የከተማ ልማት ጅቦች- ሳታማኸኙ ብሉንቀስቶ – ከጣናዳር

1 min read

ለክቡር ዶ/ር አምባቸዉ መኮነን የአብክመ ርዕስ መስተዳዳር

ለክቡር አቶ ዮሐንስ ቧያለዉ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽቤት ኃላፊ

በያላችሁበት

ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ በአማራ ክልል በአዲስ መልክ የለውጥ አመራር ምደባ እንደሚካሄድ በክልሉ ርዕስ መስተዳድር በዶ/ር አምባቸው መኮንን መገለጹን ስሰማ እኔ የምሞት ዛሬ ማታ ገብሴ የሚደርስ የፍስለታ የሚለው አባባል ትውስ አለኝ፡፡ አባባሉ ያለምክንያት አላነሳሁትም፡፡ የአማራ ክልል የመንግስት ተቋማት ከቀበሌ እስከ ክልል እየተመሩ ያሉት በደካማ አመራሮችና በኔት ወርክ ትስስር በተፈጠረላቸው ግለሰቦች እንደሆነ በየጊዜው በሕዝቡ የሚደርሰው የመልካም አስተዳደር ችግርና እንግልት እማኝ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

File Photo

ይሄም ሄደ ያም መጣ በአማራ ክልል ለውጥ ሳይሆን ነውጥ ብቻ ነው እያየነውና እየሰማን ያለው፡፡ የክልሉ ውሎ አዳር ሰርክ ስጋት ነው፡፡ ለክልሉ ሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ የተደራጁ የመንግስት መ/ቤቶች በሕግ የተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት ወደ ጎን ትተው ያሻቸው ሲፈጽሙ ሃይ ባይ በማጣታቸው ሕዝቡን ከማንገላታቸው በላይ ለሥራ ማስፈጸሚያ የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን እየተጣሱ ከከልሉ መንግስት ዕውቅና ውጭ ተቋሙ በሚመሩት አመራሮች ጭንቅላት ልክ እየቀደዱና እየሰፉ ለጥቂቶች መጠቀሚያ ለብዙሃኑ መጨቆኛ አሰራር በመዘርጋት ላይ ከሚገኙ ከክልሉ የመንግስት ተቋማት አንዱ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

የዚህ ተቋም ችግር ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ቢነገር ቢወራ አፍ እንጂ ጆሮና ልቦና ያለው መንግስት ባለመኖሩ ችግሩ በመገንገኑ በሽታውን መታደግ አልተቻለም፡፡ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንዲሉ ዛሬም ከቢሮ ጀምሮ እስከ ታችኛዎቹ ከተሞች በኔትወርክ የተሾሙት ጅባ ጅቦች ሕዝቡን እያሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ ከሁለት ዓመት በፊት ተግባራዊ የተደረገው በመንግስት ሠራተኛው ደረቅ ቼክ ተብሎ የሚጠራው አዲሱ የሥራ ምዘና ደረጃ አወሳሰን ጥናት (JGE) መሠረት በማድረግ የተካሄደው የሠራተኛ ድልድል ከመመሪያ

ውጭ ያፈነገጠ ድልድሎ አገልግሎትና የትምህርት ዝግጅትን ያላገናዘበ እንደነበረ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ በወቅቱ ተቋሙን በበላይነት ትመራው የነበረችው የቀን ጅቦች ወገን ገነት ገ/እግዚአብሔርና ጋሻ ጃግሬዎቿ (በምክትል ቢሮ ኃላፊነት የተቀመጡና ተከታዮቿ የጊዜው ጉምቱዎች) የዓይንህ(ሽ) ቀለም አላማረኝም በሚል በተንሸዋረረ ዕይታ የፈጸሙት ደባ አብዛኛው የተቋሙን ባለሙያዎች ያሳዘነ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ድልድሉ ፍትሐዊነት የጎደለውና መመሪያን የተከተለ ባለመሆኑ ከድልድሉ ማግስት ጀምሮ በሠራተኛው ተቃውሞ እንደቀረበና ከሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ ፍ/ቤት እስከ ሰበር ችሎት ቅሬታቸውን በማቅረብ ተከራክረው በመርታት በፍ/ቤት ውሳኔ መሠረት ተገቢውን ቦታቸው ያገኙ ግለሰቦች መኖራቸውንና ያላግባብ የተመደቡ ደግሞ መነሳታቸውን ከዚህ ላይ ማስታወስ እሻለሁ፡፡

ባለፈው የተፈጸመው ደባ አልበቃ ብሏቸው ዛሬ ደግሞ የከተማውን ነዋሪ ከማገልገልና ከተሞችን ከማልማት ይልቅ በአዲሱ የሥራ ምዘና ደረጃ አወሳሰን ጥናት (JGE) መመሪያ ውጭ በዳይሬክቶሬትነት ያሉ ቁልፍ የሥራ መደቦች ማለትም የከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንትና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና ሬጉሌሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሥራ መደብ ከቢሮው ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የክልሉን መንግስት ይሁንታ ሳያገኝ በሹመት ለማድረግ ጥናት ላስጠና በሚል ጥርስ ከሌለው ከከልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ፈቃድ በማግኘት ቀደም ሲል በድልድሉ የተመደቡትን በቂ የትምህርት ዝግጅትና አገልግሎት ያላቸውን አንስተው እንደነሱ ጅብ የሆነውን ወገናቸውን ለማስቀመጥ ሽር ጉድ እያሉ ነው፡፡

በአገርም ሆነ በክልል ደረጃ አዲሱ የሥራ ምዘና ደረጃ አወሳሰን ጥናት አተገባበር ያመጣው ፋይዳ ሳይጠና ገና ለገና በከተማ ልማት ዘርፍ የተመደቡ ዳይሬክቶሬቶች ገና ለገና አልታዘዙንም፣ ለስርቆት አልተመቹንም፣…. በሚል አጉል ምክንያት የሹመት ጥያቄ ማቅረብም ሆነ ለጥያቄው ከከልሉ መንግስትና ከመመሪያ ውጭ ምላሽ መስጠት ሁለቱም ወንጀል ነው ባይ ነኝ፡፡

አሁን በቢሮው ያሉ አመራር ጅቦቹ ያቀዱት ስልት በኔትወርክ በዘመድ አዝማድ ከላይ እስከ ታች ምንም ችሎታ የሌለዉን በቀረቤታ በመሾም እንዳሻቸው ሊፈነጩበት የቀየሱት ዘዴ እንደሆነ የፀሀፊው ዕምነት ቢሆንም አዲሱ የሥራ ምዘና ደረጃ አወሳሰን ጥናት (JGE) መመሪያ አላሰራ ካለ እንደ ክልል የክልሉ መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ አላሰራ ያለበትን ጉዳይ በጥናት ተመልሶ በክልል ደረጃ እንዲሰራ ይደረጋል እንጂ በየተቋሙ ገሚሱን በችሎታ ገሚሱን በሹመት እንመድባለን የሚሉት ፈሊጥ ተገቢ ባለመሆኑ የክልሉ መንግስት ቢሮው ያቀረበውን የሹመት ጥያቄ የከልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አሳስቶ ያስወጣዉን መመሪያ እንዲሻር አመራር ይሰጥበት ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.