸው አካላት መንግስት፤ ቤተ እምነት፤ ጥበብና ሜዲያ የመሳሰሉት በጥምረት ስርተው አይደለም እራሳቸውን ችለው እጅግ በጣም በጣም ግዙፍና ተፅኖ አሳዳሪ መሆናቸው ነው። ከፍተኛ ተፅኖ ማሳደር የአንድን አገር በነገሮች ላይ ያለ አገራዊ አተያይ መቅረፅ የሚችል አቅሙ ያላቸው መሆኑ ነው።

 

March 29, 2014 ጎሠኛነትና ሽብርተኛነት በሚለው ፅሁፋቸው ውስጥ (/ር መስፍን ወ/ማርያም)

 

“ ጎሠኛነት የዘረኛነት የባሕርይ ልጅ ነው፤ ዘረኛነትም ሆነ ጎሠኛነት መሠረታቸው ድንቁርና ነው፤ የድንቁርናው ዓይነተኛ መገለጫ ‹‹ንጹሕ›› የሚለው ቃል ነው፤ ለዚህ ዋና ምስክር አድርጌ የማቀርበው አዶልፍ ሂትለርን ነው፤ ስለ‹‹አርያን ዘር›› ማንነትና ‹‹ንጹሕነት›› የሂትለር Mien Kampf የሚለውን መጽሐፍ ነው፤

 

የሰው ልጆች ባህል የሚባለው ሁሉ፣ ዛሬ የምናየው የሥነ ጥበብ፣ የሳይንስና የሳይንስ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) ውጤት ሁሉ የአርያን ዘር የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፤ … ‹ሰው የሚባለውም እሱ ብቻ ነው። የሂትለር ዘረኛነት የሰውን ልጅ ሁሉ ጉድጓድ ውስጥ ከተተው፤ አርያኑን ከንጹሕ የሰው ዘርነት ወደብቸኛ የሰው ዘርነት አሸጋገረው፤ ይህ ንጹሕ ድንቁርና ነው፤ የጎሠኞችም መነሻና መድረሻ፣ መንገዱም ይኸው ነው:;”

 

ዘረኛነትና ጎሠኛነት ከስጋትና ከፍርሃት የመነጨ ነው፤ አልጋው ፍርሃት፣ ትራሱ ስጋት ስለሆነ ጭንቀቱ እያባነነው እንቅልፍ አይወስደውም፤ ሲያቃዠው ያድራል፤ ለየት ያለና ትንሽም ሻል ያለ ነገር ሲያይ ሆን ብሎ እሱን ለማኮሰስ ወይም ለማሳነስ የመጣበት እየመሰለው ይደነግጣል፤ ስለዚህም ከሱ የተሻለውን በማጥፋት እሱ ወደትልቅነት የሚሸጋገር ይመስለዋል፤ ስለዚህም ዘረኛነትና ጎሠኛነት የሽብርተኛነት ምንጭ አንዱና ዋናው ምክንያት ከሱ የተለየውን ለማጥፋት ያለው ዝንባሌ ነው፤ ዘረኛነትና ጎሠኛነት ልብን በጥላቻ ያቆሽሻል፤ አእምሮን በክፋት እየመረዘ ያደነዝዛል፤ ሰውነትን ወደርኩስ መንፈስነት ይለውጣል፤ በባነነና በቃዠ ቁጥር የሚታየው ማታለል፣ ማጥፋት፣ ማፍረስ፣ ማዋረድ፣ ማጎሳቆልና ማደህየት ብቻ ነው፤ ለዘረኛና ለጎሠኛ እድገት ማለት የሌሎች መቀጨጭና መሞት ነው፤ ማደህየት፣ ማሰቃየት፣ ማቀጨጭና መግደል፣ ንብረትንም ማውደም የሽብርተኛነት መገለጫው ነው፤ የሽብርተኛነት ማለትም የዘረኛና የጎሠኛ የደነዘዘ አንጎል ጥፋትን እንደልማት፣ መቀጨጭን እንደእድገት ይመለከታል።

 

 

የዘረኛና የጎሠኛ ሽብርተኛነት የሚፈጥረው የደነዘዘ አንጎል ራስንም አይምርም፤ ለራሱ ልጆችና ቤተዘመዶች አያስብም፤ በዙሪያው ያለውን ከሱ የተለየ ዓለም በሙሉ ወደአንጠርጦስ ሲከታቸው የሱም ወገኖች አብረው አንጦርጦስ ቢወርዱ ግድ የለውም! አይጸጽተውም! የተረፉት በሙታኑ መቃብር ላይ አሸብርቀው ሕያዋን መስለው ይታያሉ፤ እነሱ ባያዩትም የቆሙበት መቃብር ጠርንፎ ይዟቸዋል፤ ሕያዋኑና ሙታኑ ተቆራኝተዋል፤ ሙታኑ በተፈጥሮ ሕግ ይበሰብሳሉ፤ ሕያዋን የሚመስሉት በገዛ ሥራቸው ይበሰብሳሉ።

 

የቦሌ ልጅነት ለአዲስ አበባዎች ነው። ለክፍለሀገር ልጆች “አዲስ አበቤነት” እራሱ የቦሌ ልጅነት ነው። ይህ አዲስ አበቤነት መኮኑ መሰለኝ ። ይህን ያልኩት የህንን ፅሁፋ ያነበበኩ ጊዜ የተወሰኝ ኬንያ እያለው ከናይሮቢ ከተማ ካንፕ ልትይቅ ስለመጣች ቅምጥል የሰማሁት ነው። ጥንቸል፤ አባጨጓሬና ቀጭኔ ይመሳሰሉብኛል ነበር ያለችው። “ዘረኛነት” “ጎሰኛነት” “ሽብርተኛነት” ተመሳስለው ተዛምደው አንድ ተደርገው ተቀምጠዋል። ቅምጥል ስትሆን ችግር የለውም ሁሉንም ነገረ ማመሳሰል ቀላል ነው። ሲጀመር “ጎሰኛነት” ምንድን ነው?። መጥፎና ውስብስብ የሆነ ታቡ የሆነ ነገር ሆነ ብለው ስላደረጉት እንጂ ጎሰኛነትና አገር ወዳድነት፤ የቤተሰብ ሰው፤ ብሄርተኛ ወይም የመንደር አድባር ከመሆን በምንም እንደው በምንም አይለይም። እንደሁሉም ለጎሳው የሚቆረቆር ጎሰኛ ነው አለቀ። የቤተሰብ ሰው ሆነህ አገር ወዳድ መሆን እንዳልከለከለህ ጎሰኛ ሆኖ ቤተሰቡንም አገሩንም መወደድ ምንም የሚከለከለው ነገር የለም። አልከለከለውምም። ቢገባቸው ሁሉም ውስጥ ከራስ በላይ ማሰብ፤ መሰዋትነት፤ ተቆርቋሪነተ፤ ሌሎችን ማስቀደምና አክባሪነት ነው ያለበት። ቤተሰብህን የምትወደው እሳቸው ሊያስቀምጡ እንዳሰቡት ሌሎች ቤተሰቦችን ስለምትጠላ አይደለም። ጎሳህን የምትወደው ለጎሳህ የምትቆረቆረው ሌሎችን ስለምትጠላ አይደለም።

 

ልብ ብለን ካየነው እሳቸው ከላይ “ጎሰኛነት” ብለው የገለፁት ሌላ ምንም አይደለም “ማንነት” ነው። አንዱ አይነት ማህበረሰባዊ አደረጃጀት ነው። ጎሳ ከመጠን አኳያ ለሰው ልጆች ዝቅተኛውም የማንነት ስብስብ ወይ መገለጫም አይደለም። “ጎሳ” ብለው የገለፁትን ማንነት ከዘረኝነት ጋር ማዛመዳቸው ብዙም አይገርምም። በኛ አገር “ዘረኝነትን” ከዚህ ውጪ በትክክለኛው መንገድ እንዲገለፅና ዜጋው እንዲረዳው በጭራሽ አይፈለግም።

 

”አርያን ዘር” ያሏቸው ጀርመናዊያን ናቸው። ችግር የለውም እሳቸው እንዳሉት ጎሳ ናቸው ብለን እንወስዳቸዋለን። በዛን ጊዜ በአለም ላይ የነበሩት “አርእያን” ጎሳዎች ብቻ ነበሩ ወይ? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምለስ ኣልነበሩም የሚል ነው። እሳቸው ጎሳን በተረዱበት መንገድም ብዙ ጎሳዎች የዛን ጊዜ በአልም ላይ ነበሩ። ሁሉም “ንፁህ” ዘር ነን አላሉም። አርያኖቹ ግን “ንፁህ” ዘር ነን ብለው እራሳቸውን ልዩ አድርገው ማሰባቸው ብቻ አይደለም ሌሎች ጎሳዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅመወል። ታዲያ በአለም ላይ የነበሩ ጎሳዊች ሁሉ በአርያኖቹ ወንጀል ምክንያት “ዘረኛ” “ደንቆሮ” “ አረመኔ” ለምን ይባላሉ። የሳቸው አረዳድ በቀጥታ ስለሚያደርጋቸው ነው። ሁሉንም ደባልቀህ ውቃው ነው። አዳፍኔ መሆኑ ነው።

 

በሌላ አንግል ደግሞ የዚህን አይነት ዘግናኝ ዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀሙት “አርያን ጎሳ” ስለሆኑ ነው ወይስ ‘ንፁህ” ነን ብለው ስላሰቡ ነው?። እሳቸውም ቢሆን ጥያቄው በዚህ መንገድ ቢቀርብላቸው የሚመልሱት መልስ አልፎም ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ እኛ “ንፁህ” ነን ብለው ስላሰቡ ነው የሚለው ነው። አልያም { ሂትለር ዘረኛ ስለሆነና እኛ ”ንፁህ” ነን ብሎ ስላሰበ ነው የሚል ነው}። ቤተሰብ፤ መንደር፤ ጎሳ፤ ብሄር ብሔረሰብ ይህ የሰው ልጆች ማህበረሰባዊ አደረጃጀት ከፍ ሲልም አገር መሆኑ አይቀርም “ሀሳብ” አልያም “ ግንዛቤ” ከሆነው “ዘረኛነት” ጋር ያዛመዱት እሳቸው እራሳቸው የናዚ ቢጤ “ዘረኛ” ስለሆኑ ነው። እኔ ከዚህ የወሰድኩት ድምዳሜ ማለቴ ነው። ለዚህ ሌሎች ብዙ ምክንያቶችም አሉኝ።

 

ከዚህ ዘግናኝ ወንጀል ጋር አዛምደው ስብእናውን ሊያጠፉት የፈለጉት ኢትዬጵያዊ ብሔረሰብ {በሳቸው አገላለፅ ጎሳ} ስላል ነው። ለዚህ ሌላው አስረጅ ይህ ፅሁፍ በተፃፈበት ጊዜ አገራችን ውስጥ የነበረው መራሄ መንግስት ጨፍጫፊ አንባገነን ነበር። በሽብረተኛ የሚከሳቸው ዘግናኝ ጭፍጨፋ የሚፈፅምባቸውና ወደ እስር ቤት የሚያግዛቸው ማህበረሰባችን ክፍሎች ነበሩ።ይህን ስለሚያውቁ “ጎሶኞች” ያሏቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች “ከሽብርተኛነትም” ጋር አዛምደው ለገዥዎች አመክንዬና አቅም መሆን ፅሁፉ ነበረበት።

 

 

ኢትዮጵያዊ ነኝ ስትል ዘረኛ እንዳልሆንከው- በተመሳሳይ አንድ ሰው “ገላን ነኝ” ሲል ዘረኛ በጭራሽ አይደለም። “ገላን” ነኝ የሚለው ገላን ስለሆነ ነው። ገላንነቱም እንደ ኢትዮጵያዊነቱ ማንነቱ ነው። ጎሰኛነቱ ተፍጥሯዊ ነው ማለት ነው። ሲወለድ ህፃን እያለ፤ እራሱን ካወቀ በሗላም አርጅቶም ከጃጀ በሗላም ኢትዬጵያዊ እንደሆነው ሁሉ ይህ ዜጋ ገላንም ነው። ማንነቱን ልተወው ብሎ የሚተወው አይደለም። አልያም ዲናር አጡዞ ጎፈር ወይም ዘውድ ብሎ አንዱን የሚወሰደው ሌላውን የሚተወው አይደልም። እንተ ተው ስላልከውም እንዲሁ ትፈነዳለህ እንጂ አይተወውም። እሱ ቢተወውም ኢትዬጵያዊ አይደለሁም ቢለን ሌሎቻችን እንደማንተወው፤ ገላን ከሆነ ገላን ተደርጎ በሚያውቁት ሁሌም ይወሰዳል። “ኢትዮጵያዊነት ሚስጥር ነው። ኢትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ነው” “እኛ የተለየን የተሻልን ነን” እያልን ማሰብ ስንጀምር ግን ዘረኛ እየሆንን እንደምንሄደው ሁሉ “ገላኖች ንፁህ ነን፤ የተለየን ነን፤ ገላንነት ከሌሎቻችሁ ከጎሳዎች ሁሉ በላይ ነው፤ ሚስጥር ነው” ብሎ ማሰብና መዝፈን ሲጀምር ይህ ዜጋ ዘረኛ ሆኗል ማለት ነው። በነገራችን ላይ “ገላን ፊኒፊኔ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አሳደን ገፍትን ገፍተን ካጠፋናቸው የኦሮሞ ጎሳዎች ወስጥ አንዱ ነው።

 

ዘረኞች ሲያጨናብሩ “ማንነትን” “ከዘረኛነት” ጋር የዛምዱታል፤ አልፈውም አንድ ነው ይሉናል። “ዘረኛነት” የእምነት፤ የግንዛቤና የሀሳብ ጉዳይ ነው። ስለዚህም የግድ እናዛምደው ካልን ክትምክተኛነት አስተሳሰብ ጋር በእጅጉ ይዛመዳል። የሚዛመድም ብቻ ሳይሆን ዘረኛነት ትምክተኛነት ነው ብሎ መናገር ብዙም ስህተተኛ አያደርግም። አልያም ‘ዘረኛነት” ሲጀምርህ “ትምክተኛ” ያደርግሀል ልንል እንችላለን። ትምክተኛ ሆኖ ዘረኛ ያልሆነ ሰው ሊኖር ይችላል፤ ዘረኛ ሆኖ ትምክተኛ ያልሆነ ሰው ግን ስትፈልግ ትሞታለህ እንጂ የለም። በሌላ በኩል እኛ በተለምዶ “ከዘረኛነት ጋር የምናዛምደው ማንነት መንደርተኛ፤ ጎሳም እንበለው ብሔርተኛነት አመፀኛ፤ ተነጫናጭና ጠያቂ ከሆነ “ዘረኛነት” የነበረ ያለ ለመሆኑ አንዱና ዋናው ማሳያ ነው፤ ሌሎቹ ማሳያዎች አንባገነንነት፤ አድሎ፤ ጭቆና ፤ቅሚያ፤ ስግብግብነት፤ ይህንኑ የማህበረሰብ ክፍል ማሰጠን….. ወዘተ በዛ አገር ውስጥ ነበር ማለት ነው። በነገራችን ላይ ብሄርተኛነት{ መንደርተኛ፤ ጎሰኛ፤ ጎጠኛ… እንበለው።} ሁሌም ያለ የሚኖርም ነገር ነው። ጠንካራ ብሄርተኛነትን የሚፈጥረው ግን ‘የዘረኛነት መኖር” ነው።

 

 

አዳፍኔ {የፕ/ፌ ምስፍን ወልደማርያም

 

‘እራሱን እንደነጻ ስው፤ እንደግለሰብ ማየትና በዚያው መሰረት መወሰን የማይችል ፍጡር ከአየራልንድም ይምጣ ከስኮትላንድ ፤ ከኢትዮጵያ ይምጣ ከኬንያ ወይም ከሱማልያ ገና ዝቅተኛ የሰውነት ደረጃ ላይ ያለ ነው።ገና የራሱ ባለቤት አልሆነም ማለት ነው። ወደግለሰብነት ደረጃ ላይ ያልደረሰና የግለሰብነት የሀላፊነት ባለቤትነትን ያልተረዳ በሰውነት ደረጃው ዝቅተኛ ነው”። አስከትለው ስልጣን መቼ ትለቃለህ ተብሎ መለስ ዜናዊ ሲጠየቅ “ድርጅቴ ነው የሚወስነው” ሲል የመለሰው ላይ ትንሽ ያብራራሉ። ይህ ለማምታት የገባ ነው። በማስከተል

 

ይህንን ያልተማረ ወይም ያልተገነዘበ ግለስብ ከእንሰሳት ደረጃ አልወጣም። ነግረ ግን በዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩና የሚማሩ ሰዎች በጎሰኛነት ሕመም ተይዘው ማደግና መሻሻል የሚባሉት ነገሮች በየት በኩል ግብቶ ቦታ ያገኛል።” እያሉ ፕሮፌሰሩ በመፀሀፋቸው ያትታሉ።

 

ይህን አተያያቸን መፀሀፋቸውን አዳፍኔን “ክሽፈትንም አዳፍኔንም” አየሁበት በሚል አርእስት በጊዜው ዘረኛነታቸውን በማሳየት ሞግቼዋለው። እንግዲህ ጎሰኛ የተባሉት መምህራንና ተማሪዎች ለዚህ ደረጃ የደረሱት {የከፍተኛ ደረጃ መማር ማስተማር ሂደት ውስጥ} እራሳቸውን ችለው እያሰቡና እየወሰኑ ነው። እኔ ነበርኩ የማስብና የምወስንላቸው የነበረ መቼም አይሉም። በጎሳ ያስባሉ ሲሉም ጭንቅላታቸውን የሸረሪት ድር በመሰለ ነገር አገናኝተው አንድ ትልቅና ውስብስብ አይምሮ ፈጥረዋል ለማለትም አይደለም። ይህ ቢሆንም ምንኛ ድንቅ ነበር። ኢትዬጵያ አይደለችም አለም በታደለች ነበር። ይህ “ስላሴዎችን” ሆነዋልም ሊሆን ይችላል እና። እነዚህ ተማሪዎች በጋራ ስለሚያስቡ እንደ አስተማሪነታቸው እሳቸው ይሰጧቸው በነበሩ ፈተናዎች ላይ ጎሰኛ ልጆቹ ውጤታቸው ሁሌም ተመሳሳይ ነበር እያሉንም አይደለም። ለማለት የተፈለገው በኢትዬጵያ ስም ብቻ ካልሆነ ሌሎች ማንነቶችን ለምን ኖሩ ነው። ለምን በሌሎች ማንነቶቻቸው ይኮራሉ። ለምን እራሳቸውን በሌሎች ማንነቶች ይግለፃሉ ነው። ችግሮች ቢኖርም እንኳ ክኢትዮጵያዊነት ውጪ በሌሎች ማንነቶች ስር መናገር መተባበር የለባቸውም ነው። ይህን የሚያደርጉ ክሆን ግን በሰውነታቸው ከኔ እኩል አይደሉም ነው ስብከቱ። አልያም የሰውነት ደረጃ ስላልደረሱ ነው ብዬ አምኛለው ነው ፕሮፈሰሩ የሚሉት።

 

 

እዚህ ላይ ከለውጡ በፊት በወያኔ ኢሕአዲግ ስርአት ነፃነቴን አጥቻለው የምንል “እኔ” ነበርን ወይስ “እኛ” ነበርን?። እውነታው “እኛ” ተበድለን ስለነበር “እንደኛ” ነበር የታገልነው። ችግሩ የጋራ መሆኑን አውቀን፤ ተባብረን ታግለናል። ታዲያ ዝቅተኛ የሰውነት ደረጃ ላይ ነበርን ማለት ነው?። ትግሉ ውስጥ ድርሻ ያለው ሁሉ በግሉ ችግር አለ መፍቴሄም ይሻል፤ ለዚህም ትግሉ ላይ የድርሻዬን ማበርከት አለብኝ ብሎ በደንብ አስቦበት ውሳኔ አድርጎ ተሳተፋል። ከሌሎች ጋር አስተዋፆውን አስተባብራል። ታዲያ በሰውነትህ ያነስክ-ነህ የሚያስብለው የትኛው ተግባሩ ነበር። ከሳቸው እኩል የሚያደርገውስ?። ሲጀመር ሰው መህበራዊ ፍጡር የሆነውስ እንዴት ነው?።

 

ጎሳም እንደቤተሰብ፤ መንደር፤ ብሔር፤ ብሔረሰብ፤ ያንድ አገር ህዝብ፤ ጥቁር ህዝብ፤ ጋናዊ፤ አረብ፤ ክርሲቲያን…ማንነት ነው። ማህበረሰባዊ አደረጃጀት ነው። ልዩነቱ በብዛቱ፤ በቆዳ-ቀለሙ፤ በእምነቱ በዜግነቱና በሚኖርበት ቦታ ነው። ሁሉም ግን ከግለሰብ በላይ የሆኑ የሰዎች ስብስብ ናቸው። እንደተለያየ ማህበረሰብነታቸው ልዩ ባህሪ ያላቸው የጋራ ችግር ይኖራቸዋል። የጋራ ፍላጎት፤ የጋራ ጥያቄ፤ የጋራ ጭቆና ይኖርባቸዋል። ወይ አለ ብለው ካመኑ በጋራ ሆነው ቢታገሉ፤ ድምፃቸውን ቢያሰማ፤ ቢቃወሙ፤ ቢዋጉ ጭምር በእንሰሳት ደረጃ ያሉ የሚያደርጋቸው ምኑ ነው?። ግለሰብ ሆኖ የዚህ ወይስ የዛ ስብስብና የማህበረሰብ አደረጃጀት ውስጥ ሳይካተት የሚኖርስ ማነው?። በቤተሰቡ ላይ የተቃጣን አደጋ በተለየ የማይሰማው እውን በዚህ አለም አለን?። በቤተሰብ ደረጃ የተለየ ፍላጎትስ የሌለው?። በአገር ደረጃስ ቀናዊነት የማይሰማው ሰው ማነው። እንግዲህ በሁሉም ደረጃ የሰው ልጅ ሂወቱን መስጠት ድረስ ለሁሉም ማንነቱ ቀናዊ ነው። እንጂ በጎሳ ደረጃ ብቻ መጥፎ የሚሆንበት ምንም እንደው ምንም ምክንያት የለም። አንድና አንድ ዘረኛነታቸው ብቻ ነው። እሳቸው በገለፁት በጎሳ ደረጃም ቢሆን እግዚአብሔር ያሳያችሁ የሰውን ልጅ ለዛውም አንድን የማህበረሰብ ክፍል “በእንሰሳት ደረጃ” ነው ያለው ለማለት ሌላው በምን ተሽሎ? በምንስ አንሶ ነው?። በይበልጥም በኢትዮጵያ ሁኔታ። የሚገርም አይን ያወጣ ዘረኛነት የሚሆነው ለዚህ ነው።

 

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ትግሬ፤ ኦሮሞ፤ ጉራጌ…. ለምን ይባላል። ዘረኛነት ነው በሚለው አስተምሮዎቹ ይታወቃል። “ ሰው

 

ነን”። ወይ “ዘረኛ የሆነን ግለሰብ መከራከር ከባድ ነው። የሰው ልጅ ካፈር ነው የተሰራው ስትለው ከነጭ ከሸክላ ክጥቁር አፈር ብሎ ሙግት ይገጥምሀል” በሚሉት ዝናኛ አስተምሮዎቹ ታወቂ ነው። መልእክቱ ጠቅለል ሲደረግ ብሄር ምሆናችሁን ለምን እሰማለው ነው። ኦሮሞ አኝዋክ ሱማሌ ሀድያ፤ አገው፤ትግሬ … ለምን ይባላል ነው። ማንነት ዘረኝነት ነው = ዘረኝነት ማንነት ። እምነቱ ስለሆነ ነው።

 

አሁንም በጊዜው በመጀመርያ ሰው ነን የሚለው ፅሁፉን በሞገትኩበት ፅሁፌ “ሲጀመር ሰው አይደለህም ያለህ የለም፤ አይደለሁምም ያለ የለም። “ዜግነት፤ ሰፈር፤ ብሄረሰብ፤ ስራ፤ እምነት፤ ጎሳም በለው ከመሳሰሉት ማንነቶች ተፅኖ ውጪ እየኖርኩ ነው። ወይ መኖር ይቻላል ከሆነ ክርክርህና ፉከራህ እንቅጩን አይቻልም ብዬው ነበር። የማይቻል መሆኑንን ለማሳየት ትናንት ከተነገረና ከተፃፉ እንዲሁም ከተኖረ ሂወትህ በዙ ማሳጫ ማቅረብ ይቻላል ነበር ያልኩት። ይህን ያልኩት በጊዜው መረጃ ኖሮኝ አልነበረም። ዛሬ ዲያቆን ዳንኤል የሚለውን እንዳልሆነ በመቅረፀ ምስል የተደገፉ ብዙ መረጃዎች ወጥተውበት አይቻለው። በነዛ መረጃዎች ተነስቶ ዳንኤል ክብረት እዛ የብቃት ደረጃ ላይ ደርሶ ‘ሰው” ብቻ ሆኖ ሊኖር አይደለም ዛሬ ላይ በጥላቻና ንቀት ያበደ “ዘረኛ” ነው ብሎ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።

 

ባጭሩ ለሌሎቻችንም ይሄ “ሰው ነን” የሚለው መመፃደቅ ላይ ግልፅ ሊሆንልን የሚገባ ነገር አለ። ሌላ ብዙ ኮተት ተሸክመን ብምንኖርበት በዚህ አለም አይደለም “ሰው ነንን”- “ኢትዮጵያዊ ነን” እያልን እየኖርነው ነው የምንለው ሂወት በጭራሽ አይደለም። ልንል እንችላለን በህግ ክልክልነት የለውም። ነገር ግን ትልቅ ቀጣፊነት ነው የሚሆነው። በዚህ አለም ላይ በነበረው ሳይሆን በእምነት ደረጃ መንግስተ ሰማያት ውስጥ እንኖረዋለን የሚባለውን ምን አልባትም እዚህም ከሆነ ከፍተኛው የብቃት ደረጃ የደረሱ ይሰወራሉ የሚባሉት ለዛውም ከሉ የሚኖሩትን ሂወት አልያም አለምና የሚያዩበትን አተያይ ነው። “ሰው ነኝ” ትተን እስቲ በአቅማችን “ኢትዮጵያዊያን ነንን” መጀመርያ በቅጡ እንኑረው። በመጀመርያ ሁሉንም ኢትዬጵያዊያን የአገራችሁን ልጆች በእኩል ወዳችሁ በእኩል አይታችሁ ነፃ ሆነው የፍላጎታቸውን አድረገው ሲኖሩ አይታችሁ ሳትራገሙ ሳትሳደቡ አይናችሁ ሳይቀላ ዘረኛ ጎጠኛ መንደርተኛ ብላችሁ ሳታንጓጥጡ መኖርን እንቻልበት።

 

አንዱ እንደዘመኑ ፋሽን “አዳምና ሄዋን ዘር አልነበራቸውም” የሚል መፈክር ይዞ አየሁት። “ጅሎ” ያልዞረለት ግን አገርስ መቼ ነበራቸው።ዜግነትስ፤ ነጭ ጥቁር ቢጫስ መቼ ነበሩ። ይህመ ብቻ አይደልም ሱሪ፤ ጦር፤ ማረሻ፤ ላብ-ታብ…ወዘተ መቼ ነበራቸው። ምንስ? ነበራቸው። ሌሎች ዘር ቁጥሩ ችግር የለውም አዳም ጋር እንገናኛለን ይሉሀል። እነሱ ኮከብ የሚቆጥሩ

 

 

ይመስላቸዋል። የጋሽ እንትና ልጅ፤ የንትን ሰፈር ልጅ፤ ኩሩ ኢትዬጵያዊ ነኝ የማይሉ ይመስላሉ። ይህ ሁሉ ዜጎችን በማንነታቸው ኮርተው እንዳይኖሩ ለማሸማቀቅ ነው። ሊያጠፏቸው የሚፈልጓቸው የሚጠየፏቸው ማንነቶች ስላሉ ነው። በግልፅ ይህን የሚሉት ዘረኛ ስለሆኑ ነው። በልዩነት መኖርን ስለማይችሉበት ነው።

 

ፓስተር ቶለሳ ዘረኛነትን አምርረው በነቀፉበት አንድ በሶሻል ሜዲያ ሲሰራጭ በነበረ አስተምሮቸው። “ቅማንት፤ ትግሬ፤ ገለብ…. ምናምን አትበሉ። ዘረኛነት ነው። መፀሀፍ ቅዱስ ውስጥ የኢትዮጵያ ስም እንጂ ቅማንት ከንባታ ጋንቤላ ኦፋር የሚል ስም የለም። ስለዚህ አግዚአብሄር አያውቃችሁም”። ማለት ደረጃ ደርሰው ነበር።

 

ይህ አገላለፅ በራሱ ዘርኛ ነው። በሌላው አለም ዘረኛ የሚባለው ይሄ ነው። ስለዚህም እኔንም ጨምሮ በብዙዎች በጊዜው ተተችተዋል። አሁን ድረስ ኦሮሞ ለዛውም ፓስተር ቶለሳ ጉዲና ይህው “ዘረኞች” ናችሁ ብለዋል ለማለት ለማሸማቀቅያ በሶሻል ሜዲያ ይህንን ቪዲዮ ዘረኞች ለጉድ ያዟዙሩታል። በአጠቃላይ አስተምሮው ዘረኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከእምነትም አኳያ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ብዙ ስህተት ነበረው። በጊዜው እንደዚህማ ከሆነ እግዚአብሔር “እኔን “ዳዊትን” እንጂ እርሶን “ቶለሳ ጉዲናን” የት ያውቃል” ብያቸው ነበር። ከዛ በሗላ ሌሎች ዘረኛነት ላይ ያስተማራቸውን የተሻለ መልእክት ያላቸውን አስተምሮዎች አይቼላቸዋለው። የሳቸውንም ሆነ የሌሎችንም የተከበሩ ሰዎች ስም ያነሳሁት በዋናነት “ዘረኛነት ማንነት ነው = ማንነት ዘረኛነት ነው”። የሚለው ኢትዮጵያዊ አረዳድ ከእውቀትና ከክብር አኳያ ከምን ከፍታ ላይ እንደሚለቀቅ ለምን በማህበረሰቡ ዘንድ ግዥ ሀሳብ እንደሆነ ለማሳየት ነው።

 

ጠቅላይ ሚንስትራችን ዶ/ር አብይ አህመድ። ብዙ ጊዜ ስለዘረኛነት አንስተው ተናግረዋል። ሽፍንፍንነት ቢኖረውም አረዳዳቸው እንደ አገሬው ዘረኛነት ማንነት ነው= ማንነት ዘረኛነት ነው የሚል ይመስላል። ውስጣዊ {ግለሰባዊ} ተደርጎ የሚገለፀው ዘረኛነት ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ። የሂወት ጉዟቸው ደግሞ የሚያስብልም ነው። በአስራ ስድስት አመት ለዛውም የወያኔ ጦር ውስጥ መግበት ማደጎነት ነው። ዞሮ ዞሮ የሳቸውን በገሀድ ገፍቶ እስኪወጣ እንጠብቀው። አንድ ህቅ ግን አለ። ዛሬ እሳቸው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ኢትዬጵያን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በአየለ በመንግስት በተደገፈ መልኩ ዘረኛነት ማንነት ነው= ማንነት ዘረኛነት ነው የሚለው አስተሳሰብ እንደገና ጉልበት አግኝቶ እየተቀነቀነ ያለበት ጊዜ ነው። ማንነቶች ዘረኛ ተብለው እየተቀጠቀጡ ነው። ዘረኛ ተብለው እንዲሸማቀቁ እየተደረገ ነው። ኦሮሙማ ዋንኛ ጠላት ተደርጓል። ሲዳማነት ይቀጠቀጣል። ትግሬነያዊነት ይቀጠቀጣል። ቅማንትነት ሚሊሻ ተነድቶበታል። ሌሎቹም ፈርተው አርፈው ካልተቀመጡ ጥያቄ ይዘው ወደፊት መምጣት ሲጀምሩ መቀጥቀጣቸው አይቀርም። ለዚህም ይመስለኛል ዘረኛነት ላይ አገራዊ አረዳዱ ይስተካከል የሚለው በ1966 የተረሳ ልንለው እንችላለን አልያም ከዛ በሗላ ጉልበት ያገኘ ትልቅ የመብት ጥያቄ እየወጣ ያለው። “ ዘረኛነት ምንድን ነው?” “ዘረኛው ማነው?” የሚለው ላይ አገራዊ አረዳዱ ይስተካከል!!!? ።

 

 

ዛሬ አንድ የተለወጠ ነገር ቢኖር የመንግስት ሜዲያ አብዛዊነት መቻቻል የብሄረሰቦች መብት በሚለው ምትክ ብሄርተኛነት ዘረኛነት ነው በሚለው ተተክቷል። ቀንና ማታ በዚህ አተያይ የተቃኘ ቅስቀሳ ነው የሚያካሂደው። ጠቅላይ ሚንስትሩ የጥበብ ሰዎችን ሰብስብው አቅጣጫ መስጠታቸውን ሁላችንም እናስታውሳለን። ደግሞ ደግሞ እንደታየውና በቂ ተሞክሮ እንደወሰድንበት አቅጣጫ አስይዘው እንጂ ይህ ክፍል ይግተለተልልሀል። ታማኝ ነዋይና አለምፀሀይ ደርግን አገለገሉ፤ ሰራዊት ፍቅሬና ሸዋንዳኝ ደስአለኝን የመሰሉ ደግሞ ኢህአዲግን አገለገሉ፤ ታዲያ ምን ልዩነት አለው፤ ዋናው እና ጠቃሚው ነገር ዛሬ እንኳ ሰራዊትንና ሸዋንዳኝን አቅርበው የሚያሳጡ እነሱ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን ቢጠየቁ ነበር። ሜዲያውና የጥበብ ሰዎች እንትናን ወይም እነንትናን አልያም አንድን ብሔረሰብ ብቻ አይደለም ዘረኛ ያደረጉት። አገሬውን በሙሉ ዘረኛ አደርገውት ቁጭ ብለዋል። በነሱ አተያይ ኢትየጵያ ዘረኛ ሆናለች። ኦሮሞ ዘረኛ ከሆነ፤ ትግሬ ዘረኛ ከሆነ፤ ሲዳማ ዘረኛ ከሆነ፤ ቅማንት ዘረኛ ከሆነ፤ ጋንቤላው ዘረኛ ከሆነ፤ ሱማሌው ዘረኛ ከሆነ….ያልሆነው ማነው። እነዚህን ከለውጡ ተዛምዶ

 

በቅርብ ግዚያት ከዘረኛነት ጋር የተዛመዱትና የተባሉትን ነው። እስከሁን ዘረኞች ያደረጓቸውን ደምረው ከጠቅላላው ዜጋ ስለ ምን ያህሉ እያወሩ እንደሆነ አውቀዋል?።

 

ቀደም ብሎ ከለውጡ መፋጠን ጋር ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ቅርበት ባላቸው የጥበብ ሰዎች የጀመረ ቢሆንም ከዛ በሗላ የወጡ የጥበብ ስራዎች የበዙት “ማንነት ዘረኛነት= ዘረኛነት ማንነት ነው” በሚል አተያይ የተቃኙ ናቸው። አንዳንዶቹ የጥበብ ስራዎች ላይ ይሄው መልእክት ፍጥጥ ብሎ አሳፈሪ በሆነ ሁኔታ ይወጣል። ዋ እንግዲህ እያሉ ማስፈራራት ሁሉ አለበት። ተሰባስበው “አማራ ጉራጌ ትግሬ ማለት ዘረኛነት ነው”፤ ቃል በቃል ይህን አይነት መልእክት ያለው ማስታወቂያ

 

 

ሁሉ መልቀቅ ድርስ ደፍረዋል። ሰሞኑን ደግሞ “እኔ እንትና ነኝ፤ እኔ እኛ ነን” የምትል ሌላ ማስታወቂያም አይቻለው። አላማው እኛና እነሱ የሚባል ነገር የለም ለማለት ነው። እኛ ነን የምንሆነው ነው። እውነት ለመናገር ጠቅለል ባለ ዘረኛ ፕሮፓጋንዳው የተቃኘበተን አገራዊ ሁኔታና ስፋቱ ባይሆን ይህን በቀናነቱ አይቼው ላልፈው እችላለው። ዘረኛነት የሚቀነቀንበት ደረጃ ለማለፍ አይፈቅድም።

 

“እኔ ዳዊት ነኝ። አንተ እኔ ነኝ ብትልም አንተ እንትና ነህ። እኔም አንተም እንዳለነው ሁሉ እኛ ካለን እነሱ ይኖራሉ። እኔ እኛ ብቻ የምንሆንበት ስሌት በጭራሽ የለም። እኔ እኛ ብቻ ሳይሆነ እነሱን ልንሆን ግጥም አድርገን እንችላለን። ልዩነትን አምርረን ስለምንጠላና ዘረኛነታችን እንጂ እኔ፤ አንተ፤ እኛና እነሱ መኖራችን ጥሩ ነው። ደስም የሚል ነው። ተዋደን ለመኖር ይህ ችግርም አይደለም። እንደው ድከሙ ቢላቸው ነው እንጂ ይህን በማድረግ ልዩነትን “እኛና-እነሱን” ማጥፋት አይቻልም። ይህ ሁሉ ልፋት እንግዲህ ኢትዬጵያችን ውስጥ ልምን ሌላ አይነት ማንነት ይኖራል ከሚል ነው፤ ሁሉንም ባይሆን መጥፎ ተደርገው የወሰዷቸው ማንነቶች ስላሉና እንዲጠፉ ነው። አላማችሁ ሊያሸማቅቋቸው የሚፈልጉ ማንነቶች ስላሉ ማሸማቀቃቸው ነው። ይህ እልም ያለ አንድ ቁጥር “ዘረኛነት” ነው። እንዳንዳንዶች ፍላጎት ቢሆን የዚህ አይነት ግለሰቦች ሰብስበው ያስፈጩኑል፤ አብኩተው አንድ ትልቅ ቂጣ አድረገው ይጋግሩናል፤ አንድ አይነት የምናስብ አንድ አይነት የምንናገር አድርገው ሊሰሩን ነው የሚፈልጉት። አንድ ትልቅ ቂጣ ሆነን ስንወጣ ምን እንደምንመስል አልመው ጨርሰዋል። ዘረኛ ሁላ። ዘረኛነት በፈጣሪ ስራ ላይ ሁሉ ነው የሚያሳምፅህ። ያልገባቸው እነዚህ ማንነቶች ከባርያ ንግድ፤ ከእጅና ጡት ቆረጣ ለዘመናት የዘለቀ ሁለንተናዊ ጦርነትና የተባበረ ዱቀሳ ተቋቅመው ዛሬ እንደውም ጎምርተው ያሉበት ሁኔታ መኖሩን ነው።

 

ፊልሞችን እዩ፤ ግጥሞቹን እዩ፤ ቀልዶቹን እዩ። ተከታታይ ድራማዎችን እዩ ሁሉም “ዘረኛነት ማንነት ነው= ማንነት ዘረኛነት ነው” በሚል የተቃኙ ናቸው። ዘፈን ክሊፕ ክፈቱ ቆንጆ ሴት ያሳይሀል። በፍቅር ይጀምርና “ማንነቴ ይሄ ነው” አትበይኝ ብሎ ዘፈኑ ያልቃል። ብዙ የዚህ አይነት ዘፈኖች አይቻለው። ብሄርተኛነት ላይ ጦርነት አለ። ጦርነቱን ያወጀው አካል ይታወቃል። እዥማቹም ዘማቾቹም እንዲሁ። እንደየትኛውም ጦርነት ይህንኛውም ጦርነት ዝቅጠት ጭካኔ አለበት፤ ካዘንኩበት የወረደ ካልኩት ጥቃቶች ውስጥ ሁለት ህፃናት ልጆችን ኢላማ ያደረጉ ቪዲዮዎችን ባለፉት ሶስት አራት ወራት ውስጥ ማህበራዊ ሜዲያ ላይ ይዘዋወር ነበር።

 

ትላልቅ ሰዎች ፅፈው አስጠንተዋቸው ህፃናት የሚተውኗቸው ቀረፃዎች ናቸው። አንዱ ቪዲዮ አሉ የሚባሉ የጥበብ ሰዎች ባሉበት መድረክ ላይ የቀረበ ነው። ብሄራዊ ቲአትር ውስጥ። ሌላኛው የተለያዩ ህፃናት ጠቅለል ባለ ለውጡ ላይ በዋናነት ግን ማንነት ላይ ጥቃት እንዲፈፅሙ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። የሁለቱም ቪዲዬዎች ይዘት ጠቅለል ሲደረግ፤ ሀድያ፤ አፋር፤ አማራ፤ ጉራጌ ከንባታ ምናምን ነን አትበሉ፤ “ዘረኛነት” ነው። እንዲህ የምትሉት ዘረኛ ስለሆናችሁ ነው የሚል ነው። በነዚህ አይነት ማቆሚያ በሌላቸው የጥላቻና ዘረኛ ቅስቀሳዎች ምክንያት ወደሗላ ተመልሶ ዛሬ ፊንፊኔ ላይ የሚኖር የማውቀው ሰው “ ምን ሲያቀብጠኝ ለልጆቼ የጉራጌ ስም አወጣሁላቸው” ማለት ደረጃ ደርሷል። ልጆቼ ትምህርት ቤት መሄድ እንቢ ማለት መጥላት ጀምረዋል ነው የሚለኝ። ችግር የሆነው ባለፈው ሀያ ሰባት አመት ዜጎች በማንነታቸው መኩራት ጀምረው ስለነበር ለልጆቻቸው በቋንቋቸው ስም ያወጣሉ። ቋንቋቸውን ጫን አድርገው ማስተማር ጀምረው ነበር። ዛሬ ላይ ወደሗላ ተመልሰን ልጆች የተለየ ስም መያዛቸው የተለየ ቋንቋ ጨምረው መናገራቸው ዘረኛ አስብሏቸው በሌሎች ህፀናትና በአስተማሪዎቻቸውም ጭምር መንጓጠጥን ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ሆኗል። የባለፈው ሳያንስ። የድሮው ብልግናና ድንቁርና ካስከተለው ትርምስና ቀውስ ሳንወጣ ለነገ ምን አይነት ማህበረሰብ እየፈጠርን እንደው እግዚአብሔር ይወቀው!።

 

“ዘረኛነት የተመለከቱ ጥቅሶችን አባባሎችን በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው “ዘረኛነት ማንነት ነው=ማንነት ዘረኛነት ነው ከሚል እሳቤ የሚነሱ ናቸው። ሁለተኛው የመጀመርያውን ኢትዮጵያዊ የሆነው አተያይ ስህተት መሆኑንን አውቆ “ዘረኛነትን” አለማቀፋዊ በሆነውና በትክክለኛው መንገድ ልንረዳው ይገባል ሲል የሚከራከረው ነው። ሶስተኛው ዝም ብሎ የዘረኛነትን ያወግዛል። የዘረኛነትን መጥፎነት ይሰብካል። አገራዊ አረዳዱ “ዘረኛነት ማንነት ነው= ማንነት ዘረኛነት ነው” የሚል ስለሆነ ግን ዘረኛነትን ከመታገል እና ጤናማ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ አስተዋፆው አሉታዊ ነው።

 

የመጀመርያው አተያይ።

 

 

“ዘሬ ኢትዬጵያዊ ነው፡ ወደ ብሄር ወርዳችሁ በዘረኛነት ለታመማችሁ ምህረት እለምናለው”

 

“ከብሄርተኛነትና ከዘረኛነት የፀዳች ኢትዬጵያን እንፍጠር”

 

“ዘር ለገበሬ ነው” ወይ “ዘር አንቁጠር ገበሬ ይመስል”።

 

“አራዳ ዘር የለውም፤ ዘረኛ አይደለም”

 

“አማራ ኦሮሞ አትበለኝ፤ ዘረኛነት ይጥፋ። አብይ ድምሮናል”።

 

“ከብሄርተኛነት የፀዳች ኢትዬጵያን እንመስርት”

 

ሁለተኛው አተያይ።

 

“ነገ መሞትህ እንደው አይቀርም! ጠልተህም የምትለውጠው ነግር የለም። ፈጣሪ እራሱ እዚህች ኢትዮጵያ የምትባል አገር ውስጥ ጉራጌ፤ ከንባታ፤ ንዌር……84 ብሔር-ብሔረሰቦች አድርጎ እንዲኖሩ ወደዚህ ምድር ያመጣቸውን ወንድምችህን

 

ማንነታቸውን አያሰማኝ ብለህ እንዳማረርክ፤ እንደተሳደብክ፤ እንደረገምክ፤ እንዳንጓጠጥክ አለህ። ስለዚህም ኢትዮጵያንም ህዝቧንም በዋናነት አምላክህን አሳዝነሀል። አንት ዘረኛ።

 

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ኢትዬጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ የመጣው የሚሰቀለው “ዘረኛ” ተብሎ ነበር። ምክንያቱም ለተጨቆኑት ወገንታዊነት ነበረውና። ማን ገራፊ ማን ጎኑን እንደሚወጋው መናገርም ከባድ አልነበረም። ጥቁር አሜሪካኖች ለእኩልነትና ለነፃነት የታገሉት በኛ አገር ውስጥ ቢሆን ኖሮ “ዘረኞች” ነበሩ። ዘረኛ ምንምን የሚሉት ዘፈንና ግጥሞች በሙሉ በቀጥታ ስለነሱ የተመረቱ ይሆኑ ነበር። አልፈንም እሳት ከሰማይ መጥቶ እንዲያቃጥላቸው ምህላ ስናደርግ ውለን የምናድረው ስለእነሱ ይሆን ነበር። አሁንም ዘረኛነት ላየ በኛ አገር ባለ አረዳድ መሰረት ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ቁንጮ “ዘረኛ” ነበር። ማንዴላ፤ ማህተመ ጋንዲ፤ ዶ/ር ጆን ካራንግ…… ሌሎችም ዘረኛነትን የታገሉ መረዎች ሁሉ ዘረኞ ነበር

 

የሚሆኑት። የአሜሪካንን ህገ መንግስት ያረቀቁትና ፌዴራሊዚም የሚል ጣጣ ያስተዋወቁና ተግባር ላይ ያዋሉ ሁሉ ዘረኞች ነበሩ፡- እኔ

 

ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ እያልክ ስለዘመርክ ዘረኛ አይደለህም ማለት አይደለም- ኦሮሞ ጥቅሜ ይጠበቅ አማራ ጥቅሜ ይጠበቅ ስላል ዘረኛ ነው ማለትም አይደለም። ዘረኛነት ሌላውን ዝቅ አድርጎ ማየት ነው። አንተ ባስቀመጥከው መለክያ “የኢትኦጵያዊነትን መስፈርት ያማያሟሉ” እያልክ መናቅ፤ ዝቅ አድርጎ ማየት ነው ዘረኛነት። ይሄን እና ያን ካላደረግክ ካልሆንክ ብሎ ሌላውን አሳንሶ ማየት ነው ዘረኛነት። የጎሳዬ፤ የብሄሬ፤ የመንደሬ፤ የሰፈሬ….ችግር ይሄ ነው መፍትሄ እሻለው

 

ብሎ ስለጠየቀ “ጎሰኛ፤ መንደሬ፤ ጠባብ፤ ዘረኛ….ወዘተ እያሉ መሳድብና እራስን ማሳበጥ ነው ዘረኛነት ።

 

ኦሮሞ ማጆሪቲ ስለሆነ ሌላወን መግዛት አለበት፤ አማራ ኢትየጵያን ስለመሰረተ ክብር ይጋባዋል ፤ ትግሬ ያመጣውን ልማት ማወደስ አለባችሁ- እኔ እንዲህ እና እንዲያ ስለሆንኩ እና ስላደረግሁ ይህን እና ያን ማድረግ ግዴታ አለባችሁ እኔ ልሁንበት ሌሎቻችሁ አጅቡኝ ማለት ነው ዘረኛነት።

 

“ ጋላ እስላም ፈረስ እና አህያን” እያለ በአንድ ላይ ደምሮ “ አረመኔ ህዝብ” የሚልን መፀሀፍ “አንድም የተሳሳተው ነገር የለም’ ማለት ነው ዘረኛነት። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ጥላቻን ታቅፎ አንዱን ሰው ፃድቅ አንዱን ሰው ደግሞ እንሰሳ የሚያደርገውን ሗላ ቀር ስብከት ትክክል ማድረግ ወይ ትክክል ነው ማለት ነው “ዘረኛነት”።( ዳንኤል ክብረት የመሳሰሉ ሰዎችን ይመለከታል) ፅሁፉ ይቀጥላል ሊነበብ የሚገባ ነው። ዮናታን ተስፋዬ።

 

አክራሪ “ኢትዮጵያዊነት” ምንድንነው…?

 

አንዳንዱ ሰው ከርሱ በላይ ኢትዮጵያዊ የለም። ስምህን እስከ አያትህ ስትፅፍ ራሱ ብሄርተኛ ወይም ዘረኛ ስለሆንክ ነው እንደዛ ያደረከው ብሎ ይከስሀል። ራሱ ካልሆነ በቀር ሌላ ሰው ሐገሩን ሲያቆላምጣት “ይቺማ ሽንገላ ናት” ብሎ ጥርጣሬ ቅርጫት ውስጥ ይጨምርሀል። በብሄር ማንነታቸው የተደራጁ ሰዎችን በሙሉ እንደ ኢትዮጵያ ጠላት እድርጎ ይፈርጃል። ሀሳባቸውን በሀሳብ ከመሞገት ይልቅ ቀድሞ “ ዘረኞች ወይም ጎሰኞች” ብሎ ያሸማቅቃቸዋል። እንደኔ ብያኔ ይህ ከኔ ውጪ

 

 

ወደ ውጪ ባይ “ ኢትዮጵያዊነት” አክራሪ ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህንንም አሳጥሬው ነው። ተፈልጎ ሊነበብ የሚገባው አጭር ማጣጥፍ ነው። አበበ ቶላ {አቤ ቶክቻው}።

 

“ቄሮ ወደ ፊኒፊኔ ከመንቀሳቀሱ የተነሳ ብዙ ጊዜ ትርጉሙ አልባ ሲመስለን የከረመው “ዘረኛ” የሚባለው የአማርኛ ቃል ምን ማለት እንደሆነ ። በምን እንደሚገለፅ። የእነማን አስተሳሰብ ውጤት እንደሆነ። አስተሳሰቡ ከየትኛው ባህል እንደመነጨ።”ዘረኞች” እነማን እንደሆኑ የአገሪቷ ህዝብ በግላጭ አይቷል። ከዚህ በሗላ “ኢትዬጵያዊነት” ማለት “ዘረኝነት” ማለት እንደሆነና “ ዘረኞች” የአዲስ አበባ {ፊኒፊኔ አላልኩም} ወጣቶች እንደሆኑ ለማመን የሚዳዳው ያለ አይምስለኝም”። ዶ/ር ኢታና ሀብቴ።

 

“ዘረኝነት ማለት ለቅሶ እየለዩ መድረስ ነው” የሚል ለቴዲ አፍሮ የተሰጠች ድንቅ መልስም አንብቤያለው ።

 

በቅርብ ዶ/ር ፀጋዬ አራራሳ።

 

ዘረኛ የሚጠላህ ለአገር ስጋት ስለሆንክ አይደለም። ዘረኛ የሚጠላህ በአንተነትህ ነው።{ኦሮሞ ከሆንክ ኦሮሞ ስለሆንክ ብቻ ነው።} አንተን መጥላት ለሱ የሂወት ዘዬው ስለሆነ ነው። ለአገር ስጋት የሚሆን ነገር ካለ፤ ይሄው የእርሱ ዘረኛነት ነው እንጂ ያነተ ማንነትህን መግለፅ አይደለም። “ዘረኛን” ማንነትህን በመደበቅ ወይም ለሱ የሚስማማ “ጨዋነት”በማሳየት፡ ለሱ የሚመች የፖለቲካ ፕሮግራም በመንደፍ ወዘተ እንዳይጠላህ ለማድረግ እትችልም። የእርሱ ጉዳይ ከድርጊትህ ወይም ከፖለቲካህ ሳይሆን ከማንነትህ ነው። ፍላጎቱም የአንተ ፍፁም መጥፋት ወይም አንተ እሱን እንዳትሆን ብቻ ነው። እራስ – ምታቱም የአንተ ህልው- መሆን{ህልውናህ} ነው። ተወው እርሳውና ኑር ዘረኛ በዘረኛነቱ ይሞታል!!!።

 

ሶስተኛው።

 

“ዘረኛነት” ልንፀየፈው ሊወገዝ ልንታገለው የሚገባ ማህበራዊ ችግር ነው። የካንሰር በሽታ ማለት ነው። ልንታገለው ግን ምን እንደሆነ በትክክል ሊገባን ይገባል። ሶስተኛውን አተያይ ልለው ያልፈለኩት የሰበሰብካቸውና ከታች የማስቀምጣቸው አባባሎች በሙሉ ይዘታቸው “ዘረኛነትን” መፀየፍ ነው። ጎጂነቱን ማሳየት ነው። መልክታቸው ትክክለኛ ነው። ያም ሆኖ “ዘረኞች” “ተበዳዮችን” ዘረኛ ብለው ማሸማቀቅ ደረጃ የሚረቀቁበት አገር ነውና ያለን እነዚህን አይነት የዘረኛነትን አስከፊነት ላማሳየት የምንጠቀምባቸው አባባሎች ይህንን ማህበራዊ ችግር ለመታገል እየጠቀሙ አይደለም። እንደውም በተቃራኒው “ዘረኞች” አብዝተው ሲጠቅሷቸው ለማሸማቀቂያ ሲጠቀሙባቸው ይታያል።

 

አንድ ሚሊዮን ቤተ-ክርስቲያኖችና መስጊዶች ቢኖሩን ትውልድን ማነፅ ካልቻሉ ምን ዋጋ አለው። ወንጌል ተሰብኮልኛል ቁርአን ቀርቻለው የሚል ሀይማኖተኛ ዘረኛነቱ ከሀይማኖተኛነቱ በልጦበት ከተገኘ ምኑ ላይ ነው እምነቱ። የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ።

 

“ዘረኛነት ከእውቀት ማነስ የሚመጣ በሽታ ነው”።

 

“ዘረኛነት የድንቁርና ምልክት ነው”።

 

“ከዘረኛ ዶክተር- ያልተማረ ገበሬ ላገር ይጠቅማል”።

 

“ዘረኝነት ጥንብ ናትና ተጠየፋት”። {ከቅዱስ ቁረኑ የተወሰደች ጥቅስ መሰለችኝ።

 

ስልጡን ከሆነክ ከዘረኛነት ውጣ። ሰው ከሆንክ ሰብዓዊነትህን አሳየኝ። ክፉ ሰው እሳት ሲለኩስ ውሀ ድፋበት እንጂ ቤንዚን አታርከፍክፍ። ስድብ ከእውቀት አልባ ጭንቅላት የሚወረወር የሰነፎች ድልዱም ጦር ነው። ማንንም አትስደብ። ቀና ቀናውን በማድረግ አገርህን ከሁከት ራስህንም ከፀፀት አድን። አምሰለት ሙጬ ይላል። ሶሻል ሜዲያ ላይ ስለሆነ ማንም ሰው ስሟን ሊጠቀም እንደሚችል ግምት ውስጥ ይግባ። ለማንኛውም ሀሳቡ እንከን አይወጣለትም።

 

በተመሳሳይ “ዘረኛነት” በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛ ደረጃው እኔ እነጂ አንተ እስከጭራሹ መኖር የለብህም ነው። አጥፍቶህ ያንተ የሆነውን ሁሉ የሱ ለማድረግ ይሄድ የነበረው ማለት ነው። ሻል ያለው- አለህ መኖርህ አንድና አንድ እኔን ለመጥቀም ነው። ብሎ የሚያስበው ነው። ሶስተኛው አለህ መኖርህ ግን ገደብ ያለው መሆን አለበት፤ መኖርህ ላይ ቁጥጥር

 

 

ይኑረኝ የሚልህ ነው። ይህ እራስህን ከመጥቀም፤ እራስህን ከመግለፅ፤ እራስህን ከማስተዳደር አንዳንዴ በማሰብና በመመኘት ጭምር በሁሉ ነገር ባስቀመጠልህ እርከንና ማእቀፍ ውስጥ እንድትኖር የሚፈልገው ማለት ነው። ከላይ ያሉትን ሁለቱን አይነት” ዘረኛነቶች” አለምም እኛም በአመዛኙ ተራምደናቸው ያለፍን ይመስላል። የመስፋፍት፤ የባርያ፤ የቅኝ ግዛትና የፊውዳል፤ የፋሽስቶች አገዛዝ የመሳሰሉት ሁሉ የነዚህ አይነት “ዘረኛነት” ውጤቶች ነበሩ። ዛሬ በአለም ላይ ጎለቶ የሚታየውና ይሄ “አነት ሲቤካ” {እኔ አውቅልሀለው ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ} የሚለው ነው።

 

“ዘረኛነት” እጅግ ከምንገምተው በላይ ጥልቅና ውስብስብ አስተሳሰብ ነው። “ አንዳንዴ ዘረኛ መሆንህን ሁሉ አታውቀውም። ተነግሮህም አይዋጥለህም። በደንብ የማውቀውና የማከብረው ግለሰብ ለራዲዮ ጣቢያ ቃለ መለጠይቅ ያን ሰሞን ሰጥቶ ሰማሁት። በጣም በስሜት ሆኖ እየደጋገመ እየደጋገመ “የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም እንደማይፈልግ ተናግሯል”። “ህዝብ ክልሎች እንዲፈርሱ ፍላጎቱ ነው” ይላል። ሙሉ ቃለምልልሱ ቃለት ወዲና ወዲያ ማድረግ ይኖረው ይሆናል እንጂ መልእክቱ ይሄው ነው። ይህን ኢንተርቪ ከማድረጉ ብፊት ያሉ ሶስትና አራት አመታት ዜጋው ነጋ ጠባ አደባባይ ላይ ነበር። ዛሬ ፍጅት ተፈፅሞበት በነጋታው አደባባይ ወጥቶ መብቱን ይጠይቅ ነበር። ጥያቄዎቹ ግልፅ ያሉ በየሰልፉ ላይ አስረግጦ የሚያነሳቸው አልፎም እንዲሰማ አድርጎ የጮህባቸው ናቸው። ጥያቄዎቹን ለመሰማት በብዙ ሺ ዎች ሂወታቸውና ገብረዋል ተግዘውበታል ። ይህ ባልንጀራዬ በየእለቱ ይሆን የነበረውን ለማወቅ የመረጃ ችግር እንደሌለበት በደንብ አውቃለው። ስለህዝብና ስለኢትዬጵያዊያን ሲያወራ “ህዘብ” ለሱ ማነው?። “ኢትዮጵያዊስ” ለሱ ማነው ነው?። የሚለውን ጥያቄ የግድ ያስነሳል። የዚህን ሰውዬ አይነት “ዘረኞች” ያዩሀል- ግን ደግሞ “አትታያቸውም”። “ይሰሙሀል-ግን ደግሞ “አይሰሙህም”። “አለህ ግን ደግሞ የለህም”። ዘረኛ መሆናቸውንምም አያውቁትም ብትነግራቸውም መቼም አያምኑም። ነግሬውም ሊያምነኝ ሊማር አልቻለም። ምን እንደማወራ ልገባው እስከጭራሹ አልቻልኩም።

 

የነዚህን አይነቶቹ “ዘረኞች” በለዘበ ሁኔታ ምሳ ልጋብዝህ ብለህ ምግብ ቤት ይዘህው ሄደህ ላንተ ፓስታ ስታዝ ጥብስ ካልበላህ ብሎ ክርክር የሚገጥምህ አይነት ሰው ማለት ነው። አልፎም ፓስታ ብለህ ማዘዝህን እየሰማ አስተናጋጁን ፓስታውን ተወውና ጥብስ ሉሁለታችንም ብሎ ተረግጦህ የሚያዝ አይነት ሰው ማለት ነው። ለዛውም ጋባዥ አንተ ስለሆንክ ነው እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው ለማዘዝ የበቃህው ብሎ ልደባደብም ሊል ይችላል።

 

ለነሱ አገራችን ውስጥ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች ጠረቤዛ ላይ ባንድ ታስረው የተቀመጡ የተለያዩ አበባዎች ማለት ናቸው። ጌጦች ናቸው ሲሉ የተለያዩ መሆናቸው ለአይን ስለሚፈጥረው ውበት ነው የሚያወሩት። የሰው ልጅ ግን አበባ አይደልም የተፈጠሩት ለጌጥነት አይደልም። ፍላጎት አላቸው፤ ችግር ይኖረቸዋል፤ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል ያኛ የሚሉት ሊጠብቁት ሊያሳድጉት የሚፈልጉት ጉዳይ ይኖራቸዋል። የኛ የሚሉት የሚኖሩበት መሬት አለ። እኩልነት ነፃነት ይፈልጋሉ። እንዲህ የሚያስቡት ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፤ መንግስትም ብቻ አይደልም ስልጣን ተቀኛቃኝ ፓርቲዎቻችን በይበልጥም አገር አቀፋዊ ፓርቲዎቹ በሙሉ ከላይ ምሳሌ እንዳደረኩት ሰውዬ አይነት ናቸው። አዎ እነዚህ የተለያዩ ማንነቶች ለነሱ ጌጦች ናቸው።

 

አለ ወይ?።

 

ኢትዮጵያዊ የሆነውንና የተለመደውን “ዘረኛነት” አረዳድ በድፍረት ከታገሉ ፀሀፍት መካከል ታስፋዬ ግብረአብ ተጠቃሽ ነው። በዚህም የተነሳ ከባድ ወጋ ክፍሎበታል። የቢሾፍቱውን ልጅ ነብስያው ከአድአ አፈር ጋር የተዋሀደውን በግድ ኤርትራዊ አስደርጎታል። ይህ ፀሀፊ ለመጀመርያ ጊዜ እኔ ዛሬ መዓት ገፅ የምቸከችክበትንና የምለፋበትን ሌሎችም እንዴት እንደሚገልፁትና እንደሚታገሉት ግራ የገባቸውን በአገር ደረጃ “ዘረኛነት” ላይ ያለውን የተወላገደ አረዳድ በአንድ አጭር እውነተኛ ታሪክ ሁሉ ሊሰማው በሚችል መንገድ ቁጭ ማድረግ የቻለ ድንቅ ፀሀፊ ነው። “አገሬው ተሳስቷል ዘረኛነት አለ፤ ዘረኛነት ይሄን ይመስላል፤ ዘረኞ የሚባሉት እነዚህን አይነት ሰዎች ናቸው” ብሎ መፈናፈኛ በሌለበት እስከአፀያፊነቱ በአጠቃላይ ሙሉ ስእሉን ቁጭ አደረገልን።

 

በጫልቱ እንደሄለን ታሪክ ምክንያት የመፀሀፉ እትመት ብዙ ፈተና ገጥሞታል። ደራሲው የለፋበት ስራ ያገኝ ይገባው የነበረ ኢኮነሚያዊ ጥቅም በተጨማሪ አጥቷል። የጫልቱ ታሪክ የብዙዎች ታሪክ ነው። የተቃወሙት ብዙዎቹ ተመሳሳይነት ያለው የዘረኛነት ተግባር ላይ ድርሻ አድርገው የሚያውቁ “ዘረኞች” ሊሆኑ ይቻላሉ። ዋናው ነገር ግን ይህን አይነቱ ትክክለኛው ዘረኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን መናገር የተከለከለ የሚደበቅ ስለነበረ ፀሀፊው የከፋ ውግዘት አስተናግዷል። ይህን

 

 

ያደረጉ አፋኞች ዛሬ የዜግነት ፖለቲካ ወይም ሞት ይላሉ። ለኔ ስለዜግነት ከማውራታችሁ በፊት በመጀመርያ የተስፋዬን ዜግነት መልሱለት።

 

ዘረናነት ዘረኛነት የባላል የሚፈለገው መጥፎ ወይም ጎጂ ተደርገው የተቀመጡ ማንነቶችን ማንጓጠጥ ነው። ስድብ ነው። የዘረኛነት ሰለባ የሆኑትን ቀድሞ ዘረኛ ብሎ ማሸማቀቅ በደላቸውን እንዳይናገሩ ማድረግ ነው። ተስፋዬ ግብረአብ ግን በመፀሀፉ የሀገሪቷን ሙህራን፤ ቤተ እምነቶች፤ መንግስትንና ጥበብን እንዴት አብረው እነደሚሰሩና ድርሻቸውን በዋናነትም ዘረኛነታቸውን አጋልጧል። የሚነጫነጩት የሚዘምቱበት ሲበዙ ካላችሁ ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ‘ዘረኛነት” አይደለም ለተራው ዜጋ ንጉሱ ሐይለ ስላሴ ሊጊፋጡት ፈርተውታል ነው ያላቸው። እናታቸውን ያስደበቃቸው መሆኑን “በጀሚላ እናት” አደባባይ አወጣላቸው። እውነቱን ነው ኮ/ል መንግስቱ አፍረው ከተሰደደ በሗላ ነው ከየትኛው ብሄረሰብ እንደሆኑ የተናገሩት።

 

“ዘረኛነት”፤- ጭቆና ነው፤ እልቂት ነው፤ ጥላቻ ነው፤ ፈላጭ ቆራጭነት ነው፤ አድሎ ነው፤ ስግብስብነት ነው፤ ቀማኛነት ነው፤ እብሪት ነው፤ አፋኝነት ነው።”ዘረኛነት” አለመቃፋዊ ማህበረሰባዊ ችግር ነው። ደረጃው ይለያያል እንጂ ዘረኛነት የሌለበት ችግር ያልሆነበት አገር የለም፤ ሰለዚህም የኛ አገር ብቻ ከሁሉ ተለይቶ ከዘረኛነት የፀዳ አይሆንም። ዘረኛነት አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ነው አይነት መፍትሄም ያለው ማህበራዊ ችግርም አይደለም። አለም ለዘመናት ሲታገለው እየታገለው ያለ ወደፊትም ሲታገለው የሚኖር ችግር ነው። “ዘረኛነት” እኛም አገር በከፋ ሁኔታ ነበር፤ አለ ነገም ይኖራል። መኖሩ ላይ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም። ዘረኛነት ከላ ደግሞ በተገቢው ልንታገለው ይገባል። በቀጥታ ስሙን ጠቅሰን ይህ ‘ዘረኛነት” ነው ብለን ባንታገለውም ታግለንዋል። ዛሬ ባርነት የለም፤ ዛሬ የፊውዳል ስርዓትና “ዘረኛ” ህጎቹ ተሸንፈዋል። ዘረኛ የሆነው ወያኒያዊ ስርዓት እየተንኮታኮታኮተ ነው። ይህም ሆኖ ዛሬ በአገራችንም በአለም ላይም ያለው ዘረኛነት ከዘመኑ ጋር እራሱን ያረቀቀ ነው። “አነት ሲቤካ” {እኔ አውቅልሀለው}፤ አለህ መኖርህ ላይ ቁጥጥር ሊኖረኝ ይገባል የሚለውን አይነቱ በግልፅ “ዘረኛነት” ሳንለው ልንታገለው ታግለንም ልናሸንፈው በጭራሽ አንችልም። በይበልጥም በእንደኛ አይነት ዘረኞች ተጎጂዎችን ቀድመው ዘረኛ ብለው የሚያሸማቅቁብት አገር ላይ አገራዊ አረዳዱን ታግለን ሳናስተካክል መዋጋት የሚቻል በጭራሽ አይደለም። መንግስት ዘረኛነትን መታገል ከፈለገ በመጀመርያ ደረጃ አገራዊ {ምንግስታዊ አረዳዱን} ያስተካክል።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም አይነት ግለሰባዊ{ውስጣዊ} ተጓዳኝ፤ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ የሆኑ ዘረኛነቶች አሉ። የግለሰባዊ {ውስጣዊ} ዘረኛነት በሽተኞች የመጀመርያ አይነቶቹ ትክክለኛ ማንነታቻውን ደብቀው ይኖራሉ። በማንነታቸው የሚያፍሩና የሚሸማቀቁ ናቸው። የዚህ አይነቶቹ ብዙ ናቸው። ብዙም ጎጂነትም የላቸውም። አንዳንዴ አንድን ማንነት አንጓጣጭ ተሳዳቢ አንደኛ ተፀያፊ ሆነው ይቀርቡና ሲጣራ ከዛው ማህበረሰብ የተወለዱ ሆነው ልናገኛቸው እንችላልን። ሌሎቹ ማንነታቸውን አይደብቁም፤ አንድም እንደብቀውም ቢሉ ሊደብቁት ችግር ስለሚሆንም ነው። ስማቸው ቅላፄያቸው ሌላም ሌላም ምክንያቶች ሊደብቁት ችግር ይሆንባቸዋል። ሰለዚህ “ነኝ ግን ከሌሎች ሁሉ የተለየው ነኝ” “እነሱ መጥፎ ናቸው እኔ ግን ጥሩ ነኝ” መለያቸው ይሆናሉ። ሞያ ያደርጉታል። ሁሌም ከብሔረሰባቸው በተቃርኖ ቆመው ሲከራከሩ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው ታገኛቸዋልህ። ይህን በማድረግ ከዛኛው ወገን የሚቸራቸውን አይዟችሁ ባይነትና ጭብጨባ መስከር ደረጃ አድርሶ እብድ ሁሉ ሊያስመስላቸው ይችላል። የዚህን አይነት “ዘረኞች” ከስልጣን ከሀይል ጋር ሲገናኙ መፍራት ይገባል። ጨፍጫፊ አንባገነን አልፎም ዘር ማጥፋት ደረጃ የደረሰ ወንጀል በራሳቸው ህዘብ ላይ መፈፀም ድረስ ሊሄዱ ይችላሉ። ጎሽ ባይ እና ጭብጨባ ብቻ ነው የሚፈልጉት። “ማንነት ዘረኛነት= ዘረኛነት ማንነት በሆነበት የኛ አይነት አገር ውስጥ ለንደዚህ አይነት ግለሰቦች ጥሩ መደበቂያም አላቸው። ሌለው ሁሉ ዘረኛ ሆኖ- እነሱ “ዘረኛ ስላልሆኑ ነው”

 

አንዳችን ሌሎቻችንን በሰውነት አሳንሰን እያየንና እየተፀየፍን ተጓዳኝ በሆነው “ ዘረኛነት’ ምክንያት አገራዊ ሰላማችን አጥተናል፤ በአገራችን ውስጥ ባሉ የተለያዩ ማህበረሰቦች መሀል ያለው ቁርሾ በዋናነት “ከዘረኛነት” የመጣ ነው። በዚህ የተነሳ ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ሆኗል፤ በአመፅ ተናውጠናል። አንድነታችንና ፍቅራችን ተፈትኗል። መተማመን አልቻልንም። ከባለፍው ዘሬም እንኳ ተገቢውን ጥንቃቄ አናደርግም። ቀላቶቻችንን አንመርጥም። ከጅምላ ፍረጃ አንወጣም፤ጎጠኛ መንደርተኛ ጠባብ፤ ፀረ ሰላም፤ ፀረ አንድነት ብለን አንድን የማህበረሰብ ክፍል ያለ ምንም በቂ ምክንያት ስንፈርጅ አይሰቀጥጠንም። ወደ አንድ ማህበረሰብ ባነጣጠረ መልኩ ሗላ ቀር ደንቆሮ የሚሉ ቃላትን መጠቀም የተለመደ ነው። አሽሙርና ቅኔ ልዩነቱ አይታወቅም፤ ምን አልባትም የለውም። ሁለቱም በድብቅ አንዱ ሌላውን የሚዘልፍበት “ዘረኛነቱን” ደብቆ ለትርጉም አከራካሪ በሆነ መንገድ የሚያካሂድበት አልፎም መሳደቢያ መሳርያ ነው።

 

 

ሳውዝ ዳኮታ ሱፎልስ እኖር በነበረ ጊዜ ኦጄ ያጫወተኝን አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ። እሱና አብረውት አየር ሀይል ውስጥ የነበሩና የተለያየ ክለብ ውስጥ የጅ ኳስ የመሳሰሉ የተለያየ እስፖርት ክለብ ውስጥ ከነበሩ ባልንጀሮቹና አብሮ አደጎቹ ጋር ሻይ ቡና ሊሉ አንድ መለስተኛ ቡና ቤት አዲስ አበባ ውስጥ ይገባሉ። ኦጄ ከአኝዋክ ብሄረሰብ የሚወለድ የጋንቤላ ልጅ ነው። ቀንም ስለነበር ብዙዎቹ እስፖርተኞች ስለሆኑም ትኩስ መጠጦችን ነበር ያዘዝነው። ግማሾቻችን ከተገናኘን ብዙ ጊዜ ስለነበር ሰብሰብ ብለን ጥሩ ጊዜ የጦፈ ጫወታ ላይ ነበርን።

 

ኦጄ እንደሚለው። አሁን ላይ ወደሗላ ተመለሼ ሳስታውሰው ሲገባ ገና ከበር ላይ ነበር የጀመረው። “ቋሚ ደንበኛ መሆን አለበት፡ ስም ተጣርቶ ምነው በቀኑ ቤቱን አጨለምሽው ማለቱን አስታውሳለው”። ከገባም በሗላ እላያችን ላይ እየተከርከረ ሁሉ የዚህ አይነት ነገሮችን ደጋግሞ ይናገር ነበር ። በቤቱ ውስጥ ላሉ ሌሎች ታዳሚዎችን ያስቅ ያዝናና ነበር። እኛ የሱ ቅኔ መቼ ገብቶን ምን እየሆነ እንደሆነ አንዱ ጓደኛችን ለሽንት ተነስቶ ሄዶ እስኪመለስ አላወቅንም። በነገሩ የተናደደች አስተናጋጅ ሹክ ብላው ኖሮ ከማረፊያ ቤት ሲመለስ በቀጥታ ሄዲ መንጋጭላውን አወለቀው። ከዛ በሗላ አስታራቂ፤ ተቆርቋሪ ገባ። ስም ጠርቶ አልተናገረም የሚለው አላዛቢ ይሁን አብሻቂው ብቻ ቆይቶ እኛም ጉዳዩ ሲገባን ተናደድን መሰለኝ ተፈሳፈስን። ብዙ ንብረት ወደመ። ሰው ተጎዳ። ሰራ ቦታ ላይ ሁሉ በዚህ የተነሳ ችግር ገጠመኝ ብሎኛል።

 

ተቋማዊ በሆነው ዘረኛነት መንግስትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዋንኞቹ ተጠቃሽ ናቸው። ሜዲያው ጥበብም ድርሻቸው ቀላል አይደልም። መንግሰቱን እናቆየውና አብያተክርስቲያኗ “ከዘረኛነቷ” ብዛት በምድር ላይ ባለው ጥቅማ ጥቅም አይደለም ሰማያዊያዊና ለሰው ልጆች ሁሉ በነፃ በእኩል አድርሱ የተባለውን “ቃሉን” ዜጎች በሚሰሙት በሚገባቸው ቋንቋ እንዲሰሙና እንዲጠቀሙ አይፈለግም።ለማመን ቢከብድም ቃሉ አድሎ ይደረግበታል። ይህ ዛሬም ድረስ ነው። ሁሉም የአገሪቷ ክፍል ላይ ቤተ ክርስቲያና አለች፤ መኖራቸው ምዝበራንና ፖለቲካዊ ተልኮን አላማ ያደረገ ነው። እድሜያቸውን ሲቆጥሩ የሚችላቸው የለም። ከዚህ ሁሉ ዘመን በሗላ ግን ጋንቤላዊ ወይ ወላይታዊ ቄስ ማፍራት አልቻሉም። ታዲያ ይሄ ዘረኛነት ያልተባለ ምን ዘረኛነት ሊባል ነው። ታሪካቸው በሙሉ አገሪቷ ላይ ከተፈራረቁት አንባገነኖች ጋር የተዋሸመ ነው። በዚህ የተነሳ አገራችን ላይ ጭቆና እንዲነግስ ድርሻቸው ቀላል አይደልም። ባርያ ፈንጋይነት የፊውዳል ስርአት መስፋፋት ይህ ሁሉ ቅሚያና ጭካኔ ያለነሱ የነቃ ተሳትፎ የሚሆን አልነበረም። ከሁሉ ከሁሉ የዘረኛነት ሰለባ የሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎችን ለነፃነትና ለእኩለንት የሚደርጉትን ትግልና ጠቅላላ ማህበረሰቡን “ ዘረኛ” አስብላ እንዲሸማቀቁና ዝም ለማሰኘት የሚደረገው ትግል ላይ ትልቁን ሚና እየተጫወተች ያለችው ዛሬም ድረስ አብያተክርስቲያኗ ነች።

 

“ዘረኝነት ከሀገራችን አፈር፤ውሀና አየር እንዲጠፋ ከተፈለገ ከምንጩ ይድረቅ! ምንጩ ቤተ-ክህነት ነው። ዳ/ር ወርቁ ነኝ ይላል። ካማህበራዊ ሜዲያ ግለሰቡን አላውቀውም መልእክቱን ግን ወድጄዋለው።

 

ጥበብ ወደላይ ከሀይል ጋር መጣላቷ ባህሪይዋም የተለመደም ነው። ጥበብ ከህዝብ {ከተወሰነ የመሀበረሰቡ ክፍል} ጋር ጠብ ውስጥ ስትገባ አንድም ሸፍጥ አለው ወይ ወገንታዊ ሆናለች። ይህ የማህበረሰብ ክፍል ሲጨቆን ዘረኛነት ሲፈፀምበት የነበረ ከሆነ በእርግጠኛነት ጥበብ ዘረኛ ሆናለች። ከማህበራዊ ሜዲያ የተገኘ።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ አገዛዞች በሙሉ “ዘረኛ” አንባገነኖች ናችው። ጠረፍ ላይ መኖር ጠፈር ላይ መኖር አይደለም። ዛሬ በዚህ ዘመን ከሙርሲ ቤሄረሰብ የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ የሚል ነገር መስማት አልነበረብንም። እውነት ለመናገር እጅግ ያማል። ዜጋውና በሙሉ በእኩልነትና ሚዛናዊነትን በጠበቀ ቢያስተዳድሩ ኖሮ የትምህርት ተደራሽነቱ በዚህ ደረጃ የተዛነፈ ባልሆነ ነበር። የመንግስት ዘረኛነት በህግና በፖሊሲ ደረጃም ጭምር የተደገፈ ነበር። አርፈህ ይህን እምነት ትከተላለህ ያለበለዚያ አገሩን ለቀህ ውጣ ድረስ በአዋጅ ተሄዷል። በኢትዮጵያ ውስጥ አድሏዊ የሆነ ሁለት አይነት የመሬት ፖሊሲ በገሀድ ስራ ላይ የዋለበት ጊዜ ነበር። ዘረኛ የነበረው የገባር ፖሊሲ፤ ጭሰኛነት ዘረኛነት የማጠቻው ናቸው። መንግስት ዜጎችን እያደነ ለባርያነት እየሸጠ መሳርያ ይገዛ ነበር። የሰው ባሮች ለመንግስት እንደቀረጥ ይገበሩ ነበር። ይህ የሩቅ ታሪክ አይደለም። በሀይለስላሴ ጊዜ ትናንትና የተባበሩት መንግስታት አባል ለመሆን ባርያ ፈንጋይነቱ ችግር ሲሆን ስለቆመ ነገር ነው የምናወራው። ነፃ ከወጡ በሗላ ቢሆንም በኔ እድሜ ባሪያ የነበሩ ዜጎችን አይቻለው። የትናንቱን እንተወውና ዛሬ ይህው አይናችን እያየን ፓርላማ ተሰብስቦ መሬታቸውን የሚቀሙ ገበሬዎች “የመክሰስ መብታቸውን በህግ ከልክሏል” የዚህ አይነት ዘረኛ ህግ አውጥተው የኦሮሞ ገበሬዎችና መሬት እንደ መንግስት ቀምትው የኛ ያሏቸውን ዜጎች ሀብታም አድርገውበታል።

 

 

ኢትዮጵያ ወስጥ የነበረውን የዘረኛነት አይነት ሁሌ ተቋማዊ ነው፤ መዋቅራዊ ብሎ ለመለየት ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ወያኔዎች የኦሮሞ ገበሬዎችን መሬት ሲቀሙ ህግ ሁሉ አውጥተው ስለነበር ተቋማዊ ነው ልንለው እንችላለን። መሬት ቅሚያው ላይ ባለደርሻዎቹ ወያኔዎች ብቻ ግን አልነበሩም። በዛ ላይ ነገሩ የተበላሸው ገና ከመነሻው አንድ ብሎ ሲጀምር መሆኑ አንዳለ ለመቶ ሀያ አመት አካባቢ የቀጠለ ችግር ነው። በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ገበሬዎችን ደብዛቸውን ያጠፋናቸው በረጅም ጊዜ ሂደት ነው። መዋቅራዊ ነው ልንለው አንችልም። ፍላጎቱና “ዘረኛነቱ” ከሌለ ለዚህን ሁሉ አመት ውጤቱ ዘረኛ የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍልን የሚጎዳ መሆኑንን እያየን ልናከላከለው ማስተካከያ ልናበጅልት ለምን አልቻልንም? የሚል መከራከሪያ የስነሳል እና። መንግስታት ተፈራርቀዋል አንዳቸው ይህን ዘረኛ የሆነ አሰራር ትኩረት አልሰጡትም። ትናንት አይደለም ዛሬ የኦሮሞዎች መንግስት ነን የሚሉት ከገበሬዎቹ ጎን ሊቆሙ አልቻሉም። ለምን? ከኦሮሞ ህዘብ ተለየትው እነሱ ዘረኛ ስላልሆኑ፤ እነሱ ጥሩዎች ስለሆኑ ማለት ነው። እንዳይባሉም ይሆናል።

 

በተመሳሳይ ንፁህ ውሀ፤ መብራት፤ የጤና ጥበቃ አገልግሎት ለማግኘት ከተማ ውስጥ መኖር አለብህ። የበዛው የአገሪቷ ዜጋ ገበሬው የዜግነቱን የድርሻውን ለመንገስት ይገብራል። ከማንም ያነሰ አይገብርም። እንደውም የሂወት ዋገን በሚፈልገው ገበሬው የአገርን ሉአላዊነት ለመጠበቅ ሲሆን የበዛውን አስተዋፆ ያደርጋል። እነዚህ መንግስት ሊያቀርባቸው የሚገቡ አገልግሎቶች ግን በማሳው በቄው አልፈው ሲሄድ ቁጭ ብሎ ያያል። ገበሬዎች ብሶባቸው ያጉረመረሙ ያመፁ ጊዜ ዘረኞች ናቸው ይባላሉ። በአይሮፕላን ይደበደባሉ። ከተሜው እንዲህ ዘረኛ በሆነ መንገድ ነው ችግሩን የሚራዳው። የከተሜው ዘረኛነት ዱላና ቆንጨራ ይዞ ገበሬና የገበሬ ልጆችን ወደ ከተማ አትገቡም ማለት ድረስ ደርሷል።

 

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ከአንድ ብዙ ያነበቡ እውቀት ጠገብ እድሜ ጠገብ አባት ጋር በጋውን ማሳለፍ ችዬ ነበር። መነሻ ታሪኩ አይሮፒላን ጠልፎ ጄኔቫ የገባው ጀግና ይመስለኛል። የኔሰው መሰለኝ ስሙ። ወያኔዎች አገር ውስጥ የቀሩ ቤተሰቦቹን አስገድደው እብድ ነው ማስባል መቻላቸው መነሻ ሂኖናል። ከዚህ በታች የማካፍላችሁ ታሪክ ለታሪክ ተመራማሪዎች ጥቆማ ለማድረግ ያህል ነው። በቀላሉ እውነትነቱን ሊያረጋግጡት ይችላሉ። እውነት ከሆነ መንግስት ዛሬም ቢሆን በደባባይ ወጥቶ አበበ ቢቂላን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ከሚልም ነው። በጫልቱ አንደሄለን ታሪክ ዘረኛነታችን ለምን ተጋለጠ ብለው ፀጉራቸውን የነጩ ይህው ያበበ በቂላም ለማለትም ነው። ዘረኛነት የሚል አርስት አንስቼ የሰማሁትን ይህን ታሪክ ሳላነሰው ላልፈው ስላልፈለኩም ነው። ብቸ በወሬ ወሬ ይህን የቅርብ ግን የተቀበረ ታሪክ አወጉኝ።

 

“ ይህን አይነት ነውር ዛሬ የተጀመረ መሰለህ አንዴ?። ምን ሆነ መሰለህ አበበ ቢቂላ ታሪክ ላይ ጋዜጠኞች በራዲዬ ያሉኝ መሰለኝ የተወለደበት አካባቢ ሄድው ወላጆቹን አናግረው አንድ ዝግጅት ሰርተው ነበር። ከቀናት በሗላ ተመሳሳይ ዝግጅት አሁንም ስለዛው አበበ ቢቂላ አቀረቡ። ተመቻችቶልኝ ሁለቱንም አድምጬዋለው አላመለጠኝም። ተደግሞ እንደገና እንዲሰራ ያስፈለገበት ምክንያት ምን እነደሆነ ታውቃለህ? ብለው በጥያቄ እያዩኝ። ይህ ጀግና ይህ ባለ ትልቅ ዝና በመጀመሪያው ዝግጅታቸው ላይ ኦሮሞ ነው ተብሎ በግልፅ መነገሩ ነበር። የመንግስት ሰዎች ከላይ ደስ አላላቸውም ተቆጥተዋል መሰለኝ እንደገና ቤተሰቦቹ ጋር ሄደው እናቱን አስገድደው ወይ አባብለው ኦሮሞ አይደለም የጉዲፈቻ ልጅ ነው አስባሉ። አበበ በቂላ አገራችንን በአለም አደባባይ ከፍ አደረጋት። ኢትዮጵያ ግን አፈረችበት። ጠጪ ተናዳጅ ደስታ ያልነበረው ሰው ሆኖ ሞተ”።

 

የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መኖርና እኔ ከኦሮሞ ብሄረሰብ ተወለጄ ኦሮምኛን አለመናገሬ ለማዛመድና የቋንቋ ልዩነት ምንም ማለት አንዳልሆነ ወይም ቋንቋን ከሰው ልጅ ውስጥ መዘን ስናወጣው ልዩነት በሙሉ ይጠፋል ብለህ ካልክ መደንዘዝ አለ ማለት ነው። ሲጀመር ለምንስ ነው ተመዞ የሚወጣው። አልፎም በነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች መሀል ያለው ልዩነት የቋንቋ ብቻ አይደለም። የሀዲያንና የጋንቤላ ህዝብ ልዩነታቸው ቋንቋ ብቻ ነው የሚለው ውሸት ነው። በጭራሽ አይደለም። ይህ ማለት ግን መግባባት ያልቻልነው ብዙ የሚያሳስቡን የምንጮህባቸው የቋንቋ አይነት ልዩነት ስላለን ነው እያልኩም አይደለም።

 

አላኗኑር አላግባባ ያለው ሲጀመር ልዩ ናችሁ ብለው ድምድመውና በዋናነት ልዩነቶቹን ተጠቅመው ሲበድሉ፤ ሲዘርፉ፤ ሲያሳድዱ፤ ባርያ ሲያደርጉና ጭሰኛ ሲያደርጉ የነበሩ “ዘረኞች” ስለነበሩ ነው። ይህ “ዘረኛነት” አገራዊ ስለነበር ነው፤ ይህ ዘረኛነት መንግስታዊ ስለነበር ነው። ያም ሆኖ ይህም መነሻ የማያግባባን ሆነ እንጂ ዛሬ ላይ ዋናው ምክንያት ይሄም አይደለም። አይደለም እኛ አያቶቻችን ቅድም አያቶቻችን ያለፈ የትናንት ታሪክ ነው ብለው ይህን ተሻግረውታል። እዚህ የደረሰንውና ዛሬም ድረስ አብረን እንደ አንድ አገር ህዝብ ያለነው የትናንቱን ዘረኝነት ይቅር ይበላቸው ብለን ስለተሻገርነው

 

 

ነው። አያቶቻችን አባቶቻችን ከዛ በሗላ አብረው ሂውት ገብረዋል፤ ገብረውም አገር አቆይተውልናል፤ ተጋብተዋል። እኛም የክፍለ ዘመኑን አይደለም የዛሬውን የወያኔን ይቅር አልን እኮ። ተውነው ተሻገርን። ዛሬ አዲስ ጅማሮ፤ ዛሬ አዲስ እድል አለን።

 

ያለያየን ዋናው ምክንያት በማንኛውም በሚሰኝ አገራዊ ጉዳይ ላይ አረዳዳችን መራራቁ ነው። አለም አንድ አይነት አረዳድ በወሰደባቸው ጉዳዬች ሳይቀር እኛ አረዳዳችን አራባና ቆቦ እየሆነ መቸገራችን ነው። አንድን አሳብ ወደ አይምሯችን የምናስገባበት፤ የምናብላላበትና የምንግልፅበት መንገድ ነው ሊያቀራራብን ያልቻለው። አንዳንዴ የተላያየ አይምሮ ተገጥሞልን ይሆን? የሚያስብል ነው!። እዚህ ላይ እነደ አዲስ ስንጀምር ትኩረት ሰጥተን መስራት ያለብን።

 

አገር፤ ታሪከ፤ መሪ፤ ዜጋ፤ ባንዲራ፤ የህዝብ መዝሙር፤ ዲሞክሪያሲ፤መብት፤ ዘረኝነት፤ ጀግና፤ ብሄረሰብ፤ እድገት፤ ጎሳ፤ አገር–ወዳድ፤ ጥሩ ዜጋ፤ ከፋፋይ፤ አስገንጣይ፤ ሽብርተኛ…..በምንም ነገር ላይ መስማማት አልቻልንም።

 

ይህንን ያመለካከት ልዩነት አማራ ኦሮሞ ብሎ መመደብ ሙሉ አያደርገውም። ብሄረሰባዊ ብቻ ሳይሆን ጂኦግራፊያዊ ቅርፅም አለው። እውቀት አስተዳደግ ባህል፤ አምልኮ የመሳሰሉት ጉዳዬች አሁን ለምናየው ልዩነት አስተዋፆ አድርጓል። ክርስቲያኑ በክርስትናው እንደሚከተለው ሀይማኖት፤ ሙስሊሙ ዋቄፈታው፤ የማያምነው አካባቢውን የሚያይበት መነፅር አንድ አይደለም። ልምሳሌ ‘አገር’ የሚባለውን ታላቅ ቁም ነገር በየእምነቶቹ ውስጥ የምእመናኑን አራዳድ ብናጠናው ተመሳሳይ ስእል የምናገኝ አይመስለኝም። የሚያጣሉን አላግባባ ያሉን እነዛ ልዩነቶች ከቅርፅ፤ ከሚሰማውና ከሚታየው ይልቅ ክቃንቋው ከባህሉ ይልቅ፤ ጥቅሙንና ፍላጎቱን መሰረት ያደረገው አስተሳሰባዊና የዛሬ ማንነቱ የተቀረፀባቸው ሁኔታዎች ናቸው። ግልፅ መሆንና ብዥታ ውስጥ ልንገባበት የማይገባው ያልተስማማነው የምንጨቃጨቀው ስለትናንት አይደለም። ስለዛሬ ነው። ስለትናንት አይደለም ስለነገ ነው። ስለትናንት እያወራን እየተጨቃጨቅን እየገጠምን እየዘፈንን ዛሬን እና ነገን ለኔ ለምንለው የምንጠቀምበትን ስሌት ውስጥ አስጋብተን ነው የምናወራው። ችግር የሆነው ይህን ስለምነደብቀው ነው። ይህን በሽፋን ስለምናካሂደው ብቻ ነው።

 

ይሄ እኛ የምንጨነቅበት ልናጠፋው የምንፈልገው የቋንቋ፤ የባህል፤የእምነት፤የቁመና ልዩነቶች ማንም ምንም ሊያደርጋቸው የሚችል አይደለም። ልዩነት መኖሩ ዛሬም የማይዋጥላቸው ምቾች የማይሰጠው ቢኖርም ልፋ ያለቸው ናቸው። ቢጎረብጣቸውም ይህንን በሆዳቸው መያዝና መኖር መልመድ አለባቸው። ከዚህ አልፈው የሚመጡትን በህግ ለህግ ያየሉትን በሀይልም ቢሆን እንዲውጡት እንዲለምዱት ማድረግ ብቻ ነው አማራጩ። አኝዋኩ አፋሩ ከንባታው የቀይ ዳማዎች ረጃጅሞች ሙስሊሙ ክርስቲያኑ ሴቶች ወንዶቹ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ልዩነቶች ሁሉ ለዘላለሙ ባልላችሁም በሙሉነታቸው በናንተ በልጅ ልጅ- ልጅ- ልጅ- ሎጆቻችሁ ዘመን በእርግጠኛነት ይኖራሉ። ልታጠፏቸው ማሰባችሁ በራሱ ዘረኛነት ነው። ዘረኛ ሆነችሁ ስትቃጠሉ ኑር ብሏችሁ ነው እነጂ ልታጠፋቸውም አትችሉም።

 

ክጥቅም ጋር ክፍላጎት በነገሮች ላይ ያለንን አተያይ ግን ማቀራረብ ማዘመን እንችላለን። ከዘረኛነት እናውጣው። ለፌደራላዊ ሰርአቱ ዘብ እንቁም መዳኒትነቱ ለአንባገነኖች ብቻ አይደለም ለዘረኞችም ነውና።

 

ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ!!!።

 

 

4 Comments

 1. ዳዊት ዳባ፣ እኔን የገረመኝ ይህን የመሰለ ጽሁፍህ በዚህ ድረገጽ ላይ እንዴት ሊወጣ እንደቻለ ብቻ ነው። እንደኔ አይነቱማ ፍንፍኔ ማሃል ኦሮምኛ እያወራን ስንሄድ ከማርስ እንደመጣን ያህል ሰዎች ዞር ብለው የሚመለከቱን ጊዜ ዉስጥ ያለፍን ስለሆነ አይገርመውም። (በትርፍ ጊዜዬ) አንተ ኦሮምኛህን ትተህ ለምን አማርኛ አትናገርም ብሎ የሰደበኝ የስራ ባልደረባ ነበረኝ! አዎ፣ ኦሮሞ ነኝ ማለትን ዛሬም “ዘረኝነት ነው” ብለው የሚወስዱ ከተራ ሰው እስከ ሃገር መሪ እስከ ዶክተር ፕሮፈሶር ድረስ አሉ። (It has become the mainstream thinking!) ጣታቸውን ወደ እኛ ሲቀስሩ ዘረኝነቱ ከራሳቸው እንደሆነ ግን አይገባቸውም። መረዳትም አይችሉም!

  ማንነትን በ”ዘረኝነት” የሚተረጉሙት እንዴት ጭቆናን ትቃወማለህ የሚሉት ናቸው! አልፈውም ኢትዮጵያ ዉስጥ ጭቆና አለ ስላልክ ይቅርታ ጠይቅ እስከማለት ደርሰዋል! ይህ አብሮ ያኖራል?? እኔ ለኢትዮጵያ ተስፋ ከቆረጥኩ ቆይቻለሁ!!

 2. Dawit:

  Speak the truth. We do not call you narrow nationalist “zeregna” when you speak in Oromo language or when you say you are Oromo, but only when you call Addisababans who live there for centuries “sefaris”, when you say everything is “kegna” including Addis, when you displace millions of people in Gedeo, when you occupy almost all minister positions, all the kebele and kefetgna leaderships in Addis, when you say when do not sell stuff to you unless you speak the Oromo language (as told by your narrow cousin), when you do the crazy thing you did at the Target stadium, Minnesota, in front of Abiy and Lemma, when you put yourselves always as victims (hiding what your people did while expanding to Northern Ethiopia) etc.

  Now, I hope you know why we call you “zeregna”

 3. Meseret; there you exposed your streotypical prejudice to call Oromos “Zeregna”! If someone states that what belongs to him is his, does it make him racist?? What percent of the residents of Addis have lived there for more than a generation? Residents of all big cities (not only in Ethiopia) are actually ‘sefaris’. How does calling a spade a spade make someone racist? Serving the people, especially customers of your business, in the language they understand is a promoter of your business, but you insult the customers as racists if they speak your language!

  You see now how ignorant and a racist full of hatred you are! And surely most racists are ignorants!

  • Mr Chala,

   Try to read between the lines. I never said Oromos are “Zeregna”. I was simply addressing the matter to Dawit. I never curse Oromos as a society although there are bad apples. Also, it seems you are happy to call non-oromo Ethiopians living in Addis as “sefaris”. I think this is right only among mentally retarded olfites. I suppose you are from Minnesota. Does any Minnesotan call you/your children/loved ones “sefaris”? Of course the answer is no as this is a place where civilized people are living. If you have still some healthy neurons left in your brain, try to learn from your environment and admit that you made a mistake. Ethiopians should be free not only to live in any part of the country but also to elect/be elected. This is human, logical and a 21st century idea.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.